ሁላችንም ቀኑም ሆነ ሌሊቱ እንዲረዝምልን ወይም እንዲያጥርልን የተመኘንባቸው በርካታ ገጠመኞች ይኖሩናል። በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ይህ ምኞት እውን ሆኖ እናገኘዋለን። በእነዚህ ቦታዎች፣ ቀን ለጨለማ የሚያደርገው ተፈጥሯዊ ሽግግር የተራዘመበት ቀን በመፍጠር ፀሐይ የማትጠልቅበት እንዲሁም የረዘመ ሌሊት በመፍጠር ልዩ ክስተት የሚስተናገድባቸው ናቸው። መቼ መተኛት እና መነሳት እንዳለብን ግልፅ የሆነ አመላካች ነገር ባለመኖሩ በሰዓት ላይ ያለው ግንዛቤ እስከ መጥፋት ሊደርስ ይችላል፤ በእነዚህ አካባቢዎች። ይህ ስለ ቀን እና ሌሊት ያለንን የተለመደ ግንዛቤ የሚፈትን ክስተት ወደ ሚስተዋልባቸው አካባቢዎች እንውሰዳችሁ፡፡
በሰሜን የአርክቲክ የሀሳብ መስመር በኩል የፀሐይ ብርሃን እስከ ስድስት ወራት ያለማቋረጥ ይታያል። በተቃራኒው ደግሞ ግማሹ ዓመት ፀሐይ ፈፅሞ የማትታይበት ጨለማ ነው።
በርግጥ ይህ ክስተት በአርክቲክ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በደቡቡ የምድራችን ክፍል በአንታርክቲካም የሚስተዋል ሀቅ መሆኑን ልብ ይሏል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች በጊዜ ብዛት ረዥሙን የቀን ብርሃን ወይም ጨለማ ተላምደውታል። ለአዲስ መጤዎች ወይም ለጎብኝዎች ግን ለመላመድ የሚፈተኑበት እና ለመኝታ ችግር የሚዳረጉበት ነው። ለማንኛውም እነዚህን ስፍራዎች አብረን እንጎብኛቸው።
እያወራን ያለው በዓለማችን ፀሐይ ለወራት በፍፁም ስለማትጠልቅባቸው አካባቢዎች ነው። በእነዚህ ስፍራዎች ቀኑ መጨረሻ የለውም፤ እናም አስቡት መቼ እንደምትተኙ፣ መቼ እንደምትነሱ… የማታውቁባቸው እንግዳ ስፍራዎች። ለነገሩ እንግዳነቱ ለእኛ እንጂ ተወልደው ላደጉበቱማ የእለት ተእለት ሕይወታቸው ነው። ታዲያ የት ነው ይህ አስገራሚ የተፈጥሮ ክስተት ያለው ካላችሁ በቅድሚያ ወደ ስካንዲኔቪያኗ ሀገር ወደ ኖርዌይ ልውሰዳችሁ።
ኖርዌይ “የእኩለ ሌሊት ፀሐይ ምድር” እየተባለች ትታወቃለች። በከፍታ የምትገኘ በመሆኗ ወቅትን በተከተለ መልኩ የቀኑ ብርሃን ርዝማኔ ይለዋወጣል። በዚህ ሀገር ውስጥ ከግንቦት መጨረሻ እስከ ሐምሌ መጨረሻ ባሉት 76 ቀናት ውስጥ ፀሐይ ከ20 ሰዓታት በፊት አትጠልቅም።
ፀሐይ ከሚያዚያ 20 ቀን ከጧቱ 1:52 እስከ ነሐሴ 22 ቀን ከጧቱ 12:49 ድረስ ፀሐይ አትጠልቅም። ማለትም ሚያዚያ 20 ቀን ከጧቱ ሁለት ሰዓት ሊሆን አስር ደቂቃ ሲቀር የወጣችው ፀሐይ የምትጠልቀው በነሐሴ 22 ከጧቱ 12:49 ሰዓት አካባቢ ከወራት በኋላ ነው። ይህ አካባቢ በዓለም ሰሜናዊው ጫፍ ላይ የምትገኘው የኖሮዌያውያኑ የደሴት ከተማ፣ ስቫልባርድ ከአርክቲክ መስመር በላይ ራቅ ብላ ያለች ከተማ ናት። በሰሜናዊ ኖርዌይ ውስጥ ምናልባትም ጎረቤትዎ ሌሊት ላይ ቡና ሊጋብዝዎ ቢችል እንግዳ ነገር አይደለም። ግብዣውን ተቀብለው የሚሄዱ ከሆነ ታዲያ ከፍተኛ አቅም ያለው ጠብመንጃዎን ይዘው መሆን አለበት። ይህ በስቫልባርድ ከተማ ህገ የተፈቀደ ነው። ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ፣ አደገኛው ድብ የተባለው አውሬ በመንገድ ሊያጋጥምዎ ይችላል።
የሺህ ሐይቆች እና ደሴቶች ምድር እየተባለች በምትታወቀው ፊንላንድ አብዛኛው ክፍል ፀሐይ በበጋ ወራት ለተከታታይ 73 ሰዓታት ታበራለች። በክረምት ወቅት ግን ሀገሪቱ ምንም የፀሐይ ብርሃን አታይም። በዚህ ስፍራ ሰዎች በበጋ ወራት የሚተኙት ጥቂት ብቻ የሆነበት፣ በክረምት ግን ረጅም ሰዓታት የሚተኙበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። በአርክቲክ መስመር በላይ በሚገኙ ሀገራት ለአፍታ ያህል ፀሐይ ከአድማሷ ገብታ ወዲያው ትወጣለች። ይህ ልዩ ተፈጥሯዊ ክስተት ማራኪ ሰሜናዊ ብርሃናት አይነት ልብን የሚያጠፉ ድንቅ እይታዎችን የመስጠት ድንቅ አጋጣሚን ከመስጠት ባለፈ እንደ የበረዶ ሸርተቴ እና ሌሎች ስፖርታዊ ልዩ ልምምዶች እንድናደርግ እድል ይሰጠናል።
አሁን ደግሞ ከስካንዲኔቪያን ሀገሮች አንዷ ወደ ሆነችው ስዊድን እናቅና። ከግንቦት ወር መጀመሪያ እስከ ነሐሴ ወር መጨረሻ አካባቢ ፀሐይ በእኩለ ሌሊት አካባቢ ትጠልቅ እና እንደገና ከጧቱ አራት ሰዓት አካባቢ ትወጣለች። በዚህ ሀገር ውስጥ ቋሚ የፀሐይ ብርሃን ለስድስት ወራት ይዘልቃል። ነገር ግን ዓመቱ እየገፋ ሲሄድ በአስደናቂ ሁኔታ ነገሮቹ ይገለበጣሉ። የክረምት ወራት ፀሐይ ለ6 ሰዓታት ብቻ የቀን ብርሃን ለግሳ ስታፈገፍግ የምትታይበት ወቅት ይሆናል። ቀሪው ቀን ቀለማማ በሆነ ጨለማ ይዋጣል፡፡ ይህም በበረዶ ለተሸፈነው መልክዓ ምድር የተለየ ሞገስ ይደርብለታል። ምንም እንኳን የፀሐይ ብርሀን ቢገደብም ስዊድናውያን ይህን የክረምት ጨለማ ወራት ቤታቸውን እና ጎዳናዎችን በደማቅ መብራት አፍክተው በደስታ እና በክብር ይቀበሉታል።
በአላስካ ፀሐይ ከግንቦት መጨረሻ እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ አትጠልቅም። በሚከብደው የክረምት ወራት ጨለማ ሀገሪቱ እጅግ ውብ ትሆናለች። በአስደናቂው የበረዶ ካፊያ እና በረዶ በተሸፈኑ ተራሮቿ ትታወቃለች።
ፀሐይ መጥለቅ የሚባል ነገርን ወደረሳችበት አይስላንድ እንጓዝ። ከታላቋ ብሪታኒያ ቀጥሎ በአውሮፓ በሁለተኛው ትልቁ ደሴት አይስላንድ ውስጥ ፀሐይ በፍፁም አትጠልቅም፤ ሌሊቱን ሙሉ በአድማሷ አግድም ትጓዛለች። ደሴቱ ምንም ጨለማ አያይም፡፡ ምክንያቱም ከግንቦት ወር መጀመሪያ እስከ ሐምሌ ድረስ ፀሐይ ሁሉንም ጊዜ ከአድማሷ በላይ ስለሆነች። ልብን ከሚያጠፉ ሰሜናዊ ቀለማማ ብርሀናት በተጨማሪ ሀገሪቱ እንደ የእግር ጉዞ፣ የዱር እንስሳትን የመመልከት እና አሳ ነባሪ የመመልከት፣ የዋሻ ጉብኝት፣ ሳይክል የመጋለብ እና ብሔራዊ ፓርኮችን የመጎብኘት የመሳሰሉ አስደሳች ተግባራትን ይፈጽማሉ።
የወባ ትንኝ የሌለባት ቦታ መሆኗ ሌላው መገለጫዋ በሆነው አይስላንድ በሰኔ ወር ፀሐይ ፈፅሞ አትጠልቅም። የእኩለ ሌሊት የፀሐይ ብርሃንን ከእነ ሙሉ ሞገሱ ለማየት የአኩሪ እና የግሪምሲ ደሴትን መጎብኘት ይችላሉ።
ወደ ካናዳ ደግሞ ልውሰዳችሁ። የዓለማችን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ካናዳ እንደ ኢኑቪክ እና ሰሜን ምዕራብ ክፍል ባሉ ከተሞች በበጋ ወቅት ለሃምሳ ተከታታይ ቀናት ያህል የፀሐይ ብርሃን ትታያለች፤ ይህም ካናዳን በዚህ ወቅት ምንም ጨለማ የሌለባት ሀገር ያደርጋታል። ሀገሪቱ ዓመቱን ሙሉ በበረዶ ትሸፈናለች። ኑናቬት ከአርክቲክ የሀሳብ መስመር ሁለት ድግሪ ላይ የምትገኝ፣ የሰሜን ምዕራብ ካናዳ አካል ናት። ይህች ስፍራ የሁለት ወራት የ24 ሰዓት የፀሐይ ብርሃን የሚታይባት ሲሆን፣ በክረምት ወቅት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በጨለማ የተዋጡ 30 ተከታታይ ቀናትን ታስተናግዳለች።
በአጠቃላይ ፀሐይ የማትጠልቅባቸው ወይም የማትወጣባቸው ሀገራት እና አካባቢዎች የተፈጥሮ ቅኝት በጣም ልዩ የሆነባቸው ማራኪ ቦታዎች ናቸው። እነዚህ ልዩ ክስተቶች፣ ለኗሪዎቹ እና ለጎብኝዎቹ በእኩለ ሌሊት ማለቂያ የለሽ ቀናት እስከ የመፀው ወራቱ የጨለማ ወራት የማይረሱ ልምዶችን ይሰጧቸዋል። በስድስት ወራት ጨለማ ውስጥ መኖር ከባድ ቢሆንም ከውጨ ያጡትን ብርሃን በቤት ውስጥ በመፍጠር ያካክሱታል። ሥራን ቤት ውስጥ ሆኖ በማከናወን ማህበራዊ ግንኙነታቸውን በማጠናከር አስቸጋሪውን ወቅት ለማለፍ ሲሞክሩ ይታያሉ።
ምንጭ- ዎነድሮፖሊሰስ ዶትኮም፣ ተራቭላክስ.ኮም፣ ዘ ዴይሊ ጋረዲያን
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም