መረን የለቀቀዉ ክፍያ

0
161

የእግር ኳስ ስፖርት በሀገራችን በተጀመረበት ጊዜያት ተጫዋቾች ለአምሮታቸው እና ለፍላጎታቸው ብቻ ይጫወቱ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ቀስ በቀስ ግን እግር ኳስ መጫወት ሥራ ሆኖ የገቢ ምንጭም ሆኗል። ተጫዋቾችም ለአንድ ክለብ ፊርማቸውን ሲያስቀምጡ ዳጎስ ያለ ክፍያ ይሰጣቸዋል።

የቀድሞው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) የተጫዋቾች ክፍያ እንዴት እንደተጀመረ በሊብሮ ጋዜጣ ባሰፈረው ጽሑፍ እንዲህ ያስረዳል። በሀገራችን የመጀመሪያው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ(በቀድሞ ስያሜው የአራዳ ልጆች ቡድን) እንደሆን ታሪክ ያስረዳል። ታዲያ ይህ ቡድን ከአርመን ኮሚኒቲ ቡድን ጋር ጨዋታቸውን ለማከናወን ቀነ ቀጠሮ ይይዛል።

የሁለቱ ቡድን ተጫዋቾች በዶሮ ማነቂያ ሲሰባሰቡ ከአራዳ ልጆች ቡድን ስብስብ መካከል ግን አንድ ተጫዋች ይጎላል። በወቅቱ በአጋጣሚ በመንገድ ሲያልፍ የተገኘው ይድነቃቸው ተሰማ የጎደለውን ሰው ተክቶ እንዲጫወት ያግባቡታል። በሀሳባቸው የተስማማው ይድነቃቸው ተሰማም “ለእናንተ ለመጫወት ተስማምቻለሁ ግን ለኔ ምን ታደርጉልኛላችሁ?” ብሎ ይጠይቃል።

የአራዳ ቡድን ስብስብም “ቆሎ” እንገዛልሀለን ማለታቸውን ጽሑፉ ያስነብባል። በወቅቱ ቆሎው ለሙያው የተከፈለ ደሞዝ መሆኑ ነው። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያው የፊርማ ታሪክ ተብሎ ሊወሰድ እንደሚችልም የቀድሞ ጋዜጠኛው ያሰፈረው ጽሑፍ ያትታል።

ለእግር ኳስ ስፖርት የሙያ ጥቅም፣ እውቅና እና የገንዘብ ክፍያ በይፋ የተጀመረው በ1980ዎች መጨረሻ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ሶከር ኢትዮጵያ ከአራት ዓመታት በፊት የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ክፍያ መረጃ አስባስቢያለሁ ባለው መሰረት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ መልኩ ከመጀመሩ በፊት ፋሲል አብርሃ ለኒያላ ሲፈርም አንድ ሺህ ብር መቀበሉን ያወሳል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ መልኩ በተዋቀረበት 1990 ዓ.ም ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቴዎድሮስ በቀለን በ15 ሺህ ብር ክፍያ ማስፈረሙን ያስነብባል። ከሁለት ዓመታት በኋላም አንተነህ አላምረው ከሱዳኑ አል ሂላል ተመልሶ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፊርማውን ሲያስቀምጥ ክብረወሰን በሆነ 30 ሺህ ብር እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል።

በቀጣዮቹ ዓመታት አንድ ጊዜ ከፍ ሌላ ጊዜ ዝቅ ሲል የነበረው የተጫዋቾች ክፍያ ከሚሊኒየሙ ወዲህ እጅግ ጨምሮ ታይቷል። አሚኮ በኲር ዝግጅት ክፍል በተጫዋቾች ደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ዙሪያ  የእግር ኳስ ተጫዋቾች ተጠቃሚ መሆን የለባቸውም የሚል እምነትም አቋምም እንደሌለው ከወዲሁ ማስገንዘብ እንፈልጋለን።

አሁን ላይ  በአንድ የዝውውር ወቅት ብቻ ክለቦች 11 ተጫዋችን ከማስፈረምም አልፈው 17 ተጫዋቾችን ቢያስፈርሙ ሊገርምዎት አይገባም፤ ጨዋታዎችን እየተመለከታችሁ ሁሉም ተጫዋቾች የቀድሞ ክለባቸውን እየገጠሙ መሆኑን ቢያውቁም ብዙ አትገረሙ፤ ለአንድ ክለብ ታምነው የሚጫወቱ ተጫዋቾች ቢጠፉ፣ ጠንካራ እና ስኬታማ ክለቦች በውድድር ዓመቱ ቡድናቸውን አፍርሰው እንደገና ቢገነቡም ብዙ አይደነቁ፤ ምክንያቱም ይህ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ነው።

በውድድሩ አጋማሽ ላይ በርካታ ክለቦች ስላጋጠማቸው የገንዘብ እጥርት ቢሰሙም ሊያስደንቆዎት አይገባም። ምክንያቱም ይህ ፍትሐዊ የገቢ እና የወጪ ምጥጥን ሕግ የሌለበት፣ ክለቦችም በአግባቡ ዓመታዊ ኦዲት የማይደረጉበት እና የክለቦች ድርጅታዊ የፋይናንስ መዋቅር የሌለበት የእግር ኳስ ስርዓት ነው።

በ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከተጫዋቾች ክፍያ ጋር በተያያዘ አዲስ ሕግ ማጽደቁ አይዘነጋም። ሕጉም ለተጫዋቾች የሚከፈል የፊርማ ክፍያ ቀርቶ በደሞዝ ብቻ እንዲጫወቱ የሚያስገድድ ሕግ ነበር። ይህ ግን ቅጥ ያጣውን እና ከልክ ያለፈውን ሥርዓት አላስተካከለውም። አሁን ላይ የፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋቾች ወርሃዊ ደሞዛቸውን መስማት ጆሮን ጭው ያደርጋል።

በታውንሰንድ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት መምህር  ጋሻው አበዛ(ዶ.ር) ባሳለፍነው ዓመት የተጫዋቾችን ክፍያ ማጥናታቸው ይታወሳል፡፡ በአማካይ የአንድ የፕሪሚየር ሊግ ተጫዋች ወርሃዊ ደሞዝ ከ130 ሺህ ብር በላይ መሻገሩን  ያብራራሉ።

የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች 70 በመቶ የሚሆነው ወጪ ለተጫዋቾች ደሞዝ ክፍያ እንደሚውልም በጥናታቸው አስረድተዋል። 16ቱም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች እያንዳንዳቸው በዓመት በአማካይ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያወጡም ጋሻው አበዛ (ዶ.ር) አስታውሰዋል።

የስፖርት ኒውስ አፍሪካ መረጃ ግን ከዚህም እንደሚበልጥ በድረገጹ ያስነብባል። በመረጃው መሰረትም ልክ እንደ ዛምቢያ ሁሉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በአማካይ ለአንድ ተጫዋች ሰባት ሺህ ዶላር ወርሀዊ ደሞዝ እንደሚከፍሉ ያስረዳል። ይህም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከአፍሪካ ከፍተኛ ደሞዝ ከሚከፍሉት መካከል ከቀዳሚዎች ተርታ እንዲሰለፍ አድርጎታል ይላል መረጃው።

በ2011 ዓ.ም የተጫዋቾች የደሞዝ ጣሪያ 50 ሺህ ብር ተወስኖ እንደነበር የሚታወስ ነው። ነገር ግን ውሳኔው ተግባራዊ መሆን አልቻለም። ክለቦች ውስጥ ለውስጥ ወይም በጓሮ በር ለተጫዋቾች ተጨማሪ ክፍያዎችን እና ጥቅማጥቅሞችን በመስጠት ተጨዋቾችን ያስፈርሙ እንደነበር በስፋት ሲነገር እንደነበር አይዘነጋም። ይህ ደግሞ መንግስት ከታክስ የሚያገኝውን ተገቢውን ጥቅም ጭምር ሲያሳጣው ቆይቷል። ለክለቦቹ ደግሞ የገንዘብ ቀውስ ፈጥሮባቸዋል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከጥቂት ክለቦች በስተቀር አብዛኞቹ የከነማ ክለቦች በመሆናቸው  የመንግስት ጡረተኞች ናቸው። እነዚህ ክለቦች ይህ ነው የሚባል የረባ የገቢ ምንጭ ስለሌላቸው መንግስት የሚበጅትላቸው ገንዝብ ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው ነው ። ይህ ደግሞ የክለቦችን ቀጣይ ህልውና  አሳሳቢ ያደርገዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ በርካታ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ገና በውድድሩ አጋማሽ ላይ የገንዘብ እጥረት ገጥሟቸው ሲንገዳገዱ ተመልክተናል። መንስኤው ከልክ ያለፈ የተጫዋቾች ወርሃዊ  ደሞዝ እና የዝውውር ክፍያ እንደሆነ አያጠያይቅም። ችግሩ በጊዜ መፍትሄ ካላገኝ ከዚህ የከፋ ውድቀት ሊያስከትል እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

ጥያቄው እግር ኳሱ የሚያወጣውን  ወጪ ያህል  ገቢ እያስገኝ ነው? አይደለም! በሎ መናገር ይቻላል፡፡ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ወጪ እና ገቢያቸው ተመጣጣኝ ቢሆን ኖሮ ብዙዎቹ ክለቦች ገና በውድድሩ አጋማሽ የገንዘብ እጥረት አይገጥማቸውም ነበር። ለአብነት በ2014 እና 2015 ዓ.ም ከጥቂት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በስተቀር ብዙዎች የገንዘብ ችግር እንደነበረባቸው አይዘነጋም።

ሊጉ በዲኤስቲቪ አማካኝነት የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ማግኘት ከጀመረ ወዲህ ክለቦችም የገንዘብ ጥቅም ማገኘት ጀምረዋል፡፡ ከዲኤስቲቪ የሚገኝው ገቢ 85 በመቶ ለክለቦች የሚከፋፈል ሲሆን ከዚህ ውስጥ 50 በመቶውን እኩል ይከፋፈሉታል፤ ቀሪውን ደግሞ እንደየደረጃቸው የሚያገኙ ይሆናል፡፡ ለአብነት በ2015 ዓ.ም ክለቦች እንደየደረጃቸው ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር ጀምሮ አግኝተዋል።

ከሚያወጡት ወጪ አንፃር ግን ይህ አነስተኛ ገንዘብ መሆኑ አያጠያይቅም። የሥራ ማስኬጃ፣ የጉዞ፣ የሆቴል እና መሰል ወጪዎችንም መሸፈን አይችልም። አልፎ አልፎ ከስፖንሰር እና ከሌሎች ድጎማዎችም ገቢ ቢያገኙም የከተማ አስተዳደር ክለቦች አብዛኛው ወጪ የሚሸፈነው ግን ከመንግስት በጀት ነው ማለት ይቻላል።

የአፍሪካ ሀገራትን የሊግ ደረጃ ያወጣው ቲም ፎርም የተባለው ድረገጽ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ከደካማዎች ተርታ አስልፎታል። ምንም እንኳ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ እየፈሰሰበት ቢሆንም ከአፍሪካ ሀገራት የእግር ኳስ ሊጎች መካከል 26ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ለዚህ ደካማ የእግር ኳስ ሊግ ከፍተኛ ወጪ መውጣቱ ጥያቄን ያጭራል።

ብዙዎቹ የፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች ለሙያቸው ብቁ (Unprofessional) እንደሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በኲር ጋዜጣ በህዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም ባስነበበችው ጽሑፍ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በአካል ብቃት ጥንካሬ፣ በታክቲክ እና በቴክኒክ አረዳዳቸው እንዲሁም የማሸነፍ ስነ ልቦናቸው ደካማ መሆናቸውን ዓለም አቀፉ ዳኛ ኃይለ እየሱስ ባዘዘው(ዶ.ር) መናገሩ ይታወሳል።

አንድ ቡድን ሜዳ ላይ የጎደለውን ተገንዝቦ ጉድለቱን ለመሙላት በተጫዋቾች ዘንድ የፍላጎት ብቻ ሳይሆን የእውቀት ውስንነትም እንዳለባቸው ገልጿል። በተጨማሪም የፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች ሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጪም ትልቅ የስነ ምግባር ጉድለት እንዳለባቸውም የእግር ኳስ ባለሙያው መናገሩ አይዘነጋም።

ታዲያ በዚህ ሁሉ ችግሮች የተተበተበው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለተጫዋቾች ከፍተኛ ደሞዝ ከሚከፍሉ የአፍሪካ ሀገራት ተርታ መሰለፉ ግራ ያጋባል። ዜጎቿ በድህነት በሚማቅቁባት ሀገር ውስጥ መሆኑ ደግሞ ለሰሚው ያስደነግጣል። የእግር ኳስ መሰረተ ልማቶች ገና ባልተስፋፉበት ሀገር ዋንጫ ለመሰብሰብ ብቻ ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣቱ ተገቢ አለመሆኑ ብዙዎች የሚስማሙበት ሀሳብ ነው።

ሁሉም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ደረጃውን የጠበቀ ስቴዲየም፣ የመለማመጃ ቦታ እና ጅምናዚየም የላቸውም። በወጣቶች ላይም ትኩረት አድርገው ሲሠሩ አይስተዋሉም። ዋነኛ የእግር ኳስ መሰረተ ልማቶች ሳይኖራቸው ለተጫዋች ግዢ ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣታቸው ክለቦችንም እግር ኳሱን የሚመራውን አካልም ትዝብት ውስጥ ይከታል።

ክለቦች ከገቢያቸው በላይ ወጪ እንዳያወጡ የእግር ኳሱ ዓለም የሚመራበትን ፍትሐዊ የወጪ እና የገቢ ምጥጥን (Financial fair play) ሕግን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ሕግ ክለቦች የገንዘብ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ ይጠብቃቸዋል። የተጠኑ ዝውውሮችን መፈጸም፣ ለተጫዋቾች ረጅም የውል ስምምነት መስጠት እና የግዥ እና የሽያጭ ስርዓቱንም እንደገና መፈተሽ ያሰፈልጋል።

ክለቦች ወጪያቸውን በኦዲተር አስመዝግበው ለሚመለከተው አካል እንዲያቀርቡ አስገዳጅ ሕግ ካልተቀመጠ ችግሩ በቀላሉ ይቀረፋል ተበሎ አይታሰብም። በዘልማድ እንዳይመሩም ድርጀታዊ የገንዘብ መዋቅር እንዲኖራቸው እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ቁጥጥር የማድረግ  ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የተጫዋቾች ክፍያ እና አጠቃላይ የክለቦች ወጪ ያሳሰበው የፕሪሚየር ሊጉ አክስዮን ማህበር አካሄዳቸው ጥሩ አለመሆኑን በመገንዘብ በቅርቡ አዲስ ውሳኔ ማስተላለፉ አይዘነጋም። ባለፉት ሁለት ዓመታት የሊጉ ክለቦች ለተጫዋቾች እና ለአሰልጣኞች ለደሞዝ እንዲሁም ለማበረታቻ ያወጡት አጠቃላይ ወጪ ታሳቢ ተደርጎ ነው ውሳኔ የተላለፈው።

ከ2017 የውድድር ዓመት ጀምሮ አንድ ክለብ ለደሞዝ 52 ሚሊዮን ብር እና ለማበረታቻ አምስት ሚሊዮን ብር በድምሩ ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ እንዳያወጡ ውሳኔ ተላልፏል። የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር ይህን ውሳኔ ሲያስተላልፍ ክለቦችን የሚቆጣጠርበትን ስርዓት መዘረጋቱን ግን አብሮ አላሳወቀም። ይህ ካልሆነ ደግሞ ችግሩ አሁንም ይቀረፋል ተብሎ አይታሰብም።

በፕሪሚየር ሊጉ የሚታየው ይህ ከልክ ያለፈ የተጫዋቾች ክፍያ እና ወጪ በመጨረሻ ራሳቸውን ክለቦችን ጠልፎ እንዳይጥላቸው እና ውድቀታቸውን እንዳያፋጥነው  ያሰጋል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here