የሁለት ሙያዎች ባለቤት ናቸው፤ መምህር እና ሙዚቀኛ:: ለ37 ዓመታት በሚወዱት መምህርነት ወገኖቻቸውን አገልግለዋል። ብዙ ተማሪዎችንም ጥሩ ደረጃ አድርሰዋል:: በሙዚቃው ደግሞ አልበም ሠርተዋል፣ ከታዋቂ ሙዚቀኞች ጋር አቀንቅነዋል:: ከወራት በፊት የለቀቁት “ላየ” የተሰኘው ባሕላዊ ነጠላ ዜማ ተወዶላቸዋል፡- እንግዳችን መምህር እና ድምጻዊ ፈንታው አበራ ናቸው:: ከአሚኮ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እነሆ::
መምህር እና ድምጻዊ ፈንታውን ባሕላዊ እና ዘመናዊ ሙዚቃዎችን ይጫወታሉ። ወደ ሙዚቃው እንዴት ገቡ?
የተወለድኩት በላሊበላ ከተማ ነው:: ሙዚቃ የጀመርኩት በደርግ ዘመነ መንግሥት ነው:: በወቅቱ ታዳጊ ኪነት የሚባል ነበር:: በታዳጊ ኪነት ውስጥ ገብቼ የተለያዩ ፖለቲካዊ መዝሙሮችን አቀነቅን ነበር:: ቀጥሎም ወደ ከፍተኛ ኪነት ገባሁ:: ደጀኔ ከፍተኛ ኪነት የሚል ስያሜ ነበረው:: በከፍተኛ ኪነት በድምጻዊነት በማገልገል ላይ እያለሁ የደርግ መንግሥት ላሊበላ ከተማን በህወሃት ታጣቂዎች ተነጠቀ:: ስለዚህ ተፈናቅለን ወደ ደሴ ከተማ ለማቅናት ተገደድን::
ደሴ ከተማ ውስጥ ብዙ የሙዚቃ ልምድ አግኝቻለሁ:: በተለይ ፖሊስ ኦርኬስትራ ውስጥ ኃይለማርያም የሚባል ልጅ ነበር:: እሱ ብዙ ነገር አስተምሮኛል:: በወቅቱ ፒያኖ የሚባል ነገር እንኳ አላውቅም:: በፒያኖ አጅቦ ያሰለጥነኝ ነበር:: ከዚያም ወሎ ባሕል አምባ ውስጥ ጥቂት ሠራሁ፤ ልጅነት ስለነበረ ብዙም አልቀጠልኩም::
በትርግራይ ኪነት ውስጥም የአማርኛ ዘፋኝ ነበርኩ:: አሰብ ድረስ እየሄድን የጥበብ ሥራዎቻችንን እናቀርባለን:: ታዋቂው የትግርኛ ዘፋኝ ኪሮስ አለማየሁ ከአዲስ አበባ እየመጣ ነበር አብረን የምንሠራው:: በጊዜው “መለሎዬ” እና “ብርዝዋ” የሚሉ ሙዚቃዎች ነበሩኝ::
ቀጥሎም የአክስቴ ልጅ ክራር መጫወት ይችላል:: ከእሱ ጋር ሆኜ በክራር ብቻ አልበም አወጣሁ:: በዛን ጊዜ ስቱዲዮ የሚባል አናውቅም ነበር:: ስለሆነም ሙዚቃውን የቀረጽነው በሶኒ ሙዚቃ ማጫወቻ ቴፕ ነበር:: በዚህ ሁኔታ የተሠራው አልበም 10 ሙዚቃዎችን የያዘ ነው::
ሙዚቃን ለማስተማሪያነት እንደሚጠቀሙ ሰምተናል። እንዴት እንደሆነ ቢነግሩን?
ሙዚቃ ጥሩ ከሚባሉት የማስተማሪያ ዘዴዎች ውስጥ አንዱ ነው ይባላል፤ ትምህርቱን በየትኛውም ደረጃ ላሉ ተማሪዎች በሙዚቃ አዋዝተህ ስትሰጣቸው በእጅጉ ይመሰጣሉ፤ ይሳባሉ:: በማስተምርበት ሰዓት በተለይ ከሰዓት በኋላ ሙቀት ስላለ ተማሪዎች ይደክማሉ፤ ይሰላቻሉ:: በዚህ ጊዜ ሙዚቃ ጣል አደርግላቸዋለሁ፤ “ጋሽ ፈንቴ መጣ” ብለው በደስታ ነው ክፍል ስገባ የሚቀበሉኝ::
በመምህርነት በገጠር እና ከተማ ለ37 ዓመታት አገልግያለሁ:: ላሊበላን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች አያሌ ልጆችን አስተምሬያለሁ:: በተለያዩ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ሕዝባቸውን እያገለገሉም ይገኛሉ:: የራሳቸውን የንግድ ሥራ ፈጥረው ውጤታማ የሆኑም አሉ::
ሁለቱን ሙያዎች ጎን ለጎን ነው የማስኬዳቸው:: በመምህርነት በመጀመሪያ በቲቲአይ ነው የተመረኩት:: ቀስ በቀስ ደግሞ ወደ ዲፕሎማ ከዚያም ወደ ዲግሪ ማሳደግ ችያለሁ:: በእርግጥ ሁለቱን ሙያዎች በአንድ ላይ ማስኬድ ከባድ ነው:: ሙዚቃውን ግጥም እና ዜማ ሠርተህ ለማስቀረጽ አዲስ አበባ ነው የምትሄደው:: በስቱዲዮ ሙዚቃው ከተቀዳ በኋለ የተንቀሳቃሽ ምስል ማሠራት ይኖርብሃል:: እነዚህ ነገሮች በማጨናነቅም ቢሆን ለማስኬድ እና ለማኅበረሰቡ ሥራየን ለማቅረብ ሞክሬያለሁ:: ትምህርቱን እያስተማርኩ ሙዚቃ ልምምዴን ግን አላቆምኩም:: በዋናነት የምተዳደረው በመምህርነት ነው::
በሙዚቃ ሥራዎት የማይረሷቸው ገጠመኞች ካሉ ቢያጫውቱን?
አንድ ጊዜ ከከተማ ወጧ ብዬ የሙዚቃ ልምምዴን አደርጋለሁ:: ብቻየን ነው ያለሁት:: የሆነ ሰው ከርቀት ወደ እኔ በፍጠነት እየሮጠ ሲመጣ አየሁ:: ሊደበድበኝ ነው ብየ አሰብኩ። በፍርሃት ድንጋይ ከጎኔ አድርጌ ቁጭ አልኩ:: አሁንም በኃይል እየተነፈሰ መምጧቱን ቀጠለ:: እኔም ተዘጋጅቻለሁ:: ልክ እንደደረሰ ቁጨ አለና “እረ ጋሼ ያችን ሙዚቃ ክፈቱልኝማ” አለኝ:: ለካስ የእኔን ድምጽ ሰምቶ ነው የመጣው:: እኔም እስኪጠግብ ድረስ ዘፈንኩለት::
ሌላ ጊዜ ደግሞ መድረክ ላይ ሙዚቃ ልናቀርብ መለዮ ልብሴን (የኒፎርም) አጥቤ አስጥቻለሁ:: ነገር ግን ቶሎ ድረሱ የሚል አስቸኳይ መልዕክት ደረሰን:: ስለሆነም እርጥቡን መለያዬን ለብሼ መድረክ ላይ ወጧሁ:: ሰውነቴም ልብሴም ረጥቧል:: ሰው ሊያቅፈኝ እና ሊሸልመኝ ሲጠጋ እኔ ወደ ኋላ እሸሻለሁ:: ክራር ተጯዋቹ ልጅ ደግሞ ወደ ፊት ይገፋኛል:: በዚህ ሁኔታ ሙዚቃውን ሠርቼ ጨረስኩ::
በደርግ ዘመነ መንግሥት ደግሞ ሆያ ሆዬ ጨፍሬ 120 ሺህ ብር ተሸለምኩ:: ያንን ብር ይዤ በደስታ ስጓዝ ጓደኞቼን አገኘኋቸው:: የ60 ብር ምግብ፣ የ60 ብር ጠጅ አዘዝን:: ያኔ ኑሮው እንደ አሁኑ እሳት አልነበረም:: ምግብ እና መጠጡ ለዘጠኘ ሰዎች በቃን:: አንዱ ጓደኛችን ሆዱ ሞልቶ እና ሞቅ ብሎት ተኛ:: ቀስቅሰው “ምን ሆነህ ነው የተኛኸው?” ሲባል “120 ገሎኝ” አለ (ሳቅ):: ከዚያ በኋላ ሙዚቃ ሳቀነቅንም ሆነ በሌላ ጉዳይ 120 እያለ ነበር ሰው የሚጠራኝ:: አሁንም ድረስ ትርጉሙን ባያውቁትም 120 እያሉ ይጠሩኛል::
ሙዚቃ በምን ጠቅሞዎታል?
በገንዘብ ጠቀመኝ ባልልም በሌላ መልኩ ጠቅሞኛል:: በሕይወቴ እንዳልጨናነቅ ያደርገኛል:: በምዘፍንበት ሰዓት አዕምሮዬ ረፍት ያገኛል:: ቤተሰቦቼ እና ጓደኞቼ ስዘፍንላቸው ደስ ይላቸዋል:: ተማሪዎቼ ሲከፋቸው ጭምር ቢሮ ድረስ መጥተው እንዳንጎራጉርላቸው ይጠይቁኛል:: ሰልፍ ላይ የኢትዮጵያ መዝሙርን አስዘምራለሁ:: ይህን የሰው ፍቅር ሙዚቃ ሰጥቶኛል:: እኔም እደሰትበታለሁ::
በአሳለፉት የሙዚቃ ሕይወት ባደርገው ኖሮ ብለው የሚቆጩበት ነገር አለ?
አዎ አለ። ኪነ ጥበብ በጣም ሰፊ ነው:: ወደ ውስጥ እየገባህ ባወቅክ ቁጥር የሚሰማህ ነገር አለ:: ብዙ ሥራዎቼ ዘመናዊ ሙዚቃዎች ናቸው:: የአማራን ሕዝብ ታሪክ እና ባሕል በደንብ አውጥቼ ባለመሥራቴ ይቆጨኛል:: የወሎ ብቻ ሳይሆን የጎጃም፣ የጎንደር እና የሸዋ ባሕል፣ ታሪክ እና ትውፊቶችን ማስተዋወቅ ነበረብኝ እላለሁ:: በተጨማሪ ለአማተር ሙዚቀኞች ከዚህ የበለጠ ዜማ እና ግጥም አለመስጠቴ ይቆጨኛል:: ወደፊት ከላይ ባነሳኋቸው ጉዳዮች ላይ በሰፊው ለመሥራት አቅጃለሁ::
የሙዚቃ ሥራ አልፊ ነው። በአንድ ጊዜ ወደ ላይ መውጣት እጅግ ከባድ ነው:: እኔ በበኩሌ በጣም ለፍቻለሁ:: በዚህ ልፋት ውስጥ ገንዘብ ማግኘቴ ለእኔ ምንም ፋይዳ የለውም። ዝምድናዬ ከገንዘቡ ጋር አይደለም:: አማተር ድምጻዊያን ብዙ መልፋት አለባቸው:: በሙዚቃ ሁሌም ትማራለህ። አለቀ ተብሎ የሚቆም ነገር አይደለም። ዘመኑም፣ ቴክኖሎጂውም አጋዥ ነው። በርትቶ ከሠሩበት ውጤታማ መሆን ይቻላል:: መርጋት፣ መስከን እና ቁጥብ መሆን ያስፈልጋል::
በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት ሀሳብ ካለ?
በመጀመሪያ ፈጣሪየን አመሰግናለሁ:: በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላሙን አግኝቶ በደስታ እና በፍቅር መኖር እንዲጀምር እመኛለሁ:: የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንንም አመሰግናለሁ::
እናመሰግናለን!
እኔም አመሰግናለሁ!
(ቢኒያም መስፍ)
በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም