ስለመጥሪያ ምን ያህል ግንዛቤ አለዎት? ከፍርድ ቤት አሠራር ጋር ተያይዞ በፍርድ ቤቱ በኩል የሚዘጋጅ ሕጋዊ ሰነድ እንደሆነ በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ አቶ ቢራራ ወርቁ አብራርተዋል:: መጥሪያ አንድ ሰው በሕግ ተቋማት ቀርቦ የሚፈለገውን መረጃ እንዲያስረዳ በውቀት የሚሰጥ ሰነድ ነው:: ተከሳሽ ከሆነ ደግሞ ፍርድ ቤት ላይ መጥሪያ ሲሠጠው በምን ጉዳይ እንደተከሰሰ ጉዳዩን እንዲያውቅ ፣ መቼና የት? እንደሚቀርብ፣ ተከሳሽ ለቀረበበት ክስ የመከላከያ ማስረጃዉን በፅሁፍ እንዲያቀርብ የሚያዝ ፤ መልሱን ባያቀርብም ጉዳዩ መሰማት እንደሚቀጥል የሚገልፅ እንደሆነ እና ተገቢውን ክርክር እንዲያደርግ የሚገልፅ ሰነድ መሆኑን አብራርተዋል::
ባለሙያው አቶ ቢራራ እንደሚሉት በአጠቃላይ መጥሪያ ለማንኛውም ሰው ሊሰጥ የሚችል እንዲሁም የሚፈለግ አካል ጥሪውን አይቶ እንዲቀርብ የሚሠጥ ትዕዛዝም ነው:: መጥሪያ በምስክርነት የሚጠሩ ሰዎች ቀርበው ሀሳባቸውን እንዲያስረዱ ሊሰጣቸው ይችላል:: ፍርድ ቤት ለተከሳሽ መጥሪያ ሲሰጥ የትኛው ፍርድ ቤት የትኛው ቦታ እንደሚቀርብ ትዕዛዙ ላይ በግልፅ ከመቀመጥ ባሻገር ለክሱ መልስ ይዞ መቅረብ እንዳለበት፣ መልሱን ይዞ መቅረብ ካልቻለ ፣እሱም በአካል መቅረብ ካልቻለ እንኳን በሌለበት ክሱ እንደታይ በግልፅ ጽሑፉ ላይ ተገልፆ የሚቀርብ ትዕዛዝ ነው:: በዚህም መሠረት መጥሪያ ሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች እኩል ቀርበው የመከራከር መብት እንዲኖራቸው በማድረግ ጉዳዩ ፍትሐዊ በሆነ አኳኋን እንዲወሰን ለማድረግ የሚቻልበት አንዱ መንገድ ነው::
እንደ ባለሙያው ገለጻ መጥሪያ ለተከሳሽ የሚላክበት ዋና ዓላማ ተከሳሽ መከሰሱን አውቆ ለቀረበበት ክስ የበኩሉን መከላከያ ለማቅረብ እንዲችል ዕድል ለመስጠት ነው:: በዚህም ተከሳሽ የተከሰሰበትን ጉዳይ እንዲያውቅ እና በአግባቡ እንዲከላከል እንዲሁም ሲመሰከርበት ለምስክሮች መስቀለኛ ጥያቄ በማቅረብ እና የራሱንም ምስክሮች የማሰማት መብት አለው:: ስለዚህ ተከሳሽ ወደ ፍርድ ቤት ቀርቦ ራሱን ለመከላከል እንዲችል የቀረበበትን ክስና ይህንን ክስ ለመከላከል የት? እና መቼ? መቅረብ እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል:: ባጠቃላይ የከሳሽ እና ተከሳሽ ዳኝነት የሚሰጠው የአንድን ወገን አቤቱታ በመስማት ብቻ አይደለም::
መጥሪያ እንዴት ይደርሳል?
ባለሙያው አቶ ቢራራ እንደሚሉት መጥሪያ ከፍርድ ቤት ወጭ ከተደረገ በኋላ በቀጥታ ለተከሳሹ መድረስ አለበት ሲል የፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ አስገዳጅ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ አድርጎ አስቀምጦታል:: ተከሳሹ ለራሱ፣ ካልተገኘ ደግሞ ጠበቃ ካለ ለጠበቃው ወይም ተከሳሽ ለወከለው አካል መጥሪያው መሰጠት መቻል አለበት:: እነዚህን ሰዎች ማግኘት ካልተቻለ ግን እንደተከሳሹ ባህሪ ለተከሳሹ ቅርብ ሰዎች በሚገኙበት ማህበር፣ ዕድር…. የመሳሰሉ ማህበራዊ መሰብሰቢያ ቦታ ፈልጎ መስጠት:: በዚህ መንገድ የሚፈለጉ ሰዎችን ማግኘት ካልቻለ ምትክ የመጥሪያ ማቅረቢያ ዘዴዎች እንዲሰጡት አቤቱታውን ለፍርድ ቤቱ ድጋሚ በመሀላ ያቀርባል::
ባለሙያው እንደሚያብራሩት “በየትኛው ዘዴ ብሰጥ ሊደርስ ይችላል?” ብሎ አስቦ 18 ዓመት የሞላው ልጅ ካለ ለልጅ፣ ለሌላ የቤተሰብ አባላት ወይም መጥሪያውን ጥሪ የተደረገለት ግለሰብ በሚኖርበት ቀበሌ ሊለጠፍ ይችላል:: ድርጅት ከሆነ ደግሞ ድርጅቱ በር ላይ መጥሪያው ሊለጠፍ ይችላል:: መጥሪያው በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት እንዲለጠፍ ትእዛዝ ከተሰጠ 10 ቀን መለጠፉ መረጋገጥ የግድ ነው:: የመጨረሻው አማራጭ ክልላዊም ይሁን ሀገራዊ ጋዜጣ ላይ ጥሪ እንዲተላለፍ ማድረግ ይችላል:: እነዚህን የምትክ መጥሪያ ዘዴዎች እንዲጠቀም የሚያደርገው /የሚመርጠው/ ፍርድ ቤት ነው::
ተከሳሹ በአማራጩ ካልቀረበ ግን በሌለበት ታይቶ ፍርድ ይሠጣል:: በመጥሪያ አደራረስ ሂደት ላይ ተከሳሽ ታሞ አልጋ ላይ ሆኖ፣ ፀበል ሂዶ ፣ ስደት ላይ በመሆኑ ጥሪውን ለማግኘት እድል እንደሌለው ከሳሽ እያወቀ ደብቆ ካስወሰነ ፍርድ ቤቱ ሁኔታውን አረጋግጦ ፍርዱ እንደገና ሊሰማ ይችላል::
መጥሪያ የተላከለት ሰው የመቀበል ግዴታ አለበት:: “አልቀበልም!” በማለት ከሳሽን መግጠም የለበትም:: መጥሪያ የሚሰጥ ሰው ሁለት እማኝ ይዞ በቃለ መሀላ አረጋግጦ ለፍርድ ቤቱ ማቅረብ ነው:: ይህ ሲሆን ጉዳዩ በሌለበት እንዲታይ ይደረጋል:: በአፈፃፀም ሂደት ሊታሰርም ይችላል::
ከሳሾች ግን በግዳጅ “ውሰድ? ተቀበል?” በማለት ጠብ ውስጥ መግባት የለባቸውም:: መሠረታዊ የምስክሮች ቃል ግን አስፈላጊ በሆነበት ሁኔታ ምስክር የተባለ አካል ፍላጎት ከሌለው የሕግ አካል ይህንን አረጋግጦ እና አስሮ እስከማቅረብ ያለውን አማራጭ ሊያቀርብ እንደሚችል ባለሙያው አብራርተዋል::
የዐቃቢ ሕግ ባለሙያው አቶ ቢራራ እንደሚሉት ፍርድ ቤት በአፋጣኝ ፍርድ እንዲሰጥ በማሰብ ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቦ ምስክር አልመጣም ካለ “በተደጋጋሚ ምስክር ለማቅረብ የተሠጠህን ጊዜ አልተጠቀምህም” በሚል ምስክር ሳያሰማ መወሰን መቻል በአንዳንድ ፍርድ ቤቶች ቢደረግም ይህ ሁኔታ ሕገ መንግሥታዊ ምስክር የማሰማትን መብት የሚጥስ እንደሆነ ነው:: ተከሳሽ ላይ ብቻ ሳይሆን ከሳሽ መጥሪያውን ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለበት:: በከሳሽ ቸልተኝነት እና በተከሳሽ ንዝህላልነት ያለ በቂ ምክንያት ከሆነ የቀረበውን ክስ ፍርድ ቤት ሊዘጋው የሚችልበት ዕድልም ይኖረዋል:: ስለዚህ መጥሪያ ማድረስን በትክክለኛው መንገድ መፈፀም መቻል አለበት::
ቀላል የሆኑ ወንጀሎች መጥሪያ የደረሰው ግለሰብ ካልተገኘ የሚሰጠው ፍርድ እስርም ሊሆን ይችላል:: ከፍተኛ ውሳኔ የሚያስወስኑት ከ12 ዓመት በላይ እስር እና ሞት ከሆኑ ደግሞ በጋዜጣ ተጠርቶ ካልመጣ ጉዳዩ በሌለበት ተወስኖ በተገኘበት ጊዜ ፍርዱ ተፈጻሚ እንደ ሚሆን ባለሙያው አብራርተዋል::
የሕግ አንቀጽ
መጥሪያ ስለማድረስ በፍሐብሔር ሕጉ የተቀመጠው
- መጥሪያ ላይ ጉዳዩ ተዘርዝሮ መቅረብ እንዳለበት በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 233 ተቀምጧል፡፡
- በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 95 ንኡስ አንቀፅ (1) መሰረት መጥሪያ ፍርድ ቤቱ ባዘዘው ሰው ወይም በማንኛውም ሰው በኩል ይላካል፡፡
- በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 102 እንደተደነገገው መጥሪያ ሰጪው ለተከሳሽ፣ ለጠበቃው፣ ለወኪሉ ወይም መጥሪያውን ለመቀበል አግባብ ለሆነ ሰው በሚሰጥበት ወቅት ተቀባዩ የደረሰው ስለመሆኑ መፈረም አለበት፡፡
- መጥሪያ የተቀበለበትን ቀን በመጻፍ እንዲሁም ተቀባዩ ሲቀበል የነበሩ ምስክሮች ስም በዝርዝር ተጽፎ ማስፈረም አለበት፡፡ ይህንን ተቀባዩ መጥሪያውን ስለመቀበሉ የፈረመበት እና ራሱ ያረጋገጠበትን ለፍርድ ቤቱ እንደሚመለስ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 104 ይደነግጋል ፡፡
- መጥሪያው ለተከሳሽ በቀጥታ ለራሱ መስጠት፤ ይህ ካልተቻለ ደግሞ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ከቁጥር 96 እስከ 110 ላይ የተመለከቱትን የመጥሪያ አሰጣጥ ዘዴዎች በመጠቀም መጥሪያው ለተከሳሽ ማድረስ አለበት፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የጳጉሜን 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም