የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ሥብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም አካሒዷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብሰባ የሰላም እና የፀጥታ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው በአባላቱ ተነስቷል። መንግሥት የሰላም እና የፀጥታ ችግርን ለመፍታትም ከወታደራዊ እርምጃ ይልቅ ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት እንዳለበትም ተነስቷል፣ እውነተኛ ውይይት እና ድርድር መከተል እንዳለበትም ነው የተነሳው።
የጅምላ እስር፣ ዜጎች በነፃነት እና በሰላም ተንቀሳቅሰው መሥራት አለመቻላቸው፣ የሰዎች እገታ፣ ፆታዊ ጥቃት፣ መፈናቀል፣ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ ግጪት ንፁኃንን ዋጋ እያስከፈለ ስለመሆኑ እና መሰል ጉዳዮች በምክር ቤት አባላት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ይገኙበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰጡት ምላሽ ሰላም ለሁሉም ነገር ወሳኝ ነው ብለዋል። ከመሞት እና ከመግደል ሰላምን ማስቀደም አዋጪ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከኃይል ይልቅ ሰላም በእጅጉ አዋጪ መንገድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከኃይል አማራጭ ይልቅ የሠላም አማራጭ ውጤቱ ከፍተኛ እና ተመራጭም ነው” ብለዋል።
“ጦርነትን በተግባር እናውቀዋለን። ብዙዎችን ቀጥፎብናል። ሰላምን በእጅጉ እንፈልገዋለን” ብለዋል። ሕልም ስላለን እና ያን ማሳካት ስለምንፈልግ ሰላምን እንሻለን” ነው ያሉት። እንደ ዶ/ር ዐቢይ ማብራሪያ መንግሥት ለሰላም ሁል ጊዜም በሩ ክፍት ነው። አሁንም ለሰላም የሚያቀራርብ ካለ መንግሥት ዝግጁ ነው።
በሰላም ከመኖር ይልቅ ጦርነትን የሚመርጡ አካላት እንዳሉም ገልጸዋል። ሰላምን የሚነሱ አካሄዶች ባለፉት ዓመታት መኖራቸውን በማስታወስ ሰላምን የሚነሱ ጉዳዮች በብዙ መንገድ ጉዳት ማስከተሉን ተናግረዋል።
አላስፈላጊ መባላት ከየትኛውም ጫፍ ይምጣ እንደማይጠቅም አንስተዋል። በምክንያት የሚያስብ እና የሰከነ ፖለቲካ እንደሚያስፈልግ በመጠቆም በንግግር እና በውይይት መሄድ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አንዳንድ ሰዎች እዚህም እዚያም የሚሉ እንዳሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ እኛ በጅምላ አናስርም፣ የመረጃ ችግር የለብንም፣ የምናስረው በጅምላ ሳይሆን በግብር ነው ብለዋል። ይህም አያዋጣም፣ የሚጠቅመው ይቅር ተባብለን በሰላም መኖር ነው ብለዋል።
እንደ ዶ/ር ዐቢይ ማብራሪያ መንግሥት ለሰላም ሁል ጊዜም በሩ ክፍት ነው። አሁንም ለሰላም የሚያቀራርብ ካለ መንግሥት ዝግጁ ነው ብለዋል። በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሰላም ንግግር እንዳለም አመላክተዋል። ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ተሳስተን ከሆነ እናርማለን፣ ይህን የምናደርገው ደግሞ ተቀራርበን ስንወያይ ነው ብለዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም)