“እረኛ ምን ይላል? በል!”
“ኧረ ምንም አይል ጌታየ!”
“እህ! ወስላታ! እሰማለሁኮ! ይልቅስ ንገረኝ!”
“ኧረ ምንም አልሰማሁ ጌታየ!”
“ንገረኝ! የማልሰማ መሰለህ! ይህ፤ አህያ መጣች ተጭና ቁልቋል የሚለው እንዴት ነው?”
“ኧረ እንጃ ጌታየ፤ አላውቀውም::”
“ንገረኝ! ፈሪ!”
“ ምን ብየ ልናገር ጌታየ?”
“አህያ መጣች ተጭና ቁልቋል፤ ብሎ መድፊያው እንዴት ነው?”
….
“ተናገር እንጂ ከርፋፋ!”
“ምኑን ነው ጌታየ?”
“አህያ መጣች ተጭና ቁልቋል፤ ብሎ የሚቀጥለው እንዴት ነው?”
“አህህ!… እህህ!…
አህያ መጣች ተጭና ቁልቋል
ደጃዝማች ማሩ ታመድ ላይ ወድቋል፤
አህያ መጣች ተጭና ገሳ
ማሩ ቢወድቅ ክንፉ ተነሳ::
ያጎቱን መንገድ ክንፉም አይርሳ
ሁሉን ጨፍላቂው ይመጣል ካሳ…
ነው የሚሉት ”
“ካሳ ደግሞ ማን ይሆን?…”
ይህን ቃለ ምልልስ የምናገኘው በደራሲ አቤ ጉበኛ “አንድ ለእናቱ” ታሪካዊ ልብ ወለድ መጽሐፍ ውስጥ ነው:: ቃለ ምልልሱ የተደረገውም በዚያ ዘመን (ዘመነ መሳፍንት) የደምቢያ እንዲሁም ያካባቢዉ ገዥ በነበሩት በደጃዝማች ማሩ እና ባገልጋያቸው መካከል ነው:: በዚያ አፍላ ጉልበተኛ ጦር አስከትሎ ወደ ፈለገው ግዛት በመዝመት ተዋግቶ ድል ከነሳ ሥልጣን በሚጨብጥበት ዘመን መረጃ እንደ ልብ አይገኝም ነበር:: መሳፍንቱ ኢትዮጵያን “የጎንደር፣ የጎጃም፣ የትግራይ፣ የወሎ፣ የሸዋ… ንጉሥ” በሚል ተከፋፍለው ርስ በርስ እየተሻኮቱ ያስተዳድሩ በነበረበት በዚያ ዘመን ለነገሥታቱ እንዲሁም ለሕዝቡ ሁነኛ የመረጃ ምንጭ ሆነው ያገለግሉ የነበሩት እረኞች ናቸው:: እረኞች ቀጣዩ ንጉሥ ማን እንደሚሆን፣ በዙፋኑ ላይ ያለው ንጉሥ ዕጣ ፋንታ ምን እንደሚሆን ይተነብያሉ ተብሎ ስለሚታመን የእረኞች መረጃ ለነገሥታቱ እጅግ ተፈላጊ ነበር:: እናም እረኞች በየጋራው፣ በየሸንተረሩ፣ በሜዳ እና በዱሩ እልቅታቸውን ባመልካች ጣታቸው ወግተው ጣታቸውን እጥፍ ዘርጋ እያደረጉ ማን እንዳለው የማይታወቀውን ግጥም፣
“አህያ መጣች ተጭና ገሳ
… ቢወድቅ… ተነሳ፤
አህያ መጣች ተጭና ዳባ
— ሸሽቶ — ገባ…”
ሲሉ ግጥማቸው መሬት ጠብ የማይል ትንቢት ተደርጎ ስለሚታይ በሕዝቡም ሆነ በነገሥታቱ ባንክሮ ይደመጥ ነበር:: እናም ደጃዝማች ማሩ እረኞች የከብት ጭራ እየተከተሉ፣ በየተራራው ጫፍ እየተንጠላጠሉ፣ ቀየውን ቁልቁል እየተመለከቱ ስለ እርሳቸው ሲገጥሙት የሚውሉትን ትንቢትም እንበለው ሟርት አዘል ግጥም ለመስማት ስለቋመጡ አገልጋያቸውን እረኞች የሚሉትን እንዲነግራቸው አጥብቀው ለመለመን ተገደዋል:: ለምነው አልነግራቸው ሲልም “ፈሪ! ወስላታ!” እያሉ እስከ መስደብ ደርሰዋል:: እረኛው ደግሞ በእኛ ለምድሩ ለሰማዩ በከበዱት አስፈሪ መኮንን ፊት እረኛ እንዲህ እያለ ነው ውድቀትዎ አይቀሬ መሆኑን የሚተነብይልዎ ብሎ ለመናገር ድፍረት በማጣቱ ሀገር ሰምቶት፣ ሀገር አውርቶት የጨረሰውን፣ ከእሳቸው ጆሮ ግን ያልደረሰውን ያደባባይ ጉዳይ ለመናገር ሲጨነቅ እናያለን:: ሆኖም የደጃዝማች ማሩ ልመና እና ስድብ ሲበዛበት መረጃውን ሲዘረግፍላቸው እናነባለን::
ደጃዝማች ማሩም እረኞች ስለ እሳቸው መውደቅ፣ ስለ ካሳ መነሳት የገጠሙትን ግጥም ወይም የተናገሩትን ትንቢት ከእረኛው አንደበት ከሰሙ በኋላ የእረኞች ትንቢት በእሳቸው ላይ እንደሚፈጸም በማመን፣”ካሳ ደግሞ ማነው?” የሚል ጥያቄ ራሳቸው ለራሳቸው በመምዘዝ በሀሳብ ጭልጥ ብለው ሲጠፉ እናያቸዋለን::
በጥንቱ ዘመን እረኞች የነገሥታቱ ዕጣ ፋንታ ምን ሊሆን እንደሚችል በግጥማቸው ሲተነብዩ ነገሥታቱ የእረኞችን ግጥም ይዘት በመመርመር ሕዝቡ የሚፈልገው ምን እንደሆነ ለይተው መፍትሄ በመፈለግ ፋንታ ትንቢት የተነገረለትን ሰው ወይም አልጋችንን ይወርሳል ብለው ያሰቡትን ወገናቸውን እያሳደዱ ማጥፋት ላይ ተጠምደው ኖረዋል:: ደጃዝማች ማሩም የዚያ ዘመን ሰው ነበሩና በልጃቸው አልጋ ይተካል በሚል በእረኞች የተተነበየለትን ካሳን በአራስነቱ ሊያስገድሉ ቆርጠው ሲነሱ እናያለን፤ የማታ ማታ ባይሳካላቸውም ቅሉ:: በእሳቸው እግር የተተኩት ደጃዝማች ክንፉም ቢሆኑ ወንድማቸውን ካሳን ሲያሳድዱት እንመለከታለን፤ “እርሳቸውን የሚተካ እሱ ነው” የሚል ወሬ ይናፈስ ስለነበር::
መረጃ በጥንቱ ዘመን ይህን መሰል ጉልበት ነበረው፤ ነገሥታቱን ጭንቀት ውስጥ ከትቶ ርምጃ እስከመውሰድ የሚያነሳሳ ጉልበት:: መረጃ በጥንቱ ዘመን ስጋትን በማንገሥ ለርስ በርስ ግጭት ምክንያት ይሁን እንጂ፣ በኋለኛው ዘመን ኢትዮጵያ ሀገራችን በነጻነት ጸንታ ትኖር ዘንድ ሁነኛ ሚና ተጫውቷል:: ስለ ሀገር ነጻነት እና ስለ መረጃ ሚና ሲነሳ ደግሞ ያድዋ ድል በቀዳሚነት ይታወሳል:: መንገድም ሆነ የሠለጠነ የመጓጓዣ ዘዴ ባልነበረበት በዚያ ፈታኝ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር ዳር በነቂስ ወጥቶ ለወራት በእግርና በፈረስ ተጉዞ ዓድዋ ድረስ የዘመተው፣ “ሀገርህ በጠላት ተወራለች፤ ክተት፤ ዝመት…” የሚል ጥሪ ከመሪው ስለደረሰው ነው::
በዚያ ዓለም እንደ ዛሬው ባልሠለጠነችበት ዘመን መረጃ የኢትዮጵያን ሕዝብ ባንድነት ዓድዋ እንዲከትም ከማድረጉም በላይ ኢትዮጵያ ጦርነቱን በድል አድራጊነት ትፈጽም ዘንድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል:: ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ከባለቤታቸው ከእቴጌ ጣይቱ ጋር በመመካከር ጠላት ስለኢትዮጵያ ጦር አሰላለፍ እና ዝግጁነት የተሳሳተ መረጃ እንዲደርሰው በማድረግ ወደ ጦርነቱ እንዲገባ በመገፋፋት ባልጠበቀው እንዲሁም ባልተዘጋጀበት ሁኔታ በማጥቃት ድል ሊያደርጉት ችለዋል::
ባንጻሩም ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ከአርባ ዓመታት በኋላ በ1928 በድጋሚ ስትወር የዓድዋውን ድል መድገም ሳይቻል ቀርቷል:: ለዚህ ከሚቀርቡ ምክንያቶች አንዱ ፋሽስት ጣሊያን ዓድዋ ላይ ድባቅ ተመትታ ከተባረረች በኋላ ላርባ ዓመታት የጦርነት ዝግጅት ስታደርግ ኖራ ኢትዮጵያን ድንገት መውረሯ ነው:: ጣሊያን ከዓድዋ ከተባረረች በኋላ ለዳግም ወረራ ዝግጅት እያደረገች ስለመሆኗ እና ድንገት ልትወራት እንደምትችል ኢትዮጵያ መረጃው ቢኖራት ኖሮ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ የዓድዋን ድል መድገም በቻለች ነበር:: ሆኖም መረጃው ስላልነበራት ጣሊያን ተመትታ በመመለስ ፋንታ ለጊዜውም ቢሆን የወረራ አድማሷን በመላው ኢትዮጵያ ሊባል በሚችል ደረጃ ልታስፋፋ ችላለች::
የኢትዮጵያ መንግሥታት ሕዝባቸውን ሲያስተዳድሩ የኖሩት በመረጃ ላይ ተመሥርተው ነው:: ሆኖም ከደጃዝማች ማሩ እና ካገልጋያቸው ቃለ ምልልስ እንደተረዳነው በቀደመው ዘመን መረጃ ማግኘት በእጅጉ አስቸጋሪ ነበር:: ለዚህም ነው ነገሥታቱ “እረኛ ምን አለ?” በማለት መረጃ ለማነፍነፍ ይገደዱ የነበሩት::
ዛሬ ደግሞ ያ እውነታ ተቀይሯል:: የሰው ልጅ መረጃ የሚያነፈንፍበት ጊዜ አልፎ መረጃ የሰውን ልጅ በገባበት ገብቶ አንብበኝ፣ አዳምጠኝ፣ ተመልከተኝ… ከሚልበት ዘመን ላይ ደርሰናል:: ዛሬ የሰው ልጅ መረጃ ለማግኘት እረኛ መጠየቅ ይቅርና ጋዜጣ ገልጦ ማንበብ፣ ሬድዮ ከፍቶ ማዳመጥ ወይም ቴሌቪዥን ከፍቶ ማየት ከማይገደድበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው:: መረጃ ካንዱ የዓለም ጫፍ ወደ ሌላው በቅጽበት እየተሠራጨ ነው:: የእጅ ስልክ የያዘ ግለሰብ ሳይቀር መረጃ ፈብራኪ እና አሠራጭ ሆኗል:: የማህበራዊ ትስስር ገጾች አለቅጥ ተስፋፍተዋል፤ መረጃ አሠራጮችም አጓጉል ፉክክር ውስጥ ገብተዋል:: ይህ ክስተት ለሀሰተኛ መረጃ መፈብረክም ሆነ መሠራጨት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል::
ተደራጅተው ማህበራዊ የትስስር ገጽ እንዲሁም መደበኛ የብዙኃን መገናኛ አውታር ያቋቋሙ አካላት ሳይቀሩ ብዙ አንባቢ፣ አድማጭ እንዲሁም ተመልካች ማግኘትን ተከትሎ ለሚመጣ ገንዘብ፣ ክብርም ሆነ ዝና ክፉኛ በመጓጓት እውነትን ከመፈለግ ይልቅ አስደንጋጭ ወይም የሚጮህ ርዕስን በማስቀደም፣ ፈጽሞ ያልተደረገ ወይም ሀሰተኛ መረጃን እውነተኛ አስመስለው በማቀናበር፣ በሳይቀድሙኝ ልቅደማቸው ሩጫ በስፋትና በፍጥነት ያሠራጫሉ:: መረጃውን የሚያነብ፣ የሚያዳምጥም ሆነ የሚመለከት ወገንም “እውነት ነው” ብሎ በመቀበል እነሱ ላይ ተጥዶ በመዋል በማደር ጊዜውን፣ ዕውቀቱን፣ ገንዘቡን… ያባክናል፤ ዓይኑን ያጠፋል፤ አእምሮውን ያደክማል፤ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ይደርሳል፤ የተሳሳተ ውሳኔ ይወስናል፤ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ… መሠረቱን ያናጋል፤ ፍርሃትን፣ ስጋትን፣ ጭንቀትን… በራሱ ላይ ያሰፍናል፤ ተስፋ ይቆርጣል::
በሀሰተኛ መረጃ የተነሳ በግለሰቦች ላይ እየደረ ያለ ጉዳት ሲደማመር ማህበረሰብ፣ ከፍ ሲልም ሀገር ትርምስ ውስጥ ይገባል፤ ሀብት ንብረት ይወድማል፤ የነበረው እንዳልነበረ ይሆናል:: ይህን አሳዛኝ ክስተት በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገራችን ተከስቶ አይተናል:: ሀሰተኛ መረጃ ከዚህም ከዚያም ይጎርፋል፤ መረጃው የሚደርሰው ወገን ደግሞ ያላንዳች ማጣራት እውነት ነው ብሎ በመቀበል ሰላሙን ሲያጣ፣ ለሌላውም በማጋራት ሰላም ሲያሳጣ ይታያል::
ሀሰተኛ መረጃ እየፈበረኩ በማሠራጨት ላይ የተሰማሩ ወገኖች በዚህ ተግባራቸው ለጊዜው ጥቅም ያገኙ ቢመስላቸውም የእውነት ፀሐይ ስትወጣ ሲጋለጡ እና እርቃናቸውን ሲቀሩ ተመልክተናል፤ እየተመለከትንም ነው:: ሆኖም ሀሰተኛ መረጃ ፈብራኪዎችና አሠራጮች የእውነት ፀሐይ ወጥታባቸው እስኪጋለጡ ድረስ የሚያደርሱት ጉዳት ቀላል አለመሆኑን ተገንዝበናል:: ስለሆነም ሁላችንም በሀሰተኛ መረጃቸው እንዳንታለል እና እንዳንጎዳ፣ ተታለንም ሆነ ተጎድተን ለሌሎች መታለል እንዲሁም መጎዳት ምክንያት እንዳንሆን፣ ሀገራችንንም እንዳንጎዳ… መረጃ ስንቀበልም ሆነ ስናቀብል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል:: በመጀመሪያ ደረጃ የትኛውንም መረጃ እውነት ነው ብለን ከመቀበላችን እና ለሌሎች ከማቀበላችን በፊት ከራሱ ከምንጩ እንዲሁም ከተለያዩ ምንጮች በማመሳከር እውነትነቱን ደግመን ደጋግመን ማረጋገጥ አለብን:: መረጃው እውነት ሆኖ ቢገኝ እንኳን ለሌሎች ከማጋራታችን በፊት የመረጃውን ፋይዳ ደግመን ደጋግመን መመዘን ይኖርብናል:: መረጃ አሠራጮችም ቢሆኑ እየዋሹ መኖርም የሚቻለው ሀገር ስትኖር መሆኑን አውቀው ለራሳቸው ህልውና ሲሉ ሀሰተኛ መረጃ ከመፈብረክም ሆነ ማሠራጨት መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል::
(አባትሁን ዘገየ (ቦ.ዘ.አ.)
በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


