ከሦስት ዓመት በፊት እ.አ.አ የካቲት 24 ቀን 2022 የሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እስከ 200 ሺህ የሚደርሱ ወታደሮች ወደ ዩክሬን እንዲገቡ ትዕዛዝ የሰጡበት ዕለት ነበር፤ ዓላማቸው ደግሞ በቀናት ውስጥ ዋና ከተማዋ ኪየቭ ድረስ ዘልቆ በመግባት የምዕራባውያን ደጋፊ የሆነውን መንግሥቷን በመገልበጥ ዩክሬንን ወደ ሩሲያ መመለስ ነበር። ይሁንና ፑቲን ግባቸው ሳይሳካ ከሦስት ዓመታት በላይ በጦርነት ዘልቀዋል፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው ፑቲን የዩክሬንን አንድ አምስተኛ ግዛት በሩሲያ እጅ አስገብተዋል፡፡ ሆኖም አሁንም ጦርነቱ አላቆመም፤ ከሁለቱም ወገን ሰዎች እንደቅጠል እየረገፉ ነው፡፡
ሁለቱን ሀገራት ወደ ሰላም ለማምጣት በርካታ ሥራዎች ቢሠሩም ለውጥ አልመጣም፡፡ በቅርቡ ከተደረገው ካልተሳካው ከኢስታንቡሉ ድርድር በኋላም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ ለሁለት ሰዓታት የፈጀ ዘለግ ያለ ንግግር አድርገዋል፡፡ ከፑቲን ጋር ጥሩ የሆነ ውይይት እንዳደረጉም ነው ትራምፕ የጠቆሙት፡፡ ከንግግሩ በኋላም ሁለቱ ሀገራት በፍጥነት ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ እና ጦርነቱ እንዲያበቃ እንደሚፈልጉ ነው ያስታወቁት፡፡
ፑቲንም ከትራምፕ ጋር ካደረጉት ንግግር በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሞስኮ ከዩክሬን ጋር ስለወደፊቱ የሰላም ስምምነት በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን ነው ያስታወቁት፡፡ “ወደ ሰላም የምንሄድበትን በጣም ውጤታማ መንገዶችን ብቻ መወሰን አለብን” ብለዋል፡፡
ኪዬቭ ቅድመ ሁኔታ የሌለው የተኩስ አቁም እንዲደረግ ትፈልጋለች፡፡ ሩሲያ በበኩሏ ለቀውሱ መንስኤ የሆኑትን ጉዳዮች ማስወገድ ዋና ነገር መሆኑን ነው የምትናገረው፡፡
እንደሚታወቀው ሩሲያ ዩክሬን ከኔቶ ጋር ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት እንድታቋርጥ እና ወታደሮቿን በከፊል በሩሲያ ጦር ከተያዙት የዩክሬን ክልሎች እንድታስወጣ ትፈልጋለች፡፡ ሩሲያ ለዓመታት የኔቶ ምሥራቃዊ መስፋፋት ለደኅንነቷ ስጋት እንደሚፈጥር በመግለጽ ቅሬታዋን ስትገልጽም ቆይታለች፡፡ እንዲሁም ፑቲን ዩክሬን ወደ ሕብረቱ የምትቀላቀልበትን ማንኛውንም ዕድል እንደ ዋና ቀይ መስመር ይመለከቱታል።
ሆኖም ትራምፕ አፋጣኝ ውይይቶችን ለማድረግ ቢገፋፉም ሞስኮ ጉዳዩን ለመፍታት ምንም አይነት ችኮላ አላሳየችም። ፕሬዚዳንቱ የተኩስ አቁም ድርድር ወዲያውኑ እንደሚጀመር ቢናገሩም ሞስኮ ለቀጣይ ዕርምጃዎቿ ቀነ ገደብ አላስቀመጠችም። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ከሁለቱ ፕሬዝዳንቶች የስልክ ንግግር በኋላ በሰጡት አስተያየት “ምንም የጊዜ ገደብ የለም፤ እናም ምንም ሊኖር አይችልም” ብለዋል፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው ደግሞ በቅርቡ በቱርክ ኢስታንቡል የተካሄደው የሰላም ድርድር ውጤት አላስገኘም፤ ዩክሬንን ወክለው የተሳተፉ የዩክሬን ባለስልጣናትን ዋቢ አድርጎ አልጀዚራ እንደዘገበው የሩሲያ ባለስልጣናት ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በፊት ሞስኮ “ይገቡኛል” በሚል ከያዘቻቸው የዩክሬን ግዛቶች የኪዬቭ ጦር ተለቃቅሞ እንዲወጣ መጠየቋ ለድርድሩ መፍረስ ምክንያት ሆኗል፡፡
ባለፈው ዓመት በምረጡኝ ዘመቻቸው ወቅት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም ቃል ገብተው ነበር። ነገር ግን ስልጣን ከያዙ በኋላ ባሉት አምስት ወራት ውስጥ ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ ቢታገሉም አልተሳካላቸውም። ትራምፕ በጥር ወር ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ከተመለሱ በኋላ ከሩሲያ አቻቸው ጋር ለመገናኘት እየሞከሩ ነው። ከሰሞኑ በሁለቱ ፕሬዚዳንቶች መካከል ለሦስተኛ ጊዜ ረዥም የስልክ ንግግር ተደርጓል፡፡ እንዲሁም ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛቸውን ስቲቭ ዊትኮፍን ሞስኮ ውስጥ ከፑቲን ጋር እንዲገናኙ በተደጋጋሚ ልከዋል።
በተመሳሳይ ትራምፕ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ጋር ያላቸው ግንኙነት ብዙ ጊዜ እንደታየው ፈታኝ ነው። በነጩ ቤተ መንግሥት ውስጥ እንዲመጡ በማድረግ ለውይይት ቢቀመጡም ጠብ የሚል ነገር ሳያስገኝ፣ ከጉንጭ አልፋነትም ሳይሻገር ነው የተቋጨው፤ ትራምፕም ዜሌንስኪ ጦርነቱን ማቆም አይፈልግም ሲሉ መተቸታቸውም ይታወሳል። በሌላ በኩል ዜሌንስኪ ከትራምፕ ጋር ከሰሞኑ ባደረጉት የስልክ ንግግር ዩክሬን ሙሉ እና ቅድመ ሁኔታ ለሌለው የተኩስ አቁም ዝግጁ መሆኗን ለፕሬዚዳንት ትራምፕ በድጋሚ ማረጋገጣቸውን ነው ያሳወቁት፡፡
ትራምፕ ከተሾሙ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የአሜሪካ ተወካዮች በዩክሬን ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ከሩሲያ እና ከዩክሬን ባለስልጣናት ጋር በሳዑዲ አረቢያ ተገናኝተዋል። ትራምፕ ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማደስም ሞክረዋል።
አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው ደግሞ ሦስት ዓመታትን ባስቆጠረው የሩሲያ – የዩክሬን ጦርነት የተጀመሩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡ በመሆኑም የኪዬቭ አጋር የሆኑት የአውሮፓ ሀጋራት ሞስኮ ላይ አዲስ ማዕቀብ ጥለዋል። የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ “ሩሲያ ጦርነቱን እና ወረራውን ለመቀጠል ጊዜ ለመግዛት እየሞከረች ነው። በመሆኑም ሩሲያዊያን የተለየ ባህርይ እንዲኖራቸው ጫና ለመፍጠር ከአጋሮች ጋር እየሠራን ነው” ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ አያይዘውም ሩሲያ ለተኩስ አቁም ካልተዘጋጀች በሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ መጨመር አለበት ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡ “በሩሲያ ላይ ያለው ጫና ወደ እውነተኛ ሰላም ይገፋፋታል። ይህ በዓለም ዙሪያ ላሉ ሰዎች ሁሉ ግልጽ ነው፡፡ ሩሲያ የጀመረችውን ጦርነት ማቆም አለባት” በማለት ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
አዲሱ የአውሮፓ ሕብረት ማዕቀብ ወደ 200 የሚጠጉ የሩሲያን ነዳጅ ዘይት የሚያጓጉዙ መርከቦች ላይ ያነጣጠረ ነው፤ በተለያዩ ባለስልጣናቷ ላይ እና በበርካታ የሩሲያ ኩባንያዎች ላይም የንብረት እና የጉዞ እገዳም ጥሏል። የእንግሊዝ በሩሲያ ላይ የምትጥለው ማዕቀብ የሩሲያን የጦር መሳሪያ አቅርቦት ሰንሰለትን ለማደናቀፍ ያለመ መሆኑን ነው ባለሥልጣናቷ የተናገሩት። እንዲሁም በ100 የሩሲያ መርከቦች ላይም የእንቅስቃሴ እገዳ ጥላለች፡፡
በቅርቡ ካናዳ አልበርታ በተካሄደው የቡድን ሰባት (G7) የፋይናንስ ሚኒስትሮች ጉባኤ የዩክሬኑን የገንዘብ ሚኒስትር ሰርጊ ማርቼንኮን በእንግድነት ተጋብዘው ተገኝተዋል። ከስብሰባው ጎን ለጎን ማርቼንኮ በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች እንዲጣሉ ጠይቀዋል፡፡ ይህም የቡድን ሰባት (G7) አባላትን ጨምሮ በበርካታ ሀገሮች በሩሲያ ድፍድፍ ዘይት ወደ ውጭ መላክ ላይ የተጣለውን የ60 ዶላር በበርሜል ዋጋ መቀነስን ይጨምራል፡፡ ስብሰባው በሰኔ ወር ከሚካሄደው ትልቁ የቡድን 7 ስብሰባ በፊት የተካሄደ ሲሆን በካናዳ አስተናጋጅነት የሚካሄደው ዋናው ጉባኤ በዩክሬን መልሶ ግንባታ ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል።::
(ሳባ ሙሉጌታ )
በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም