መሪው መንገድ በ30 ዓመታት

0
172

የሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚፋጠነው፣ ሉዓላዊነት ተከብሮ የሚኖረው፣ የአማራ ክልል ሕዝብም ከቀሪው የዓለም ክፍል ጋር በቅርበት የሚገናኝበት እና ተወዳዳሪ የሚሆነው  ዋናው መንገድ ትምህርት ነው:: ለዚህም ዕውን መሆን ከትምህርት ተቋሙ የበላይ ጠባቂ በመቀጠል ሚሊዮኖችን ተደራሽ የሚያደርጉት የብዙኃን መገናኛዎች ሚና ከፍተኛ ነው::

በአሁኑ ወቅት በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሥር እየታተመች ዘወትር ሰኞ ለአንባቢያን የምትበቃው በኵር ጋዜጣ የትምህርትን አዎንታዊ አስተዋጽኦ በጉልህ በመረዳት ከምስረታዋ ጊዜ ጀምሮ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች::  ጋዜጣዋ በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚዋ ክልላዊ ጋዜጣ ሆና ከአንባቢያን እጅ መድረስ የጀመረችው ታኅሳስ 7 ቀን 1987 ዓ.ም ነው:: የአማራ ክልልን የረጅም ዓመታት የመልማት ጥያቄ ለመመለስ አጋዥ መሳሪያ እንደምትሆን የታመነባት ጋዜጣዋ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በእርግጥም ለክልሉ ልማት እና ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክታለች።

ታዳጊዎች የወደፊት መዳረሻቸው የሚወሰነው በትምህርት መሆኑን አውቀው ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ፣ ትምህርታቸውንም ያለምንም መቆራረጥ በጥሞና እንዲከታተሉ የማስገንዘብ ሚናዋን ስትወጣ 30 ዓመታትን ዘልቃለች፣ በቀጣይም ዋና አጀንዳዋ አድርጋ ትጓዛለች::

በኵር ወላጆች ልጆቻቸው ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ክትትል እንዲያደርጉ ከማድረግ ጀምሮ፣ የዛሬው ያልተማረ ኅብረተሰብ ችግር የሚፈታው ዛሬ ላይ ትምህርትን በልዩነት ባስቀደሙ ልጆቹ መሆኑን አውቀው ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት እንዲልኩ በማንቃት ረገድም ጉልህ አበርክቶ ተወጥታለች።

የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት እንዲረጋገጥ በመንግሥት በኩል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ከመደገፍ ጀምሮ ተግዳሮት ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችን ለይቶ ለሚመለከከተው የመንግሥት አካል በማሳወቅ መፍትሔ እንዲሰጣቸው አጋር ሆና እየሠራች ነው::

በኵር ጋዜጣ በትምህርት አምዷ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ እና ክልሉ የብቁ ዜጎች መናኸሪያ እንዲሆን የሚያደርጉ ሥራዎችን ሠርታለች። በትምህርት አቀባበላቸው የተሻሉ ተማሪዎች በትርፍ ጊዜያቸው ሌሎች ተማሪዎችን እንዲያግዙ፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመለሱ ተማሪዎችም ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት  እንዲሰጡ፣ ተማሪዎች ትርፍ ጊዜያቸውን ለመልካም ነገር እንዲያውሉ፣ ትምህርት ቤቶች በግብዓት እንዲበለጽጉ፣ ቤተ ሙከራዎች እና ቤተ መጻሕፍት እንዲሟሉ በመጠየቅ እና ተሞክሮ በማጋራት ሰፋ ያለ ሥራ አከናውናለች።

የአማራ ክልል ሁለንተናዊ ዕድገቱን በትምህርት ዕውን ለማድረግ ሲያስብ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጎችን ማፍራት የሚያስችሉ ሥራዎችን ትኩረት አድርጎ ሲሠራ ኖሯል:: ለአብነት የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን ማበረታታት፣ የትምህርት ቤት ምገባን ተግባራዊ ማድረግ፣ የተማሪ ምዝገባን በአንድ ቀን በማካሄድ ዓመቱን ሙሉ ያልተሰናከለ መማር ማስተማር መስጠት ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ::

በኵር ጋዜጣ በመስከረም 2 ቀን 1993 ዓ.ም በትምህርታቸው ብልጫ ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዕውቅና መሰጠቱን ዘግባለች:: በዚህ ዘገባ በ1992 ዓ.ም 12 ሺህ 687 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መውሰዳቸውን፤ ከዚህም የማለፊያ ነጥብ ማስመዝገብ የቻሉት 7 ሺህ 840 ተፈታኞች ብቻ መሆናቸውን ሰንዳለች:: በወቅቱ ከ3 ነጥብ 6 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ 93 ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ማግኘታቸውን ለአንባቢያን አጋርታለች::

“ምሳ ለትምህርት” የተሰኘ ፕሮግራም በ2007 ዓ.ም ሲቀረጽ የአቋራጭ ተማሪዎችን ቁጥር ሙሉ ለሙሉ በማስወገድ ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር ትኩረት ተደርጎ የተሠራበት ሥራ ነው:: በአሁኑ ወቅትም የትምህርት ቤት ምገባ በሚል ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል::

“አንድ ቀን ምዝገባ – ዓመት ሙሉ ትምህርት” በሚል ርእስ ሥር መስከረም 5 ቀን 2007 ዓ.ም ለሕትመት የበቃው ጽሑፍ ደግሞ አሁን ላለው ነባራዊ ሁኔታ ትምህርት የሚሰጥ ነው:: በኵር በወቅቱ ይህንን ዘገባዋን ያጠናከረችው በደቡብ ገጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ ሽማግሌ ጊዮርጊስ ቀበሌ በመሀልጌ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት ነበር:: ጽሑፉ በዘመኑ ሁሉም ነገር ከትምህርት በኋላ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው።

የዘገባው ይዘት በአጭሩ ይህንን ይመስላል፡- “ቀኑ አርብ ነሀሴ 23 ቀን 2006ዓ.ም ነው፤ የቀበሌያቸው አጥቢያ ቤተክርስቲያን ወርሀዊ በዓል በመሆኑ በቀበሌው ውስጥ በእርሻም ሆነ በአረም የተሰማራ አርሶ አደር አልነበረም።  ነዋሪዎች ቀደም ብለው መክረው እና ዘክረው ይህን ዕለት ልጆቻቸውን በዚህ ቀን ብቻ ለማስመዝገብ ወስነዋል… ’ቃል ከሚጠፋ…’ ነውና በገቡት ቃል መሠረት ከብቶቻቸውን አሰማርተው፣ ከየቤታቸው ያሉትን ለትምህርት የደረሱ ህፃናት ይዘው ትምህርት ቤት ደርሰዋል። የአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ ካህናትም ጥላና ከበሮ ይዘው በመገኘት ትምህርት ቤቱን በዝማሬያቸው አድምቀውታል።

“ሕፃናት ልዩ ልዩ መፈክሮችን በማሰማት በየክፍላቸው መመዝገቢያ ፊት ተሠልፈው ይመዘገባሉ፤ ወላጆች ደግሞ ከልጆቻቸው ጎን ቁመው ‘ልጄን አስተምረህ ለቁም ነገር እንድታበቃልኝ” በማለት  አደራ ሰጠሁህ በሚል አይነት ያስመዘግባሉ::

አማራ ክልል የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራትን አስተሳስሮ ለመጓዝ የሚያደርገው ጥረት ግን በተለይ ከ2013 ዓ.ም ወዲህ እንደ ሀገርም ሆነ  እንደ ክልል እያጋጠሙ ባሉ ግጭት እና ጦርነቶች እየተደናቀፈ ይመስላል:: የትምህርት ቤቶች ለጉዳት መዳረግ፣ የውስጥ ግብዓታቸው መዘረፍ እና ከጥቅም ውጪ መሆን፣ የሚሊዮን ተማሪዎች እና የመምህራን ከትምህርት ውጪ መሆን ክልሉ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት የሚያደርገው ጥረት ፈታኝ ተግዳሮት ሆነው በአሁናዊነት ይነሳሉ::

ትምህርት እንደባለፉት ዓመታት ሁሉ በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ተቋማት የሚጠበቅ እንዲሆን ማድረግ ዋናው መውጫ መንገድ ሊሆን ይገባል:: ከቅርብ ጊዜያት  ወዲህ በመንግሥት እየተገነቡ ካሉ ትምህርት ቤቶች  ውስጥ የማኅበረሰቡ ተሳትፎም ከፍተኛ ነው:: ይህም “አለመማር በእኔ ይብቃ” አይነት መልዕክት የሚስተጋባበት ነው:: በመሆኑም ሕዝቡ በራሱ ሀብት እና ጉልበት የገነባው ትምህርት ቤት በግጭቶች እና በተለያዩ ችግሮች ለጉዳት እንዳይዳረግ በቅርበት መደገፍ እና መጠበቅ ይኖርበታል:: ልጆቹን ማስመዝገብ እና እስከ መጨረሻው ትምህርታቸውን እንዲያስቀጥሉ ማድረግ፣ ለዚህም በምንም አይነት ችግር ለማይስተጓጎል የትምህርት እንቅስቃሴ ዘብ መሆን ከሕዝብም ሆነ ከመንግሥት  ይጠበቃል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የታኅሳስ 7  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here