መበታተን የጀመረዉ የአንፊልድ ምሽግ

0
237

የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አምና ያነሳው ሊቨርፑል ዘንድሮ ገና ከወዲሁ መንገዳገድ ጀምሯል፡፡ የ2025/26 የውድድር ዘመን ለቀዮቹ የ32 ዓመታት ታሪክን ወደ ኋላ የጎተተ የጨለማ ዘመን መጀመሪያ ሆኗል። በአሰልጣኝ አርነ ስሎት የሚመራው ቡድን በመጀመሪያዎቹ ዐስር የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በአራቱ ተሸንፏል፡፡ በተለይም ከሜዳው ውጪ በብሬንትፎርድ የደረሰበት የሦስት ለሁለት ሽንፈት የችግሩን ጥልቀት እና ስፋት በግልጽ ያሳያል። ይህ ችግር የአንድ ጨዋታ ውጤት ብቻ ሳይሆን በአንፊልድ ሮድ ኮሪደሮች ውስጥ የሚስተጋባውን ጥልቅ እና ውስብስብ ቀውስ ያመለክታል።

አርነ ስሎት አምና በየርገን ክሎፕ ቡድን ላይ ምንም ዓይነት መሰረታዊ ለውጥ ሳያደርግ በቀላሉ የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫውን ማንሳቱ የሚታወስ ነው፡፡ ዘንድሮ ግን ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ዐስረኛ ሳምንት ድረስ ከመሪው አርሴናል ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት ሰባት ደረሷል፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡም ሦስተኛ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ አሰልጣኙ ግን ምንም እንኳ ደካማ እንቅስቃሴ እያደረጉ ቢሆንም ማንቸስተር ሲቲ እንጂ የአረሴናል አቋም ጥሩ መሆኑ አያሳስበኝም ሲል ተደምጧል፡፡

ክለቡ በክረምቱ የዝውውር ወቅት 415 ሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብ በማውጣት ስምንት ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡ ይህም በአውሮፓ እግር ኳስ ታሪክ በአንድ የዝውውር ወቅት አዲስ ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይሁን እንጂ ሂውጎ ኤኪቲኬ፣ፍሎሪያን ቪርትዝ እንደ አሌክሳንደር ኢሳቅ ያሉ አዲስ የክለቡ ተጫዋቾች እስካሁን ድረስ የሚጠበቀውን ያህል ጥሩ አቋም አላሳዩም። በክረምቱ የፈረሙት ተጫዋቾች ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው እና የአርነ ስሎትን ሀሳብ ለመስማት ዝግጁ መሆናቸውን የክለቡ ኃላፊዎች ተነግሯል፡፡

ከካራባዎ ዋንጫ በጊዜ በክሪስታል ፓላስ የተሰናበተው ሊቨርፑል በተከታታይ ፈታኝ መርሀግበሮችን አከናውኗል፡፡ በቅርቡ በብሬንትፎርድ በሦስት ለሁለት ከተሸነፉ በኋላ ስሎት ራሳቸው ጨዋታውን “የዚህ የውድድር ዘመን እጅግ የከፋ ውጤት” ሲሉ ገልጸውታል። ሊቨርፑል በተከታታይ በክሪስታል ፓላስ፣ በቸልሲ፣ በማንቸስተር ዩናይትድ እና ብሬንትፎርድ ሽንፈት መከናነቡ አይዘነጋም፡፡ ሜዳ ውስጥ የሚያሳየው አቋም በመልበሻ ክፍል ውስጥ ያለውን የቡድን መንፈስ እና የደጋፊዎችን ስሜት በአሉታዊ መልኩ ይቀይራል፡፡ ነገር ግን ችግሩ እስከ ታኅሣሥ ወር በሆላንዳዊው አሰልጣኝ ጫናው  መጨመሩ አይቀርም።

ሊቨርፑል እ.አ.አ ከ1993 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በመክፈቻው ዐስር ጨዋታዎች በአራቱ ሲሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በዐስር ጨዋታዎች ብቻ 14 ግቦች ተቆጥረውበታል፤ ቀዮቹ ባለፈው የውድድር ዘመን ይህን ያህል ግብ የተቆጠረባቸው እስከ 16ኛው ሳምንት እንደነበር አይዘነጋም። ይህ ታዲያ ጊዜያዊ የአቋም መዋዠቅ ሳይሆን  የክለቡን መዋቅር፣ ስነ-ልቦና እና የወደፊት አቅጣጫ የሚፈታተን ከባድ ቀውስ መሆኑን የቢን ስፖርት መረጃ ያስነብባል።

የችግሩ ዋናኛ ምንጭ የሁለት ተቃራኒ  የእግር ኳስ ፍልስፍናዎች እንደሆነ የጎል ዶትኮም መረጃ ያመለክታል። ለዘጠኝ ዓመታት የሊቨርፑል መለያ የነበረው የየርገን ክሎፕ ያለ እረፍት ተጭኖ መጫወት የእግር ኳስ ፍልስፍና  በስሜት፣ በከፍተኛ ጉልበት እና ቀጥተኛ ማጥቃት ላይ የተመሰረተ ነበር። የክሎፕ “ጌገንፕሬሲንግ” ኳስ ሲነጠቁ በሽርፍራፊ ሴኮንዶች ውስጥ ተጋጣሚን እንደ ንብ መንጋ በመውረር  ኳስን መቀማት እና በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ዋነኛ ፍልስፍናው ነበር። ይህ ፍልስፍና ታዲያ በክሎፕ፣ በተጫዋቾቹ እና በደጋፊዎች መካከል ሙቀት በመፍጠር አንፊልድን ወደ ኮንክሪት ምሽግ ቀይሮት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።

በአንጻሩ አዲሱ አሰልጣኝ አርነ ስሎት ይዞት የመጣው ፍልስፍና በስሌት እና በትዕግስት ላይ የተመሰረተ ነው። የስሎት ቡድን ኳሱን በትዕግስት በማንሸራሸር የተጋጣሚን አደረጃጀት ቀስ በቀስ በመሰንጠቅ ክፍተት መፍጠርን ይመርጣል። እያንዳንዱ ተጫዋች የት መቆም እንዳለበት በጥብቅ ስርዓት የተደነገገ ሲሆን ይህም ከክሎፕ “ተጭኖ በመጫወት” ላይ ከተመሰረተው እንቅስቃሴ በእጅጉ እንደሚለይ ቢን ስፖርት ይተነትናል።

ታዲያ የአንፊልዱ ክለብ አቋም መዋዠቅ የስሎት ፍልስፍና መጥፎ ስለሆነ ሳይሆን ለዓመታት የክሎፕን ፍልስፍና የተለማመደ ቡድን ላይ ቀጥታ በመተግበር የተፈጠረ ግጭት ነው። በክሎፕ ዘመን እንደ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ያሉ የኋላ ተመላላሾች ኳስን ወደፊት እንዲገፉ ሲበረታቱ በሆላንዳዊው አለቃ ስር ደግሞ ተጫዋቾች ቦታቸውን በንቃት እንዲጠብቁ ይፈለጋል። ይህም በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ግራ መጋባትን እና በቡድኑ ማንነት ላይ ቀውስ እንደፈጠረ ኤስፒኤን አመልክቷል።

በዚህ ምክንያት የኋላ ክፍሉ በቀላሉ ግብ እየተቆጠረበት ነው። የግል ስህተቶች መብዛት፣ ከአማካይ ክፍል በቂ ሽፋን አለማግኘት እና ቅጣት ምቶችን መከላከል አለመቻል ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው። የፊት መስመሩም ቢሆን ቅንጅት የጎደለው ነው፡፡  ቡድኑ በአጠቃላይ በኋላ ክፍሉ እና በፊት መስመሩ ያለውን ሚዛን አጥቷል።

የየርገን ክሎፕ ቡድን ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ  ለማገገም ብዙ ጊዜ የሚወስድበት አልነበረም፡፡ አሁን ላይ ግን  አንድ ግብ ሲቆጠርበት በቀላሉ ተስፋ የሚቆርጥ እና ጀኔራሉ እንደተማረከበት ወታደር በቀላሉ የሚበታተን ሆኗል። ሜዳ ላይ ቡድኑን የሚያነቃቃ ግልጽ መሪ የጠፋም ይመስላል። ይህ ቀውስ ወደ ደጋፊውም ተዛምቷል። ሁሌም በድጋፋቸው ተጋጣሚ ቡድንን በፍርሀት የሚያርዱት ስመ ጥሮቹ የአንፊልድ ደጋፊዎች የሊቨርፑል 12ኛ ተጫዋች መሆናቸው አያጠያይቅም። አሁን ግን ያ ሁሉ ጠፍቶ በልጆቻቸው እና በአሰልጣኙ የነበራቸው እምነት ተሸርሽሯል፡፡ የሚያሳልፉት ዘጠና ደቂቃም በድጋፍ ሳይሆን በጭንቀት ተተክቷል። ይህ ጭንቀት ወደ ተጫዋቾቹ በመተላለፍ ጫናውን አባብሶታል ይላል የኤስፒኤን መረጃ።

የመረሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል  ለችግሩ በጊዜ መፍትሔ ካልሰጠው የውድድር ዘመኑ ሙሉ በሙሉ ሊበላሽበት ይችላል። በአጭር ጊዜ አሰልጣኝ ስሎት ግትርነቱን ትቶ ወደ መሰረታዊ የመከላከል መርሆዎች መመለስ እና  የጠፋውን የቡድኑን በራስ መተማመን መገንባት ይኖርበታል። የመልበሻ ክፍሉን መንፈስ መመለስ እንዲሁም ከደጋፊዎች ጋር መታረቅ ወሳኝ ነጥብ መሆኑ ጎል ዶት ኮም ያመለክታል።

እንዲሁም ክለቡ በጥር የተጫዋቾች ዝውውር ወቅት ቁልፍ ድክመቶችን የሚሸፍኑ በተለይ የተከላካይ አማካይ እና ጥሩ የመሀል ተከላካይ ማስፈረም እንደሚጠበቅበት ከወዲሁ ኤስፒን ጥቆማውን አስቀምጧል። ለአሰልጣኙ ጊዜ መስጠት አስፈላጊ ቢሆንም ስሎትም ከስህተቱ የመማር እና የመለወጥ ፈቃደኝነት ማሳየት አለበት ተብሏል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የህዳር  1  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here