መዓዛ – የጋዜጠኝነት ተምሳሌት

0
254

“የሚሠራውን የሚወድ፣ የሚወደውን ለመሥራት ሁልጊዜም አዳዲስ መላዎችን ይፈልጋል” ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ::

“በአንድ ጊዜ ብዙ ሰዎች ጋር ስለምንደርስ ብዙ ሰዎችን እናሳስታለን፤ በአዋቂዎች ትዝብት ውስጥም እንገባለን”

ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የሬዲዮ ሥራ በተለየ ጥንቃቄ መሠራት እንዳለበት ከገለፀችው::

በዛሬው የበኲር የኛ ገጽ አምድ እትማችን የምናስነብባችሁ ስለአንጋፋዋ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ነው:: ስለ መዓዛ ብሩ መረጃዎችን ለአንባቢያን ለማድረስ ተምሳሌት መጽሔትን፣ ተወዳጅ ሚዲያን እና ሌሎች ስለ መዓዛ የተከተቡ ጽሑፎችን በምንጭነት ተጠቅመናል:: ጋዜጠኛዋን በስልክ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ግን ያለመሳካቱንም  በዚሁ አጋጣሚ መግለጽ እንፈልጋለን::

ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በ1950 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደች ቢሆንም እስከ ዘጠኝ ዓመቷ ድረስ የኖረችው በምዕራብ ሀረርጌ በምትገኘው ሂርና ከተማ ውስጥ ነው:: የታዳጊነት ጊዜዋን በሂርና ያሳለፈችው መዓዛ በወቅቱ የቤተሰቦቿ ጐረቤት የነበሩት ኦሮሞዎች፣ የሀረሪ፣ የየመን እና የሶማሌ ተወላጆች በመሆናቸው ለባሕላዊ እሴቶች እና ለርስ በርስ ትስስሮች ቅርብ ሆና አድጋለች፤ ይህም ለሥነ ጽሑፍ ከነበራት ዝንባሌ ጋር ተዳምሮ ለዛሬው ማንነቷ መሰረት ጥሎላታል::

ጋዜጠኛ መዓዛ ዘጠኝ ዓመት ሲሆናት ወላጆቿ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የቅድስት ማርያም ካቶሊከ አዳሪ ትምህርት ቤት አስገብተዋታል:: በ1967 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለች ደግሞ በእድገት በህብረት የዕውቀት እና የሥራ ዘመቻ በትግራይዋ ውቅሮ ከተማ  ለስድስት ወራት አገልግላለች:: በ1970 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብታ በሥነ ልሳን ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች::

መዓዛ ከሬዲዮ ሥራ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀችው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሆና በተፈጠረ አጋጣሚ ነው:: ይሄው አጋጣሚም በወቅቱ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ተወዳጅ ከነበረው የእሁድ ፕሮግራም ጋር ለነበራት የስምንት ዓመታት ቆይታ ምክንያት ሆኗታል:: ይሁን እንጂ ጋዜጠኛ መዓዛ በመጀመሪያ በቋሚነት የተመደበችበት ሥራዋ በባሕል ሚኒስቴር ሥር የመርሃ ስፖርት ጋዜጣ የስፖርት ዘጋቢ ሆና ነው::

ጋዜጠኛ መዓዛ በብሔራዊ ባንክ የ”ብሪቱ” መጽሔት ዋና አዘጋጅ በመሆን የምጣኔ ሀብት ዜናዎችን እና አጫጭር ታሪኮችን በመፃፍ እና በአርትኦት አገልግላለች:: በ1984 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ተቀላቅላ የፕሬስ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያ በመሆንም ለአራት ዓመታት ሠርታለች:: ከዚያም በግል አማካሪነት እና በሕዝብ ግንኙነት እንዲሁም ማስታወቂያዎችን ስትሠራ ከቆየች በኋላ በ1987 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮ በ97 ነጥብ አንድ የሬዲዮ ጣቢያን የዓየር ሰዓት በመጠቀም የቅዳሜ ከሰዓት የጨዋታ ፕሮግራምን ከባለቤቷ ከከያኒ አበበ ባልቻ እና ከረዥም ጊዜ ጓደኛዋ ከያኒ ተፈሪ ዓለሙ ጋር ለስምንት ዓመታት አዘጋጅታለች::

አንጋፋዋ ጋዜጠኛ መዓዛ በ2000 ዓ.ም  ሸገር ኤፍ ኤም 102 ነጥብ አንድን እውን ለማድረግም በቅታለች:: መዓዛ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳን የመጨረሻ ዓመት ተማሪ በነበረችበት ወቅት የመኝታ ቤት /ዶርም/ ተጋሪዋ የነበረችውን ከያኒ መንበረ ታደሰን ፍለጋ የመጡት አንጋፋዎቹ የቲያትር ባለሙያዎች አስታጥቃቸው ይሁን እና ተፈሪ ዓለሙ መንበረን ስላጧት በእርሷ ፈንታ መዓዛ አብራቸው ሄዳ ጭውውቱን አብራቸው እንድትሠራ ሞግተዋታል፤ እሷም ከብዙ ሙግት በኋላ ፈቃደኛ ሆናለች::

ጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህ በሚያዘጋጀው በኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሁድ ፕሮግራም ላይ ድምጿን አሟሽታ፣ በኤፍ ኤም አዲስ በኩል ተሻግራ በሸገር የተገለጠችውን መዓዛን ያገኘናት በዚህ መልኩ ነው:: የጋዜጠኝነት ሙያ ሲነሳ ስሟ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚነሳው መዓዛ ብሩ “ገና  ምንም አልሠራሁም” በማለት ህልሟ  አሁን ካለችበትም ከፍታ ሌላ የተሻለ ከፍታ ላይ መገኘት መሆኑን ትናገራለች::

የዚያንጊዜው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈቃዱ እምሩ ለከያኒ አበበ ባልቻ /የመዓዛ ባለቤት/ ኤፍ ኤም አዲስ ላይ የዓየር ሰዓት ወስዶ ሥራ እንዲጀምር ሀሳብ ያቀርቡለታል:: ይሄ ሀሳብ የጨዋታ ፕሮግራም ጥንስስ ሆነ:: መዓዛ እና ተፈሪ ዓለሙ በኋላም ጌታቸው ማንጉዳይ፣ ብርሃኑ ድጋፌ፣ ግሩም ዘነበ እና ደረጄ ኃይሌ ተቀላቅለው ጨዋታ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ዓየር ላይ ዋለ::

በሬዲዮ መጽሔት ቅርጽ የሚዘጋጀው የቅዳሜው ጨዋታ ፕሮግራም ለሸገር ኤፍ ኤም እንደ መንደርደሪያ ሆኖ አገልግሏል:: መንግሥት ለግል የሬዲዮ ጣቢያ ፈቃድ እንደሚሰጥ ሲያስነግር እና  አበበ ባልቻ ለባለቤቱ በዕድሉ መጠቀም እንዳለባቸው ሲነግራት “ፈቃዱን ብናገኝስ ምኑን ከምኑ ልናደርገው ነው? ትንሽ መቆየት አለብን” እንዳለችው ስለ መዓዛ በተሰነዱ ታሪኮች ውስጥ ተገልጿል:: የመዓዛ የወቅቱ ሥጋት ከ90 ዓመቱ አንጋፋው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋር ፉክክር ወይም ውድድር ውስጥ መግባት አለመቻላቸው መሆኑም ተጠቅሷል::

መስከረም 25 ቀን 2000 ዓ.ም ወደ አድማጮች መድረስ የጀመረው ሸገር ኤፍ ኤም 102 ነጥብ አንድ ለዓመታት ዘልቋል:: ከእሁድ ጠዋት አጫጭር ጭውውቶች የተነሳው የመዓዛ የሬዲዮ ዘመንም እሷን በጋዜጠኝነት መንበር ላይ አስቀምጦ ዓመታትን አስቆጥሯል:: “እኔ እና ተፈሪ ዓለሙ በሰዎች ጆሮ ውስጥ ነው ያደግነው” የሚለው የመዓዛ ንግግርም የተቀዳው ከዚሁ ስኬቷ ነው::

“ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ከምትሠራቸው የሬዲዮ ፕሮግራሞች መኮረጅ መቻል ራስን ከፍ ወዳለ ጋዜጠኝነት መውሰድ ነው” የሚሉ አድናቂዎቿን ያፈራችው አንጋፋዋ ጋዜጠኛ፣ በብዙ ነገሮቿ ለጀማሪ ጋዜጠኞች አርአያ የምትሆን ናት። አንዳንድ ጋዜጠኞች ደግሞ ስለመዓዛ ሲናገሩ “እሷን እያየሀት እና እየሰማሀት ትማርባታለህ፤ የጋዜጠኝነት ጉልበቷ ሁሌም አዲስ እና የማይዝል ነው፤ ለእያንዳንዱ ፕሮግራሞቿ ከዝግጅት እስከ ቀረፃ ያለው ትጋቷ አስገራሚ ነው” ይሏታል።

“መዓዛ በሚዲያ ሥራ የካበተ ልምድ ያዳበረች ናት፤ ያንን ልምዷን ከቃለ መጠይቋ ላይ ማግኘት ይቻላል:: የመዓዛ እውቀት ከንባብ የመጣ ነው:: ክህሎቷ በየጊዜው ያዳበረችው እና ብዙ ነገሮችን የጨመረችበት ነው:: እኔ ሸገር ካፌንም ሆነ ጨዋታ መሰናዶን በንቃት አዳምጣለሁ፤ የእንግዳ እና የርዕሰ ጉዳይ ምርጫዎቿ ይደንቁኛል:: ያላት አቀራረብ፣ ቁጥብነቷ እና ሌሎች ችሎታዎቿ አድማጭን ይማርካሉ፤ እርጋታዋ ይስበኛል፤ መዓዛ ቃለ መጠይቋ የሚጠገብ አይደለም:: የመዓዛን ቃለ መጠይቆች እየደጋገምኩ የማዳምጥበት ጊዜ አለኝ፤ ከመዓዛ ድምፀት የውስጥ ማንነቷን ማወቅ ይቻላል፤ ጨዋነት እና መረጋጋት የእሷ መክሊቶች ናቸው” ስትል ስለ መዓዛ አስተያየቷን የሰጠችው ደግሞ የቲያትር መምህርት እና ባለሙያዋ ማህሌት ሰለሞን ናት::

መዓዛ ብሩ በማህሌት ዕይታ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ የመጣች ባለሙያ ናት:: “ከሸገር ጥንካሬ ጀርባ ያለችው ዋናዋ ሰው መዓዛ ናት” ስትል ማህሌት የመዓዛ ጥንካሬ እና ጥረት ለብዙዎች ተምሳሌት እንደሚሆን ትናገራለች።

“መዓዛ ፕሮግራሞቿን ተጨንቃ የምታቀርብ በመሆኑ በአድማጭ መከበር እና መወደድ ችላለች፤ የምትሠራቸው ፕሮግራሞች ዓየር ላይ ከመዋላቸው በፊት በቂ ጥናት እንደተደረገባቸውም ያስታውቃሉ” ያለችው ደግሞ የጨዋታ እንግዳ ፕሮግራም 20ኛ ዓመትን አስመልክቶ መዓዛን በአጭሩ ያናገረቻት የሸገር ባልደረባዋ ሕይወት ፍሬስብሃት ናት:: መዓዛ በሕይወት ፍሬስብሃት የጨዋታ ዝግጅትን ከነ ሙሉ ክብሩ ለ20 ዓመት ማቆየት እንዴት ተቻለሽ?” ተብላ ስትጠየቅ፣ “የሚሠራውን የሚወድ፣ የሚወደውን ለመሥራት ሁልጊዜም አዳዲስ መላዎችን መፈለግ ይችላል” ብላ መልሳላታለች::

አንጋፋዋ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ለሬዲዮ የተፈጠረች፣ ይህን መክሊቷንም አውቃ በምትወደው ሙያ የተሰማራች ታላቅ ሰው ናት:: መዓዛ ላለፉት 40 ዓመታት ከሚዲያው ገጽ ላይ ጠፍታ አታውቅም:: ሙያዋን አክብራ እሷም ተከብራበታለች:: ከመታየት ይልቅ መሥራትን ያስቀደመችው መዓዛ የሙያውን ሕግ ተከትላ በከፍታ ነግሳበታለች:: መዓዛ በአንድ በኩል የመጀመሪያውን የግል ሚዲያ የከፈተች ጠንካራ ጋዜጠኛ ስትሆን ዓየር ላይ የምታውላቸውን “ምርጥ” መሰናዶዎች በማድመጥ ወጣቱ በመልካም ባሕርይ እንዲቀረጽ ባደረገችው ጥረትም ዓርአያ የምትደረግ ናት::

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 16/2015 ዓ.ም ባካሄደው የተማሪዎች ምረቃ ለጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መስጠቱ ይታወሳል:: ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የግል ኤፍ ኤም ሬዲዮ የሸገር መሥራች እና ባለቤት በመሆኗ፣ የመጀመሪያዋ ሴት የሬዲዮ ማሰራጫ ድርጅት መሥራች እና ባለቤት በመሆኗ፣ በእንግዶች ምርጫ፣ በምርምር በተደገፈው የመጠይቅ ዘይቤዋ፣ በትህትናዋ፣ በአነጋገር ለዛዋ፣ በቀጥታ ሥርጭቶቿ፣ በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ አሻራ የተወች እና ባጠቃላይ በዚህ ዘርፍ ለተሰማሩ ጋዜጠኞች አርአያ በመሆኗ የዩኒቨርሲቲውን የክብር ዶክትሬት አግኝታለች::

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንም የካበተ ልምዷን እና ችሎታዋን ታሳቢ በማድረግ በ2014 ዓ.ም አንጋፋዋን ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩን ወደ ተቋሙ በመጋበዝ ተሞክሮዎቿን ለሌሎች ጋዜጠኞች እንድታካፍል አድርጓል::

እኛም የአንጋፋዋን ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩን ቅንጭብ ታሪክ በበኲር ጋዜጣ የኛ ገጽ አምድ ላይ ስናሰፍር ለብዙ ጋዜጠኞች ተምሳሌት እንደምትሆን በማመን ነው::

 

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here