መርዶ አርጂዎቹ ግቦች

0
61

ይህንን ተጫዋች ብዙዎች በአርሰናል ቤት ያውቁታል፤ ሁለገብ አማካይ ነው፤ በትንሽ እድሜው አምበል በመሆን ባለክብረወሰን ነው- አሮን ራምሴ። ዌልሳዊው የቀድሞ የእግር ኳስ ኮከብ በካርዲፍ ሲቲ አድጎ በኤምሬትስ እና በጁቬንቱስ ስቴዲየም ምርጥ ጊዜ ያሳለፈ የመሀል ሜዳ ተጫዋች ነበር። የቀድሞው አማካይ ለኖቲንግሀም ፎረስት፣ ሬንጀርስ እና ኒስም ተጫውቶ አሳልፏል።

አሮን ራምሴ በእግር ኳስ ህይወቱ የሊግ ዋንጫን ማሳካት የቻለው ግን “ከአሮጊቶች” ጋር ነው። ከጁቬንቱስ ጋር የሴሪ ኤ፣ የኮፓ ኢታሊያ እና የሱፐር ኮፓ ኢታሊያ ዋንጫንም አሳክቷል። በአጠቃላይ በተለያዩ ክለቦች 542 ጨዋታዎችን አከናውኖ 79 ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል። ራምሴ የሀገሩን ብሄራዊ ቡድን ረዘም ላሉ ጊዜያት አገልግሏል። ከ20 ዓመት እድሜው ጀምሮ  ብሄራዊ ቡድኑን በአምበልነት የመራው ራምሴ በትንሽ እድሜው ቡድኑን በመምራት  ባለክብረወሰንም ጭምር ነው።

የ34 ዓመቱ አሮን ራምሴ የ204/25 የእንግሊዝ ሻምፒዮን ሺፕ ውድድር ከመጠናቀቁ ሦስት ጨዋታዎች ቀደም ብሎ የካርዲፍ ሲቲ አሰልጣኝ ሆኖ መቀጠሩ የሚታወስ ነው። የቀድሞው የካርዲፍ ሲቲ አሰልጣኝ ኦመር ሪዛ ከካርዲፍ ሲቲ ጋር መለያየቱን ተከትሎ ሚያዚያ 19 ቀን 2025 እ.አ.አ አሮን ራምሴ የልጅነት ክለቡ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆኖ ተሹሟል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የተቀመጠውን እና አስከፊ የውድድር ዓመት ያሳለፈውን ካርዲፍን ሲቲን ለመታደግ ኃላፊነቱን ቢረከብም አልተሳካለትም፤ ክለቡም ወደ ታችኛው የሊግ እረከን ወርዷል።

እግር ኳስ ሁል ጊዜ አስገራሚ ታሪኮችን ትቶ ያልፋል፤ በዌልሳዊው የቀድሞ ተጫዋች አሮን ራምሴ የእግር ኳስ ህይወት አስገራሚ እና እንግዳ ታሪኮች ተፈጥረዋል፤ እየተፈጠሩም ነው። አጋጣሚውን ግን ከእርግማን ጋር በማያያዝ ብዙዎች እየወነጀሉት ነው። ራምሴ ግብ አስቆጠረ ማለት በፕላኔታችን አንድ አሳዛኝ ዜና ይሰማል። ክስተቱ መደጋገሙን ተከትሎ “የራምሴ እርግማን” የሚል ስም አሰጥቶታል። በተለይ ተጫዋቹ በኤምሬትስ በነበረው የ11 ዓመታት ቆይታ ያስቆጠራቸው ግቦች ደመ መራራ አድርገውታል።

አሮን ራምሴ የካርዲፍ ሲቲ አሰልጣኝ ሆኖ በተሾመ በሁለተኛው ቀን የሮማው ካቶሊክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳ ፍራንሲስ ህይወታቸው አልፏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከሳንባ ምች ጋር መያያዙን  የሜል ስፖርት መረጃ ያመለክታል። በባእድ አምልኮ ልምድ ውስጥ የሚገኙ የእግር ኳስ ደጋፊዎች የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱን ሞት ከቀድሞው የአርሰናሉ አማካይ ጋር አያይዘውታል። “የአሮን ራምሴ እርግማን” እየተባለ የሚጠራው አጉል እምነት ራምሴ ግብ ካስቆጠረ ትልቅ ስም ያላቸው ሰዎች ህይወታቸው ያልፋል።

ምንም እንኳ ራምሴ በቅርቡ ግብ ባያስቆጥርም ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆኖ ግን ተቀጥሯል። ይህንን ተከትሎ ነው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ የሞቱት በሚል ብዙዎች ማመናቸውን የሜል ስፖርት ዘገባ አመልክቷል። ራምሴ በጥቅምት 21 ቀን 2008 እ.አ.አ አርሰናል ከፌነርባቼ ጋር በነበረው ጨዋታ ለመድፈኞቹ ዋናው ቡድን የመጀመሪያ ግቡን አስቆጥሯል።

በማግስቱ እንግሊዛዊው ተዋናይ እና የቴሌቭዥን አቅራቢ ዴቪድ ሎይድ ግሬዲት ህይወት አልፏል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ራምሴ ግብ ሲያስቆጥር በዓለማችን ላይ ዝነኛ እና ታዋቂ የሆነ ሰው ወደ መቃብር ይወርዳል የሚል አጉል እምነት በእግር ኳስ ማህበረሰቡ ዘንድ ተፈጠረ። የራምሴ ኳስ እና መረብ ማገናኘትም እንደ እርግማን እና መጥፎ እድል መታየት ጀመረ።

በወርሃ ነሐሴ 2009 እ.አ.አ አርሰናል ከፖርትስማውዝ በነበራቸው ጨዋታ ራምሴ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል። ታዲያ ከአራት ቀናት በኋላ ታዋቂው የአሜሪካ ፖለቲከኛ ቴዲ ኬነዲ ህይወት ማለፉን የሜትሮ ስፖርት መረጃ አስነብቧል። የ34 ዓመቱ ራምሴ በተጫዋችነት ዘመኑ በአጠቃላይ 79 ግቦችን አስቆጥሯል። ከእነዚህ ግቦች መካከል 30 ግቦች  በተቆጠሩ ማግስት በእያንዳንዳቸው ግቦች የአንድ ዝነኛ እና ታዋቂ ሰው ህይወት አልፏል።

የእግር ኳስ ደጋፊዎች “የአሮን ራምሴ እርግማን” አለ ብለው ማመን የጀመሩት እ.አ.አ ከግንቦት 2011ጀምሮ ነው። በርካታ የአውሮፓ የስፖርት መገናኛ አውታሮችም ጉዳዩን ትኩረት መስጠት የጀመሩት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው። ግንቦት ሁለት ቀን 2011 እ.አ.አ አርሰናል በኤምሬትስ ማንቸስተር ዩናይትድን ባስተናገደበት ጨዋታ አሮን ራምሴ የማሸነፊያ ግቧን አስቆጥሯል። ከቀናት በኋላ የአሸባሪው አል ቃኢዳ መሪ የነበረው ኦሳማ ቢላደን መሞቱ ተረጋገጠ።

በዚሁ ዓመት ጥቅምት 2011 እ.አ.አ በሰሜን ለንደን ደርቢ አርሰናል ከቶትንሀም ሆትስፐርስ ጋር በነበረው የፕሪሚየር ሊግ መርሀግብር አሮን ራምሴ ግብ አስቆጥሯል። ታዲያ ከሦስት ቀናት በኋላ የአፕል ካምፓኒ መስራቹ ስቴቭ ጆብስ ህይወት ማለፉ ተነገረ። በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ተጨማሪ አሳዛኝ ዜና ተሰምቷል። አርሰናል ከፈረንሳዩ ክለብ ማርሴ ጋር በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በነበረው ጨዋታ ራምሴ የማሸነፊያ ግቧን ከመረብ አገናኝቷል።

ከቀናት በኋላም የሊቢያው መሪ ሙአመር ጋዳፊ በአሜሪካ ወታደሮች መገደሉን መላው ዓለም ሰማ። ይካቲት 11 ቀን 2012 እ.አ.አ ዌልሳዊው የቀድሞ ተጫዋች በሰንደርላንድ መረብ ላይ ግብ ካስቆጠረ ከቀናት በኋላ እንግሊዛዊቷ አቀንቃኝ ዊትኒ ሆስተን በመኖሪያ ቤቷ ህይወቷ አልፎ ተገኘች። እ.አ.አ ታህሳስ 30 ቀን 2013 ራምሴ በቀድሞ ክለቡ ካርዲፍ ሲቲ መረብ ላይ ሁለት ግቦችን ካስቆጠረ ከሰዓታት በኋላ አሜሪካዊው የቀድሞ ዝነኛ ተዋናይ ፖል ወከር ህይወቱ አልፏል።

መጋቢት ስድስት ቀን 2016 እ.አ.አ ደግሞ በሰሜን ለንደን ደርቢ በቶትንሀም መረብ ላይ ግብ ካስቆጠረ ከቀናት በኋላ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን ባለቤት ቀዳማዊት እመቤት ናንሲ ሬገን ማረፏን ግዙፉ የአሜሪካ የቴሌቭዥን ጣቢያ ሲኤን ኤን ዘግቧል። ሰኔ 17 ቀን 2021 እ.አ.አ በአውሮፓ ዋንጫ ተርኪዬ ላይ ግብ ካስቆጠረ በኋላ የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ኬኔት ካውንዳ ህይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል።

መጋቢት 14 ቀን 2018 እ.አ.አ በታላቁ መድረክ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ  አርሰናል ከጣሊያኑ ክለብ ኤስሚላን ጋር በነበረው  መርሀግብር ራምሴ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ታዲያ አሁን ደግሞ ማን ሊሞት ነው ተብሎ ሲጠበቅ ከቀናት በኋላ የምድራችን ታዋቂው የፊዚክስ ሊቁ ስቴፈን ሀውኪንግ የመሞቱ ዜና ተሰማ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንሲ ከመሞታቸው ቀደም ብሎ በመስከረም አራት 2023 እ.አ.አ ካርዲፍ ሲቲ ከኤፕስዊች ታውን ባደረጉት ጨዋታ አሮን ራምሴ ለልጅነት ክለቡ ግብ አስቆጥሯል። እንደተለመደው ከሁለት ቀናት በኋላም ታዋቂው የፖፕ የሙዚቃ አቀንቃኝ ስቴቭ ሀርዌል ህይወት ማለፉ አይዘነጋም። ከዚሁ ግጥጥሞሽ ጋር በተያያዘ እ.አ.አ በ2015 ስፖርት ሜጋዚን ለአሮን ራምሴ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ሜትሮ ስፖርት አስነብቧል። ታዲያ ዌልሳዊው የቀድሞ አማካይ “እኔ ግብ ሳስቆጥር ታዋቂ ሰዎች የሞቱባቸው አጋጣሚዎች አሉ፤ ይህ እንግዳ ነገር ነው። ነገር ግን ከእርግማን ጋር የሚያያዝ አይደለም” ሲል ተደምጧል።

በተመሳሳይ ተዋናዮቹ ጁን ብራውን፣ በርት ሬይኖልድስ፣ ሮጀር ሙር እና አለን ሪክማን ሙዚቀኞቹ ዴቪድ ቦዌ፣ ግሬግ አልማን እና ኪት ፍሊንት ቡጢኞቹ ኬን ኖርተን እንዲሁም ሩቢን ካርተር እና የመሳሰሉት አሮን ራምሴ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ህይወታቸው ያለፈ ዝነኞች ናቸው።

ምንም እንኳ የአሮን ራምሴ ግብ ማስቆጠር የታዋቂ ሰው ሞትን የሚያስከትል ቢሆንም እንደ ትልቅ ግጥምጥሞሽ እንጂ እንደ መጥፎ እርግማን ግን መታየት እንደማይችል የስፖርት ካስቲንግ መረጃ አስነብቧል። ስፖርት ካስቲንግ ለዚህ ማስረጃ ሲያቀርብ በአጠቃላይ ከእርሱ ግቦች ጋር ተያይዘው ሞቱ ከተባሉት 30 ሰዎች አብዛኞቹ ህይወታቸው ያለፈው ራምሴ የአርሰናል ተጫዋች በነበረበት ወቅት እንደሆነ መረጃው ያስረዳል።

(ስለሺ ተሸመ)

በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here