ሙስናን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር ይገባል

0
127

የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ ፖሊስ ኮሚሽን እና ፍትሕ ቢሮ ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር ሙስናን ለመታገል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

ተቋማቱ በውይይታቸው ተቀራርቦ እና ተቀናጅቶ በመሥራት ሙስናን መከላከል ስለሚቻልበት ስልት ሃሳብ  ተነጋግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሐብታሙ ሞገስ የሙስና መከላከል ስትራተጂ ተዘጋጅቶ እና በመከላከሉ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ኮሚሽኑ የባለሙያዎች እጥረት እንዳለበት ያነሱት ኮሚሽነር ሐብታሙ በተመረጡ የሙስና ወንጀሎች ላይ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ተቀናጅቶ መሥራትም የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

“ከራሳችን ጀምረን ሃብት ማስመዝገብ አለብን” ያሉት ኮሚሽነር ሐብታሙ ፖሊስም ሃብታቸውን የማያስመዘግቡ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ተባባሪ እንዲሆን ጠይቀዋል። የራስን ተቋም ንጹህ አድርጎ አርዓያ የመሆን ኀላፊነት አለብን ብለዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች ጭምር በሙስና እንደሚዘፈቁ አመላክተዋል፡፡ በመሆኑም  በየደረጃው የሚገኙ መሪዎችን ስለ ሙስና ያላቸውን አመለካከት መቀየር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የወቅቱን የጸጥታ ችግር እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ከፍተኛ የሃብት ምዝበራ እየተፈጸመ ነው ያሉት ኮሚሽነር ደስዬ በተቋማቱ መሪዎች በኩልም የሰብዕና መጓደል እንዳለ አንስተዋል። ሕዝቡ ያለ እጅ መንሻ አገልግሎት እያገኘ አለመሆኑንም ጠቅሰዋል።

“የሃብት አመላለስ በሰላማዊ ጊዜም ችግር የነበረበት ነው፤ አሁን ደግሞ የበለጠ ልንቸገር እንችላለን እና በትኩረት መሥራትን ይጠይቃል” ብለዋል።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም (ዶ/ር) ሙስና እየተስፋፋ እንደሆነ እና የሚቋረጡ የጸረ ሙስና የክስ መዝገቦች መብዛት ከሙስና ውስብስብነት ባህሪ የሚመጣ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ ሙስናን በሰው ምስክር ብቻ ለመታገል አስቸጋሪ መሆኑን የሚቋረጡ የክስ መዝገቦች እንደሚያሳዩ ነው ያብራሩት። በተቋማት መካከል የሚፈጠረው የመረጃ መጣረስ ሌላኛው ሊፈታ የሚገባው ችግር እንደሆነም አመላክተዋል።

በአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር) ሙስናን ለመከላከል በባለ ድርሻ አካላት መረጃ የመለዋወጥ ችግሮች እንደነበሩ አንስተዋል። ሙስና እየከፋ በመሄዱ ሀገር ከማፍረስ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የጥቆማ ሰጪዎችን ደኅንነት መጠበቅም ለጸረ ሙስና ትግሉ አጋዥ እንደሆነ ያነሱት ሠብሣቢው ምክር ቤቱም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

ተቋማቱ ሙስናን ለመታገል የሚያስችል የትብብር ሥምምነት ተፈራርመዋል።

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የታኅሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here