መሪ ራስ አማን በላይ

0
12

“እህቶቸ እና ወንድሞቼ ሆይ ሃገር ማለት ራሳችሁ ስለሆናችሁ የራሳችሁን ታሪክ ከራሳችሁ ተምራችሁ እና አውቃችሁ ለሌላው አስተምሩ አንጂ ታሪካችሁን ከሌላ አትማሩ። እናንተ የራሳችሁን ታሪክ ካላወቃችሁ ሌሎች የናንተን ታሪክ እንዴት አውቀው እናንተን ሊያስተምሩ ይችላሉ?

በውጭ ሃገር ሰዎች የተጻፉት ሊሆን ይችላል ተብለው በግምገማ (በግምት) የተጻፉ እንጂ ከእውነተኛው ታሪክ የተገለበጡ አላገኘሁም” በማለት የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው መቅድም ላይ  ያሰፈሩት  መሪ ራስ አማን በላይ ናቸው።  ለመሆኑ መሪ ራስ አማን በላይ ማን ናቸው?   ይህ ጽሁፍ ምላሹን ያስነብበናል።

መሪ ራስ አማን በላይ የታሪክ ተመራማሪ፣ የነገረ መለኮት አዋቂ እና የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክን ጨምሮ 24 መጽሐፍትን ለንባብ ያበቁ ታላቅ ደራሲ ናቸው። መሪ ራስ አማን በ1942 ዓ.ም በሰሜን ጎንደር በለሳ ነው የተወለዱት። የልጅነት እድገታቸው በቤተክህነት አካባቢ ስለነበር በቀላሉ ዘመናዊ ትምህርትን ለማወቅ እንዳስቻላቸው ፕረስ ዶት ኢት ድረ ገጽ ላይ ተገልጿል።

“መሪ ራስ” የሚለውን የማዕረግ መጠሪያ ከስማቸው አስቀድመው ይጠቀማሉ። ምክንያታቸው ደግሞ በነአፄ ይኩኖ አምላክ ዘመን ንጉሡ ዘንድ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ተቀብሎ መልዕክቱን በጽሑፍ ለሚያደርስ ባለሟል የሚሰጥ ማዕረግ በመሆኑ እሳቸውም ዘመኑን ለማስታወስ እንደተጠሙበት ተገልጿል።

መሪ ራስ አማን በላይ በ1957 ዓ.ም የትውልድ ሃገራቸውን በለሳን ትተው የቤተክህነት ትምህርት ፍለጋ ወጡ። ቅኔ መወድስ፣ አቋቋም፣ ድጓ እና ጾመ ድጓ፣ ቅዳሴ፣ ብሉይ እና ሃዲስ እንዲሁም ዜማን ከአንዱ ወደሌላው አካባቢ እየተዘዋወሩ ተምረዋል።

የዕጽዋት መድሃኒትን፣ የሃረግ ስዕልን፣ የኢትዮጵያ ታሪክ አቡሻክርን /ባህረ ሀሳብን/ ለማወቅ ጎጃም፣ ወሎ እና ሸዋን ዞረዋል። በዚህም ምክንያት ከሰላሳ ዓመታት በላይ ወደ ትውልድ ቀያቸው ሳይመለሱ ዕውቀት ፍለጋ ተጠምደው ማሳለፋቸውንም የህይወት ታሪካቸው ያስገነዝባል።

መሪ ራስ አማን በላይ መጀመሪያ የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ጥበብ ሥራዎች ተረጎሙ። የዜማ ልክን መሠረት አድርገውም የጽሑፍ ሥራቸውን አሀዱ ብለው ጀመሩ። በወቅቱ መሪ ራስ አማን ውስጣቸው ወደብህትውና ዓለም ያደላ ነበር። አጋጣሚ ሆኖ በቅርብ ካገኟቸው ሁለት መነኮሳት ጋር ወደ ግብፅ ሃገር ለመሄድ ጉዞ ጀመሩ። ሱዳን ደርሰው ለሱባኤ ከገቡበት ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ በርከት ያሉ የቤተ ክርስቲያን ዕቃዎች፣ መጽሐፍት እና ውድ ጌጣ ጌጦች በሳጥን ተቀብረው ቋጥኝ ስር አገኙ። የተገኙት መጽሐፍት በሃገራችን ያልነበሩ ግን ስለኢትዮጵያ ታሪክ የሚያወሱ የብራና ላይ ጽሑፎች ነበሩ። አብረዋቸው የነበሩ ሰዎች ከተገኙት ንብረቶች መካከል ተሽጠው ይጠቅሙናል ያሏቸውን መርጠው ወሰዱ፤ መሪ ራስ አማንም ፀሑፎችን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።

ሃገር ቤት አንደደረሱም ወደ ሸዋ በማምራት “ሽንኩርት ሚካኤል” ከሚባል ቦታ ተቀመጡ። ከዚያም በግዕዝ፣ በሱባ ቋንቋ እና በጥንት አማርኛ የተጻፉትን ከሱዳን ሃገር የተገኙ መጽሐፍትን በማስተርጎም  የሚታወቁበትን “የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ” መጽሐፍ ለመጻፍ በቁ። መጽሐፉን ጽፈው ያጠናቀቁት በ1962 ዓ.ም ነበር። በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቶ ለመታተም የበቃው ግን በ1985 ዓ.ም ነው።

መሪ ራስ አማን በላይ ካሳተሟቸው 24 መጽሐፍት መካከል፤ የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ፣ የሱባ ቋንቋ መዝገበ ቃላት፣ መጽሐፈ ብሩክ /ብሩክ ዣንሸዋ/፣ የልቤ ወዳጅ፣ የሰው ዘር ልጅ፣ ምክር ከእኔ ስማ አንተ ወገኔ፣ መጽሐፈ ሰረገላ ታቦር፣ መጽሐፈ ፈውስ፣ ብርሃነ ህይወት ዘበአማን የሚሉት ይገኙበታል።

የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ መጽሐፋቸው ላይ የደራሲውን ስም የጻፉት “ኤ. ኤም. በላይ” በሚል ነው። ለምን እንደዚህ ሆኖ ተጻፈ ተብለው ሲጠየቁ “በጥንቱ የነገድ ታሪክ ላይ መጽሐፍ የሚጽፍ ሰው እድሜው አጭር ነው ተብሎ ይነገራል። ስሜም እንዳይታወቅ በምህፃረ ቃል ተጠቀምሁ” በማለት መልስ ሰጥተዋል።

ስለሃገራቸው ከፍተኛ ፍቅር የነበራቸው መሪ ራስ አማን ተደብቆ የቆየውን የኢትዮጵያ ታሪክ ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገር ቆይታቸው ሁሌም መጻሕፍትን ከመጻፍ ተለይተው አያውቁም። ህይወታቸውን በሙሉ ስለሃገር እና ወገናቸው ታሪክ በመጻፍ ማሳለፋቸውን የሰምና ወርቅ (ነፃና ሁለገብ የጥናት እና ምርምር መጽሔት) ያስረዳል።

መሪ ራስ አማን በላይ መጽሐፎቻቸውን ለማሳተም በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል። ነገደ ኢትዮጵያ መጽሐፋቸው የጀርባ ገጽ ላይም እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፤ “በጊዜው የነገሥታትን ታሪክ ማሳተም እና ማወደስ አደገኛ ነበር። ሁኔታውም በጣም አሰጋኝ፤ እናም ብዙ ሺ ማይልስ ከኔ ጋር ለብዙ ዓመታት ተንከራተተ። አሁን ጊዜውና አጋጣሚው ፈቅዶ፤ አቋርጦ ከሄደበት ከምድረ አሜሪካ በሃገሩ በኢትዮጵያ ወንድሞቸ ብርታት ለመታተም በቃ። ቀስ በቀስም እውነተኛው የኢትዮጵያ ታሪክ እየታወቀ ይሄዳል።”

ታላቁ የጥበብ ሰው፣ ተመራማሪ፣ ደራሲ እና ፈላስፋ መሪ ራስ አማን በላይ ይኖሩበት ከነበረው ሰሜን አሜሪካ ሎሳንጀለስ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በ65 ዓመታቸው የካቲት 21 ቀን 2006 ዓ.ም ህይወታቸው አለፈ።

ታላቁ ስራቸው ግን ህያው ምስክር ሆኖ ታሪካቸውን ሲያስጠራ፤ ሃገር እና ወገናቸውን ሲያኮራ ይኖራል። አኛም በመሪ ራስ አማን በላይ ስራዎች እና የህይወት ታሪካቸው ዙሪያ ለዛሬ ያልነውን በዚሁ ቋጨን፤ ቸር ይግጠመን።

 

ሳምንቱ በታሪክ

 

መስከረም አንድ

መላው ዓለም ጉድ ያለበት ዘግናኙ የሽብር ጥቃት የተፈፀመው መስከረም አንድ ቀን 2000 ዓ.ም ነበር።

በአሜሪካ ሰማይ ላይ አራት ትላልቅ የመንገደኞች አውሮፕላኖች በታቀደ መልኩ  ተጠልፈው በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ላይ ተከሰከሱ፤ እናም ወደ 3000 የሚጠጋ ሕይወት መቅጠፉ የተሰማበት በአሜሪካ ታሪክ አስከፊው አደጋ ነበር።

አሸባሪዎቹ መንገደኛ መስለው በመግባት አውሮፕላኖቹን በማስገደድ በታቀዱት ከተሞች እና ሕንፃዎች ጋር እንዲላተሙ የማድረግ የአጥፍቶ መጥፋት ዘግኛኙን ተልእኮ በመፈፀም ከባድ እና አሰቃቂ ውድመት አስከተሉ።

አሜሪካም የበቀል እርምጃ እንድትወስድ በቁጣ ያስነሳ እና ይፋዊ ፀረ ሽብርተኝነትን ጦርነት እንዲታወጅም ምክንያት ነበር።

ምንጭ፦ሂስትሪፕሌስ

 

ጃንሆይ ወረዱ

መስከረም 2 ቀን 1966 ዓ.ም ዓ/ም   58 ዓመታትን በሥልጣን፤ መጀመሪያ በአልጋ ወራሽነትና የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴነት፤ ከመጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በንጉሠ ነገሥትነት ኢትዮጵያን የመሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በደርግ የአብዮት ሥርዓት ተሽረው ከሥልጣን ወረዱ።

ኢትዮጵያን ለ44 ዓመታት ያስተዳደሩት ጃንሆይ፤ የፋሽስት ኢጣሊያን ዳግም ወረራ በአለማቀፍ መድረክ በመሞገት ዲፕሎማሲያዊም ወታደራዊም ድል አስመዝግበው ነፃነት ያስከበሩ ታላቅ መሪ ነበሩ።

ከድል በኋላ የኢትዮጵያን መንግሥት እንደገና መልሶ በመገንባት ወደ ለውጥ ማራመድ ጀምረው ነበር። ለውጡ ግን ብዙም ተስፋ የተጣለበትን ያህል ሊሄድ ባለመቻሉ በንጉሡ ላይ ተደጋጋሚ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች እንዲደረጉ ክፍተት ፈጥሯል። መስከረም 2 ቀን ከተሳካው ግልበጣ በፊት ሁለት ያልተሳኩ ሙከራዎችም ተደርገው ነበር።

 

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር የጳጉሜን 3   ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here