ተፈጥሮ ፊቷን ያዞረችበት የ2015 ዓ.ም የክረምት ወቅት አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን መጋቢ እጆችን ለልመና እንዲዘረጉ አስገድዷል:: በአማራ ክልል በዝናብ እጥረት ምክንያት የተከሰተው ድርቅ በዘጠኝ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ 43 ወረዳዎችን እና 429 ቀበሌዎችን ተጋላጭ ማድረጉን የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን መረጃ ያሳያል::
አርሶ አደር እንዳለ ተገኘ ድርቁ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ የከፋ ተጽእኖ አሳድሮበታል በተባለው በሰሜን ጎንደር ዞን የጃናሞራ ወረዳ ነዋሪ ናቸው:: “ያ ክፉ ዓመት!” ሲሉ የጠሩት 2015 ዓ.ም በታሪክ ሲታወስ እንደሚኖር ጠቁመዋል:: ለ2015/16 የመኸር ወቅት በበጋው ማሳቸውን ሲያጸዱ፣ ሲያርሱ እና ሲያለሰልሱ የተሻለ ምርት ወደ ጎተራቸው እንደሚያስገቡ በመተማመን ነበር:: ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር እንዳሰቡት አልሆነም:: ክረምቱ በጋ ሆኖ ምንጮች ነጥፈዋል፤ ወንዞች ደርቀዋል፤ ዛፎች ያለ ቅጠል ቀርተዋል። እንስሳት የሚበሉት እና የሚጠጡት አጥተው ሞተዋል፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እንስሳትም ምግብ እና ውኃ ፍለጋ ተሰደዋል::
አርሶ አደሩ ክረምቱን ተማምኖ በውድ የገዛውን ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ ላልራሰው መሬት አደራ ሰጥቶታል፤ ሰማዩ ግን ምላሽ አልሰጠም:: ዛሬን ለተሻለ ነገር አስቦ ትናንት ያመረተውን በመሸጥ የግብርና ግብዓትን ገዝቶ ለመሬቱ በአደራ የሰጠው አርሶ አደር ማሳውን እየተመላለሰ ቢመለከትም መልስ አጥቶ መጋቢ እጁን ለልመና ዘርግቷል::
አርሶ አደር እንዳለ እና ሌሎች ለድርቁ ተጋላጭ የሆኑ ወገኖች ከመንግሥት በኩል የዕለት ደራሽ ምግብ እየቀረበላቸው ሕይዎታቸውን እስካሁን አቆይተዋል:: በአንድ የቤተሰብ አባል 15 ኪሎ ግራም የዕለት ደራሽ ምግብ እየቀረበ መሆኑን አቶ እንዳለ በስልክ ገልጸዋል:: ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የድጋፍ አቅርቦቱ እየቀነሰ መምጣቱን አስታውቀዋል:: ይህም ለመጪው የክረምት ወቅት በስፋት አምርቶ ከተረጂነት ለመውጣት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በማደናቀፍ ችግሩ ወደ ቀጣይ ዓመትም እንዳይሻገር ሥጋታቸውን ገልጸዋል::
“እኛ አሁንም የምንፈልገው 15 ኪሎ ግራም ድጋፍ አይደለም። የሞቀ ቤታችን እንዲመለስ እንፈልጋለን። ከራሳችን የምግብ ፍጆታ አልፈን ለገበያ ማቅረብ እንፈልጋለን። በአሁኑ ወቅት ለዘር እየተዘጋጀን ነው፤ ነገር ግን ብር ስለሌለን የግብርና ግብዓት እጅ በእጅ /በካሽ/ መግዛት አልቻልንም። እኔ ከሁለት ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እፈልጋለሁ፤ በቂ የአፈር ማዳበሪያም ወደ ወረዳው እየገባ ነው፤ እኔን ጨምሮ በርካቶች ግን አሁንም ድረስ የግብርና ግብዓት መግዛት እና መጠቀም አልቻልንም። ምክንያቱም ከዚህ በፊት በነበሩ ዓመታት የግብርና ግብዓት የምንገዛው ካመረትነው ሽጠን በምናገኘው ገንዘብ ነበር። አሁን ግን የምንሸጠው ባለማግኘታችን የመንግሥትን እጅ እያየን ነው” በማለት ትናንትን ከዛሬ እያነጻፀሩ የችግሩን ስፋት አብራርተዋል::
አሁን ያለው የተረጂ ቁጥር እንዳይቀጥል፣ ተማሪዎችም ያለምንም ሀሳብ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ፣ የተሰደደውም ወደ ቀዬው ተመልሶ የተለመደ የልማት ሥራውን እንዲያስቀጥል መንግሥት በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ከሌላው በተለየ መንገድ የግብርና ግብዓት ሊያቀርብ እንደሚገባ አርሶ አደሩ ጠይቀዋል::
የዕለት ደራሽ ምግብ ድጋፍ እየተከናወነ ቢሆንም በበቂ መጠን እየቀረበ አለመሆኑን በስልክ ያነጋገርናቸው ሌላው የጃናሞራ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር መንገሻ አዲሴ ናቸው:: “ያም ሆኖ ይህ ወቅቱ የክረምት እርሻ ሥራ የሚጀመርበት መሆኑ ችግራችንን እረስተን ለነገ መልካም ቀን ተስፋን ሰንቀን እየተንቀሳቀስን ነው” ብለዋል::
“እንደ እጅ ጠባቂነት የሚያሳፍር ነገር የለም” ያሉት አርሶ አደሩ፣ ለተጎጂ ወገኖች የዕለት ደራሽ ምግብ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ ከማስቀጠል ጎን ለጎን ለዘላቂ መፍትሄዎች ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል:: በዓመቱ የተሻለ የአፈር ማዳበሪያ እየገባ እና እየተሰራጨ መሆኑ ደግሞ የአርሶ አደሩን ከተረጂነት የመውጣት ፍላጎት ከዳር ለማድረስ የሚያግዝ እንደሚሆን ጠቁመዋል::
አንድ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በአራት ሺህ 40 ብር እየተሸጠ መሆኑን ያስታወቁት አርሶ አደሩ፣ ይሁን እንጂ ይህ ዋጋ ሁሉ ነገራቸውን በድርቅ ላጡ አርሶ አደሮች ፈታኝ እንደሚሆን ራሳቸውን አብነት በማድረግ ጠቁመዋል:: በ2015/16 የምርት ዘመን ያጋጠመው የዝናብ እጥረት ከምርት ውጪ እንዲሆኑ ማድረጉ፣ እንስሳቱን በስደት እና በሞት ማጣቱ በዘንድሮው የመኸር እርሻ በስፋት አምርቶ ከተረጂነት ለመውጣት ፈተና እንደሚሆንም ጠቁመዋል::
“ተረጂነት ወይም ልመና ፈተና ነው” የሚሉት አርሶ አደሩ፣ ከጠባቂነት ለመውጣት በጋውን በዘር የሚሸፍኑትን መሬት ደጋግመው በማረስ እና በማለስለስ አሳልፈዋል:: አርሶ አደሩ በመጭው መኸር አንድ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን ነው ዝግጅት እያደረጉ ያሉት:: ለዚህም ሁለት ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋቸው አቅደዋል:: ነገር ግን አሁን ባለው ዋጋ ሁሉንም ለመግዛት ባለመቻላቸው እስካሁን ከ50 ኪሎ የበለጠ አልገዙም:: ይህንንም በብድር እንደገዙት ተናግረዋል::
መንግሥት የዕለት ደራሽ ምግብ ከማቅረብ በተጨማሪ የተለያዩ ረጂ ድርጅቶችን በማስተባበር የግብርና ግብዓትን በድጋፍ ወይም በብድር ለማቅረብ እንዲተጋ ጠይቀዋል::
ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ማንነት ተኮር ጥቃቶች፣ የፍትሐዊነት እና የእኩል መልማት ጥያቄዎችን መነሻ አድርገው እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች እና በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥሙ ተፈጥሯዊ ችግሮች የብዙኃኑን የምግብ ዋስትና አደጋ ውስጥ ጥለዋል:: የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የቅርብ ጊዜ ሪፖርት እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የምግብ እርዳታ ድጋፍ ይሻሉ::
የፌዴራል አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን በበኩሉ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ስድስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተረጋግጦ የተቀናጀ ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን በድረ ገጹ አስታውቋል:: በአማራ ክልል ያለው የተረጂ ቁጥርም ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን መድረሱን የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታውቋል::
የጃናሞራ ወረዳ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሷሊህ ሐሰን በወረዳው 20 ቀበሌዎች የተከሰተው የዝናብ እጥረት ከ3 እስከ 12 ወር የሚደርስ የምግብ ክፍተት መፍጠሩን አንስተዋል:: ይህንንም ክፍተት ለመሙላት መንግሥት እና የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ርብርብ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል:: አሁንም ሕዝቡን ከረሀብ ማውጣት ባይቻልም ችግሩን ማስታገስ መቻሉን ግን በስልክ በተለይ ለበኲር ተናግረዋል::
የርዳታ አቅርቦቱ በአሁኑ ወቅት እየቀነሰ መምጣቱን አቶ ሷሊህ እንደ ስጋት አንስተዋል:: የዓለም ምግብ ፕሮግራም ችግሩ መኖሩ ይፋ በተደረገበት ወቅት በወረዳው 179 ሺህ ወገኖች የምግብ ክፍተት እንዳለባቸው ማሳወቁን፣ ካለበት የሀብት ውስንነት አኳያም ከዚህ ውስጥ መደገፍ የሚችለው 103 ሺህ 52 ብቻ መሆኑን ማስታወቁን ተናግረዋል:: ለአንድ ዙር ርዳታ ካቀረበ በኋላ አሁንም የሀብት እጥረት እንዳጋጠመው በመግለጽ የተረጅዎችን ቁጥር ወደ 81 ሺህ ማውረዱን ጠቁመዋል::
“ርዳታ ሰውን ከማቆየት ባለፈ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን አይችልም” ያሉት አቶ ሷሊህ፣ በመኸር እርሻው ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል:: በመሆኑም በድርቅ የተጎዱ ወገኖች የግብርና ግብዓትን ገዝተው ለመጠቀም ፈተና እንዳይሆንባቸው የሚያደርጉ አሠራሮች ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል:: የጃናሞራ ወረዳ እስካሁን ከ3 ሺህ 500 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በማሰራጨት ላይ መሆኑን እና በቀጣይ ግዥ መፈጸም ለማይችሉ ወገኖች የማዳበሪያ አቅርቦትን በብድር እስከማመቻቸት እንደሚደርስ ጠቁመዋል::
በዝናብ እጥረት በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከፍተኛ የዕለት ደራሽ ምግብ የሚፈልጉ ዜጎች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች መካከል ሌላኛው የደቡብ ጎንደር ዞን ነው:: የዞኑ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በላይ አስራደ በስልክ እንዳስታወቁት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የሚገኙትን ጨምሮ በዞኑ 238 ሺህ ዜጎች የምግብ ርዳታ ይፈልጋሉ:: ለእነዚህ ወገኖች የዕለት ደራሽ ምግብ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ቢሆንም የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ግን ተደራሽነቱ በሚፈለገው ልክ እንዳይሆን ማድረጉን ጠቁመዋል:: በአሁኑ ወቅት ከኮማንድ ፖስቱ ጋር በመተባበር ችግር ወዳለባቸው አካባቢዎች ርዳታ የማድረስ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ርዳታውም ድጋፍ የሚሹ ወገኖች አምርተው ራሳቸውን እስከሚችሉ መቀጠል እንዳለበት ቢታመንም እያጋጠመ ያለው የሀብት እጥረት ግን በሚፈለገው ልክ እንዳይደገፉ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል። በአሁኑ ወቅት ታች ጋይንት፣ ሰዴ ሙጃ፣ እብናት እና መቀጣዋ በሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የረሀብ እና የሞት ምልክቶች እየታዩ መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ባለሀብቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ፣ መገናኛ ብዙኃንም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው በመሥራት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለመኸር እርሻ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ የተለያዩ አጋር አካላት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ፕሮጀክቶች በስፋት እንዲሳተፉ እየሠራ እንደሚገኝ እና ሁሉም ቀናኢ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ዐቢይ ኮሚቴ እስካሁን በተሠሩ ሥራዎች እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል:: የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ርዳታ የሚፈልጉ ወገኖች ይገኛሉ:: በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ርብርብ ምላሽ እየተሰጠ ያለው ግን በድርቅ ለተጎዱ እና በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች ነው::
የክልሉ መንግሥት የተከሰተውን ድርቅ እና ያስከተለውን ችግር መነሻ በማድረግ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል:: ችግሩ የምግብ አቅርቦትን በማሟላት ላይ ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ እና የእንስሳት መኖ፣ ውኃ፣ መድኃኒት እና ሌሎች ድጋፎች እንደሚያስፈልጉም ተናግረዋል::
እንደ ኮሚሽነሩ እስካሁን የተከናወነው ሥራ አበረታች እና ችግሩን መቀነስ የቻለ ነው:: የክልሉ መንግሥት ችግሩን ታሳቢ በማድረግ በጀት መድቦ ለወገኖች ድጋፍ የሚሆን ግዥ መፈፀሙን ተናግረዋል:: ከተመደበው 410 ሚሊዮን ብር በ300 ሚሊዮን ብር ግዥ መፈጸሙንም አስታውቀዋል:: አሁንም ተጨማሪ መጠባበቂያ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል::
ይሁን እንጂ ከችግሩ ስፋት አኳያ በክልሉ ያለው የተረጂ ቁጥር እና የፌዴራል አደጋ ስጋት የሰጠው ምላሽ የመጣጣም ጉድለት እንዳለበት ኮሚሽነሩ ገልጸዋል:: ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ አምርተው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል:: በመሆኑም አሁንም ድጋፍ የማድረስ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል::
በክልሉ የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል እና ለመቀነስ የተሠሩ ሥራዎች ድርቁ ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት በእጅጉ የቀነሰ እንደነበር የገለጹት ደግሞ በውይይቱ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ናቸው:: ለችግሩ እተሰጠ ያለው ምላሽ አሁንም መቀጠሉን የተናገሩት አቶ አብዱ፣ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚፈልግ ግን ጠቁመዋል:: በመሆኑም በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ በማቅረብ ከችግር የሚወጡበትን መንገድ ማመቻቸት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራት እንዳለበት ገልጸዋል:: ለአቅርቦት እንቅፋት የሆነውን የሰላም እና የጸጥታ ችግር መፍታት ከሁሉም እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም