“አርሲ አሰላ ከተማ ከምማርበት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ፊት ለፊት ከፍ ካለው ቦታ ላይ ሆስፒታል ነበር:: በኛ ጊዜ የነበሩ የድሮ ነርሶች አለባበሳቸው ፅድት ብሎ ከራሳቸው ላይ ነጭ ኮፍያ አደርገው ስናይ ሁሌ እነሱን እያየን ደስ ሲሊ! ስናድግ እነሱን ብንሆን!” እያልን እንመኝ ነበር በማለት የሕይወት ጉዧቻን ያካፋሉን በነርሲንግ ሙያ በህክምናው እና በማስተማር ዘርፍ ላለፉት 39 ዓመታት ያገለገሉት ሲስተር ቀለሟ ጉልላት ናቸው:: በዚህ እትም የባለሙያዋን የሕይወት ተሞክሮ ልናስነብባችሁ ወደናል::
“ልጅ እያለሁ የጤና ባለሙያዎች አለባበሳቸው፣ ህሙማን ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ ለመርዳት ሲሯሯጡ፣ ከትምህርት ቤታቸው ፊት ለፊት ሲወጡ እና ሲገቡ… ከዋናው መኪና መንገድ ላይ ፊት ለፊት ሆኜ ስመለከት እኔም እንደእነሱ መሆን እመኝ ነበር:: በትክክል ነርስ እሆናለሁ ብዬ ግን አላስብም ነበር ” በማለት የሚናገሩት ሲስትር ቀለሟ በ1974 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት እንዳወቁ ሆስፒታሉ ማስታወቂያ አወጣ:: ዕድሉ ደግሞ ቀጥታ ተወዳድረው ወደ ሙያው እንዲገቡ የሚያስችል ስለነበር ተዘጋጅተው ፈተናውን አለፉ::
“ቤተሰቦቸ ገጠር ስለነበሩ ፈተናውን ተፈትኜ ሳልፍ ወደ ቤተሰቦቼ በመሄድ ነገርኋቸው:: ወላጆቸ የሚያስፈልገኝን ገንዘብ ከብት በመሸጥ ሰጡኝ ፣ ስንቅም ቋጥሬ ወደ ኮሌጅ ገባሁ” በማለት ያስታውሳሉ::
ሲስትር ቀለሟ በወቅቱ ትምህርቱ ሦስት ዓመት የሚፈጅ ቢሆንም በ1977 ዓ.ም በሀገራችን በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን ሆስፒታል የመርዳት ኃላፊነት በመውጣት ስድስት ወር ጨምረው ለመመረቅ በቁ:: ወደ አሰላ ሆስፒተል በመመለስ ምድብ ቦታቸውን እጣ ሲያወጡ በቆጂ ጤና ጣቢያ ደረሳቸው:: ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሲስተር ቀለሟ የልጅነት ህልማቸው ተሳካ::
“በወቅቱ የሥራውን አድካሚት አናውቀውም ነበር:: ዋናው ሥራውን ሰርተን በሙያው ተቀጥሮ ማሕበረሰቡን ለማገልገል ስለሆነ ወደ ሥራ ምንገባው እንደ ዛሬ ወጣቶች ስለክፍያ አንጨነቅም፤ ሰዓት አንሸራርፍም” በማለት ያስታውሳሉ:: የጤና ሙያ ከሌላው የሚለየው ከሕይወት ጋር መኖር እና አለመኖር ጋር የተያያዘ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ብቁ ባለሙያ እንዲሆን በፅሁፍ ተምሮ ጤና ድርጅቶች ላይ በመሄድ በአካል ተመልክቶ ብዙ ፈተናን ተፈትኖ ተግባራዊ የሚደረግ ተግባር እንደሆነ ያነሳሉ::
“አንድ በነርሲንግ ሙያ የተመረቀ ነርስ ብዙ ሃላፊነት አለው:: በሽታ እንዳይከሰት ማህበረሰቡን ማስተማር፣ አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ፣ ቶሎ ቶሎ የቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ መምከርና፣ በሽታ ከተከሰተ ደግሞ ህሙማንን እንደ አባት፣ እንደ እናት፣ እንደ እህትና እንደ ወንድም በማየት ሙሉ ህክምና በመስጠት በቶሎ ከበሽታቸው እንዲድኑና ወደ ቀድሞው ጤንነታቸው እንዲመለሱ ማድረግ… “የባለሞያው ትልቅ አደራ መሆኑን አስገንዝበዋል::
የሰውን ልጅ ያህል ትልቅ ፍጡር በሚቸገርበት ወቅት ማገዝና መረዳት የህሊናም የመንፈስም እርካታ የሚሰጥ ትልቅ ተግባር ነው::
ነርስነት ማንም ሰው የሚመኘው ሙያ መሆን አለበት:: ነርስ መሆን እድለኝነት ነውና መረጋጋት፣ የታመመውን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ከህመሙ እንዲድን ማድረግ፣ የተቸገረውን ከችግሩ እንዲላቀቅ ካልተቻለ ደግሞ የችግሩን መጠን እንዲቀንስ ማድረግ ፣ ጭንቀቱን እና ውጥረቱን ማቃለል…የሚችሉበት ሙያ እንደሆነ ባለሙያዋ ያምናሉ:: አሁን አሁን ግን ይላሉ ሲስተር ቀለሟ የድካሙን ያህል ገንዘብ ስለማይገኝበት ወጣቱ የሚመርጠው አለመሆኑን አንስተዋል::
ሲስተር ቀለሟ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲገጥም ስለሚጠሩ ኑሯቸውም በዛው ጤና ጣቢያ አካባቢ ነው:: ሲስተር ቀለሟ ነርሶች ብዙ ስላልሆኑ ሁለገብ ሁነው የሚሠሩ ሲሆን የመጀመሪያ የሥራ ቦታቸው ግን ምርመራ ክፍል እንደሆነ ያስታውሳሉ::
ባለሙያዋን ስለቤተሰቦቻቸው ሁኔታም ጠይቀናቸው ነበር፤ እርሳቸው እንደሚሉት መጀመሪያ ሥራ በጀመሩበት ቦታ ትዳር መሥርተው ሁለት ልጆች አፍርተዋል:: ከሦስት ዓመት በኋላ በዝውውር በቀድሞ አጠራሩ ክልል ሦስት ሲቋቋም ወደ ፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ተመድበው ሥራ ጀመሩ:: ለሦስት ወር በባለሙያነት ቀጥሎ ደግሞ አጠቃላይ የሆስፒታሉ ባለሙያ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል:: ከዛም ወደ ባሕር ዳር ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ተዘዋወሩ::
“በዝውውር ወደ ፍኖተሰላም ከመምጣቴ በፊት ጳውሎስ ሆስፒታል የማስተማር ስልጠና ወስጄ ስለነበር በባሕር ዳር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመምህርነት ሥራ ጀመርሁ:: ከማስተማር ጎን ለጎን የራሴን አቅም ለማጎልበት በባሕር ዳር ከተማ የግል ኮሌጅ ሲከፈት በግል ከፍዬ በመማር ዲግሪዬን ያዝሁ:: ሳስተምርበት የነበረው ኮሌጅ በግል ለተማረ ዕድገት አንሰጥም በማለቱ ሥራውን ትቼ ወደ አልካን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር በመሆን ገባሁ:: ሦስት ወር እንደሠራሁ ወደ ነበርሁበት የባሕር ዳር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተመለስሁ”በማለት ያስታውሳሉ::
የእርሳቸውንም ሆነ የባለቤታቸውን ቤተሰቦች አብሮ የማስተማር ልምድ ያላቸው ባለሙያዋ፤ አሁን ላይ ያሳደጉትን ጨምሮ ሁለቱ ልጆቻቸው በጤናው ዘርፍ ተሰማርተዋል:: ሥራው ትኩረትን የሚፈልግ፣ ብዙ ጊዜን የሚወስድ እና አድካሚ በመሆኑ ሙያን በገንዘብ ብቻ መለካት እንደማይጋባ ሲስተር ቀለሟ መክረዋል::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም