ከዓለም አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት አምስት በመቶ የሚሆነው በሙስና ምክንያት ይመዘበራል:: እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ከሆነ ዓለም በሙስና ብቻ በየዓመቱ ሁለት ነጥብ ስድስት ትሪሊዮን ዶላር ታጣለች::
በሌላ በኩል “300 ሚሊዮን ዜጎች በዓለም አቀፍ ደረጃ አስቸኳይ ድጋፍን ይሻሉ” ይላል የድርጅቱ መረጃ፤ በብልሹ አሠራር እና ባልተገባ መንገድ ራስን ለመጥቀም የሚደረገው ሌብነት ታዲያ እጅግ አሳሳቢ ነውም ብሏል::
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ጉዳዮች (UNECA) ይፋ እንዳደረገው ደግሞ በአፍሪካ ከ134 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ የዕለት ደራሽ ምግብ ይሻሉ፤ በሙስና ምክንያት ደግሞ በየዓመቱ 88 ነጥብ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር አህጉሪቱ ታጣለች:: ጥናታዊ ጽሁፎች ይፋ በሚደረጉበት ሪሰርች ጌት ላይ የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ደግሞ በአፍሪካ መንግሥታዊ አገልግሎት ከሚሹ አራት ሰዎች አንዱ የእጅ መንሻ ይጠየቃል::
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል እ.አ.አ በ2014 የዓለም ሀገራትን የሙስና ደረጃ ይፋ አድርጓል፤ ደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ሙስና የሚፈጸምባት ሀገር መሆኗን አስቀምጧል፤ ኢትዮጵያም ከ180 ሀገራት በ99ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች::
ኢትዮጵያም ሙስና እና ብልሹ አሠራርን የዕድገቷ ስጋት በማድረግ ለይታለች:: ሙስና በገንዘብ ዝርፊያ ብቻ የሚቆም ሳይሆን የመልካም አስተዳደር እጦት እንዲሰፋ በማድረግ በሕዝብ እና በመንግሽት መካከል መተማመን እንዳይፈጠር የሚያደርግ ነው:: የሕዝብን እና የመንግሥትን ጥቅም የሚጎዳ፣ በማኅበረሰብ ውስጥ የሞራል እና የሥነ ምግባር ውድቀትን በማምጣት ለማኅበራዊ ቀውስ የሚዳርግ፣ ሃብትን የሚያወድም አደገኛ ትግባርም ነው:: ሀገር በሰላም እጦት፣ በፍትሕ መጓደል፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በስደት እና በኢኮኖሚያዊ ብክነት ውስጥ እንድታልፍ ሙስና ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል::
ተጽእኖ ብዙ የሆነውን ሙስና ለመከላከል በየጊዜው የተለያዩ መሪ ሐሳቦች እየተመዘዙ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ይሠራል:: የዘንድሮው የጸረ ሙስና ቀንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ22ኛ፣ በሀገራችን እና በክልላችን ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ ታስቦ ውሏል፤ “ትውልድን በሥነ ምግባር፣ ተቋምን በአሠራር” የሚለው ደግሞ መሪ መልዕክቱ ነው:: መሪ መልዕክቱ ሙስናን (ሌብነት) በዘላቂነት ለማስወገድ ቀዳሚው ጉዳይ የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ መሆኑን አጽንኦት ለመስጠት፣ ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ወላጅ ልጆቹ የራሳቸው ያልሆነን ጥቅም የማይፈልጉ እንዲሆኑ አድርጎ የማሳደግ ግዴታ እንዳለበት ለማመላከት ነው:: ከዚህ ባለፈ ትምህርትን ጨምሮ በተዋረድ የሚገኙ ተቋማት የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታን በልዩ ትኩረት እንዲሠሩበት የቤት ሥራ ለመስጠት ስለመሆኑ ነው የተመላከተው::
ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት አለመስጠት ዋናው የሙስና ምንጭ ነው፤ በመሆኑም ሙስና አድማሱን አስፍቶ ሀገር ወደማትወጣው አዘቅጥ ውስጥ እንዳትገባ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ከእጅ ንክኪ ነጻ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የአማራ ክልል የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል:: የጸረ ሙስና ቀን መሪ መልዕክትም ታዲያ የፍትሐዊ አገልግሎት አሰጣጥን ወሳኝነት ለማሳየት የተመረጠ ነው::
ሙስና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ መንግሥት በተደጋጋሚ አስታውቋል። በዚህ ከቀጠለ ታዲያ የነገዋ ሀገራችን እጅግ የከፋ ችግር ውስጥ ነው የምትገባው።
የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል መረጃ እንደሚያመላክተው ዴንማርክ በዓለም ሙስና በመከላከል፣ በመቀነስ እና ውጤት እንዲመጣ በማድረግ ቀዳሚ ሀገር ናት። የመገናኛ ብዙኃንን ነጻነት በማረጋገጥ ለፍትሕ መስፈን በትጋት እንዲሠሩ ማድረጓ፣ ግልጽነት የሰፈነበት አገልግሎት አሰጣጥ፣ ጥፋት በሚፈጽሙ ማናቸውም ላይ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ በፍትሐዊነት መውሰዷ፣ በአጠቃላይ እጅግ ስልጡን የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ማስፈኗ፣ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው ሥራቸውን ማከናወናቸው ተጠቃሾች ናቸው።
ፊንላንድ ደግሞ ሁለተኛዋ ሀገር ናት። ጠንካራ ማሕበረሰባዊ ትስስር መኖር፣ ሀገሪቱ የምታወጣቸው ሕግጋት ተግባራዊ መደረጋቸው፣ በማንኛውም ነገር ጠንካራ ሕዝባዊ ተሳትፎ መገንባቱ እና ዴንማርክ ውጤት ያስመዘገበችባቸው አሠራሮች በዚህችም ሀገር ተፈጻሚ መደረጋቸው ሀገሪቱ ላይ እጅግ ዝቅተኛ የሆነ ሙስና እንዲኖር አድርጓል::
በሌላ በኩል ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶሪያ እና የመን በቅደም ተከተል ሙስና በእጅጉ የተስፋፋባቸው ሀገራት (በቅደም ተከተል) መሆናቸውን ነው ድርጅቱ ያስታወቀው። ደካማ የመንግሥት ሥርዓት መኖር፣ የፖለቲካ ብልሽት፣ የተቋማት ደካማ መሆን፣ የውጭ እርዳታ ላይ ጥገኛ መሆን፣ የርስ በርስ ጦርነት መኖር፣ ግጭት እና መሰል ችግሮች ደግሞ ሀገራቱ ሙስና እንዲስፋፋባቸው ያደረጉ ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው።
የ188 ሀገራትን የሙስና ደረጃ ያስቀመጠው ድርጅቱ ኢትዮጵያን 99ኛ ላይ አስቀምጧታል። ይህም ሙስና ስለመስፋፋቱ ማሳያ ነው። መንግሥትም አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን በተደጋጋሚ አስታውቋል። ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን ለመዋጋት እየሠራ መሆኑንም ነው የገለጸው። ለዚህም አሠራርን በቴክኖሎጂ ማዘመን እንደሚገባ ይታመናል:: የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ደግሞ ሙስናን ከሥሩ በማድረቅ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ጤናማ ግንኙነት ለመፍጠር ዋና መፍትሔ ሆኖ ተግባራዊ እየተደረገ ነው::
የአማራ ክልል የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ዓለም አቀፉን የጸረ ሙስና ቀን በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ዝግጅቶች ሲያከብር ቆይቶ ማጠቃለያውን ከመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሠራተኞች ጋር አክብሯል። የክልሉ ፍትሕ ቢሮም የሙስና ቀንን በማስመልከት ከሠራተኞቹ ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ሙስና በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት አሳሳቢ እና ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን አስታውቋል::
በቢሮው የጸረ ሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የክትትል ዐቃቤ ሕግ ፈቃዴ ምሥጋናው በ2017 ዓ.ም ሙስናን አስቀድሞ ለመከላከል በተሠራ ሥራ 16 ቢሊዮን የሚገመት ሃብት ማዳን እንደተቻለ ተናግረዋል:: ያለ አግባብ ሊመዘበር የነበረን ከ132 ሚሊዮን ብር በላይ የሕዝብ ሃብት ማዳን መቻሉንም አስታውቀዋል:: 12 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር ወደ መንግሥት ካዝና እንዲመለስ (ተዘርፎ የነበረ) መደረጉንም ገልጸዋል:: እነዚህ አኃዞች ሙስና አሁንም ፈታናኝ መሆኑን እና በከፍተኛ ደረጃ መታገል እንደሚገባ የሚያሳዩ ስለመሆናቸው ነው ያመላከቱት::
የአማራ ክልል የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ የሥነ ምግባር መጓደል እና ብልሹ አሠራር የሙስና ዋና ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል:: ሙስና በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ከተጽዕኖው ለመውጣት ትውልድ ላይ ሥነ ምግባር ግንባታ እና የመንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጎ መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ የተቋም ሪፎርም ትኩረት እንደተሰጠው የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትንም በመልካም ጅምርነቱ አንስተዋል። የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ተገልጋዩ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኝ ከማድረግ ባለፈ ብልሹ አሠራሮችን በማስወገድ ሙስናን ለመቀነስ ከፍ ያለ ፋይዳ እንደሚኖረው ነው ያስታወቁት። ብልሹ አሠራሮችን ሙሉ ለሙሉ በማስወገድ ተቋማት ለሕዝብ እንዲሰጡ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ሁሉም ተቋማት የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሠራርን መተግበር እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል።
ሕዝቡ ቀደሞ የነበረውን የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ አሁንም አጠናክሮ እንዲያስቀጥል፣ ብልሹ አሠራርን እና ሙስናን ለመታገልም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል:: በሥነ ምግባር ያልታነጸ ትውልድ ሀገርን ለመረከብ እና ዕድገትን ለማረጋገጥ አይችልም ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ለዚህ መሻሻል ደግሞ ሁሉም ኃላፊነት አለበት ነው ያሉት። በየደረጃው ለትውልድ ስነ ምግባር ግንባታ እና ሙስናን በመከላከል ተቋማት ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና ሰው ኃብት ልማት ኮሚሽንም የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን እስከ ገጠር ለማስፋት በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል:: የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ባንቺዓምላክ ገብረማርያም እስካሁን እንደ ክልሉ የተጀመረውን ጨምሮ ባሕር ዳር እና ደሴ ከተሞች የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታቸውን አጠናቀው ለሕዝብ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል:: የጎንደር ከተማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በግንባታ ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል::
በቀጣይም በደብረ ብርሐን፣ ኮምቦልቻ፣ ወልዲያ፣ ደብረ ማርቆስ እና ደብረታቦር ለማስፋት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል:: በአንድ ከተማ አንድ ማዕከል ዕቅድ መውረዱን የተናገሩት ኮሚሽነሯ በዚህም 24 ከተሞች መንግሥታዊ አገልግሎትን በአንድ ማዕከል እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል:: በጊዜ ሂደትም የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በክፍለ ከተሞች እና በገጠር ለማስፋት ይሠራል ብለዋል::
የተቋም ግንባታ በሀገረ መንግሥት ምሥረታ ላይ የጎላ ተጽዕኖ እንዳለው ያነሱት ኮሚሽነሯ፣ ተቋማትን መገንባት እና አሠራርን ማዘመን ሲቻል አገልግሎት እየተሻሻለ ይሄዳል ነው ያሉት:: በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ሁሉም በግልጽ በእኩልነት የሚስተናገድበት ተቋም መሆኑን ገልጸዋል:: ይህም ሙስናን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ዋነኛ መፍትሄ እንደሚሆን ነው የገለጹት::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የታህሣስ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


