የመስኖ ልማትን በመኸር የታጣውን ምርት ማካካሻ አድርጎ እየሠራበት መሆኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የተፈጥሮ አደጋዎች የብሔረሰብ አስተዳደሩን ሕዝብ የምግብ ዋስትናን በተደጋጋሚ የሚያውኩ ክስተቶች ናቸው፡፡ ለአብነት በ2015/16 የምርት ዘመን እንደ ክልል በዘጠኝ ዞኖች ያጋጠመው ድርቅ በተለይ የዋግን ሕዝብ ወደ ጠባቂነት እንዲሸጋገር አድርጎት ቆይቷል፡፡
በ2016/17 ዓ.ም ያጋጠመው የዝናብ መብዛት ደግሞ የምርታማነት ክፍተት መፍጠሩን የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን አካሂዶ በነበረበት ወቅት የብሔረሰብ አስተዳደሩ የምክር ቤት ተወካይ ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የክልሉን ምርታማነት ሊያሳድጉ በሚችሉ አሠራሮች ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር በመከረበት ወቅት ተገኝተው ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ለአሚኮ እንዳስታወቁት በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት እያጋጠመ ያለውን የምርት ክፍተት ለመሙላት መስኖ ላይ ትኩረት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በብሔረሰብ አስተዳደሩ በመጀመሪያ ዙር (ነባር እና አዲስ) መስኖ አራት ሺህ 20 ሄክታር መሬት ማልማት የተቻለ ሲሆን በሁለተኛ ዙርም ከዕቅድ በላይ 250 ሄክታር መሬት ብልጫ ያለው ልማት እየተከናወነ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡
በዚህም ሁለት ሺህ 500 ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
የመስኖ እንቅስቃሴው ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ መምጣቱ ተመላክቷል፡፡ 437 ሺህ ኩንታል የአትክልት ምርት መመረቱን ማሳያ አድርገዋል፡፡ ምርቱም ወደ አጎራባች የትግራይ ክልል እና አዲስ አበባ ከተማ በመላክ የጸጥታ ችግሩ የፈጠረውን የገበያ ትስስር ችግር ለመፍታት ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
መምሪያ ኃላፊው ለመስኖ ልማቱ መሻሻል አበርክቶ አድርገዋል ያሏቸውን ምክንያቶች ጠቅሰዋል፡፡ በተለያዩ የአትክልት አይነቶች የመስኖ ክላስተር (ኩታ ገጠም) በስፋት ተተግብሯል፡፡ የአርሶ አደሩን የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ማሻሻል መቻሉም ሌላው የዘርፉ ውጤታማነት ምክንያት ነው፡፡
በክልሉ ግብርና ቢሮ እንዲሁም በክልሉ መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አማካኝነት የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን ለአርሶ አደሩ ማከፋፈል መቻሉ ደግሞ አርሶ አደሩ ራሱን በምግብ ለመቻል የተለያዩ አማራጮችን እንዲጠቀም እንዳስቻለው መምሪያ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሚንቀሳቀሱ ፕሮጀክቶች (ድርጅቶች) የመስኖ ልማትን እንዲደግፉ ጠንካራ ሥራ መሠራቱ እና አማራጭ የገበያ ትስር መዳረሻዎችን መፍጠር መቻሉ አርሶ አደሩ የተበጣጠሰ መሬቱን በክላስተር በማደራጀት ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ እገዛ ማበርከቱን አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ የመኸር ወቅትም 120 ሺህ 138 ሄክታር መሬት እንደሚለማ በመግለጽ ምርታማነትን ሊያረጋግጡ የሚችሉ አሠራሮች እና ግብዓቶች ትኩረት እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም