ዓለማችን ባለችበት ቦታ እየረገጠች አይደለም:: ብዙ ነገሮቿ ተቀያያሪዎች ሆነዋል:: የሰው ልጅ የራሱን አምሳያ ለማጥፋት ይጠቀምባቸው የነበሩት ዱላ፣ ጦር፣ ጎራዴ እና ሌሎችም ኋላ ቀር መሣሪያዎች በዘመናዊ የመግደያ መሣሪያዎች ተተክተዋል:: አንድ ሀገርን በውስን ሰዓቶች ማጥፋት የሚችሉ የኒዩክሌር መሣሪያዎች እየተፈበረኩ፣ የሰው ልጅ ቴክኖሎጂዎችን ማሳደጉ በጥሩ እና በመጥፎ የሚታይበት ዘመን ላይ ደርሰናል::
የዛሬው ትዝብቴ ማጠንጠኛም ይሄው የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን ጉዳይ ነው:: ከእነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከልም ስልክ ላይ አተኩራለሁ:: በእጃችን የምንይዛቸው ስልኮች “ሃሎ!” ከመባባል ባለፈ ለፈጣን መልዕክቶች መላላኪያ፣ ለጥናት እና ምርምር፣ ለትምህርት፣ ለፈጣን ግብይት፣ለፈጣን የመጓጓዣ አገልግሎት ማግኛ እና ለሌሎችም ጠቃሚ ነገሮች መዋላቸው የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በጎ ገጽታ ማሳያዎች ናቸው::
አደጉ የምንላቸውን ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ መጠቀም ሲሳነን ግን ጉዳታቸው በተጨባጭ የሚታይ ይሆናል::በሀገራችን ውስጥ በተለይም የማኅበራዊ ትስስር መረቦችን የምንጠቀምበት መንገድ በአግባቡ መፈተሽ ይኖርበታል:: ለዚሁ አባባሌ አብነት ይሆኑኝ ዘንድም በ‘ቲክ ቶክ’ ያየኋቸውን ጥቂት መታረም ያለባቸውን ነገሮች አነሳለሁ::
ማሳያ አንድ፡-ልጁ አብሮት በሚተውነው ሌላ ልጅ ከቀኝ መዳፉ ላይ የሆነ ነገር “እፍ…” ብሎ በሚተነፍስበት ጊዜ ልጁ ተዘርሮ ሲወድቅ ይታያል፤ ልጁን አስማት በሚመስል ነገር የጣለው አስመሳዩ ልጅ መዳፉን እንደዘረጋ በሌሎች ሰላማዊ ሰዎች ላይ “እፍ…” ለማለት ሲሰናዳ ሰላማዊ ሰዎቹ በድንጋጤ የሚሆኑትን ሲያጡ ይታያሉ::
ይሄው ትዕይንት እንደ መልካም ነገር በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ለዕይታ የሚበቃው በድብቅ ካሜራዎች እየተቀረጸ ነው:: እዚህ ጋር ማስተዋል ያለብን በሰዎች ከፍተኛ ድንጋጤ ለመዝናናት እና ለማዝናናት ብለው ከሚተውኑት በተጨማሪ ይሄንኑ ጥፋት እንደ ጥሩ ፊልም ቀርጸው የሚያስቀሩት የካሜራ ባለሙያዎችም ጥፋተኞች መሆናቸውን ነው::
በዚህ ድርጊታቸው የተናደዱ ሰዎች የአሳዛኙን ድርጊት ተዋናዮች ለመምታት ሲንደረደሩ “ፕራንክ” መሆኑን እና ለመማታት ያሰቡት ሰዎችም በካሜራ ዐይኖች ዕይታ ውስጥ መሆናቸውን ይነግሯቸዋል::የዚህ ድርጊት ቀጥተኛ ተባባሪዎች የካሜራ ባለሙያዎቹ ቢሆኑም ለዕይታ የበቃውን ቪዲዮ ‘ላይክ’፣ ‘ሼር’ ፣ ‘ሰብስክራይብ’ እና ሌላም በማድረግ አጥፊዎቹ ከማኅበራዊ ትስስር ገጾቹ በገንዘብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የምናደርገው ግን እኛው ራሳችን ነን::
እንደ ሁለተኛ ማሳያ ፡-በትከሻው ላይ በርካታ ትላልቅ የተደራረቡ ካርቶኖችን ተሸክሞ የሚታይ ወጣት ሰዎች በሚበዙበት አካባቢ ሲደርስ በመንገዳገድ እነዚያ ትላልቅ ካርቶኖች ሊወድቁበት ያስመስላል፤ በልጁ ትከሻ ላይ የሚታዩት እነዚያ ትላልቅ ካርቶኖች አናታቸው ላይ ወድቀው ጉዳት እንዳያስከትሉባቸው የሚሸሹ፣ በእጅጉ የሚደነግጡ፣ የሚጮሁ እና በቅጽበቱ ሌላም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ በሚገቡ አዛውንቶች ድንጋጤ መዝናናት ከኢትዮጵያዊነት ባሕል፣ ትውፊት እና ሥነ ምግባር ፍጹም ማፈንገጥ ነው::
ሦስተኛ ማሳያ፡-አንዷን ወጣት መሀል መንገድ ላይ አስቁሞ ይህንን እሽግ ከጀርባው አይተሽ ምን ዓይነት ማስቲካ እንደሆነ ከነገርሽን እና ካወቅሽ ይሄንን ያህል ብር ትሸለሚያለሽ ይላታል፤ ልጅቱም ወጣቱ የያዘውን እሽግ ከጀርባው እያየች ምን ማስቲካ እንደሆነ ለማወቅ ትጥራለች፤ወጣቱ ግን እሽጉን ለሌሎች ተመልካቾች በሚታይ መልኩ እያስቀረጸ የኮንዶም ማስታወቂያ ሲሠራ ይስተዋላል:: እዚህ ጋር ልብ መባል ያለበት ነገር ያለወጣቷ ፈቃድ የሚሠራው የኮንዶም ማስታወቂያ በልጅቱ ሥነ ልቦና ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ነው::
እኔ ለአብነት እነዚህን ሦስት ምሳሌዎች አነሳሁ እንጂ የማኅበራዊ ትስስር መረቦችን በመጠቀም የሚፈጸሙት አስነዋሪ ነገሮች በርካታ ናቸው:: እነዚህ ድርጊቶች በሌላ ሀገር ውስጥ እንደ ጥሩ መዝናኛ ሊወሰዱ ይችላሉ፤በኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሴቶችን እና ትላልቅ ሰዎችን በማስደንገጥ ምንም ዓይነት መዝናኛ ሊኖር አይችልም፤ ይልቁንም መዝናኛ ተብለው የቀረቡት ነገሮች ነውረኛ መሆናቸውን ሁሉም ሰው የሚስማማበት ይመስለኛል:: “ፕራንክ” ይሉት ቧልትም ከኛ ሀገር ማኅበራዊ መስተጋብር ጋር ፈጽሞ ዝምድና የሌለው ነው::
በኛ ሀገር ውስጥ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለተፈጠሩበት ዓላማ ከማዋል ይልቅ በተቃራኒው መጠቀምን ልምድ እያደረግነው መጥተናል:: ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት በማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚተላለፉት ነውረኛ ንግግሮቻችን ናቸው:: እንደ ኢትዮጵያዊ ሳስበው ቤተ እምነቶችን እና ትላልቅ ተቋማትን በማኅበራዊ የትስስር ገፆች ከመሳደብ የሚበልጥ ነውረኝነት በየትም ቦታ ሊኖር አይችልም::
የግለሰቦችን ስም እየጠቀሱ ሲሳደቡ እና ሲዝቱ የነበሩ ሰዎች በተከታዮቻቸው ይሁንታ ተበረታተው አንድን ማኅበረሰብ፣ ተቋም፣ አማኝ እና ሌላውንም ሲሳደቡ መስማት የተለመደ ሆኗል:: እነዚህ ተሳዳቢዎች ለስድብ የሚጠቀሟቸው ቃላት እንኳንስ በኔ ተደግመው ሊነገሩ ይቅርና በተናገሯቸው ሰዎች ድፍረትም የምገረምባቸው ናቸው:: ከምንም በላይ የሚያስገርመኝ ግን እነዚህ ተሳዳቢ እና ነውረኛ ሰዎች ያሏቸውን ተከታዮች ያህል ማኅበራዊ የትስስር ገፆችን ለበጐ ዓላማ የሚጠቀሙ ሰዎች ተከታይ የሌላቸው መሆናቸው ነው::
ሀገራችን ኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርን የሚያወግዝ እና በሕግም የሚያስጠይቅ መሆኑን የደነገገች ብትሆንም በማኅበራዊ የትስስር ገጽ መንደር ይህ ሕግ ስለመኖሩም የሚታወቅ አይመስለኝም:: አሁን አሁን ላይ የጥላቻ ንግግር መናገር ብቻ ሳይሆን የሰውን ልጅ በሀይማኖቱ፣ በብሔሩ፣ በቋንቋው ወይም በሌላ ማንነቱ እየለዩ በአደባባይ የመስደብ፣ የመደብደብ እና ከዚህም አለፍ ሲል የመግደል ድርጊታቸውን በምስል እየቀረፁ ለእይታ የሚያበቁ ሰዎችም ተፈጥረዋል::
በሬ ሰርቆ የተያዘው ልጅ “እናቴ በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ ኖሮ…” እንዳለው ሁሉ አሁን ላይ በማኅበራዊ የትስስር ገፆች የምናያቸው ነውሮች ከእንቁላል ወደ በሬ ማደጋቸው አይቀሬ ነው:: በማያስቀው ነገር እየሳቅን፣ በሚያሳዝነው ነገር ያለማዘናችን ምክንያቱም ነውሮችን መለማመዳችን ነው:: ለነውር ፈፃሚዎቹ እና ለነውራቸው ድጋፍ እየሰጠን ሌሎች ብዙ ነውረኞች እንዲፈለፈሉ የምናደርገውም እኛው ራሳችን ነን፤ ለዚህም ነው ርዕሴን መሰልጠን ወይስ መሰይጠን? በሚል መጠይቅ ያቀረብኩት::
የማኅበራዊ ትስስር ገፆችን ለገቢ ማግኛነት ወይም የተደበቁ ተሰጥኦዎችን ለማሳየት በሚጠቀሙ ሰዎች ላይ ቅሬታ የለኝም:: ማኅበራዊ የትስስር ገፆችን በመጠቀም ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለሚወጡ ሰዎች ያለኝ አክብሮትም ላቅ ያለ ነው፤ የኔ ሀሳብ ወይም ትዝብት የሚያተኩረው ማኅበራዊ የትስስር ገፆችን ለአስነዋሪ ድርጊቶች በሚጠቀሙ ሰዎች ላይ ነው::
በአደባባይ ሰዎችን በማስደንገጥ ለከፋ አደጋ የሚዳርጉ፣ ገንዘብ ያስገኝልናል ብለው ካሰቡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ነውር የሚባሉ ነገሮችን ሳይቀር የሚፈጽሙ፣ ነውረኛ ንግግሮችን የሚናገሩ፣ የሚሳደቡ እና ሌሎችንም ከኢትዮጵያ እሴቶች ያፈነገጡ ተግባራትን የሚፈጽሙ ሰዎች በድርጊታቸው ሊወገዙ እንጂ ተከታይ ሊበዛላቸው አይገባም ባይ ነኝ::
ስመ ጥር የሆኑ የመገናኛ ብዙኃንም ከኢትዮጵያዊያን እሴት ባፈነገጠ መልኩ ለቃለ ምልልስ ስለሚጋብዟቸው ሕጻናትም ቆም ብለው ማሰብ ይገባቸዋል:: በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ነውር የሚባሉ እርቃንን የሚያሳዩ አለባበሶችን ለተመልካች ዐይን መጋበዝም ቢሆን ጥፋተኛ ሊያስብል ይገባዋል፤ ሀሳቤ የተነሳሁበትን ፈር እንዳይለቅብኝ ስል የብዙኃን መዝናኛዎች ላይ የሚታዩ ህፀፆችን በዚሁ ልገድባቸው እና ስለ ሕግ አካላት ያለኝን ሃሳብ አቅርቤ ልቋጭ::
የቴክኖሎጂዎችን እድገት ለበጐ ዓላማ ከመጠቀም አንፃር ያሉብን ክፍተቶች በሕግ አግባብ ሊታረሙ ይገባል፤ አሊያ ግን በእጁ ላይ የያዘው ተንቀሳቃሽ ስልክ ከብዙ ሰዎች ጋር ሊያገናኘው እንደሚችል ታሳቢ አድርጐ ግለሰቦችን፣ ተቋማትን ወይም ሌሎችን መዝለፍ በአእምሮ መስነፍ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል::
ሀሳቤን እንዲህ ብዬ ልቋጨው፤ መሳደብ፣ ታላላቆችን አለማክበር፣ በሰዎች ድንጋጤ መደሰት እና መሰል ነገሮች የኛ የኢትዮጵያዊያን መገለጫዎች ስላልሆኑ ዛሬውኑ እንተዋቸው፤ አውቀውም ይሁን ባለማወቅ በነዚህ ዓይነት ድርጊቶች ላይ የሚሳተፉ ሰዎችን አናድንቃቸው፤ የሰዎቹ ስህተት ማኅበራዊ እና ሀገራዊ ቀውስ ከመፍጠሩ በፊት የሕግ ማዕቀፍ ይበጅለት፤ መሰልጠን ከመሰይጠን የሚለይ መሆኑንም እንወቅ::
ሰላም!
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም