የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም
“ከሰዎች ጋር የሚደረግ ግንኙነት ወይም ሥራ ከምክንያታዊነት ጋር የሚደረግ አይደለም። ይልቁንስ በስሜት፣ ጭፍን ጥላቻ፣ ትዕቢት እና ከንቱ ጉራ ከተሞሉ ፍጥረታት ጋር እንጂ” ይላል ፋርናም ስትሬት ሚዲያ። በዚህም በምድራችን ያለው ብቸኛው ተጽእኖ ማድረጊያ ሰዎች ስለሚፈልጉት ነገር ማውራት፤ እናም እንዴት ሊያገኙት እንደሚችሉ ማውራት ነው ይላል። የሰዎች ስኬትም የሚወሰነው የሌሎችን ፍላጎት በማወቅ፤ ያንንም ፍላጎት ከእነሱ እና ከራስ አንጻር መዝኖ መመልከት መቻል እንደሆነ ፋርናም ስትሬት ሚዲያ ያስረዳል።
መሪነት ቀላል የሚመስለው አለ። “ከበሮ በሰው እጅ …” እንደሚሉት፤ ሰውን መምራት ከባዱ ሥራ ነው። ኀላፊነትም ነው። ታላላቅ ሰዎች የሚገለጡት ታናናሾችን በሚይዙበት እና በሚጠብቁበት መንገድ ነው ይላል ስኮትላንዳዊው ጸሐፊ ቶማስ ካርሊል።
መሪነት ነጻነት፣ ገንዘብ፣ ዝና፣ ገደብ አልባ ስልጣን ሲሆን ብናይም ቅሉ ትክክለኛው መንገድ ይህ አልነበረም። ትክክለኛውን መስመር እስከሳተ ጊዜ ድረስ መሪነት የሀብት፣ የዝና፣ የስልጣን የብልግና ምንጭ መሆኑ የታዬ ሀቅ ነው። መሪነት ግን በለመለመው መስክ በጎቹን እንደሚያሰማራ መልካም እረኛ ያለ ነው። ከቀበሮ እና ነጣቂ የሚከላከልንም እረኛ ይመስላል። የመጠን ልዩነት ይኑረው እንጂ ሁለም ሰው መሪ ነው።
ራሱን ይመራል። ቤተሰቡን፣ አካባቢውን፣ ቀበሌውን፣ ወረዳውን እና ክልሉን በመምራት ዓለምን ወደ መምራት ያድጋል። አንድም ይሁን ስምንት ቢሊዮን ሕዝብ መሪነት አደጋን መቀነስ፣ ወደ ትክክለኛው ግብ ማድረስ ነው። መሪነት በሰዎች ሕይወት ላይ ኀላፊነት መውሰድ ነው። ሐቀኛ መሪዎች ሁልጊዜ እንቅልፍ አልባዎች ናቸው። የዓለም ጤና ድርጅት መሪ በስምንት ቢሊዮን ሰዎች ሕይወት ላይ ነው የሚወስነው። ለእያንዳንዷ ነፍስ ኀላፊነት አለበት። ይህንን ጉዳይ የኮሮና ቫይረስ የተከሰተ ሰሞን ተመልክተነዋል። ወረርሽኙን ለመከላከል፣ ክትባቱን ስለማምረት የተደረጉ ተግባራት እና ውሳኔዎች የዋና ዳሬክተሩን ጨምሮ የሌሎች መሪዎችን ሐሳብ አካተዋል።
መሪ ሁልጊዜ ብቸኛ ነው የሚለው ደራሲ እና ዲፕሎማት ኒኮሎ ማኪያቬሊ ደግሞ መሪነትን በተለየ መልኩ ይመለከተዋል። ማኪያቬሊ እ.አ.አ ከ 1469 እስከ 1527 የኖረ አዲስ የመሪነትን መጽሐፍ “ዘ ፕሪንስ” በሚል ያቀረበ ጣሊያናዊ ፈላስፋ ነው። በ16ኛው ክፍለ ዘመን በሚያነሳቸው የፖለቲካ ሐሳቦች ዝናው የናኘ ሰው ነበር። ማኪያቬሊ አሁን ዓለም የሚጠቀምባቸውን የፖለቲካ ሐሳቦች እና ፍልስፍናዎችን “ዲስኮርስ ኦን ሌቪ” በሚል ርዕስ በመጽሐፉ አቅርቧቸዋል። “መሪ ሁልጊዜ ከሞራል እና እሴት ይልቅ ለሕዝቡ የሚጠቅመው የትኛው ነው የሚለው ነገር ላይ ማተኮር አለበት” ይላል። ፖለቲካ የስነምግባር ጠበቃ መሆን የለበትም ብሎ ያምናል። ለዚህም ፖለቲካን ከስነምግባር ውጪ አድርጎ ያየዋል። መሪዎች የሚፈሩ እና የሚከበሩ መሆን እንዳለባቸው ጽፏል። ደካማ ተቃዋሚዎችን ለመጠቀሚያነት መተው አለባቸው፤ ሁለት ወገኖች ሲጣሉ መሪዎች ጠንካራውን መደገፍ አለባቸው ይላል። ማኪያቬሊያኒዝም አሁን የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ ሆኖ ይታወቃል። ይህን ፍልስፍና ሴራ፣ ተንኮል እና ግዴለሽነት አለበት ብለው የሚኮንኑት አሉ። አሁን ዘመኑ የዴሞክራሲ ቢሆንም እንኳን የዓለም ሀገራት ከሕዝባቸው እና ሀገራት ጋር ባላቸው ግንኙነት የማኪያቬሊን ፍልስፍናዎች ይጠቀሙባቸዋል። “ፖለቲካ ምንጊዜም፣ ክህደት እና ወንጀል አያጣውም” የሚለው ማኪያቬሊ መሪዎች እነዚህን ስልቶች እንዲጠቀሙባቸው ይመክራል። ዛሬ ላይ የዓለም ሀገራት በዴሞክራሲ ስርዓት ነው የምንመራው ቢሉንም ሴራ፣ ተንኮል፣ ጦርነት፣ ውሸት፣ ማታለል፣ ማጭበርበርን በመጠቀም የበላይነትን ለማግኘት የማይሞክሩት ስልት የለም። የዴሞክራሲ እናት እና ጠበቃ ነኝ የምትለው አሜሪካ እንኳን ኀያልነቷን ለማስጠበቅ የማትጀምረው ጦርነት፣ ጣልቃ የማትገባበት ፖለቲካ የለም።
ድል ካርኒጌ “ሀው ቱ ዊን ፍሬንድስ ኤንድ ኢንፍሎንስ ፒፕል” በሚለው መጽሐፉ አንኳር የመሪነት እና አሸናፊነት መመሪያዎችን ጽፏል። ሰዎችን እንዴት መያዝ ይገባል ለሚለው ካርኒጌ ሲያብራራ “አትንቀፏቸው፣ አታውግዟቸው እናም አታጉረምርሙባቸው” ይላል። ለሰዎች ልባዊ አድናቆትን መስጠት ሌላው ልብን ማሸነፊያ መንገድ ነው። ሰዎች ምኞት እና ጉጉት እንዲያድርባቸው ማድረግም ካርኒጌ የሚመክረው ጥበብ ነው።
በሰዎች ዘንድ መውደድ እና ሞገስ ማግኘት ለመሪ ቀላል ነገር አይደለም። ፈገግ ማለት፤ ሰውን በስሙ መጥራት፤ ማድመጥ፣ ዋጋ እንዳላቸው ማሳየት እንዲወዱህ ያደርጋልም ይላል። መሪዎች ከመወደድ በኋላ የሚፈልጉት ሌላው ጉዳይ ሰዎችን ወደ እነሱ አስተሳሰብ ስቦ መውሰድ እና ለተግባር ማዘጋጀት ነው። እናም ካርኒጌ ሰዎችን ወደ እናንተ አስተሳሰብ ለማምጣት አትከራከሩ ይላል። ተሳስተሃል/ሻል አትበሉ፤ በቅንነት ስህተታቸውን እንዲያዩ አድርጉ እንጂ ይላል። ስህተታችሁን በቀና መንፈስ ተቀበሉ ሰዎች ይከተሏችኋል፤ ለሰዎች ትኩረት ስጡ ያምኗችኋል ብሏል ካርኒጌ። በተናጋሪው ወገን ሆኖ መስማት፣ ርህራሄ፣ ብዙ ማድመጥ ተገቢነቱን አንስቷል።
ፎርብስ መሪነት ጥበብም ሳይንስም ነው ይላል። መሪነትንም ሲተረጉመው “ለአንድ ዓላማ ወይም ተግባር ማነሳሳት፣ ተጽዕኖ ማሳደር እና ውጤት እንዲያመጡ ማስቻል ነው” ይለዋል። ስኬታማ መሪዎች የመሪነትን የጥበብ እና ሳይንስ ሁለት ክፍሎች መጥነው መጠቀም የቻሉት ናቸውም ብሏል።
የመሪነት ጠቢባን ሁለት ከመሪዎች ተሳትፎ ጋር ተያያዥ ሐሳቦችን ያነሳሉ። ቴርሞ ሜትር እና ቴርሞ ስታት ይባላሉ ሁለቱ ጽንሰ ሐሳቦች። በአንድ ክፍል ውስጥ ያለን የሙቀት መጠን የሚነግረን መሳሪያ ቴርሞ ሜትር ይባላል። ቅዝቃዜ ካለም የቅዝቃዜውን መጠን ይነግረናል። ቴርሞ ሜትር ሙቀት ወይም ቅዝቃዜን ማሳየት ነው ፋይዳው። በአንጻሩ ቴርሞ ስታት የሚባለው መሳሪያ በክፍል ውስጥ ያለውን ሙቀት ወይም ቅዝቃዜ ያስተካክለዋል። በጣም የሞቀውን ቀዝቀዝ፤ በጣም የቀዘቀዘውን ሞቅ ያደርጋል። የአየሩን ሁኔታ ማስተካከል ነው ስራው።
ጄሰን ባርገር ደራሲ፣ የአመራር አማካሪ እና ስመ ጥር የመድረክ ተናጋሪ ነው። ብዙ መሪዎች፣ የኩባንያ አስተዳዳሪዎች እና ቡድኖች በቴርሞ ሜትር ሁኔታ ላይ ናቸው ይላል። ችግሮችን ከማሳየት አያልፉም። ሊለውጡት አይችሉም። ሁኔታቸው ክፍሉ ውስጥ ማን አለ የሚለውን በማየት ከፍ እና ዝቅ የሚል ነው። ስብሰባው ቀዝቀዝ ያለ ሲመስላቸው እነሱም ቢሯቸው ውስጥ ይቀዘቅዛሉ። ሕይወት ያለ አይመስላቸውም። ሁሉም ነገር ቀዝቃዛ ይሆናል። በአንጻሩ ቢሯቸው ውስጥ ሞቅ ያለ ድባብ ካለ፤ የተነቃቃ ስራ ወይም ግጭት ካለ ሁሉም ሰው ይሞቃል። በየቀኑ ሁኔታቸው እንደየቀኑ ሁኔታ ይለዋወጣል። ከፍ ወይም ዝቅ የሚለት በዙሪያቸው ያለውን ሁኔታ በማየት ነው። አለቃቸው ቆጣ ሲል ስራቸውን ጠበቅ አድርገው ይይዛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አለቃቸው ለቀቅ ሲያደርጋቸው እነሱም ስራ መኖሩን ረስተው ይዘናጋሉ። ስብሰባ አለ የተባሉ ቀን ግርግር ይፈጥራሉ። የሚነዳቸውን ሁኔታ ትከትለው ይጓዛሉ። እነዚህ ሰነፍ መሪዎች ናቸው ይላል ጄሰን ባርገር።
ጄሰን ምርጥ መሪዎችን በቴርሞ ስታት መስሎ ያነሳቸዋል። ቢሯቸው ወይም የሥራ ቦታቸው ምን ዓይነት ድባብ መኖር እንዳለበት የሚወስኑት እነሱ ናቸው። እየገነቡት ያሉት የሥራ ባህል ምን ዓይነት መልክ እንዳለው የቡድን አባላቱ እንዲያውቁ ጥረት ያደርጋሉ። ማለት የሚፈልጉትን በትክክል እና በቋሚነት ይነጋገራሉ። ሌሎችም ምን ዓይነት የሙቀት መጠን ውስጥ ቢገኙ እንደሚበጃቸው ያሰለጥኗቸዋል። ከፍተኛ ጭንቀት፣ ድብርት፣ አለመረጋጋት፣ እና ጡዘት ሲያጋጥም እንዴት ወደ ትክክለኛው መጠን መመለስ እንዳለባቸው ያውቃሉ። ክፍሉ ጸጥታ፣ ድብርት፣ ዝምታ፣ ቅዝቃዜ፣ ሲወርረው ደግሞ ማነቃቃት፣ ሕይወት መዝራት ያውቁበታል። የተፋዘዘውን በድንገት አነቃቅተው መልካም ሁኔታ ውስጥ ያስገቡታል።
ጄሰን ምርጡ መሪ ወደዚህ ሁኔታ በአንድ ቀን አልደረሰም ይላል። በየጊዜው ልምምድ እና ተጋድሎዎችን አድርገው እንጂ። ጠንካራ ሁኔታዎችን መቆጣጠር የሚችሉ መሪዎችን በየደረጃው ያስቀምጣሉ። ቴርሞ ሜትሮች በሁኔታዎች ይለወጣሉ። ቴርሞ ስታቶች ደግሞ ሁኔታዎችን ይለውጣሉ። አንዱ ተናጋሪ ሌላው ሰሪ እንደማለት ነው።
ቴርሞ ሜትር መሪዎች መስታዎቶች ናቸው። ተቋማት በጉዟቸው ትርፍ ኪሳራ፣ ውድቀት መዘጋት እና ሌሎች ችግሮች ሊገጥማቸው ይችላሉ። ሀገራትም እንዲሁ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያልፋሉ። የትክክለኛ እና ጠንካራ መሪዎች መለያ የሚመጣበት ጊዜ ፈተና ነው። “ሀገራችን ችግር ገጥሟታል፣ ጦርነት ኢኮኖሚያችንን አደቀቀው፣ የሰላም እጦት ለዜጎች እንቅስቃሴ ፈተና ሆነ” ብለው የሚናገሩት ቴርሞ ሜትር መሳይ መሪዎች ናቸው። የሆነውን ነገር አብረው እንደ ሕዝብ የሚናገሩ ናቸው። በአንጻሩ ቴርሞ ስታት መሪዎች እንዴት ሰላም ይምጣ፣ እንዴት ኢኮኖሚያችን ያገገግም፣ እንዴትስ ሀገራችን ከችግር ትውጣ ብለው መፍትሔ የሚያመጡ ናቸው። የችግሩን መኖርን እንኳን መሪ ተብዬው መንገደኛ ሰውም ይናገራል። አንዳች መፍትሔ ማምጣት እንጂ መሪ የሚያስብለው።
ጎ ባውንድ ድረገጽ ጠንካራ መሪዎች ሊኖራቸው የሚገባውን ባህሪያት ይገልጻል። ጠንካራ መሪዎች ሁልጊዜ ለውጥን ይጠነስሳሉ። ለለውጥ ምላሽ አይሰጡም። እነሱ ናቸው ለውጥን የሚፈጥሩት። ወደ ስኬት የሚያደርሷቸውን የፈጠራ ዕይታዎች ያስባሉ፤ ይጀምራሉ። ሐሳብ መቀበላቸው ሌላው የጥሩ መሪዎች መገለጫ ነው። ከወዳጆቻቸው፣ ባልደረቦቻቸው እና አሰልጣኞቻቸው ገንቢ ምላሾችን ይቀበላሉ። ገንቢ ትችት እንደ ማደጊያነት ይጠቀሙበታል። ያለማቋረጥ በጉዟቸው ሁሉ ይማራሉ። ስልጠናዎችን ይወስዳሉ፤ የመሪነት ጥናቶችን ያነብባሉ፤ የመሪነት አቅማቸውን ሊያሳድጉ የሚችሉ ስልጠናዎችን ይከታተላሉ። ዓላማ እና እሴታቸውን ለሌሎች ለማሳወቅ ጥሩ የተግባቦት አቅም አላቸው። የሚመሯቸው አባላት እና ቡድኖች መዳረሻቸውን አውቀው እንዲተጉ ያደርጋሉ። ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ ከሁኔታዎች ጋር መላመድ ሌላው የጥሩ መሪ ባህሪ ነው። ሌሎችን ሰዎች ማብቃት እና ማሰልጠን፤ እውቅና እና ሽልማት መስጠትም እንዲሁ መልካም መግለጫቸው ነው ይላል ጎ ባውንድ ድረገጽ።
ዘ ዴይሊ ኮች ገጽ መሪነት የሚያድግ ጥበብ ነው ይላል። ለነገሮች ምላሽ በመስጠት ፉታ ከማጣት ይልቅ ነገሮችን በራስ ዓላማ እና ግብ ማድረግን መልመድ ያስፈልጋል ብሏል። የስሜት ብልህነት፤ ግልጽ ዓላማ፤ ሁኔታዎችን መለወጥ፤ ተጠያቂ እና ሐቀኛ መሆን የምርጥ መሪዎች ባህሪ ነው ይላል።።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም