በመንግሥት ተቋማት ብዙዎች ከሚማረሩባቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የአግልግሎት አሰጣጥ አለመዘመን ነው። አንድን አገልግሎት ለማግኘት ያለው መባዘን የአገልግሎት ፈላጊውን ውድ ጊዜ እና ጉልበት የሚበላ ነበር።
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከጀመረቻቸው የተቋማዊ ሪፎርሞችና ትኩረት ከተደረገባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የአገልግሎት አሰጣጥ ነው።
በርካታ ዓመታትን ባስቆጠረው የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አዲስ ነገር ያሳያል የተባለለት መንግስት በቅርቡ ወደ ሥራ ያስገባው “መሶብ” የተሰኘ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫን ማእከል ሲቪል ሰርቪሱ ያለበትን ችግር የሚቀርፍና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ዘርፉን የሚያዘምን ነው፡፡
ከመጠን ያለፈ የወረቀት ሥራ እና አዝጋሚ ውሳኔ አሰጣጥ፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን ማዘግየት፣ ደካማ የተቋማት ቅንጅት በዘርፉ የሚታይ የአገልግሎት አሰጣጡን ኋላ ቀርነት እንደማሳያ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።
ይህ ዓይነት አካሄድም ተገልጋዮችን በማማረር ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት ያበላሻል። የሀገርን ሀብት እና ጊዜ በማባከን ወደ ውድቀት ያመራል። ድምሩ የመልካም አስተዳደር ችግር ይሆናል።
መንግስት ለሰው ተኮር አገልግሎት የሰጠው ትኩረት የተግባር ማረጋገጫ የሆነው ይህ ማዕከል ህብረተሰቡ ባልተንዛዛ ቢሮክራሲ እንዲሁም በተቀላጠፈ መንገድ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያደርግ ነው።
በአንጻሩ ደግሞ የተሻሻለ እና የዘመነ የሕዝብ ተቋማት የፈጠሩ ሀገራት ቀልጣፋ፣ ተጠያቂነት ያለው፣ ሁለንተናዊ እና በዜጎች ዘንድ ተአማኒነት የሚፈጥሩ አግልግሎት ይሰጣሉ። እንደዚህ ዓይነት ተቋማት በገነቡት ሀገራት መንግሥት እና ሕብረተሰብ መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ ይሆናል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተከፈተውም ለዚህ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለፓርላማ ባቀረቡት ማብራሪያ ላይ እንደገለጹት መሶብ የኢትዮጵውያን የባህል መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቱ ቤተሰብ በአንድ መሶብ ዙሪያ ተሰባስቦ እንደሚመገበው ሁሉ አገልግሎት ፈላጊዎች በአንድ ማዕከል በርካታ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ታሳቢ ያደረገ ነው።
በኲር የህዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


