“ፍቅርን በይሉንታ መውደድን በገንዘብ
ልግዛሽ ትለኝና እንዳንተዛዘብ”
የድምጻዊት ጸደኒያ ገብረ ማርቆስ ዘፈን ነው። ጉዳዬ ሙዚቃ፤ ሐሳቤም ትዝብት ነውና መጥቀሴ ለዚህ ነው።
የቀደሙ ዘመን ሙዚቃዎችን ከነ ንጽሕናቸው ልናደምጣቸው አልቻልንም። ከሙዚቃው ጋር ያለንን የስሜት እና ትዝታ ትስስር የሚያበላሹብን ዘፈኖች እየበዙ ነው። የሰው ሙዚቃ ሲያባዙ እና ሲዘፍኑ የሚያድሩ ወጣቶች እና ድምጻውያን ቁጥር በጣም እየበዛ ነው።
በሙሉቀን መለሰ እና ኤፍሬም ታምሩ ዘፈኖች ጋር ያለኝን የስሜት እና ትውስታ ትስስር የሚያጠፉ ዘፋኞች በዝተዋል። የቀደመውን ዘመን ዘፈን በሰማሁበት ጊዜ ከሙዚቃው ጋር የተቆራኜ ትውስታ አለኝ። በተለይ የኤፍሬምን ዘፈን ሰው ባይነካው፤ ከራሱ በቀር ዘፍኖ የሚያምርበት የለም።
አረጋኸኝ ወራሽ አንዴ “የዘፋኝ ጀግና የለውም፤ ዘመን እንጂ! ሁላችንም በጊዜያችን ጀግኖች ነበርን። አጥር ሰብሮ ኮንሰርታችንን የሚከታተል ሰው ነበር” ሲል ቃል በቃል ባይሆንም ሐሳብ መስጠቱን አስታውሳለሁ።
የዝና እና ተወዳጅነት ዘመን በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ውስጥ በጣም አጭር ነው። ገናና ሆነው የሚቀጥሉት ጥቂት ናቸው። የጥላሁን ገሰሰ ዝና 1960ዎች ውስጥ ክቡር ዘበኛ በነበረበት ወቅት ነበር። ቀጥሎ ሌላ ተወዳጅ ዘፋኝ ሞገዱን ይዞታል። ዛሬ የ1970ዎቹ የምንላቸው ብቅ ያሉት ያን ጊዜ ነበር።
ስለ ዝና ዘመን ሲነሳ ኤፍሬም ታምሩ የሙዚቃ አልበም እንዳይሰራ በጣም እመኝለታለሁ። ለምን ፈለግሁ? አሁን የዘመን ለውጥ አለ። አሁን የኤፍሬም ዘፈኖች እና ዜማዎች ምን ሆነው ቢሰሩ ነው ድሮ በሰማሁበት ጣዕም ልክ የምሰማቸው ብዬ እጨነቃለሁ።
አሁን ዘመኑ የድምጽ ቅጅ፣ ቪዲዮ፣ ፋሽን፣ ሞዴል እና ሌሎች ያደጉበት ዘመን ነው። በአንጻሩ ግጥም፣ ሐሳብ እና ዜማ የሚደጋገምበት፣ የሱዳን እና ሌሎች ሀገራት ዜማዎች የሚሰሩበት ነው። የድሮዎች የሚከለሱበት ጊዜ ነው።
አንዳንዶቹ ድምጻውያን የራሳቸውን ዜማዎች ሳይቀር መድገም ጀምረዋል። የዜማ ድርቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይከሰት አልቀረም። የቀድሞዎቹ ዜማ ደራሲዎችም እንኳን ዘመኑን ለመምሰል ያደረጉት ሙከራ ብዙ ውጤት አላሳየም።
አንጋፋው ይልማ ገብረአብ፣ ጸጋዬ ደቦጭ፣ ተስፋ ብርሃን፣ አበበ ብርሃኔ እና ሌሎችም ሙዚቃው ውስጥ አሉ። በተጽእኖ ደረጃ ግን ስንመለከታቸው እንደቀደመው ዘመን አይደሉም። በከበሮ ኳኳታ እና መሳሪያ ባጀበው የሙዚቃ አሰራር ውስጥ ተውጠዋል። ዘመኑ ፋሽን ያደረገው ሌላ ዓይነት የሙዚቃ መልክ እና አካሄድ አለ። አፍሮ ቢት እያሉ ይጠሩታል።
የሙዚቃ ሐያሲው ሰርጸ ፍሬ ስብሐት በአንድ ወቅት የሀገራችንን ሙዚቃ ገልጾት ነበር። “የአሁን ሙዚቃዎች ሪትሚክ (የምት) መልካቸው እየበዛ ነው። የቀድሞዎቹ ሜሎዲክ (ዜማ ተኮር) ነበሩ” ማለቱን አስታውሳለሁ።
ይህ ሐሳብ ሲብራራ የድሮ ዘፈኖች ዜማ ነበራቸው። ዋናው ጣዕማቸው ዜማው ላይ ነበር። የዘንድሮዎቹ ደግሞ በምት ላይ የበዛ ትኩረት ያላቸው ናቸው እንደማለት ነው። ጥላሁን ገሰሰ ያለምንም የሙዚቃ መሳሪያ ቢዘፍን ሳይጎረብጠን እንሰማው ነበር። ዘንድሮ የሚወጡ ዘፈኖች ግን በድምጽ ብቻ ቢሰሙ ዜማ የሌላቸው ስድ ግጥም ንባቦች ይሆናሉ የሚል ነው። ሙዚቃውን ‘‘የሚያሳምረው’’ ዜማው ሳይሆን በውስጡ ያሉት ሳክስፎን፣ ጊታር፣ ከበሮ፣ ክራር፣ ክላርኔት፣ ማሲንቆ፣ ኪቦርድ ወይም ሎሎች መሳሪያዎች ጫጫታ ነው።
ዜማውን አልን እንጂ ግጥሞችም በጣም እየወረዱ ነው የመጡት። ሙዚቃ በሁለት መልኩ ልትዳኝ ትችላለች። የመጀመሪያው ጥበብ በመሆኗ ስሜታዊ ባህሪ ኖሯት በስሜት ወይም በአድማጭ እና ተመልካች ትዳኛለች። ሁለተኛም ሳይንስ ናትና በሙያ ዓይን ትተነተናለች።
ግንቦት 28 ቀን 2009 ዓ.ም የሙዚቃ ባለሙያው ሰርጸ ፍሬስብሐት ከበኩር ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር። “ሙዚቃ ከእውቀት ይልቅ በስሜት እየተመራች ነው” ሲል የሙዚቃው ዘርፍ ውድቀት ውስጥ መግባቱን ተናግሮ ነበር። ዛሬ የሙዚቃ ሽልማት ፕሮግራሞች የሚሸልሟቸው ዘፋኞች በስሜት በኩል በማጋደል ሕዝብ ወዷቸዋል በሚል ሰፊ ድምጽ እና ድጋፍ የሚያገኙትን መሆኑ ለዚህ ማሳያ ነው።
ሕዝቡ ለሙዚቃ የስሜት እንጂ የእውቀት ማስተዋል የለውም። ድምጻውያን ደግሞ የሕዝቡን ስሜት ተከትለው ዘፈኖችን ማዘጋጀት መጀመራቸው ሙዚቃ ከክብሯ እንድትወርድ እያደረጋት ነው። ድምጻውያኑ ቀድመው ሕዝቡን ከስሜት ወደ እውቀት አከል የሙዚቃ አድማጭነት መምራት ነበረባቸው። ሙዚቃ ለገበያ መቅረቡ ርግጥ ሆኖ ሳለ ለሽያጭ ብቻ አስቦ መስራት በዘርፉ ላይ እሾህ እየተከለበት ነው። ሙዚቀኞቹ በእውቀት ቀድመው ወደ ትክክለኛው መስመር ካልመሩት ሕዝብ በስሜት ጋልቦ ጋልቦ ውድቀት ውስጥ ሊገኝ ይችላል።
ዜማ ለምን ጠፋ፣ እንደገና የሰው ዘፈኖችን መስራት ለምን በዛ? ስንል የሚመልሰን የሙዚቃ ዘርፉ ወደ ገጠሙት ችግሮች ነው። ምንድን ነው የኢትዮጵያ ሙዚቃ የገጠመው ችግር? ቴክኖሎጂ ቀዳሚው ጠላቱ ነው። ቴክኖሎጂ እድልም ፈተናም ነው። ለሀገራችን ግን ፈተና ሆኖ ቀርቷል። ዘመናዊ ሙዚቃችን ጅማሮው በመንግሥት ሰራዊት ቤቶች ነው። በሀገር ፍቅር፣ በክቡር ዘበኛ፣ በፖሊስ ሰራዊት፣ በምድር ጦር ኦርኬስትራ፣ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት፣ በብሔራዊ እና ራስ ትያትር ቤቶች ውስጥ ዘመናዊ ሙዚቃ ተወልዶ አድጓል።
በዚህ ዘመን ሙዚቃ ለዝና እና ለተልእኮ የሚሰራበት ዘመን ነበር። የወር ደሞዝተኛ ሆነው ሙዚቃን ለሕዝብ የሚያቀርቡበት ዘመን ነበር። ዘመኑ ሲለወጥ የግል ባንዶች መምጣት ጀመሩ። ተፈራ ካሳ፣ እሳቱ ተሰማ፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ ተዘራ ኀይለሚካኤል ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ከመንግሥት ቤቶች ተደብቀው ማታ ማታ ክለብ ይዘፍኑ ነበር። ሾፌሮች ቡና ቤት እና አሪዞና ክለቦች ለዚህ ማሳያዎች ናቸው።
አንጋፋው ማህሙድ አህመድ 1954 አሪዞና ክለብ ውስጥ ከወጥ ቤት ሰራተኛነት ተነስቶ ነው በተፈራ ካሳ እና ጥላሁን ገሰሰ ዘፈኖች ጉሮሮውን አሟሽቶ ዘፋኝ የሆነው።
በኋላም የግል ባንዶች መስፋፋት ሲጀምሩ ሙዚቃ ከስም እና ዝና በላይ የገንዘብ ምንጭነቷ ጨመረ። ማህሙድ አህመድ 1965 ዓ.ም ክቡር ዘበኛን ለቆ ራስ ሆቴል ውስጥ ሙዚቃ ያቀርብ የነበረውን አይቤክስ ባንድን ተቀላቅሏል። ተጨማሪ ገንዘብ አገኘ። በሙዚቃ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ለማስተዋወቅ ቻለ።
ሙዚቃ በየጊዜው ገንዘብ የምታበላ ስራ መሆኗ ጨመረ። የካሴት ዘመን 1970ዎቹ ላይ ገናና ሆኖ እስከ 90ዎቹ አጋማሽ ቀጠለ። ሲዲ እና ዲቪዲ ዘመኑን ተረከቡት። በዚህም አልቆመም። የፍላሽ ዘመን መጣ። ሙዚቃ በካሴት መሸጥ የሚፈልግ ዘፋኝ ሙዚቃው ዋጋ እንዲያወጣለት ብዙ ዓመታትን በምሽት ክለቦች ይሰራል። ሙዚቃ ቤቶችም የዘፋኙን ስራ እና ድምጽ አይተው ካልተመቻቸው ተፈራርመው ስለማይገዙት ለጥራት የዓመታት ልምምድ ያደርግ ነበር። ሙዚቃ ማቀናበሪያ ማሽኖች፣ መሳሪያዎች፣ ሙዚቀኞች በቀላሉም የሚገኙ አልነበሩም።
ዘፋኙ ስራውን በጥሩ ዋጋ ለመሸጥ ሲል ጥሩ ዜማ እና ግጥም ይሰራል። ጥሩ አቀናባሪዎች ጋር ይገናኛል። ሙዚቃ ዋጋ ስለነበራት ብዙዎች ይሳተፉባታል። እርስ በርስ መገምገም እና ለጥራት ተገቢውን ትኩረት መስጠትም ነበር። ዜማዎችን በጋራ መስራት፣ መዋዋስ ነበር። አንዱ የሌላውን አቅም አውቆ በልኩ ግጥም እና ዜማም ይሰራለት እንደነበር ድምጻውያኑ ሲያወሩ ከትዝታዎቻቸው ሰምተናል።
በፍላሽ ዘመን ሙዚቃ በሕገ ወጥ ቅጂ ሁሉም ሰው ዘንድ የሚደርስበት ሆነ። የፈጠራ ባለ ቤቶችን እና ሙዚቀኞችን ተስፋ ያስቆረጠ የቴክኖሎጂ ጉዳት ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወዲህ ፈተና ሆኖ ጥቂት ዘፋኞች ብቻ በአስር እና ሰባት ዓመታት ሙዚቃ የሚያወጡበት ሆነ። የነጠላ ዜማ ድግግሞሽ የበዛበት ነበር። ገበያ ሲጠፋ አልበም የሚያወጣ ዘፋኝ ቁጥር ቀነሰ። ገበያው አበረታች ቢሆን ምን እንቅልፍ ይኖር ነበር? ዘመን ተሻጋሪ ስራስ ለመስራት ማን ይቸገር ነበር?
ቴክኖሎጂ እድል ይዞ መምጣቱን የተረዱ ሙዚቀኞች ብቅ ያሉት በ2016 ዓ.ም ነው። ከዚህ በፊት የሙዚቃ ቤቶችን ሚና የሚወክሉ የግለሰብ የየቱዩብ ቻናሎች ነበሩ። ሆኖም የዘፋኙን ወጪ ሸፍነው ጥቅሙን ማስከበር የሚያስችል ክፍያ አልነበራቸውም። ባለፈው ዓመት በግል ቆጠራዬ 20 የሙዚቃ አልበሞች ለአድማጭ ደርሰዋል። ምን ያህሉ ጥሩ ናቸው የሚለው ለባለሙያዎች የሚተው ቢሆንም ከ75 በመቶ በላይ አልበሞች በዘፋኞች የግል የዩቱዩብ ቻናል የተለቀቁ ናቸው። ይህ አካሄድ ቴክኖሎጂን ከፈተና ወደ እድል የመቀየር ጥረት ቢሆንም እንኳን ገንዘብ ያለው ሁሉ ዘፋኝ፣ ገንዘብ ማምጣት የሚችል ሁሉ ዘፈን እንዲሆን የማድረግ ስጋት አለበት። የሁሉም ሙዚቃዎች መዳረሻ ዩቱዩብ ነው። ሙዚቃን በቀጥታ የሚገዛ ጠፍቶ ሙዚቀኛው ለዓመታት የለፋበትን ስራ በነጻ ከተመልካች የሚገኝን ክፍያ በማሰብ ያሰራጩታል።
ከባለፈው ዓመት አንጻር በያዝነው 2017 ዓ.ም አዳዲስ የሙዚቃ አልበሞች ቀንሰዋል። ተመልሰን ነጠላ ዜማ እና የድሮ ዘፈኖችን መከለስ ውስጥ ገብተናል። የሚለቀቁ ነጠላ ዜማዎችም ከቀናት በኋላ የሚሰለቹ ሆነው ይሰሙኛል። የሱዳን ቢት ዘፈኖች ዛሬም እንደገና ፋሽን መስለው መሰማት ቀጥለዋል።
ቀደም ሲል የተለመደው ዘመናዊ ሙዚቃዎችን እንደገና መስራት ነበር። ዘንድሮ ደግሞ ባህላዊ ሙዚቃዎች ሁሉ ድጋሚ እየተዘፈኑ ለዛ እና ወዛቸው እየጠፋ ነው። ይህ አካሄድ አንድም በሙዚቃ ላይ ጠንካራ በትሩን ያሳርፋል። ሁለትም ገንዘብ ያስገኛል በሚል ጥራት የሌላቸው ገበያ ተኮር ስራዎች እንዲበራከቱ ያደርጋል። ሦስትም ቀደምት ድምጻዊያን የሰሯቸው ዘፈኖች ድጋሚ እንዲሰሩ የድግግሞሽ መንገድ ይፈጥራል።
ብዙአየሁ ደምሴ በግሉ ሁለተኛ አልበም ሲጠበቅ የሙሉቀን መለሰን ቁረጥልኝ ሆዴ ዘፈን ደግሞ ሰራ። ዳዊት ጽጌ ሁለተኛ አልበምን ያወጣል ሲባል የእሳቱ ተሰማ ዘፈኖችን ደግሞ ሰራ። ፈቃዱ ትዕዛዙም በግሉ ሲጠበቅ የተፈራ ነጋሽን አልበም ሙሉውን እንደገና ሰራው። አዲስ ስራ ማቅረብ በጣም ከብዷል። ክፍተቱ ከዓመታት በኋላ የሚታወቀን ይመስለኛል። አሁን ኳኳታው ጆሯችንን ይዞታል።
አሁን የሙዚቃ ስራዎች ለዩቱዩብ ገንዘብ ያስገኛሉ በሚል የሚሰሩበት ዘመን ሆኗል። አዲስ ዜማዎችን የሚያስደምጡን ሰዎች ውስን ናቸው።
ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ዛሬም በነጻ ሙዚቃ ሰርተው የዓመታት ልፋታቸውን ውጤት እና ሀብት ለሚለግሱን ድምጻውያን ምስጋና እና ድጋፍ ያስፈልጋል። ሙዚቃ በሀገራችን ከመድረክ ማድመቂያነት ባለፈ መንግሥት በፖሊሲ እና ሕግ ሊደግፈው ካልቻለ ብቻውን ተጉዞ ተጉዞ ሊወድቅ ይችላል። ርግጥ አሁንም ሙዚቃ ወድቋል፤ ዘመን አይሻገርም የሚሉ ብዙ አሉ። ያም ሆኖ ሙዚቃ ለመውደቋ ብዙ ምክንያቶችን ብናስቀምጥ መፍትሔው ከሌለ ከንቱ ድካም ነው።
ለአዳር የሚጨፈርባቸው ሙዚቃዎች ብዙ ናቸው። ድለቃ እና ከበሮ በብዛት ይሰማል። ተቀራራቢ ቀለም በሙዚቃችን ውስጥ ማየት የብዙዎች ምኞት ነው። እንደቀደሙት ዘፈኖች ትውልድ በቅብብሎሽ የሚያደምጣቸው፣ በዜማ፣ በሐሳብ ከፍ ያሉ ስራዎች በነጻ አይገኙም። ሁሉም ባለድርሻ የሚገባውን ድርሻ መክፈል አለበት።ተገቢው ዋጋ በጊዜ ካልተከፈለ ቴክኖሎጂ ያፈራቸው ፍራሽ አዳሽ ዘፋኞች እንደ አሸን ፈልተው የድሮ ዘፈኖችን እንደገና እየሰማን እንቀጥላለን። ሰው እንቀይራለን ዘፈን እንደግማለን።
በሀገራችን ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ አይዶል፤ ባላገሩ አይዶል፣ ፋና ላምሮት፣ ኤንቢሲ ትናንት ሾው፣ ደሞ አዲስ፣ በቅርቡ ደግሞ በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የሙዚቃ ውድድሮች እየተደረጉ ቀጥለዋል። ከባላገሩ አይዶል በቀር ሁሉም ውድድሮች መድረክ ከማሞቅ ያለፈ ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ የረባ ተተኪ አፍርተዋል ለማለት አልደፍርም። የጥላሁንን ሲጫዎቱ ጎበዞች ናቸው። በግላቸው ሲመጡ ተፅእኖ አይፈጥሩም። የሚያቀርቡት የድሮ ዘፈኖችን ነው። አዲስ ፈጠራ በራሳቸው እንዲሰሩ እንኳን አይደረግም። ይህ የድሮ ዘፈኖችን እየደጋገሙ መዝፈን ለውድድር የሚመጡ ወጣቶች በየክለብ ቤቶች ሲዘፍኑት የኖሩ ነው። ብዙዎች የሙዚቃ ልምድ ያላቸው ናቸው። ረጂም ዓመታት ክለብ ውስጥ ዘፍነዋል። እነዚህ ወጣቶች የሙዚቃ ዝግጅቶች መድረክ ላይ ሲዘፍኑ ምን የተሻለ ነገር ያመጣሉ? ጥላሁንን፣ የሙሉቀንን፣ የአስቴርን፣ የብዙነሽን ለዓመታት ምሽት ቤቶች ውስጥ ዘፍነው የለ እንዴ? ባይሆን አዲስ ዜማ ይዘው፣ በራሳቸው ፈጠራ እንዲመጡ የሰው ከማስመሰል ባለፈ ራሳቸውን ሆነው እንዲወጡ መደረግ ነው የነበረበት። የሙዚቃ ዝግጅቶች ግን የማስታወቂያ ገቢ እና ራሳቸውን ማስተዋወቅ ስለሚበጃቸው ልምድ ያላቸውን ዘፋኞች ነው ድጋሜ ሲያዘፍኑብን የሚውሉት። አይዶል ላይ ከዘፈኑት ይልቅ በግላቸው የሚመጡ ልጆች የተሻለ ተፅእኖ ሲፈጥሩ አይተናል። ለምን?
ባላገሩ አይዶልን በልዩነት አየዋለሁ። ዛሬ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ተተኪ የሚባለውን ዳዊት ጽጌን የሰጠን እሱ ነው። ኢሳያስ ታምራትም ቢሆን በሚጠበቀው ልክ ሳይሆን ቢቀርም የባላገሩ ፍሬ ነው። ይህ አይዶል ምንም የሙዚቃ ልምድ የሌላቸውን ባለተሰጥኦዎች ነው ለዓመታት አሳድጎ ሙዚቀኛ የሚያደርገው። እንዴት አፋቸውን መክፈት እንዳለባቸው እንኳን የማያውቁ ልጆችን አሳድጎ ምርጥ ዘፋኝ አድርጓቸዋል። አክሊሉ አስፋው እና ብሩክ ሙሉጌታ በባላገሩ አይዶል ያደጉ አሸናፊዎች ናቸው። አሁን በራሳቸው ቀለም የሚመጡበት አልበም ፕሮጀክት ጀምረዋል። ባላገሩ አይዶል አያያዙ ጥሩ ነበር። ድጋፍ ቢደረግለት ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ትልቅ ፕሮጀክት ነበር። ሙዚቀኞቹ በልምምድ ጊዜ የሌሎችን ዘፋኞች ስራዎች ቢያቀርቡም እንኳን የመጨረሻው ቀን ግጥም እና ዜማ አዘጋጅቶ እንዲያቀርቡ ያደርጋቸዋል።
ሙዚቃ በቴክኖሎጂ ነው ጉዳት የደረሰበት የሚለውን ሐሳብን አጠናክሬ ልጨርስ። የሙዚቃ አቀናባሪዎች ዛሬ ብዙ ናቸው። ቅንብሩም ቀላል ሆኗል። በአንድ አዳር ሙዚቃ ሰርቶ መጨረስ ቀላል ነው። ማሳ ውስጥ ሆኖ የሚዘፍንን ሕጻን ድምጽ ወስዶ በሙዚቃ አቀናብሮ መልሶ ለተመልካች ማድረስ ቀላልም ፋሽንም ሆናል። ቴክኖሎጂ በዚህ ልክ ቀላል ሲያደርገው ጊዜ እና ትኩረት የሚፈልገው የዜማ ስራ ችላ ተባለ። ከባድ ሆነ። እስኪ እንነጋገርበት? በዚህ ጉዳይ ላይ ሌሎችም ባለሙያዎች ሐሳብ ስጡበት።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም