ሙሉቀን መለሰ- የሙዚቃ መለኪያው

0
242

ቄሰ ገበዝ ታምር ጥሩነህ የሙሉቀን መለሰ አባት ናቸው:: አጎቱ አቶ መለሰ አሳደጉት እና በመለሰ ይጠራል:: አባት ልጃቸው የቤተክስርቲያን አገልጋይ እንዲሆን ብርቱ ፍላጎት ነበራቸው:: “አባቴ ምንጊዜም ቢሆን ቤተክስቲያን ይዞኝ በመሄድ ከበሮ አመታት፣ አቋቋም፣ ዝማሬ የቤተክህነት ስርዓትም ያስተምረኝ ነበር”በማለት ሙሉቀን ተናገሮ ያውቃል:: አባት የፈለጉት አልሆነም:: ልጃቸው በወቅቱ ደማቅ ከተማ፣ ደማቅ ሰፈር በነበረችው ውቤ በረሃ አደገ:: ሙሉቀን ሙዚቃን የተቀላቀለው በ13 ዓመቱ ነው::

“እምቧ ስል አድራለሁ ግድግዳ ስጭር

ለዓይነ ከብላላ ልጅ ለጠይም አጭር” ተወዳጅ ዘፈኑ ነው::

እናቱ በልጅነቱ በመሞታቸው ምክንያት ህይወቱ መከፋት እና መጎሳቆልን እንዲያልፍ አድርጎታል:: በፖሊስ ኦርኬስትራ ቆይታው ተስፋየ አበበ  “እናቴ ስትወልደኝ” የሚለውን ጽፈው የሰጡት የራሱን ታሪክ በማስተዋል  ይመስላል::

”እናቴ ስትወልደኝ መቼ አማከረቺኝ

የፊት ጉዴን ትታ እደግ ማሞ አለቺኝ

በምጥ መጠበቧ እምየ ስትወልደኝ

ማስተማሯ ኖሯል ኑሮ እንደሚጨንቀኝ”

“እሽሩሩ በሉት” በሚለው ሌላ ዘፈኑ ሙሉቀን የራሱን ታሪክ የዘፈነ ይመስላል::በልጅነት ዕድሜው አዲስ አበባ ውስጥ ለማደግ ብዙ አስቸጋሪ ዓመታትን አልፏል:: ዘፈኑ  የሙሉቀንን ታሪክ ለሚያውቅ አንዳች ትርፍ የሌለው የራሱ እውነት ነው። ሙሉቀን ታሪኩን ዘፍኖታል:: መሸሸጊያ አልባ ሆኖ በረንዳ ከውሻ ጋር አድሯል፣ እንባ ፊቱን አጥቁሮታል::

“ወላጆቹ ሞተው እንባ እያፈሰሰ

መፈጠሩን ጠልቶ  ጨቅላው አለቀሰ

የእናቱን ውለታ ልቡ እያስታወሰ

ረዳት ስላጣ ጨቅላው አለቀሰ

ዘመድ የለሹ ልጅ በሀዘን ተውጦ

ማነው እደግ ብሎ የሚሰጠው ጡጦ”

ሙሉቀን ሶስት ጊዜ ራሱን ለማጥፋት ሞክሮ ሰዎች ደርሰው አድነውታል:: ከችግሩ ለመላቀቅ ሎተሪ ቢቆርጥም አልሳካለት አለ:: ቀጥሎም ፈጣሪ የለም ወደሚል ድምዳሜ መድረሱን በህይወት እያለ ተናግሯል:: የአባቱን  ፍላጎት ተከትሎ ቄስ ባይሆንም እንኳን በዘፈኖቹ መንፈሳዊ ቃላትን በመጠቀም ለዘፈን ማሳመሪያነት ይጠቀምባቸው ነበር:: ደብር፣ ቄስ፣ ምንኩስና፣ ገዳም የመሳሰሉ ቃላትን በሙዚቃዎቹ እናገኛለን:: የአባቱ መንፈሳዊ ፍላጎት በዓለም እሳቤ በመጠለፉ “እመንናለሁ ስል ደብረ ሊባኖስ፣ መልሶ ሰደደኝ ፍቅርሽ እንደ ቄስ” በማለት ዘፍኗል::

ዓለም ፀሀይ ወዳጆ የሙሉቀን መለሰን እስከ 70 በመቶ የሚሆኑትን ዘፈኖች ግጥም ጽፋለታለች:: ከጋዜጠኛ  ቴዎድሮስ  ጸጋየ ጋር  በነበራት ቃለ ምልልስ “ሙሉቀን በጣም የማከብረው፤ በጣም የምወደው የኢትዮጵያን የዘፈን ደረጃ ካስቀየሩት ሰዎች እና ወጣቶች መካከል አንዱ ነው ብየ አምናለሁ። በወቅቱ የነበሩትን የግጥምን ደረጃ የመለወጥ፣  ዜማን መለወጥ ፣ የሙዚቃ አሬንጅመንትን /ቅንብርን/፣ ሁሉንም እድገቱን ከፍ ያደረገ ልጅ ነው ሙሉቀን:: ይሁን እና እሱ ራሱ የሚወዳቸው ነገሮች አሉት:: አንድ ዘፈን ለማውጣት 30 እና 40 ዘፈን ያዳምጣል:: አስር ዘፈን ለመስራት 100 አና 200 ዘፈን ያዳምጣል:: ገዳም ፣ መነኩሴ የሚሉ ሐሳቦችን ግጥሞቼ ውስጥ እየከተተ የእኔ ናቸው ለማለት እቸገር ነበር” ስትል ተናገራለች:: ለማሳያነት ዘፈኖቹን እንመልከታቸው እስኪ::

“እመነኩሳለሁ ግዙልኝ ቆቡን

እሷም አልተገኘች ያለ እሷም አይሆን”

ሲል “እምቧ ዘቢደር” በሚለው ዘፈኑ ውስጥ መንፈሳዊ ቃላትን እናገኛለን:: “ዓይኔማ ወዳጅሽ” በሚለው ዘፈኑ ውስጥም እንዲሁ “በአዛኝቱ ማርያም በወላላይቱ፤ የታመመ ሳይድን አይንጋ ሌሊቱ” ይላል:: “አልማዜዋ” በሚለው ዘፈኑ ውስጥ ደግሞ  “ታቦት እንዳጀበ ለማየት ዓይንሽን፤ እሽከረከራለሁ ደጃፍ ደጃፍሽን” ይላል፡፡ ይረገም በሚል ሙዚቃው ውስጥ እንዲሁ

“ስፍራሽ እንኳ ታውቆ እንደ ኢየሩሳሌም

አይከፋኝም ነበር መጥቼ ብሳለም፤

እንደ ቄሱ ጭራ እንደ እንዝርቷ ብናኝ

ይሄው መጣሁላት ደግማ ታንገላታኝ፤

ስትፈለግ ጠፍታ እሁድ ቀን በሰንበት

ባዘቦት ቀን መጣች ጻዲቅ በሌለበት”

ሰውነቷ በሚለው ዘፈኑ ውስጥም

“አንቺ ካለሽበት ከቆምሽበት ምድር

መነኩሴው ከገዳም ጎሽ ይወጣል ከዱር”

“እኔስ ተሳስቼ” በሚል ዘፈኑ ውስጥም

“እመነኩሳለሁ እገባለሁ ገዳም

ደግሞ እንደ ስጋየ በነፍሴ አልጎዳም”

“የኔ ዓለም” በሚል ሙዚቃውም

“ሳዱላ ተሰርተሽ አልቦሽን አርገሽ

ለሰው ሳትነግሪ ኩታ ደርበሽ

ዳገት ኮረብታውን ቤተስኪያኑን አልፈሽ

ነይ ነይ ጉብል ሸጋ ጫካ ደኑን ጥሰሽ”

እንዲሁ በሌላ ዘፈኑ

“ተስካሬም አይውጣ አይብላው ካህን

በመውደድ ሞቻለሁ እንዳልኮነን” ሲል እንሰማዋለን::

ማርያም፣ ኢየሩሳሌም፣ የቄስ ጭራ፣ ሰንበት፣ ቤተክርስቲያን፣ ታቦት፣ ጻድቅ፣ ገዳም፣ ምንኩስና፣ ሙሉቀን ግጥሞች ውስጥ መካተታቸው በልጅነቱ አባቱ ያስተማሩት እና አብሮት ያደገው መንፈሳዊነት ማሳያዎች ተደርገው ሊጠቀሱ ይችላሉ:: ዓለም ፀሐይ እንዳለችው ሙሉቀን እነዚህን ቃላት ፈልጓቸው የሚጠቀምባቸው በመሆኑ ለሙዚቃው ትልቅ አቅም ነበሩ:: የሙሉቀን መንፈሳዊነት ጥሪ በልጅነቱ ስድስት ዓመቱ ላይ እንደነበር ተናግሯል:: ለዚያም ይመስላል 17 ዓመታት ብቻ ቆይቶ ትቶት መንፈሳዊ ዝማሬ ውስጥ የገባው:: ዓለምን “አመለጥሁሽ” ብሎ ዘመረባት::

ሙሉቀን መለሰ ባህላዊውን የኢትየጵያ ሙዚቃ   በራሱ ቀለም ዘመናዊ አድርጎ  የተጫወተ ነው ይባልለታል:: የቀደምት ዘፋኞችን ስራዎችም እንደ አዲስ እንዲደመጡ  አድርጓል::  ሊቀመኳስ ምስጋናው አዱኛ “ናኑ ናኑ ነይ” የሚለውን ድሮ ጥንት ዘፍነውታል:: ሙሉቀን ደግሞ በዘመናዊ መልኩ ሲዘፍነው ግሩም ሆነ፣ ባሕሩ ቀኘ “ጤናየዋ ለኔ” ብለው ዘፍነዋል:: ሙሉቀን መለሰ ደግሞ “ገላየዋ ነይ ነይ” ብሎ አዚሞታል:: አካል ገላ የደርባባው አቡኑ ቀደምት ዘፈን ነበር:: ሙሉቀን መለሰ ዘፈኑን ወደ ዘመናዊ መድረክ እና አድማጭ አምጥቶ “አካል ገላ”  በማለት ተወዳጅ አድርጎታል:: አበበ ተሰማ “እምቧ ዘቢደር”ን በመዝፈን ቀድሞ ይታወቃል::  ሙሉቀን መለሰ ደግሞ ለዚህኛው ትውልድ እንዲሻገር አድርጎታል:: አልማዜዋ፣ ቼ በለው፣ እምቧ በለው የሚሉ  የሕዝብ ዜማዎችን ወስዶ ከፍ አድርጎ ዘፍኗቿል::

ሙሉቀን መለሰ ለራሱ ያለው ቦታ ታላቅ ነው። በራስ መተማመኑ ግሩም ነው:: “ከሻይ ቤት ሀርሞኒካ እስከ ዳህላክ ባንድ” በሚል ርእስ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር በ1973 ዓ.ም ፀደይ መጽሔት ላይ ሙሉቀን መለሰን በ28 ዓመቱ ቃለመጠይቅ አድርጎት ነበር:: ስብሐት የሙሉቀንን ባህሪ ሲገልጸው “ለሁለት ሰዓት ያህል ስንነጋገር እንደገመትኩት ሙሉቀን ሀሳቡን በቀጥታ የሚናገር ሰው ነው። ማለቴ፣ “እንዲህ ያልኩ እንደሆነ እንደዚህ ተብሎ ሊተረጐምብኝ ይችላል” የሚል ሥጋት የለበትም” በማለት ጽፏል::  የሙሉቀን ባሕሪ ከሙዚቃው ከወጣ በኋላም አብሮት ኖሯል::

ሙሉቀን ከስብሐት ጋር በነበረው ቆይታ ስለዘፈኖቹ ይናገራል “እኩል ነው የማያቸው። ግን … በጣም የሚያረኩኝ … በዜማውና በዘፈኑ … ‘ሰውነቷ’ እና ‘ሆዴ ነው ጠላትሽ’ …… በሙዚቃ ጥራትና ባሠራር ደግሞ፣ ሙላቱ አስታጥቄ  ያቀነባበራቸውና ከዳህላክ ባንድ ጋር የዘፈንኳቸው ‘ቼ በለው’ እና ‘ውቢት’።” ናቸው ብሏል::

ሙሉቀን መለሰ ዘፈንን በ1976  በግልጽ ማቆሙን ታሪኩ ያስረዳል:: በሙዚቃ 17 ዓመታትን ቆይቶ 10 ካሴቶችን ለአድማጭ ማድረስ ችሏል:: እስከ እለተ ሞቱ ድረስ ቀሪውን ዘመኑን በዘማሪነት አገልግሏል::

እውነትም ታላቅ የሚባሉ፣ በድሮው ሰው ዘንድ የሚታወስባቸው፣ በአሁኑም ትውልድ እጅግ ተናፋቂና የማይሰለቹ ስራዎችን ያበረከተ የኪነ ጥበብ ሰው ነበር። ነበር የምለው ዛሬ ይሄ ሰው እንደ ትናንቱ  ሁሉ

“ኮራ ያለ ዳሌ ጉትት ያለ አንጀት

ከእሷ ጋር አድሬ ሲነጋ ልሙት” ሲል ልንሰማው ስለማንችል ነው። “የኢየሱስ ወታደር ነኝ” ብሏል፤ ቀድሞም ዘርፍ ቀይሯል:: ሰዉነቷ፣ ናኑ ናኑ ነይ፣ ሰውነቷ ፣ ምነው ከረፈደ፣ ቁረጥልኝ ሆዴ፣ እቴ ወተቴ ማሬ፣ አይኔማ ወዳጅሽ፣ በምስጢር ቅበሪኝ፣ ውቢት፣ ሌቦ፣ ተወራርጃለሁ፣ ናፍቆቴና ሌሎች ሙዚቃዎቹን የሚያውቅ ይሄንን ሰው እንዴት አድርጎ ሊረሳው ይችላል!!

ናኑ ናኑ ነይ በሚል ዜማው ዝነኛ ሆኖ የተደነቀበትና ወደ ፊት ሄዶ ሌሎች ሙዚቃዎችን በጥሩ ሁኔታ ለመስራቱ በማሳያነት ሊጠቀስ ይችላል። አድማጭም የዚህ ሙዚቃ ዜማውን ቢረሳው እንኳን ግጥሙ ራሱ ስእል እየሰራ አእምሮ ውስጥ መላወሱ አይቀርም።

የዚህ ናኑ ናኑ ነይ ብሎ የሚዘፍነው ሙዚቃ ፤ግጥሙ እንዲህ ይወርዳል። የማይቀረውን ሞቴን በእሷ ልሙተው ሲል።

“ተረከዘ ሎሚ ጠብደል ያለ ባት

ሰፋ ያለ ዳሌ ጉትት ያለ አንጀት

ከእሷ ጋር አድሬ ሲነጋ ልሙት

ላፈር አይደለም ወይ የተፈጠርሁት”

ሰውነቷ በሚል ዜማው በእውኑ ዓለም ያለችን ሴት  ስንመለከት፣ አንዲት ሴት እንዴት ሆና ነው ቀጥሎ በግጥሙ ውስጥ የተዘረዘሩትን መልከ መልካምነቶች አሟልታ ልትገኝ፤ እግዜሩስ እንዴት አድርጎ ፈጥሯት ይሄንን ሁሉ ውበት ልትይዝ ትችላለች?  ብለን ልንገረም እንሻለን:: ዓለም ፀሐይ ወዳጆ የሴትን ልጅ ውበት ሴት ሆና እንዴት ነው በዚህ ደረጃ መግለፅ የቻለችው የሚለው ይገርመኛል:: የተቃራኒ ጾታ ስበት ወንዱን በሴት፣ ሴቷን በወንድ ቢያስሞግስ አይደንቀን ይሆናል:: ሴቷን  ሴት ስታደንቃት ግን ግሩም ነው::

አቤት ግሩም፤ አጀብ ነው መቼም የዚህች ልጅስ ውበት ብለን እንድንገረምና አይተናት የማናውቅ አይነት ቆንጆና ሁለመና ሙሉ የሆነች ሴት በኅሊናችን እየሳልን እንድንመለከት ያደርገናል። ደግሞ አድርጎናል።ለዘመናት ሳይደበዝዝ በዘለቀ ተደማጭ ዜማው።

ይሄ ሐሳብ በተነጻጻሪ ዘይቤ የቀረበ የዓለም ፀሀይ ወዳጆ ግጥም ነው። አሁንም ይህችን ልጅ መሳላችንና ዓይናችንን ጨፍነን መመልከታቸንን አላቆምንም። እስኪ ሰጎንን አስታውሳችሁ የልጂቱን አንገት ተመልከቱት።

አቤት እንዴት አድርጎ ሰራት ለመሆኑ? የሚርበተበት ከንፈሯን ያየ ሁሉ በፍቅሯ ተነድፎ የሚወድቅላት፤ የቀትር እባብ መሳይ አስደንጋጭነት ያላ ቆንጆ። ዘፋኙ ይህችን መሳይ ልጅ በልቡ አዳራሽ ገብታ እንደ ፈለገች እንድትንፈላሰስበትና መጨነቁ ካልቀረ ለእሷ ሁሉም ይሁን ብሎ ፈቃደኝነቱን የሰጠበት ግጥም ነው።

“የውበቷ ግርማ ከሩቅ የሚስበው

ዳሌ ተረከዟ ሽንጧ ያረገደው

አይኗ እንደ ጦረኛ የሚያስበረግገው

ደረቷ እንደ ጋሻ ደርሶ ሰፋ ያለው

ጡቷ እንደ አራስ ነብር አትንኩኝ የሚለው

አንገቷ እንደ ሰጎን ተመዞ የወጣው

አፏ እንደ ሕጻን ልጅ የሚርበተበተው

እንደ ቀትር እባብ ፍቅሯ የሚነድፈው

የልቤን አዳራሽ እልፍኟ ታድርገው

አንጀቴ ውስጥ ገብታ ልቤን ታስጨንቀው”

ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ያለፉትን በርካታ ዓመታት በክርስቶስ መንገድ ሲጓዝ፤ ክብሩን ሲቀድስ፤ ሲያመሰግን፤ ሲዘምር እነሆ ደብዛው ጠፍቶ ኖሮ፤ በራድዮም በቴሌቪዠንም፤ አልፎም በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ ብቅ ብሎ ስለ ቀድሞ ማንነቱ፤ ስለ ልጅነቱ፤ ከ17 ዓመት ስለማይበልጠው የሙዚቃ ሕይወቱ፤ ማርኮ የክብሩ አገልጋይ ስላደረገው ክርስቶስ ባለፉት ቅርብ ዓመታት አውርቶ ነበር::

ጎጃም የተወለደው ይህ ሰው ሰርግ ቤቶች በሄደበት የልጅነት ጊዜው የዘፈን ፍቅር እንዳደረበትና አብሮት ዓመታት ዘልቆ፤ ደግሞ የክርስቶስ መንፈስ ጥሪ እንደደረሰው ተናግሮ ነበር::

ኮልፌ ጡረታ ትምህርት ቤት ሙዚቃን በስድስት ወይም በሰባት ዓመቱ እንደጀመረ ታሪኩ ያስረዳል። በዚህ እድሜው ከትምህርት ይልቅ ለመዝሙርና ለሙዚቃ ትልቅ ዝንባሌ ነበረው።

የጥላሁን ገሠሠ፤ የአለማየሁ እሸቴና የታምራት ሞላ ዘፈኖችን በፒያሳ ሻይ ቤቶችና በውቤ በረሀ መንገዶች፤ በልጅነት እዕድሜው በሃርሞኒካ እየታጀበ አንጎራጉሯል።

ለሙሉቀን የሙዚቃዎቹ መወደድ ምስጢር ደግሞ እርሱ እንደሚለው ሙዚቃን በማወቅና በመልፋት፤ ጊዜ ወስዶ በመለማመድ ድካም የተገኘ ነው።

የሙሉቀን መለሰ ታሪክ ውጣ ውረድ፣ መገፋት፣ የቤተሰብ ፍቅር ማጣት፣ መገለል፣ ርሃብ፣ ችግር፣ ስቃይ እና መከራን ተቀብሎ ማለፍን፤ በመኖር ውስጥ ደግሞ ስኬትን ከስቃይ እቅፍ ውስጥ አውጥቶ የሞቀን አንድ ተወዳጅ ዘፋኝ ያሳያል።

እናቱን በአምስት ዓመቱ እንዳጣ አዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ሰፈር ይኖር የነበረ  አጎቱ ጋር ለተወሰኑ ጊዜያት ኖሯል

ሙሉቀን ከፈጣን ኦርኬስትራ በመቀጠል  ዙላ ናይት ክለብን ተቀላቀለ። በወቅቱ በሰለሞን ተሰማ የተደረሰውን “የዘላለም እንቅልፍ” እና አቡበከር አሽኬ የደረሰውን “ያላየነው የለም”ን ይዞ በቴሌቪዥን ቀረቦ ነበር:: ሙሉቀን በአዲስ አበባ እውቅናው ተናኘ:: የፖሊስ ኦርኬስትራ መሪዎች አራት መቶ  ብር እንከፍልሃለን ብለው ቀጠሩት::በቆይታውም  ተስፋዬ አበበ የደረሳቸው ሶስት የዘፈን ድርሰቶችን “እምቧይ ሎሚ መስሎ፣ እናቴ ስትወልደኝ እና  ያ ልጅነት” የተሰኙትን  በህዝብ ፊት በመዝፈኑ ታዋቂ ሆነ። ሙሉቀን መለሰ ከፖሊስ ኦርኬስትራ ጋር በነበረው ቆይታ ከተስፋዬ አበበ ጋር በመገናኘቱ ትልቅ ሙያን ለመማር በቅቷል። ከዚያም ወደ ግዮን ሄቴል በመሄድ ዳሕላክ ባንድ ጋር ሆኖ ተወዳጅና ተናፋቂ ሙዚቃዎችን ሰራ። ሙሉቀን መለሰ አሰገደች አላምረው ቡና ቤት፣ ፖሊስ ኦርኬስትራ፣ ዙላ ክለብ፣ ቬኑስ ክለብ፣ ኢኩዌተርስ፣ ዳሕላክ ባንድና ሮሃ ባንድን በመሳሰሉ የወቅቱ ተወዳጅ ባንዶች ዘመን ያልለወጣቸው ዜማዎችን ሰርቷል።

በርካታ የካሴት ስራዎችን ሰርቷል፣ ናኑ ናኑ ነይ፣ ሰውነቷ፣ እምቧ ዘቢደር፣ እምቧ በይ ላሚቱ፣ ሀገሯ ጓሳ መገራ እና ሌችም ሙሉቀን በግዮን ሆቴል ቆይታው ከዳሕላክ ባንድ ጋር የሰራቸው ተወዳጅ ካሴቶች ናቸው።

ኖሮ ኖሮ ከመሬት ውሎ ውሎ ከቤት ነውና ሙሉቀን በ1946 ተወልዶ 2016 አልፏል::እሱ መዝፈን አቁሞ 40 ዓመታት ያህል የተደመጡት ስራዎቹ  ነገም ይቀጥላሉ:: ስራ ያለው ሰው ያልፋል እንጂ መች ሞትና:: ለዚያውም ምርጥ ምርጥ ዘፈኖች ያሉት ሰው:: ሕዝብ ልቦና ውስጥ ይቀጥላል::ሙሉቀን መለሰ በቀጭን ድምጹ ባንጎራጎራት “ሄደች አሉሄደች” የዜማ ግጥም እንሰነባበት። አልሞትም ቢልም ሞት አልቀረለትም:: ክፉ እጣ አለብን አይደለ:: ነፍስ ይማር::

“ሲያምሽ ታምሜያለሁ

ሲያግሙሽም ደም ወጣኝ

ስትሞች ግን አልመሞትም

ደሀው ምን በወጣኝ”

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here