“አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” ይሉት በሳል ሃገርኛ አባባል አለን። እንደነገሩ የተከናወነ ተግባር፣ መሰረት የሌለው፣ ከተወሰነ ቆይታ በኋላ የሚፈርስ፣ የፀና ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት፣ እንደነገሩ ለጊዚያዊ መፍትሄ ተብሎ የተከወነ፣ በጥድፊያ የተፈፀመ … ሌላም ሌላም በማለት የአባባሉን እምቅ ገላጭነት መዘርዘር ይቻላል። ምክንያቱም በእውነት ላይ ያልተመረተ ድርጊት ሁሉ ዘላቂነት ሊኖረው እንደማይችል አያጠራጥርም። ትክክለኛ መግባባት ላይ የሚያደርስ ንግግር እና ውይይትም የተረጋገጠን ሰላም እና ፍትህ በግል፣ በማህበረሰብም ሆነ በሃገር ደረጃ ያጎናጽፋል።
የሰው ልጅ በምድር እስካለ ድረስ ከራሱ እና ከሌሎች ጋር መግባባት ይኖርበታል። አንድ ግለሰብ አልናገርም፤አልግባባም መልስ አልሰጥም ማለት እንደማይችል የሥነ-ልቦና ጠበብት ይናገራሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያስቀምጡት ዝምታ ራሱ መልዕክት አለው የሚል ነው። መግባባት አንድ ሰው ከራሱ ጋር በውስጡ የሚያደርገውን የሃሳብ ውጣ ውረድ፣ በሁለት እና ከዚያ በላይ ሰዎች፣ በአንድ ቡድን ውስጥ በሚገኙ አካላት እንዲሁም በሁለት ቡድኖች መካከል የሚደረግን የሃሳብ ልውውጥ ያጠቃልላል።
መግባባት በሰዎች ላይ መከሰት የሚችልን ጭንቀት እንዲሁም በግል እና በቡድን ደረጃ የሚደርስን ግጭት ያስቀራል፤ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያስችላል። በሚፈጠር መልካም መስተጋብርም አንዱ ከሌላው ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ በሠላም እንዲኖር ያስችለዋል።
መግባባትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመፈጸም ደግሞ ከስሜታዊነት የጸዳ ሰብዕና ይሻል። የጀምስ አለን “አዝ ዘ ማን ቲንከዝ” መፅሐፍ እንደሚያስገነዝበው “ተጎድቻለሁ”፤ “ተታልያለሁ” እና “ተበድያለሁ” የሚሉ ሃሳቦች በአንድ ሰው አእምሮ ላይ መነሳት ከጀመሩ ሰውየው እስካሁን ድረስ እውነትን አላወቀም ማለት ነው።
የሌሎች ሰዎች ድርጊቶች፣ ውጫዊ ነገሮች፣ አካባቢዎች እና ሁኔታዎች በራሳቸው ጥሩም መጥፎም አይደሉም፤ ነገር ግን ጥሩም መጥፎም የሚያደርጋቸው የአእምሮ አመለካከት እና የልብ ሁኔታ ነው። በጣም የሚያስቸግረው በእውነተኛ ፍላጎት ትክክለኛውን የአእምሮ ሁኔታ መፈለግ ነው። ሰው የሚገኝባቸው ሁኔታዎች ያሉትን እምቅ ኃይሎች የሚያበረታቱ አድርጎ ሲቆጥር ወደ መመግባባት የሚያደርሰውን ስኬት ማግኘት ይጀምራል። አእምሮው ሙሉ እና በትክክል የተቃኘ ከሆነ በሚገኝበት ሁኔታ ለሚያጋጥሙት ችግሮች ስሜታዊ ሳይሆን እና ቅሬታ ሳይሰማው ተነሳስቶ ያሳድጋቸዋል።
አንድ ሰው ሃሳቦቹን በተመለከተ የሚከተለውን ጥያቄ መጠየቅ ይገባዋል፤ “ሃሳቦቼ ወደ እስር ነው ወይስ ወደ ነፃነት የሚመሩኝ?” እንዲሁም የሚያስሩትን ሃሳቦች መተው እና ነፃ የሚያወጡትን የመግባቢያ ሃሳቦች ማሳደግ እንደሚገባው ጀምስ አለን ይገልፃል።
በሰው ልጅ ህይወት ጥልቅ ስሜታዊነት የመጨረሻው ዝቅተኛ ደረጃ ነው። በንግግር እና ውይይት የሚደረስበት መግባባት ላይም ከማያደርሱ ሳንካዎች መካከልም ይጠቀሳል። ከፍተኛ ጉጉት፣ አጥቁሮ ማየት፣ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ግብዝነት፣ ኩራት፣ ስግብግብነት፣ በቀል፣ ቅናት፣ ሃሜት ውሸት፣ ስርቆት፣ ማታለል፣ ማጭበርበር፣ ጭካኔ እና ምቀኝነት የመሳሰሉት በታችኛው የጥልቅ ስሜታዊነት የታወሩ ጨካኝ ሃይሎች ናቸው። በመሆኑም ብልህ ያልሆኑ ሰዎች የንፅህና ሰላምን ሳያውቁ አንዲኖሩ ያደርጓቸዋል። ብልሆች ግን በመግባባት ከጥልቅ ስሜታዊነት ወጥተው ሰላም እና ደስታ የሰፈነበትን ህይወት ያጣጥማሉ።
አንድ ሰው ሰላምን ማግኘት የሚፈልግ ከሆነ ከጥልቅ ስሜታዊነት መውጣት ግዴታው ነው። ብልህ ሰው ጥልቅ ስሜታዊነትን ያሸንፋል፤ ጅል ሰው ደግሞ የጥልቅ ስሜታዊነት ተገዥ ነው። በመግባባት ሰላምን የሚሻ ሰው ለቂላቂል ነገሮች ፊቱን በማዞር እምቢ ማለት ይጀምራል። ሰላምን የሚያፈቅር ሰው ወደ ሰላም በሚያደርሰው ጎዳና ውስጥ በመግባት በእያንዳንዱ እርምጃው የጥልቅ ስሜታዊነት እና ተስፋ መቁረጥን የሚያስከትሉ ነገሮችን መገኛ በመተው ተግባብቶ ወደፊት ይጓዛል።
“ጅል ሰው ሌሎችን ይከሳል፤ ራሱን ደግሞ ትክክል እንደሆነ ይቆጥራል። ብልህ ሰው ግን ሌሎች ትክክል እንደሆኑና ራሱን ደግሞ እንደ አጥፊ ይቆጥራል። ከጥልቅ ስሜታዊነት ወደ ሰላም የሚያደርሰው ጎዳና በውጫዊው የሰዎች ዓለም ውስጥ ሳይሆን በሃሳቦች ውስጣዊ ዓለም ውስጥ ይገኛል። ይህ የሚገነባውም የሌሎችን ምግባር በመለወጥ ሳይሆን የራስን ምግባሮች ፍጹም በማድረግ ነዉ” ይላል ጀምስ አለን። ይህ የሚያስገነዝበው ደግሞ ወደ ትክክለኛ መግባባት ለመድረስ ከሚያስችሉት ዘዴዎች መካከል አንዱ የኔ ሃሰብ ብቻ ትክክለኛ ነው ከሚል ግትር አመለካከት መውጣት ተገቢ መሆኑን ነው።
አንድ ሰው አእምሮውን ከመጥፎነት ወደ ጥሩነት ሲለውጥ በስህተት እና በእውነት መካከል ያለውን ልዩነት የበለጠ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ይለያል። መለየት በመቻሉም በውጫዊ ነገሮች እና በሌሎች ሰዎች ድርጊቶች እንዲሁም አመለካከቶች መወዛወዝ፣ ብሎም መገፋፋቱን ያቆማል። ይልቁንም እውነትን በተመለከተ ያለውን እውቀት መሠረት በማድረግ ይሰራል። መጀመሪያ ስህተቶቹን ያውቃል፤ ከዚያም በሚፈልግ አእምሮ እና በትሁት ልብ በመጋፈጥ በመግዛት እና በማሸነፍ ይለውጣቸዋል።
ዴል ካርንጌ የተባለው የዘርፉ ጸሐፊም ከሚታወቅባቸው ሥራዎች መካከል “ሃው ቱ ዊን ፍሬንድስ ኤንድ ኢንፍሉዌንስ ፒፕል” የሚለው ይገኝበታል። እርሱም በበኩሉ እንደሚለው በመልካም የተግባቦት ስልት ላይ የተመሠረተ ንግግር እና ውይይት ወደ ውጤታማ መግባባት ያደርሳል። በመሆኑም “እርስዎ ስለራስዎ ያለዎት አረዳድ ሰዎች እርስዎን ከሚረዱበት መንገድ የተለየ ከሆነ የእርስዎን ምስል ለሌሎች ለማሳመን በተለይም ደግሞ የሌሎቹን አረዳድ የማያውቁ ከሆነ በጣም ያስቸግርዎታል። ይሄ በብዙ ሰዎች ላይ የሚከሰት ነው” ይላል ዴል ካርኔጊ። ስለዚህ ራስን ዝቅ አድርጎ በመቅረብ የሌሎች ሃሳብ በአግባቡ በመከታተል እና ተገቢ ምላሽ መስጠት መግባባት ለመድረስ ሁነኛ ዘዴ ነው። በተቃራኒው ደግሞ ልክ ሁሉንም አዋቂ እንደሆኑ፣ የገንዘብ እጥረት የሌለብዎ ሃብታም፣ ተናግረው የማይረቱ በጠቅላላው አራጊ ፈጣሪ ሆነው በመቅረብ የሚያደርጉት ንግግር እና ውይይት ውጤት ላይ ለመድረስ አያስችልዎትም። ይልቁን ለውይይት የቀረቡበት ሂደት ያለ ስምምነት እንዲጠናቀቅ ያደርጋል።
ስኬታማ መግባባት ላይ ለመድረስ መታመን በእጅጉ ጠቃሚ ነው። በስሜታዊነት ተሸብቦ ማናቸውንም የማታለያ ተግባር መፈጸም ተገቢነት የለውም። ነገር ግን በታማኝነት ለእውነት መቆም የሚካሄድን ንግግር እና ውይይት በማይናወጥ መሰረት ላይ እንዲፈጸም ያስችለዋል።
እውነት ላይ የተመሰረተ መግባባትን ለማሳካት ከሁሉም የተግባቦት ክህሎት መካከል በብቃት ማድመጥ የግንባር ቀደምነቱን ደረጃ ይዟል። በዴል ካርኔጊ ሲገለጽ “አንዳንድ ጊዜ ጥሩ ማድመጥ ማለት የድምጽን ያህል ዝምታም ነው። ይኼም ሲባል ጥሩ አድማጭ የምንለው ሰው ሌሎችን በዝምታ እና በትዕግስት አንደሚያደምጠው ሁሉ እሱንም በትዕግስት እንዲያደምጡት ያመቻቻል። ማድመጥ የተለያዩ የሰውነት ቋንቋዎችን የሚያካትት ሲሆን ባህላዊ አገላለጾች፣ እሳቤዎች እና ሁለቱ ሃሳብ የሚለዋወጡ ሰዎች አጸፋ የሚሰጡበትን መንገድም ይወስናል። የማድመጥ ልምድ ከሰው ሰው እንደሚለያይ ግልጽ ነው። ሆኖም ግን ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ በአግባቡ ማድመጥ መግባባትን ስኬታማ ያደርገዋል።”
“ብዙዎቻችን ውይይትን መሸናነፍ እንዳለበት ጨዋታ አድርገን እንመለከተዋለን። እኛ ትክክል እንደሆንን እና ሌላው ሰው እንደተሳሳተ አድርገን እንቆጥራለን። አንደኛችን ዘንድ እውነት እንደተትረፈረፈ እና በሌላኛችን የሚነገረው ነገር ደግሞ በጨለማ የተዋጠ እንደሆነ ይሰማናል። ነገር ግን የተሻለ ልንማር እና በፍጥነት ወዳሰብንበት መጓዝ የምንችለው አንድ የስምምነት ምዕራፍ በማዘጋጀት ነው” ሲልም የ”አንሊሚትድ ፓወር” መፅሐፍ አዘጋጅ አንቶኒ ሮቢንስ የስገነዝባል።
ባጠቃላይ ከውዝግብ ወጥቶ ሰላምን ማጣጣም የሚቻለው መግባባት ላይ መድረስ ከተቻለ ብቻ ነው። የኔ ሃሳብ ብቻ ነው ትክክል ማለት ግን ሰላምን ሊያስገኝ አይችልምና የመግባቢያ ቅን ልቦናን ፈጣሪ ይስጠን በማለት ፅሑፌን ቋጨሁ፤ ቸር ይግጠመን።
(ጥላሁን ወንዴ)
በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም