መራራ ሐቆች

0
171

እናት በአንድ ማሕጸኗ የጸነሰቻቸውን ልጆች አንዱን ከሌላ ማበላለጧ ይገርመን ይሆናል። እውነታው ግን እኩል ሚባል ነገር አለመኖሩ ነው የዓለም ሐቅ።

ምድራዊ የሰው ልጅ በአኗኗሩ የተስማማባቸው የዘመናት እውነቶች አሉት። እውነት ደግሞ አንፃራዊ መሆኑ ለአንዱ የተስማማው ለሌላው ይጎረብጣል።

በአንድ ወገን ስድስት ሆኖ የታየው በሌላ ወገን ዘጠኝ ይሆናል። ከሳሽ ተከሳሽ እና ዳኛን ወስደን የእውነትን ሦስት አንጻር እንመልከት።

ከሳሽ የሚለው አለው፣ ተከሳሽም በአንጻሩ የሚናገረው አለው::ሽማግሌ ወይም ዳኛው ከህይወት ልምዱ በመነሳት ፍርድን ከራሱ እውነት አንጻር ይሠጣል። እውነትን በሦስት ወገን ብንመለከታትም እንኳን ሦስቱም ወገን የማይደፍሩት የሐቅ መስመር እናገኛለን። ሁሉም የራሱን ፍላጎት ለማሳካት የማይደፍራት የመሐል ድንግል እውነት ሁልጊዜም አለችን::

የሰው ልጅ ሕይወቱ በአመዛኙ ጨፍጋጋነት ይበዛዋል። ደስታን ቢያገኝም ረጅም ጊዜ የሚቆየው ደመናማው የኃዘን ስሜት ውስጥ ነው። አንዱ በሌላ መተካካት እና መፈራረቁም ቢኖር ምድራዊው ሕይወት የሰው ልጅ እውነትን ከመቀበሉ እና ከመካዱ የሚነሱ ናቸው።

እያደር አዲስ ነው ሕይወት። የማንለውጣቸው፣ ለዘመናት የሸሸናቸው ምድራዊ ሕይወታችን ውስጥ ያሉ ሐቆችን መቀበል እና መሸሽ በአኗኗራችን ልዩነትን ይፈጥራል። ብዙዎቻችን በምድራዊ ሐቅ እንሳደዳለን። ሸሽተን ላናመልጥ ብዙ ርቀትን እንጎዛለን። ግን ከሐቅ መሸሽ የቻለ ሰው ማን ይኖር ይሆን?

እንደ ኮሶ መራር ቢሆንም ሐቅ ሐቅ ነው። አንዳንዱን እንቀበለዋለን፣ ሌላውን እንለውጠዋለን፣ ቀሪውን ደግሞ ከአኗኗራችን ጋር እናለማምደዋለን። ብዙዎችን ሐቆች ስለምንሸሻቸው እና ጆሯችንን ስለምናዞርባቸው ሲገጥሙን በትራቸውን ለመቻል ጉልበት አቅም ያሳንሳል። እየጎመዘዙን የምንቀበላቸው፣ ተገደን እጅ የምንሰጥባቸው የሰው ልጅ ምድራዊ እውነቶች አሉ።

ሰው በመሆናችን ብቻ በምድራዊ ሕይወታችን የማይቀሩልን ሐቆች አሉ ሲል ጁሌ ራይሞንድ ሲቲ ስኬፕ ካውንሲሊንግ ድረ ገጽ ላይ ሐሳቦችን አስፍሯል። እነዚህ እውነቶች የሰው ልጅ በዘር፣ በአካባቢ፣  በቋንቋ፣ በኢኮኖሚ ደረጃ፣ በስልጣን እና በሃይማኖት ሳይገደብ የሰው ፍጡር ሁሉ የሚቀበላቸው አይቀሬ እጣዎች ናቸው። ጁሌ ራይምንድ እነዚህን እውነቶች አላምደን ከመቀበል በቀር በመፍራት እና በመሸሽ ለውጥ እንደማይመጣ ጽፏል።

የመጀመሪያው የሰው ልጆችን የሚፈትነው ሐቅ መለወጥ ወይም ለውጥ ነው። በህይወት ከማይለወጡ እና ቋሚ ነገሮች መካከል አንዱ ለውጥ ነው። ሁልጊዜም፣ የትም፣  በምንም ሁኔታ ውስጥ መለወጥ አይቋረጥም። መወለድ፣ ማደግ፣ መጎልመስ እና ማርጀትን ሲጓዙ ሳናያቸው አንድ ቀን ራሳችንን ሳናስተውል ለውጥ ምን ያህል ጉልበት እንዳለው እንገነዘባቸዋለን። በየቀኑ ምንም ነገር የሚለወጥ አይመስለንም ፣ ከቀናት በኋላ ጠብታውና አለቱን እየሸረሸረች ሰብራው እናያለን። እናት የልጇን ማደግ አይታ አትገረምም፣ ጎረቤት ግን እንዴ ልጅሽ አደገች ሲሉ ይደመጣሉ። ለውጥ መስመሩ ስውር ነው። በውጤቱ እንጂ በሒደቱ ብዙም አያስደስትም። መጥፎ ነገርን ለመለወጥ ጥረት የሚያደርግ ሰው ሁል ጊዜ ትናንሽ ተግባራትን ቢከውን ተራራን በአካፋ የማፍረስ ድርጊት ውስጥ የገባ ይመስለዋል። በድምር ውጤት ግን ተአምር የሚባልን ተግባር እንዲፈጽሙ ይረዳል።

ለውጥ አይቀሬ ከሆነ ወደ መልካም ነገር መለወጥን ይመክራል ጸሐፊው ጁሌ።

ሁለተኛው እሽ ብለን የማንቀበለው ምድራዊ ሐቅ ማጣት ነው። ሁሉም ሰው በሕይወቱ የማጣት ገጠመኝ አለው። ሞት ፣ንብረት፣ ሰው እና እቅዶቻችንን ልናጣ እንችላለን። የወደፊት ተስፋችንን የማጣት ገጠመኝ ሰለባ ልንሆን እንችላለን። የህይወታችን አንዱ አካል ሆኖ ማጣት አብሮን ይኖራል። የለውጥን ባሕርይ ተከትሎ ማጣት ሁልጊዜ ከማግኘት በተቃራኒው ገጽ ይመጣል። ለሰው ልጅ ነገሮች በሁለት አንጻር ተሰጥተውታል። ማግኘት እንዳለ ማጣትም አለ:: ሰው ከአንዱ ወጥቶ ወደ ሌላው ገጽ ሲሸጋገር በንቃት ማስተዋል ይጀምራል። አግኝቶ ሲያጣ የነበረውን ነገር ዋጋ ይገመግማል።አጥቶ ሲያገኝ ደግሞ በክፋት እና ጥረት ያገኘውን ደስታ ያጣጥመዋል። ማጣት ነው የጥጋብን ስሜት ውብ የሚያደርግልን። ፉንጋዋ ናት ቆንጆዋን የምናወዳድርበት:: ጨካኙ ነው ሩህሩህን የሚያስመሰግነው። ጥላቻ ነው ፍቅርን የሚያሳየን።

ስፔንሰር ግሪንበርግ ድረ ገጽ በተመሳሳይ የህይወት አካል የሆነ አስቸጋሪ እውነቶችን ዘርዝሯል። እነዚህን እውነቶች ሰዎች  ራሳቸውን በመዋሸት፣ ከሐሳባቸው መዝገብ በማውጣት፣ የማይለውጡትን በመቀበል እና የሚችሉትን በመለወጥ ውስጥ ያልፉባቸዋል ይላል። እነዚህን እውነቶች አልቀበልም ወይም ስለ እነሱ ማንሳት አልፈልግም የምትሉ ከሆነ ግን የጻፍሁትን አታንብቡት ይላል ስፔንሰር ግሪንበርግ።

የመጀመሪያው ጉዳይ የሰው ልጅ ሁሉ ከንቱ እና ሟች ነው። የትናንት ዝነኛ እና ተሰሚ፣ ተፈሪ እና ምድር የሚርድላቸው ሰዎች ዛሬ አፈር ውስጥ ናቸው። ሞት ሁል ጊዜ አዲስ ነው። ከሞቱ አሟሟቱ እንደሚባለው ሰው ጎረቤቱን ቀብሮ ሲመለስ እሱ ወይም ቤተሰቡ በሟች ቦታ አፈር ውስጥ እንደሚቀበሩ ለመቀበል ይቸገራል። ሞትን አታንሳብኝ የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ሞቱ ባይቀር እንኳን የሰው ልጅ ወደ ሞት የሚጠራበት ቅጽበት ሁልጊዜ አዲስ እና አሳዛኝ ነው። ለዚህ ይመስለኛል የሀገራችን ሰው በግጥሙ “አሞራ እና ዶሮ ወይ እኛ እና ሞት፣ ሲሄድ መረሳሳት ሲመጣ መንጫጫት” በማለት የሚገልጸው። ዶሮ አሞራ በመጣባት ጊዜ ተሰብስባ ትንጫጫለች። አሞራው ዘወር እንዳለ ደግሞ ሁሉም ነገር ይረሳና ማሽካካት ይጀመራል።

የሰው ልጅም ከሞት ጋር ያለው ግብግብ ይህንን ይመስላል። አኗኗሩ ውስጥ ስታዩት የሰው ልጅ የሚሞት አይመስልም። አንዳች ዘላለማዊ ፍጥረት እንጂ። እውነታው መቃብር ውስጥ ነው ያለው።  የትኛውም ዘመን ላይ በተለይ በኢትዮጵያ ሞትን መቀበል ከባድ ነው። ብዙዎች በዘመድ እና በቤተሰቦቻቸው ሞት ምክንያት የአዕምሮ ጤና  እክል ገጥሟቸዋል፣ ስራቸውን፣ ዓላማቸውን ትተው ተሰናክለዋል። የእምነት ተቋማት ሞት ረፍት ነው፣ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚደረግ ጉዞ ነው ብለው በማጽናናት ቢያስተምሩም ሞትን በጸጋ መቀበል ለሰው ልጅ ዘግናኝ ሐቅ ነው።

ሌላኛው ሐሳብ ደግሞ የሰው ልጅ የመረጠውን አይደለም የሚለው ነው። ድንገት፣ ሳንዘጋጅ፣ ሳንጠይቅ፣ ሳንመርጥ ፈጣሪያችን በፈለገው ዓላማ ነው የተፈጠረነው። አንዳንዱ በመልካም ዕድል፣ ሌላው በጤና ማጣት ቀሪው በሀብታም ቤተሰብ፣ ገሚሱ ደግሞ አሳዳጊ በማጣት ይህችን ምድር ይቀላቀላል። ፈጣሪ ጤናማ ማድረግ ሲችል በሽተኛ አድርጎ ከፈጠረህ ብዙ ማትቀይረው የጤና ሁኔታ ይኖርሃል። ፈጣሪ በድህነት የሚኖር ቤተሰብ ውስጥ እንድትወለድ ካደረገህ ያንን ሁኔታ ወደኋላ ተመልሰህ መቀየር አትችልም። ትናንትን በመቀበል የዛሬውን ጤናህን ዓለም በምትፈልገው መስመር ቀይሰህ መኖር ትችላለህ። ወይ ደግሞ የወላጆችህን የድህነት ታሪክ መቀየር የምትችልበትን ጠንካራ አቅም መፍጠር ትችላለህ በማለት ስፔንሰር ግሪንበርግ ድረ ገጽ አስፍሯል።

ውግዘት ይደርስብሃል የሚለው መራር ሐቅ ቀጥለን የምናገኘው ጉዳይ ነው። አንዳንድ ሰዎች ከምንም ተነስተው ሊጠሉን ይችላሉ። የትኛውንም መልካም ተግባር ብንሰራ ሁሉም ሰው ሊቀበለን እና ሊያጨበጭብልን አይችልም:: የኛ ጉዳይ ምንም የማይመስላቸው ይኖራሉ። ተግባሩን የፈጸምንበትን መንገድ የሚጠሉት ይኖራሉ። እኛን እንዲሁ ሲያዩን የሚጠሉን ይኖራሉ። እኔ የበለጠ አሳምሬ ልሰራው እችል ነበር የሚሉ ተፎካካሪዎቻችን ይኖራሉ። በቅናት መንፈስም የሚበሳጩብን ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል።

ሁሉም ሰው ሊያደንቀን እና ሊቀበለን  እንደማይችል መገንዘብ መቻል አኗኗራችንን ብልህ ያለው ያደርገዋል። ሁልጊዜም በሚደግፉን እና ሕልማችንን በሚቀበሉ ሰዎች ዙሪያ መሆን ተገቢነት አለው። ከሚበሳጩብን ይልቅ የሚደሰቱብንን ሰዎች መቁጠር ለዚህ ጎምዛዛ ሐቅ መድኀኒቱ ነው። ታንቶዊ ጊላንግ ሚዲየም ድረገጽ ላይ ባስቀመጠው ጽሑፍ “አንዳንድ ጊዜ እውነት ምቾት ይነሳል፤በተለይ ፊት ለፊት ሲሆን” ይላል። የሰው ልጅ እውነቱን ባወቀ መጠን የበለጠ ይጎዳል። እስኪ ነገሩን ምሳሌ ሰጥተን እናፍታታው። አንድ ታዳጊ ወጣት አንዲትን ኮረዳ አፍቅሮ በፍቅር አነሁልላው ይከታተላታል እንበል። ለልጁ ምንም የፍቅር ስሜት የላትም።

እንዲያውም ልጁን ስታየው ያስጠላታል። ትንቀዋለች እንበል። የፍቅር ጥያቄውን ሲያቀርብላትም “አሁን እኔ ፍቅረኛ መያዝ አልፈልግም፤ ትምህርቴ ላይ ነው ማተኮር የምፈልገው” ትለዋለች። እየተከተለ ስላስቸገራት ነው። ይህ የልጅቱ ምላሽ መራራውን ሐቅ አጣፍጦ ለመዋጥ የተደረገ ርህራሄ የታከለበት ንግግር ነው። “ታስጠላኛለህ፣ አልወድህም” ብትለው ይህ ልጅ ስሜቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል። ደሀ ስለ ሆንሁ ነው፤ ቆንጆ ስላልሆንሁ ነው እያለ ራሱን በበታችነት ስሜት መበደል ይጀምር ነበር። እውነት የዚህን ያህል ቢመርም መቀበሉ ግድ የሚሆንባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ።

ታንቶዊ የሰው ልጅ በሕይወት የሚገጥሙትን ሐቆች በመዘርዘር፤ ሐቆችን በአዎንታዊ መልኩ ከመቀበል በቀር ሌላ አማራጭ አልተገኘም ይላል። ሁሉንም ሰው ማስደሰት አይቻልም። በሕይወት እስካለህ ሁልጊዜ ስሕተት ትሰራለህ። ሁልጊዜም ፍጹም መሆን አትችልም። የምታፈቅረው ሰው የበለጠ ይጎዳህ እና ያሳዝንሀል። የሰዎችን የስኬት ፈለግ መቅዳት (ኮፒ ማድረግ ) አትችልም:: እንዲሁም ጊዜን ይዘህ ማቆም እና ወደ ኋላ መመለስ አትችልም የሚሉ ሐቆችን አስፍሯል።

ከዚሁ በተመሳሳይ ዴይስ ኢን ዘደስት ድረገጽ ሕይወታችን በደልዳላ ሜዳ የሚጓዝ አይደለም በማለት የኑሮ አሰቃቂ ሐቆችን ተገንዝቦ መጓዝ ነጻ የሚያወጣው መስመር ነው ሲል ጽፏል። በሕይወት ቋሚ የሚባል ነገር የለም የሚለው ሐሳብ ቀድሞ ይመጣል። የመጣው ይሄዳል፤ወደ ሕይወታችን  የሚመጡ ሰዎች ብዙ ምክንያቶችን ይዘው ሊቀርቡን ይችላሉ። የሰዎች መምጣት እና  መሄድ በራሳቸው ቁጥጥር ውስጥ ያለ ጉዳይ ነው። በራሳቸው ትክክለኛ ጊዜ የሚከወን ተግባርም ነው። የቀረበን ወዳጃችን ያልነው ሰው ቢርቀን የመጣበትን ዓላማ አሳክቶ  በክክለኛው ጊዜ መሄዱ ርግጥ ነው። ሁሉንም ግንኙነታችንን ስንመለከተው የሚያስተምረን አንዳች ጥሩ ነገር ይኖረዋል። አሮጌው ግንኙነት በአዲስ መተካቱ አይቀሬ ነው። መሄድ ሲኖር መምጣት አለና።

የሕይወት አስቸጋሪ ጊዜያትን መጋፈጥ ግዴታ ነው። ያለ እነዚያ ፈተናዎች የሰው ልጆች ማንነት  ሊሰራ አይችልም:: ጽናት እና ብርታትን የምንማረው በአስቸጋሪ ፈተናዎች ውስጥ በማለፍ ነው። ፈተናዎች የማይቀሩ ናቸው። ችግሮች እና ፈተናዎች የሰውን ልጅ ገፍተው የበለጠ ማግኘት፣መፍጠር፣መመልከት  ላይ ይጥሉታል። ምድር ላይ ያሉ መልካም ነገሮች በሙሉ በችግር ውስጥ በማለፍ የተገኙ ናቸው።

ሰው በሚያፈቅረው የበለጠ ሲጎዳ እናያለን። ሌላው ሐቅ ነው። ከጠላት የበለጠ ሰው በወዳጁ ተጎድቶ አይተናል። ይህ ሐሳብ የእናቴን እና የአካባቢዬን አባባል ያስታውሰኛል። እናቴ “ደሜ መራራ ነው” ትላለች። አካባቢዬ ደግሞ “እጄ አመድ አፋሽ ነው” ይላል። የበለጠ የቀረቧችሁ፤ ምስጢራችሁን የተጋሩ፤ የምትጨነቁላቸው ሰዎች በሕይወታችሁ ከባድ ኀዘን እንዲሰማችሁ ያደርጓችኋል። በርግጥ ሊጎዱን አስበው ላይሆን ይችላል፤ ወይ ደግሞ  የሚፈልጉትን ጥቅም  ለማግኘት የውሸት ቀርበውንም ሊሆን ይችላል:: አለዚያም በበግ ለምድ ተኩላ ሆነው ቀርበውን ቢሆንስ? በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን የበለጠ የምንጎዳው ዋጋ በምንሰጣቸው እና ግድ በሚለን ሰዎች ነው። ከእነሱ ብዙ ስለምንጠብቅ  ነገሩን እኛም የበለጠ ክብደት ሰጥተን እንብሰለሰላለን።

የመጨረሻው ሐቅ፤ ማንም ነጻ ሊያወጣን አይችልም። የምንወዳቸው ሰዎች በምላሹ ክብር እና ፍቅር ሊሰጡን ይችላሉ:: እኛ ባቆምን ቅጽበት ሁሉም ያቆማል። ለዚህ ነው ራሳችንን በራሳችን ነጻ ለማውጣት ጀግኖች መሆን ያለብን። ምድራዊው ሕይወት በመስጠት እና መቀበል እንዲሁም በአሸናፊዎች እና ተሻናፊዎች መስተጋብር የቆመ ነው። የጥላሁን ገሠሠ “ከሌለህ የለህም” እና የኤፍሬም ታምሩ “መልካም ውለታ” ዘፈኖች  ከራስ በላይ ማንም እንደሌለን በሚገባ ያሳያሉ።

የማይቀየሩ፣የምንቀበላቸው እና የምንቀይራቸው ምድራዊ ሰቆቃዎች አሉ። ሁሉንም ለሕይወት በሚበጅ መልኩ ማስተናገድ በሕይወት ጉዞ መሐል በወጀብ እንዳንወሰድ ያግዘናል። በአፈጣጠራችን፣ በዕድላችን፣ በዕድሜያችን፣ በሀገራችን፣ በዘራችን፣ በሥራችን እና በሌሎች ጉዳዮች በማሳበብ እንዳንደክም የሚረዱን ሐቆችን በብልሀት መቀበል ነው።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here