ሚዛናዊ መረጃ በማድረስ ኃላፊነታችንን እንወጣ !

0
13

በዚህ ዘመን ሚዲያ ከማሳወቅ፣ መረጃ ከመስጠት፣ ከማስተማርና ከማዝናናት ያለፈ ድርብ ተግባር አለው፡፡

በተለይም እንደአሁኑ ዓይነት ዓለምን እለት ተእለት ችግርና ቀውስ በማያጣት በዚህ ጊዜ ሚዲያ በየሰዓቱ ነገርን የማርገብና የማሳወቅ ሚናው የጎላ ነው፡፡ በተለይም ለአድማጭ ተመልካች እንዲሁም ለአንባቢ መጀመሪያ አዝማሚያውን ከዚያ አለፍ ሲልም መከላከያውን በመናገርና በማሳወቅ ሚዲያ  ሀገርን ከመፍረስ  የማዳን ስራ ይሰራል፡፡

በተለይም እንዲህ የማህበራዊ ሚዲያ በየሰዓቱ መረጃን ሳያጣራና ኃላፊነት በጎደለው መንገድ መልካሙን ከመጥፎው በእኩል ማዕድ በሚያቀርብበት ዘመን የሚዲያ ሚና እጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡

መረጃ የመስጠት እሽቅድድም ውስጥ ባለ ማህበራዊ ሚዲያ መካከል ነገርን አጥርቶና ከሁነኛ መረጃ ሰጭ አገናዝቦ ለመስጠት ፋታ አይሰጥ ይሆናል፡፡ መረጃን ሳያጣሩ እኔ እቀድም እቀድም ሩጫ ውስጥ መረጃን ማድረስ አድካሚና አስቸጋሪ  ቢሆንም ማህበራዊ ኃላፊነትን በአግባቡ የሚወጣ ሚዲያን መገንባት አዋጭና ተመራጭ ነው፡፡

አንዱን በአንዱ ላይ እንዲነሳ የሚያደርግና ነገርን በማባባስ ግጭትን ከማስፋፋት ይልቅ ለችግሮች መውጫ መንገድ የሚሆንና መፍትሔ አመላካች ዘገባዎችን በመስራት ሀገርን ከግጭት ማውጣት የሚያስችል የሚዲያ ግንባታ ውስጥ መግባት እንደሀገር ትርፉ ብዙ ነው፡፡

በተለይም በቀውስ ወቅት ያለ ሚዲያ የሰላም ጋዜጠኝነትን በመጠቀም ሁለቱንም ወገን አሸናፊ የሚያደርግ አዘጋገብን መሰረት ያደረገ፣ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ የሚችልና ሁሌም ወገንተኝነቱ ከእውነትና ከህዝብ ጋር መሆን አለበት፡፡

እንደሚዲያ መረጃን ከመስጠት ባለፈ ሚዲያን በትክክል የሚጠቀም እና ማኅበራዊ ኃላፊነት የሚሰማው ህዝብ መፍጠር ላይም የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት፡፡ ቀውስ በተፈጠረ ጊዜ ቀውሱ ተባብሶ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ ቀድሞ በውይይት እንዲፈታ መውጫ መንገዶችን መጠቆምና ነገርን ማብረድ ላይ በመስራት ሚዛናዊና ምክንያታዊ የሆነ ማህበረሰብ እንዲፈጠርም በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ ሚዲያ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

የሚዲያ ሚና የታየውን ሁሉ መዘገብ ሳይሆን ለልጇ ጤንነትና ለልጇ ጉሮሮ  መጥና እንደምታጎርስና በልጇ እድጉት ላይ ኃላፊነት እንዳለባት እናት መጥኖ የመስጠትና አጣርቶ የማቅረብ ግዴታና ማህባራዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንን በማድረግ መረጃ ያለው እና ኃላፊነት የሚሰማው ህብረተሰብ መፍጠር ይቻላል፡፡

አሚኮም ባለፉት 30 ዓመታት ሚዛናዊ መረጃ በመስጠት፤ ውይይት፣ ንግግርና እርቅ የችግር መፍቻ መንገድ እንዲሆን በትጋት ሰርቷል፡፡ በችግር ወቅት ትክክለኛ መረጃን ከቦታዉ በማድረስ ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ የሰከነ፤ ከስሜታዊነት ይልቅ ምክንያታዊ የሆነ፤ መረጃን በኃላፊነት የሚጠቀም ታላሚ አድማጭ፣ ተመልካች እንዲሁም አንባቢን በመፍር ሚናው የጎላ ነበር፡፡ በቀጣይም ይህንኑ ተግባር ማስቀጠል ጠበቅበታል።

በኲር የነሐሴ 26  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here