መታደል

0
231

ልክ  የዛሬ ዓመት የገና ዋዜማ ነው፤ ስቱዲዮ ቆይቼ ስወጣ ለምን ቀዝቃዛ ነገር እየጠጣሁ ትንሽ አረፍ አልልም ብዬ መነሀሪያ ሰፈር ካለ አንድ ሆቴል ጎራ አልኩኝ:: ከፎቁ በረንዳ ላይ ተቀመጥኩ፤ ከበረንዳው መስታወት አሻግሬ ወደ አንኮበር የሚወስደውን የተንጣለለ አስፓልትና የደብረ ብርሃንን መውጫ  መልእክአ ምድር እየቃኘሁ ለስላሳ አዝዤ መጎንጨት ይዣለሁ::የሆቴሉ ፀጥታ ከመስታወቱ ጀርባ ያለው የተፈጥሮ ገፅታ እውነተኛ ሰላምም እረፍትም ይሰጣል:: ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የጥምቀት በዓል የሚከበርበት የባህረ ጥምቀቱ ሜዳም ከዚሁ ሆቴል  ግርጌ ስለሆነ ቁልቁል ይታየኛል:: የተከፈተው ለስላሳ ሙዚቃ ሌላ ለመንፈስ ተጨማሪ ምግብ ነው::ቀደም ያሉ ሙዚቃዎች ግን ከሙዚቃም ባሻገር ይመስሉኛል:: የሆነ አንዳች ምትሀታዊ ጉልበትም አላቸው:: በሀሳብ ይዘው ጭልጥ ንጉድ የሚያደርጉ፤ በትዝታ የሚወስዱ።

በስሱ በተከፈተው የሙዚቃ ማጨወቻ መልካሙ ተበጀ . . .

በሳቅ በጨዋታ በደስታ በሀዘን፣

ባለፉት አመታት ስንቱን አሳለፍን፣

ስንት ደስታ አየን ስንት አየን መከራ፣

ሲፈራረቁብን በተራ በተራ – – –

እሱ ይዘፍናል፤ እኔ በሀሳብ ሰረገላ ወደ ትናንት ወደ አፍላ ወጣትነቴ ተጉዣለሁ። ትዝታ – – – ትዝታ ግን እድሜው ስንት ነው? አራት መቶ ፍቅር ሶስት መቶ ትዝታ ነው ያለችው ዘፋኟ? እኔ ግን አይመስለኝም፤ ከኖርነው ይልቅ ትዝታው ይበዛል ባይ ነኝ፤ ሁለት መቶ ፍቅር ሶስት መቶ ትዝታ ይመስለኛል::

ለማንኛውም አራት አስርት አመታት ባልሞላው እድሜዬ ባገኘሁት አጋጣሚ በትዝታ እልም ጭልጥ የማለት አባዜ ስላለብኝ ነው ትዝታ ግን እድሜው ስንት ነው ያልኳችሁ::

ሙዚቃዎቹ ተከታትለው ይደመጣሉ፤ እኔም ከፊት ለፊቴ በሚታየኝ የተንጣለለው የደብረ ብርሃን ሜዳማ መልክአምድር ላይ ትዝታየን አስጥቼ በምናብ እየኮመኮምኩ ነው:: በነገራችን ላይ አሻግሬ የማየው ሜዳ የደብረ ብርሃን የውሃ ቋት ነው ይባላል:: በስተ ግራ በኩል የቅድስት አርሴማ ገዳምም ትታየኛለች::

ነገርን ነገር ያነሳዋል አይደል የሚባለው ከ600 ዓመት በላይ እድሜን ያስቆጠረችው ጥንታዊቷ ዳግማዊ የቀድሞዋ ደብረ ኢባ የአሁኗ ደብረብርሃን በልኳ ያልተነገረላት፣ ያልተዘመረላት ተገልጣ ያልተነበበች ቤተ-መዘክር ትመስለኛለች::

ለማንኛውም ትንሽ አረፍ ብዩ እወጣለሁ ብዬ ገብቼ ይሄው ያዘዝኩትን ለስላሳ ጠጥቼ ጨርሼ አንድ ሊትር ውሃ አዝዠ እየጠጣሁ ነው::

ንዋይ ደበበ

ያለፍኩ እንደሆን ባንች መንደር በፍቅር፣

ቅርቅር ይለኛል በዛው እደር ወይ ችግር

– – – ማለት ጀመረ፤ እርፍ ጭራሽ ከራሴ ህይወት ጋር የተጣበቀ ቁርኝት ያለው ሙዚቃ ተከፈተው:: ወይኔ ልጅዬው አደርኳታ አልኩኝ ይህንን የንዋይን ሙዚቃ ባደመጥኩት ቁጥር የተቀላቀለ ስሜት ነው የሚሰማኝ፤ ደስም ይለኛል ያብከነክነኝማል፤ ብቻ መሃሉ ስለማይነገር ምክንያቱን አልነግራችሁም።

ብቻ ማድመጤንም መመሰጤንም በትዝታ መክነፌንም ቀጥያለሁ::

ከሄድኩበት የሀሳብ ሰመመን አንድ  ድምፅ መለሰኝ:: “ይቅርታ ሰው አለው” አቤት? አልኩ እንደመደንገጥ ብዬ የመጣችውን ሴት ቀና ብዬ አየኋት፤ የለውም አልኩ። ወንበሩን ሳብ አድርጋ ተቀመጠች::

ዋው – – – በምናቤ ነው ወይስ በውኔ? የማየው ነገር ታምር ሆኖብኛል፤ ማመንም ተስኖኛል:: ትኩር ብዬ እያየኋት ነው:: የሙዚቃው ድምጽ እይታየን የሚሻማብኝ እስኪመስለኝ ቢዘጋ ብየም አሰብኩኝ:: እሷ ግን ቀና እንኳን ብላ አላየችኝም::

ይልቁንም ከባጓ ፒሲ አውጥታ ቀጥታ ወደ ስራ ገባች:: አስተናጋጇ ውሃ ይዛ መጥታ ከፍታ ብርጭቆ ላይ ቀዳችላት:: “አመሰግናለሁ” አለቻት:: ስታዛት አላየሁም አልሰማሁምም – – -።

ኦኬ ቋሚ ደንበኛ ወይም የሆቴሉ ባለቤት ልጅ ትሆናለች አልኩኝ ራሴ ጠይቄ ራሴ እየመለስኩ::

እኔ ግን መልክዓ ምድሩንም ትዝታውንም እርግፍ አድርጌ ከገባች ጀምሮ አይኖቼንም ቀልቤ ብቻ አይደለም ቀልቦቼንም ጭምር ጥየባታለሁ:: እውን ግን በውኔ ነው? እንዴት በዚህ ደረጃ ቆንጆ ሊኮን ይችላል?  እንደዚህም አምሮ መፈጠር አለ? ደግሞ እኮ ቀለበት አላደረገችም::እንደዚህ ልእልት መስሎስ ሲንግል ሆኖ መኖር ይቻላል? ውስጤ አከታትሎ ጥያቄ ይጠይቃል፤ መልስ ግን ከየት ይመጣል::

‘’ይባስ አለ ሀገርክን አትልቀቅ” አለ የሀገሬ ሰው በሙዚቃው ማደሬ ነው ስል የባሰችውን ምትሀት ጣለብኝ ከረምኳታ!!!

ውበቷን በምን ቋንቋ መግለፅ እንደምችል አላውቅም፤ ብቻ ጠይም ረዘም ያለች፣ ወገቧ ከቀጭን የቀጠነ ቀጭን፣ ዳሌዋ የተዋጣለት ሰዓሊ የሚመኘውን በምናቡ የሳለውን አስመስሎ ለራሱ አዳልቶ የሳለው የሚመስል፣ አይኗ – – – ኧረ  ጥርሷ – – – ወይ ፀጉሯማ ከፊት ከጡቶቿ፣ ከኋላ ከጀርባዋ ቁልቁል ፈሷል እኮ! ከመጥቆሩ ማብረቅረቁ ደሞ እኮ የግዥ አይደለም፤ የራሷ ከእግዜር የተሰጣት የራሷ! እንዴት አወክ?  እንዳትሉኝ፤ እመኑኝ የራሷ ነው:: በቃ እኮ በቋንቋ የማይገለፅ ውበት አጋጥሟችሁ አያውቅም? ካላወቀ እሷን ስታዩ የምለው ይገባችኋል::

ጋዜጠኛ ነኝ፤ በቋንቋ ጎበዝ እንደሆንኩም ይሰማኝ ነበር:: ለካ መቻልም እውቀትም አንፃራዊ ነው:: ነገሩ ይሄ ቁንጅና አይደለም፤ በቋንቋ በዘመናዊ የስቱዲዮ ካሜራ ቢቀረፅ ራሱ እኔ  በአካል እያየሁት ባለው ልክ ለተመልካች ማሳየት የሚቻል ጭምር አይመስለኝም:: የካሜራ ሌንስ አንዳንዴ ሰነፍ ነው፤ በአይናችን በምናየው ልክ ነገሮችን በሚገልፅ ሁኔታ ላያሳየን ይችላል:: ጥሩ ካሜራና የተዋጣለት የካሜራ ባለሙያ ሲገናኙ ምትሀታዊ ተናጋሪ ምስልን እንደሚቀርፁ ግን እየካድኩ አለመሆኑ ካደራ ጋር ይሰመርልኝ::

ለማንኛውም ውበቷ ነው የባጥ የቆጡን የሚያስለፈልፈኝ:: እየመሸ ነው፤ ታክሲ እንዳላጣም እያሰብኩ ነው:: ለምን ተዋውቄያት ስልክ ተቀብያት ሌላ ጊዜ በሰፊው አላገኛትም ብዬ ከራሴ ጋር አወራሁ:: ግን ፈራሁ፤ በዚህ ደረጃ ቆንጆ የሆነችን ሴት ደርሶ እንተዋወቅ ማለት እኮ ያስፈራል፤ ላብ ላብ ያሠኛል:: በመፍራቴ አልተገረምኩም:: ግን ለፍራቴ ፊት መስጠት አልፈለኩም፤ ደፈር ብዬ ልተዋወቃት ወሰንኩ::

“ማውራት ይቻላል!” አለችኝ፤ ፒሲዋ ላይ ትኩረቷን እንዳደረገች:: በስምአብ የመብረቅ ድምፅ የሰማሁ ያህል ነው ክው ያልኩት:: ሰማችኝ እንዴ? መደንገጤን በሚያሳብቅ ድምፀት እ ምን አልሽኝ? አልኳት::

“ተጫወት”  እ . . .  እሽ ኢሳያስ እባላለሁ አልኳት::

’’መታደል’’ አለችኝ።

ኦው ስምሽ እንደ ውበትሽ ደስ ይላል ያምራል:: “ወደድከው? አመሰግናለሁ። እናቴ በብዙ ምክንያቶች ያወጣችልኝ ስለሆነ እኔም ስሜን በጣም እወደዋለሁ::” የምታወራኝ ስራዋን እየሰራች ቀና ሳትል ነው:: ግን ዝምታው በመሰበሩ በጣም ደስ ብሎኛል:: ድምጿ ደግሞ እንዴት እንደሚያምር ልነግራችሁ ነበር:: ግን የምነግራችሁ ሁሉ ግነት እንዳይመስላችሁ ሰጋሁ:: ለማንኛውም የድምጿ ቅላፄ ሁሌም ባወራች የሚያሠኝ ነው:: በዚህ ድምፅ የሬድዮ ጋዜጠኛ ብትሆን ብዬ ለማሰብ ራሱ ብዙ እስክትናገር መጠበቅ አልኖረብኝም::

“በጣም ቆንጆ እኮ ነሽ:: ከመጣሽ ጀምሮ ውበትሽ ገርሞኝ በትኩረት እያየሁሽና ከራሴ ጋር እያወራሁ ነበር” አልኳት ፍርሃቴ እየለቀቀኝ ነው::

“ከራስህ ጋር ምንድነው የምታወራው?” አለችኝ፤ ፒሲዋን ዘግታ:: ስራ ጨርሻለሁ፤ አሁን ማውራት እንችላለን በሚል መልኩ::

ስለ ውበትሽ ተገርሜ ነው አልኳት:: “ውበት ጥሩም ነው፤ መጥፎም ነው” አለችኝ። ወንበሯ ላይ ወደኋላ ደገፍ ብላ እያየችኝ። እንዴት ማለት? አልኳት። “ቆንጆ መሆን ደስ ይላል:: በዛው ልክ ግን ቁንጅና በተለይም ለሴት ልጅ የአለም ተጨማሪ ፈተና ነው፤ እንዴት እንደማስረዳህ አላውቅም ብቻ ምን ልበልህ ቆንጆ ሴት ከትምህርት አለም እስከ ስራና ሀላፊነት አለም በውበቷና በሴትነቷ ብዙ ዋጋ እንድትከፍል ትፈተናለች::

በአጭሩ እኔ ለምሳሌ በውበቴ ከደመኩት ይልቅ የተፈተንኩት ይበልጣል” ብላኝ በረጅሙ ተንፍሳ ዝም አለች::

ስሜቷ እየገባኝ ነው:: ኦ እሱ ይገባኛል አልኳት፤ የሆነ የተደበቀ አንዳች ነገር እንድትነግረኝ ግን ጓጕቻለሁ::

“ሜዲካል ዶክተር ነኝ፤ የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት! የአንድ የውጭ አለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት አማካሪ ሆኜ እየሰራሁ ነው:: እንደምታየኝ ገና ወጣት ነኝ:: ብዙ ህልም አለኝ ፤ ዛሬ ላይ እስከደረስኩበት ባለፍኩባቸው መንገዶች ሁሉ ግን ከሴትነቴ በላይ በውበቴ ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠውብኛል:: የማልሰበር ሆኜ እንጅ ሊሰብሩኝ የሞከሩ ብዙ ናቸው::እውቀቴን ይዠ ያንኳኳኋቸው በሮች ሁሉ ከእውቀቴ ይልቅ በውበቴ ሊፈትኑኝ ዳድተዋል፤ ታግለዋልም:: ከአመታት ድካሜ ይልቅ በገላዬ ሊመዝኑኝ ሊጥሉኝ አልያም ሊያሸንፉኝ የሞከሩ ብዙ ናቸው፤ ጥቂት የማይባሉ በእውቀትህና በሰውነትህ የሚለኩ የሰውነት ውሃ ልክ የገባቸው ሠው የሆኑ ወንዶችም መኖራቸውንም በህይወት መንገዴ ተመልክቻለሁ። ግን ብቻ ምን ልበልህ ከራሴ ህይወት የምነግርህ እውነት ቁንጅናዬ እውቀቴን ደብቆብኛል፤ እውቀት ሣይሆን ውበት ፈትኖኛል፤ ፈተና ግን ከጉዞዬ አላስቀረኝም” አለችኝ። ቆንጆ ሴት መንገዷ ሁሉ በአዳኞች የተሞላ እንደሆነ ቢገባኝም በዚህ ልክ ግን ውበት የህይወት ፈተና ይሆናል ብዬ አስቤ ስለማውቅ ነው መሰል በጣም ተመስጨ ነው እያዳመጥኳት ያለሁት::

ቀጠለች “እናም በእውቀቴ ማግኘት የምችለውን በውበቴና በሴትነቴ ያጣሁበት ብዙ አጋጣሚ ስላለ ውበቴ ጠላቴ ነው ባልልህም ስለውበት ያለኝ አተያይ ከዚሁ የህይወት እልፍኝ የተቀዳ ስለሚሆን የተለየ አይሆንም:: ስለ እኔ ብዙ አወራሁ መሰል አንተስ ምንድነው የምሰራው? “ አለችኝ:: እኔ እንኳን ጋዜጠኛ ነኝ፤ ቆንጆ ስላልሆንኩም ነው መሰል እንዳንች ብዙ ያጋጠመኝ የህይወት ፈተና የለም አልኳት ፈገግ ላስብላት ብዬ::

እንዳሰብኩት ፈገግ ብላ “ኦው ደስ ይላል ጋዜጠኛና ደራሲ ሰው ደስ ይለኛል” አለች። ደስ አለኝ፤ በሆነ ርቀት እየተጠጋኋት እንደሆነ ተሰማኝ:: ቀጠለች “ጋዜጠኛም ደራሲም ስሜታቸው ስስ ይመስለኛል:: አንዳንዴ ደራሲ መሆን ያሠኘኛል:: በምናቤ የምመኛትንና የምስላትን እውነተኛ ጥሩ አለም በብዕሬ መፍጠር፣ የሚያሳምሙንን አይነት ሰዎችን እንደገና አፍርሸ መስራት! ደራሲ እኮ ነፃነት አለው፤ ሰፊ የመክነፊያ አድማስና አክናፍ አለው:: ጋዜጠኝነት ግን ይሄን አይነቱ እድል የለውም:: ያውም በልጓም የተጠፈነገ በቅሎ አይነት ነገር ስእል ያለው ይመስለኛል የእናንተ ሙያ፤ ተሳሳትኩ?” አለችኝ። ኧረ አልኩ ያለችው ተወሳስቦብኝ ሲጀመር እሧ ምንም ብትል ትክክል ናት አልኩ በውስጤ።

“ነገሩ ህሊና ያለው፣ አንባቢ የሆነ፣ የነፈሰው ንፋስ ሁሉ የማያንገዳግደው፣ የወገኑ ህመም የሚያመው ጋዜጠኛ ልጓም ከጉዞው ሊያደናቅፈው አይችልም፤ ልቡም እውነቱም የሚጓዘው ከህዝብና ከሀቁ ጋር ብቻ ነው:: ለማንኛውም ስለተዋወቅን ደስ ብሎኛል:: ቨርችዋል ሚቲንግ አለብኝ፤ ሰዓት ደርሷል፤ መልካም ምሽት” ብላኝ ፒሲዋን ከቦርሰዋ አስገብታ ተነስታ ወደ ውስጥ ገባች::ቆይታችንን ባልጠበኩት ፍጥነትና ሁኔታ አሣርጋው ለእኔ እድልም ሣትሰጠኝ ድንገት ብድግ ማለቷ እውነት ለመናገር አደነባብሮኛል። ፀጥ እረጭ ፍዝዝ ብዬ በአይኔ ሸኘኋት፤ ግን ምን ሆኘ ነው ስልክ ያልተቀበልኳት? ሺት!!!

ብሎ ጽሑፉ አልቋል።  ጽሑፉን ያገኘሁት ሱቅ ለሸቀጣ ሸቀጥ መጠቅለያ በኪሎ ከገዛሁት ወረቀት ጋር ነው፤ በሚያምር የእጅ ጽሑፍ የተጻፈ ጸሐፊው የማይታወቅ ጽሑፍ::

 

(በሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ)

በኲር የጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here