መዳረሻዉ እንዳይከስም

0
8

በዕውቀት የበቁ፣ በመልካም አስተሳሰብ እና አመለካከት የተቃኙ ዓለምአቀፋዊ ተማሪዎችን ማፍራት የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓቱ ቁልፍ መለኪያ ነው:: ለብቁነታቸውም የትምህርት ተነሳሽነት እና የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ሥራዎችን ለይቶ መሥራት እንደሚገባ ይታመናል:: ተማሪዎች የመማር ፍላጎት እና ዓላማን መርህ አድርገው እንዲነሱ ከመሥራትም በተጨማሪ በትምህርታቸው ውጤታማ እና ተወዳዳሪ ሆነው በዓለም የሰለጠነ የሰው ኅይል ገበያ ውስጥ ተፈላጊነታቸውን ከፍ ለማድረግ የጥናት ፍላጎትን ማዳበር ያስፈልጋል::

ውጤታማ የትምህርት ሥርዓት እንዲኖር በርካታ ቁልፍ ተግባራት እንዳሉ የትምህርት ባለሙያዎች ቢጠቅሱም የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባ ግን የትምህርት ተደራሽነት፣ ተሳትፎ እና ጥራት እንዲሰፋ ጉልህ ሚና ይጫወታል:: ኢትዮጵያ ለትምህርት ትልቅ ጉጉት ኖሯቸው ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ተማሪዎች በሁሉም መለኪያ ውጤታማ እንዲሆኑ ለትምህርት ቤት የተማሪ ምገባ ትኩረት ሰጥታለች::

ሀገሪቱ የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባን የትምህርት ሥርዓቱ አንዱ አካል አድርጋ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ አውርዳለች:: የምገባ መርሀ ግብሩ ግን ወቅታዊ ችግሮችን (ድርቅ…) መነሻ በማድረግ ከ1980ዎቹ ጀምሮ ሲካሄድ እንደ ነበር የትምህርት ሚኒሥቴር መረጃ ያሳያል::

የተማሪዎችን ተሳትፎ  ማሳደግ፣ የጤና እና የሥነ ምግብ ሁኔታን ማሻሻል፣ በትምህርት ቤቶች የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ማስቻል፣ የሕጻናትን አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ደኅንነት ማስጠበቅ ዓላማ ያደረገው መርሀ ግብሩ ዛሬ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በንቅናቄ እየተከናወነ ነው::

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርም ለትምህርት ቤት የተማሪ ምገባ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል:: የአስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ “አንድም ሕጻን በምግብ እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታው እንዳይለይ ኃላፊነታችንን እንወጣ!” በሚል መሪ ሐሳብ የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባ የሐብት ማሰባሰቢያ የንቅናቄ መድረክ ጥቅምት 17 ቀን 2017 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል:: የመሪ ቃሉ ዋና መልዕክት በትምህርት የሚቀየሰው ረዥሙ የሕይወት መንገድ በመሠረታዊ ፍላጎቶች አለመሟላት ምክንያት እንዳይከስም “ሁሉም ካለኝ ለሌለው” ብሎ የበኩሉን ይወጣ የሚል ነው::

”ትውልድ ግንባታ ይመለከተኛል፤ ሕጻናት ላይ መሥራት ሀገርን መሥራት ነው” ያሉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ባለሀብቶች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና ረጂ ድርጅቶች በሐብት ማሰባሰቢያ መድረኩ ላይ ተገኝተው ነበር:: በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ድርጅቶች ለምገባው ውጤታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚወጡ ተናግረዋል:: የምገባ ፕሮግራሙ ዓላማ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው ተደራሽነቱን ማስፋት ላይ እንዲተኮርም ጠይቀዋል:: ዘላቂነቱን ማረጋገጥ ደግሞ ዋናው ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል::

በመድረኩ ላይ የተገኙት የትምህርት መምሪያ ኃላፊው ሙሉዓለም አቤ (ዶ/ር) የተማሪዎችን የምግብ ፍላጎት ማሟላት አለመቻል የብዙ ታዳጊ ሀገራት ወላጆች ዋነኛ ችግር መሆኑን አንስተዋል:: ይህ ችግር በታዳጊዎች አካላዊ ዕድገት፣ የትምህርት አቀባበል፣ በመድገም እና በማቋረጥ ምጣኔ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ ነው::ሀገራትም የችግሩን ተጽእኖ በጉልህ በመረዳት የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባን የትምህርት ሥርዓታቸው አካል ማድረጋቸውን ዶ/ር ሙሉዓለም ገልጸዋል:: ለተማሪ ምገባ ልዩ ትኩረት የሰጡ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየውም በትምህርት ቤቶች የሚሰጠው ምገባ የመድገም እና የማቋረጥ ምጣኔ በእጅጉ እንዲቀንስ እንዲሁም የተማሪዎች የትምህርት ብቃት እንዲሻሻል ማድረጉን ጥናቶችን ዋቢ አድርገው አንስተዋል::

ለሀገራችን የትምህርት ሥርዓት ቁልፍ ችግሮች የመድገም፣ የማቋረጥ እና የብቃት ደረጃ ማነስ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ለዚህም መሠረታዊ ምክንያቱ ከምግብ እጥረት ጋር የተገናኘ እንደሆነ አንስተዋል:: የኢትዮጵያን የሕዝብ ጤና ጥናት ዳሰሳ ውጤትን መሠረት አድርገው እንዳነሱት ሕጻናት በጥቃቅን ንጥረ ነገሮች እጥረት ተጠቂ ናቸው:: ይህም ችግር በሕጻናት አካላዊ፣ አዕምሯዊ ዕድገት እና የትምህርት ውጤት ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚፈጥር ገልጸዋል::

ብቁ፣ በቂ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ዜጋ ለማፍራት በኢትዮጵያ የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የትምህርት ሥርዓቱ አንዱ አካል ተደርጎ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል:: የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም መምሪያ ኃላፊው አስታውቀዋል:: በ2017 ዓ.ም 10 ሺህ ተማሪዎችን በትምህርት ቤት የተማሪ ምገባ ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ መያዙ ይታወሳል:: ከዚህ ውስጥ ዘጠኝ ሺህ 267 የቅድመ፣ የልዩ፣ የአንደኛ እና የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በምገባ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል::

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ለምገባ መርሀ ግብሩ  42 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ወጭ ሆኖ በ17 ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ሆኗል:: ከዚህ ውስጥ 20 ሚሊው ከግለሰቦች እና ከረጂ ድርጅቶች በድጋፍ የተገኘ ነው:: ይህም ከመንግሥት ውጪ ያለው አካል ትኩረት እንደሰጠው ማሳያ ተደርጓል::

ከተማ አስተዳደሩ በ2018 የትምህርት ዘመን 20 ሺህ ተማሪዎችን በምገባ ተጠቃሚ ለማድረግ ማቀዱ ተጠቁሟል:: የሚያስፈልገው አጠቃላይ በጀትም 112 ሚሊዮን ብር መሆኑ ተገልጿል:: ምገባው ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ፈተና የሆኑትን ችግሮች ለመቅረፍ ከፍተኛ ፋይዳ አለው:: ከመንግሥት በተጨማሪ የከተማ ነዋሪው፣ ባለሐብቶች፣ ረጂ ድርጅቶች… ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርበዋል::

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር  ትምህርት የትውልድ ቅብብሎሽ ማስተሳሰሪያ ገመድ፣ የሀገር ዕድገት እና ስልጣኔ መሠረት መሆኑን ጠቁመዋል:: የትምህርት ዘርፉን ለማሳደግ እና አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታውን ለመቀየር ደግሞ ከታችኛው የክፍል ደረጃ ጀምሮ ያሉ ተማሪዎችን መንከባከብ እና ማብቃት እንደሚገባ አስገንዝበዋል:: ከመሠረቱ ጀምሮ ትምህርት ላይ የሚሠራ ሥራ በዕውቀት የዳበረ ችግር ፈቺ ትውልድ በማፍራት በሀገር ግንባታ ላይ ትልቅ አሻራ እንደሚያሳርፍ ተናግረዋል:: ለዚህም የማኅበረሰቡ፣ የተቋማት እና የመንግሥት ሚና ጥምርታ ከፍተኛ መሆኑን ነው ያስታወቁት::

ልጆቻቸው የሚፈልጉትን መሠረታዊ ፍላጎቶች አሟልተው ማስተማር ያልቻሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ የትምህርት ቁሳቁስ ከመሸፈን ጀምሮ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ መርዳት የሁሉም ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል:: አንድም ተማሪ በምግብ ክፍተት ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይርቅ ከመረባረብ ጀምሮ የተሻለ የትምህርት አቀባበል እንዲኖር ትኩረት መሥጠት እንደሚገባም አሳስበዋል::

በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ባለሙያ መኮንን ታደሰ ከአሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ጋር ቆይታ አድርገዋል:: በክልሉ ድርቅ እና እርጥበት አጠር በሆኑ አካባቢዎች የተጀመረው የተማሪ ምገባ ከአሥር ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ ተናግረዋል:: መርሀግብሩ  በተደራጀ መንገድ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ደግሞ በ2009 ዓ.ም  እንደሆነ ገልጸዋል:: ይህም የተማሪዎች የመቅረት እና የማቋረጥ ምጣኔ እንዲቀንስ ማድረጉን ጠቅሰዋል:: ከዚህም ባለፈ የተማሪዎች የትምህርት አቀባበል እንዲሻሻል፣  ከክፍል ክፍል መዛወር እና ውጤታቸው እየተሻሻለ እንዲመጣ ማስቻሉን ለምገባው ውጤታማነት ማሳያ በማድረግ አንስተዋል::

በ2018 የትምህርት ዘመን በክልሉ ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን በትምህርት ቤት የተማሪ ምገባ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን አቶ መኮንን አስታውቀዋል:: ለፕሮግራሙም 500 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቧል:: በአሁኑ ወቅት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም የምግብ ፕሮግራም እየተደገፉ የሚገኙ 132 ሺህ ተማሪዎች የምገባ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል::  የትምህርት ቤት ምገባን እንደ አንድ የትምህርት ግብዓት በመውሰድ ማኅበረሰቡ፣ ባለሃብቶች እና ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል።

 

መረጃ

የንባብ ክህሎት የማሳደጊያ ስልቶች

  • ዘወትር ማንበብ

ዘወትር ቀን በቀን የማንበብ ልምድ ይኑራችሁ።  በእያንዳንዱ ቀን  የምታነቡበትን ጊዜ አስቀምጡ።

  • ትክክለኛ የንባብ ቁሳቁሶችን ምረጡ

ከእድሜ እና ከፍላጎት ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ ወይም የሚጣጣሙ የንባብ ቁሳቁሶችን ምረጡ። ቀለል ያሉ መጽሐፍት ወይም ጽሑፍ በመምረጥ መጀመር፤ ከዚያም በሂደት የመረዳት ችሎታችሁን እያያችሁ ውስብስብ የሆኑ መጽሐፍትን እና ፅሁፎችን በማንበብ እራሳችሁን ፈትኑ።

  • መዝገበ ቃላት መጠቀም

አውዳዊ ፍችን በመጠቀም አዳዲስ ቃላት ተማሩ። ለየት ያሉ ቃላቶች በሚገጥሙ ጊዜ የመዝገበ ቃላት መጽሐፍ ውስጥ በመፈለግ እና በዐረፍተነገር ውስጥ እየተለማመዳችሁ ተጠቀሙባቸው።

  • የመረዳት ችሎታን ማሳደግ

አንድን ጽሑፍ ከማንበብ በፊት ፣ ስታነቡ ወይም ካነበባችሁ ቡኋላ ስለ ጽሁፉ ምንነት እና በርዕሱ ላይ ያላችሁን እውቀት እና ግንዛቤ እራሳችሁን ጠይቁ። ስላነበባችሁት ጉዳይ  ሰዎች ጋር ተወያዩ፣ ማጠቃለያ ስጡ እንዲሁም የራሳችሁን ሃሳብ እና ምልከታ አስቀምጡ።

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here