መንታ ገጽ

0
5

የተቃርኖ ሕግ ወይም ሎው ኦፍ ፖላሪቲ፤ ዓለም ከተቀበላቸው አይቀሬ ሕጎች አንዱ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ተቃራኒ እንዳለው እና እነዚህ ተቃራኒዎች ቀጣይነት ባለው መስመር ላይ የተገናኙ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡  ትኩስ እና ቀዝቃዛ፣ ብርሃን እና ጨለማ፣ ደስታ እና ኀዘንን፣ ዝምታ እና ንግግር የመሳሰሉ ጥንዶች እርስ በርስ እንደሚተረጓጎሙ ለማስረዳት ሕጉ  ያገለግላል፡፡

አንድን ነገር ያለ ተቃራኒው ሙሉ በሙሉ መረዳት እንደማይቻል ያስገነዝባል፡፡ ክፉ ሰው ባይኖር ደግነትን ማወቅ ወይም መለካት ከባድ ነው፡፡ ፉንጋዋ ቁንጅናን እንድናይ ታደርገናለች፡፡ አጭር ረጅሙን እንድናስተውል ያደርገናል፡፡ ሀብታሙ ደሀውን እንድናውቅ ያሳየናል፡፡ ለዚህም የአንደኛው መኖር ለሌላው ውበት ነው ወይም ጉዳት ሊሆን ይችላል፤ የተያያዙ ናቸው፡፡

ተቃራኒዎች የተለያዩ ብቻ ሳይሆኑ እርስ በርስ የሚደጋገፉ ናቸው። አንዱ ከሌለ ሌላኛው ሊኖር አይችልም፡፡ አንዱ ሌላውን ይገልጻል፣ ለምሳሌ ፍቅር ከጥላቻ በተቃራኒ ይታወቃል፡፡ ደስታ እና ኀዘን በአንድ ቀጣይነት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሕጉ አሉታዊ ስሜት ማጋጠሙ አዎንታዊ ተጓዳኙም መኖሩን ወይም እንደሚከተል ሊያመለክት እንደሚችል ይጠቁማል፡፡ ከደስታ በኋላ ኀዘን እንደሚመጣ ያሳያል፡፡

ሁሉንም ገጽታዎች መቀበል ደስታንም ሆነ ህመምን ማጣጣም የሙሉ የሰው ልጅ ተሞክሮ አካል ነው፡፡ አንዱ ወደ ሌላኛው ሊመራ ይችላል፡፡

የሀገራችን እውቀት ቤቶች ከሆኑት አንዱ ስነ ቃል ነው፡፡ ስነ ቃላችን ደግሞ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን ይዟል፡፡ ዝምታ እና ንግግር ላይ የተነገሩ ምሳሌዎችን ዛሬ እንፈትሻለን፡፡ ምሳሌያዊ ንግግሮቻችን ብዙ ጊዜ የሚጋጩ ይመስሉናል፡፡ “ዝምታ ወርቅ ነው ብለን፤ ዝምታ ለበግም አልበጃት ዘጠኝ ሆና ሄዳ አንድ ነበር ፈጃት” እንላለን፡፡

የተቃርኖ ሕግ እዚህ ላይ ይመጣል፡፡ ዝምታ ሁለት ጫፎች አሉት።  በአንድ ወገን አትናገር፣ ዝም በል፣ አፍህን ዝጋ የሚል ነው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ “ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል” በማለት ዝም አለማለት ከወርቅ ጋር ውድ ዋጋ ያለው ውሳኔ መሆኑን ያሳያል፡፡

ንግግር ያለ ጥበብ እና አውድ ሲሆን ዋጋ ያስከፍላል፡፡ “ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም” የሚለው የአበው ብሂል ይህን ሀቅ ለመጠቆም የተነገረ ይመስላል፡፡ “ዝምታ ማንን ገደለ” ም እንላለን፡፡ አሁን በየ ኑሯችን የሚያጋጥሙንን ሰዎች እናስታውስ እስኪ፡፡

ስብሰባ ወይም ጨዋታዎች ሲጀመሩ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ የመናገር እድል አገኘሁ ብለው ብዙ የሚያወሩ፡፡ ደግሞ ነገራቸው ፍሬ የለውም፡፡ ከጉዳዩ ጋር ትስስር የለውም፡፡ ፍርሀት እና አድርባይነትን ለማረጋገጥ የባጥ የቆጡን ይዘባርቃሉ፡፡ አድማጩ በትዝብት ይሰማል፡፡ መድረኩን የሚመራውም ሰው እነዚህ ሰዎች ከምን ስሜት እና መነሻ ምክንያት እንደሚናገሩ ያውቃል፡፡

እነዚህ ዓይነት ሰዎች ሁልጊዜ የሆነ ነጥብ ለማስቆጠር የሚናገሩ ናቸው፡፡ ወይም ሌላው ሰው በጥበብ እና በስልት ዝም ያለበትን የንግግር አውድ በድምጽ ለመሙላት የሚጥሩ ናቸው፡፡ ገና ማይክ ሲይዙ “ኧ… እሱ ነው?፣ እሷ ናት… “በማለት ታዳሚ የሚሰለቻቸው ዓይነት ሰዎች ናቸው፡፡

ንግግራቸው ሰው የሚያሰለች ይሁን እንጂ አንዳች ጊዜያዊ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ “ተውት ሰው እስኪሰበሰብ ድረስ ያውራ” ተብለው የንግግር ዕድል የሚሰጣቸው ሰዎች አሉ፡፡ ወልጋዳ እና ጠማማ ንግግራቸው ሰው ይረብሻል፡፡ ስድብ ወይም ዘለፋ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከብዙኀኑ አቋም የተለዬ ይሆንና “ዝም ቢል ምናለበት? ዝምታ ማንን ገደለ?” የሚባሉ ብዙ አሉ፡፡

የአንዳንድ ሰዎች ንግግር “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” እንደሚባለው በውስጣቸው የተከማቸውን ብሶት እና ምሬት የሚያንጸባርቅ ይሆናል። “አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል” ብለን እንድንናገር የሚያስገድደንን ሁኔታ ይፈጥራሉ፡፡ መናገራቸው ባልከፋ ነበር፡፡ ግን ንግግራቸው በዝምታ የሰጠናቸውን ክብር እና ሞገስ የሚያጠፋ ይሆናል፡፡ “አዬ ጉድ አንተዬ አያ እገሌ ደህና አዋቂ ይመስለኝ ነበር፣ እንዲህ ዓይነት ሰው ነው?” ብለን እንድንገረም የሚያደርግ የውድቀት ንግግር ይጀምራሉ፡፡

ጥሩ፣ አስተዋይ፣ ብልህ፣ የተማሩ የሚመስሉ ሰዎች መናገር ሲጀምሩ የእውቀት አቅማቸው በንግግር ይታያል፡፡ “አካሄዱን አይተው ሸክሙን ይቀሙታል” እንደሚባለው አነጋገሩን አይተው ሰብእናውን ይለኩታል፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንደ ሙሽራ አንደበታቸው ሲሸፈን መልካም ናቸው፡፡ መናገራቸው የተደበቀውን ሌላ ሰብእናቸውን ያሳይባቸውና በማህበረሰቡ ዘንድ ዋጋ ያጣሉ፡፡ ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል እንደሚባለው ብዙ ከመናገር ብክር እና ስም ይጎድፋል፡፡

“ዝም አይነቅዝም” የሚመጣው ይህን ጊዜ ነው፡፡ ደህና የተገነባን ስም ከማጥፋት፣ ከመዋረድ፣ በሌላ ገጽ ከመታየት ዝምታ በስንት ጣዕሙ የሚለው የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ እንደዚህ ቀደምት ስምና ክብርን የሚያጎድፉ አውዶች ላይ ከመናገር መቆጠብ የብዙዎችን ሰብእና ጠብቆላቸው ቀጥሏል፡፡ ከሚናገረው ዝም ያለው አስፈሪ ነው፡፡ ምን እንደሚፈልግ፣ ማን እንደሆነ ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ አለመታወቅ ምስጢራዊነትን ይፈጥራል፡፡ እንቆቅልሽ ነገር ያስፈራል፤ ፍርሀት ክብርን ይፈጥራል፡፡

“ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል” የሚልም አባባል አለን፡፡ ንግግር የሚወደስበት፣ የሚፈለግበት፣ የሚያሾምበት እና የሚያሸልምበት ጊዜ አለ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ መናገር ችግር ሆኖ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል የሚጠቁመን “ስለት ይቆርጣል ምላስ ያስቀጣል” የሚል ምሳሌ አለን፡፡ “ከማይናገር ከብቱን፤ ከማይራገጥ ወተቱን”ም ይባላል፡፡ ይህ ዝምታ ምን ያህል እንደሚጎዳ የሚያሳይ አነጋገር ነው፡፡  በአኗኗራችን ዝም የሚሉ ሰዎች እንደ ሞኝ የሚቆጠሩበት አሳዛኝ እውነት አለ፡፡ ይሉኝታ ይዟቸው ደግ ሲሆኑ ሰዎች ያለ አግባብ ይጠቀሙባቸዋል፡፡

ደግነት አንዳንድ ጊዜ ለራሳቸው ጠላት የሚሆንባቸው ሰዎች አሉ፡፡ ደግ ሆነው የማይቆጡ፣ ዝምተኞች፣ ይሉንተኞች ያፈሩትን ከብት ይነጠቃሉ፡፡ የማይራገጡ ላሞችም ለጥጃቸው ወተት እስኪያልቅ ድረስ ይታለባሉ፡፡ አባባሉም የሚለው የማይናገርን ሰው ከብቱን ይነዱበታል፤ የማትራገጠውንም ላም ወተቷን ያልቡባታል ነው፡፡ ክፉዋ ላማ’ማ ሰው ስለማታስጠጋ ትፈራለች፤ ትዋጋለች፤ ትከበራለች፡፡ በዚህ ጊዜ “የሚጮህ መዝጊያ ቅባት ያገኛል” ይላሉ አበው፡፡  መናገር ዋጋ የሚያገኝበት አውድ አለ፡፡ መብትን ፍላጎትን፣ ሐሳብን ካልተናገሩ የሰው ልቡ በምን ይታወቃል? እናማ መናገር የሰው ልጆች ምን ማድረግ እና መሆን እንደሚፈልጉ ያሳያል፡፡ ሰዎች ልባችንን ሳይሆን የምንናገረውን ቃል ነው የሚያውቁት፡፡ አንደበታችንን ሰምተው ይፈርዳሉ፡፡ ስንጠይቃቸው ይሰጡናል፡፡ ዝም ስንል ይከለክሉናል፡፡

አንዳንዱ አፈጮሌ በምላሱ ገብስ የሚቆላ አለ፡፡ ያልሰራውን እንደሰራ፤ ያልጀመረውን እንደፈጸመ ይናገራል፡፡ በምላሱ የሚያሳምን ሰው አለ፡፡ ሌላው ደግሞ የፈጸመውን መልካም ተግባር ለትሕትና ሲል ራሱን ከፍ ላለማድረግ ሲል እንዳልሰራ ዝም ይላል፡፡ ያልሰራው ሲመሰገን እሱ ችላ ሲባል ይበሳጫል፡፡ ‘አፈኛ ተወዶ’ ብሎ ይገረማል፡፡ በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም “ዝም ማለት ከሞኝ  ያስቆጥራል” የምትል አባባል የተነገረችው፡፡

የዚህ ጽሑፋችን ማሳረጊያ አባባል የምሳሌያዊ ንግግሮችን አውዳዊነት የሚያሳይ ነው፡፡ ንግግር ጉዳትም ጥቅምም አለው፡፡ መግቢያዬ ላይ እንዳልሁት የተቃርኖ ሕግ ሁልጊዜም ይሰራል፡፡ ቁም ነገሩ የምትናገርበትን እና ዝም የምትልበትን አውድ መረዳቱ ላይ ነው፡፡ ሁልጊዜ አትናገርም፡፡ ሁልጊዜ ዝም አትበል። ሁልጊዜ ዝምታ አይጠቅምም፡፡ ሁልጊዜ ንግግር አይጎዳም፡፡ በምን ሁኔታ፤ በምን ጊዜ እና በምን ቦታ ነው መናገር እና ዝም ማለት ያለብኝ የሚለውን ማወቅ ትልቁ ቁም ነገር ነው፡፡

አበው ይህንን ጉዳይ በዚህ አባባል ገልጸውታል፡፡ “ውኃ ሲጎድል ተሻገር ዳኛ ሲገኝ ተናገር” ብለዋል፡፡ ውኃ በሞላበት ክረምት ወንዝ እሻገራለሁ የሚል ሰው ሞኝ ነውና ሕይወቱን ያጣል፡፡ በበጋው ወራት ይሁን ነው ምክሩ፡፡ ሰሚ ዳኛ በሌለበት፣ ንግግር በማያስፈልግበት፣ ዋጋ ባጣበት ወቅትም መናገር ድካም ነው፡፡ ንግግር እና ዝምታ በሒሳብ መሆን አለባቸው፡፡ የሚያመጡትን ውጤት በማስላት መሆን አለበት፡፡ ብናገር ምን እጠቀማለሁ? ዝም ብል ምን አጣለሁ? ከሚል የህሊና ምክር ጋር መሆን አለባቸው የሚለው እውቀት ምሳሌያዊ ንግግሮቻችን ውስጥ የተከማቸ ሀብት ነው፡፡ ብንጠቀምበትስ?፡፡

 

ማረፊያ

 

አለቀለት ያሉት

(በእውቀቱ ስዩም)

ከጅረት አጠገብ ፥ቆሞ የኖረ ዛፍ

መብረቅ ገነደሰው

አሁን ድልድይ ሁኖ፥ ያሸጋግራል ሰው ::

“አለቀለት” ያሉት፤ ተልኮው መች አልቆ

ቆሞ የጠቀመ፥ መላ አያጣም ወድቆ፤

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here