ማህበራዊ መገናኛዎች እና ልጆች

0
38

ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ጤና እና ትምህርት እንዴት ነው? ልጆች የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ትጠቀማላችሁ? ልጆች፣ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ገደብ ሊደረግበት እንደሚገባ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይመክራሉ። የሁለንተናዊ ልጆች እድገት ባለሙያ እና የ”Child Development Network” መስራች አቶ ብርሃኑ በላቸው የልጆች የዲጂታል መሳሪያዎቸና ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በወላጅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ይላሉ፡፡

ልጆችዬ ምንም እንኳ በሀገራችን በቂ ጥናቶች ባይኖሩም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጉዳዩ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ነው፡፡ በተለይም የዲጂታል መሳሪያዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ልጆች በዕድገት ሂደታቸው ከአካባቢያቸው ጋር ከሚያደርጉት ትውውቅ ጋር የተጣጣመ እና የተገደበ መሆን ይገባዋል ይላሉ የስነልቦና ባለሙያው። ዓለምአቀፍ ተሞክሮዎችን እና የህፃናት አስተዳደግ ሳይንስ ዋቢ በማድረግ በተለይም በጉርምስና መጀመሪያ ዓመታት ላይ ያልተገደበ የመረጃ እና የማህበራዊ ሚዲያ እንዲጠቀሙ ተጋላጭ ከሆኑ ከፍተኛ የሆነ ስነልቦናዊ እና ማህበራዊ ችግር ያስከትላል።

በጉርምስና ወቅት፣ ልጆች እንደ ታይታ፣ ትኩረት እና ከእኩዮቻቸው አዎንታዊ ግብረመልሶችን የመሳሰሉ ማህበራዊ ግብረ መልሶችን መፈለግ የሚጀምሩበት ወቅት በመሆኑ፣ ለአላስፈላጊ ተፅዕኖ እንዳይወድቁ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ባለሙው መክረዋል፡፡

ባህሪን ለመግታት እና ፈተናዎችን ለመቋቋም እንዲያስችል እገዛ የሚያደርገው የአንጎል ክፍል (frontal cortex) እስከ ጉርምስና ዕድሜ ድረስ ሙሉ በሙሉ ስለማይዳብር፣ ህጻናት ማህበራዊ ሚዲያዎችን ከመጠን በላይ ከመጠቀም ራሳቸውን የመግታት ችሎታ ላይኖራቸው እንደሚችል አስረድተዋል። ይህም ላልተገደበ እና ወደ ሱስ ደረጃ የደረሰ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ስለሚያመራ ለጭንቀት ተጋላጭነትን ይጨምራል፤ ብዙ ወጣቶች ማህበራዊ ሚዲያን ካሰቡት በላይ እንደሚጠቀሙ እና አጠቃቀሙን ለማስቆም እንደሚቸገሩም በጥናቶች ተረጋግጧል።

አዕምሯችን የሚዳብረው ለምንኖርበት አካባቢ ምላሽ በመስጠት በመሆኑ ወጣቶች ቢሆኑም እንኳ ለቴክኖሎጂ እና ለማህበራዊ ሚዲያ ያላቸው ስነ ህይወታዊ ተጋላጭነት እና በነዚህ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ መጠቀማቸው የወጣቶችን የነርቭ እድገት የመቀየር አቅም አለው ብለዋል ።

ጥናቶች እንደሚገልፁት ወጣቶች የተዘበራረቀ አመጋገብ፣ ራስን የመጉዳት እና ድባቴ፣ ከመጠን ያለፈ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እና ሌሎች ጎጂ ባህሪዎችን ከችግሩ ጋር ተያይዘው የሚመጡ አደጋዎች ናቸው። በማህበራዊ ሚዲያ ውስጥ የሚታዩ አንዳንድ ባህሪያት እና ይዘቶች እንዲሁም የተጠቃሚዎች ባህሪ እንዴት ልጆቻችንን በመልካምም ሆነ በመጥፎ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እንደሚችል የታየ በመሆኑ፣ ህጻናት ማህበራዊ ሚዲያ መጠቀም የጀመሩበት ዕድሜ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ በይዘትም ሆነ በድግግሞሽ ደረጃ የወላጅና አሳዳጊ ቁጥጥር ያስፈልጋል።

ተረት

መምህሩ እና ደቀመዝሙሩ

የአንድ ቅኔ ት/ቤት ተማሪዎች ቅኔ የሚዘርፉበት እለት ነው:: ከየደብሩ፣ ከየቅኔ ትምህርት ቤት ሁሉ አንቱ የተባሉ ሊቆች ተጠርተው መጥተዋል:: ተማሪዎቹ ምን ያህል እንደተማሩና እንደረቀቁ ለማዳመጥና ለመመዘን፣ እግረ-መንገዳቸውንም የነሱ ዘመነኛ የሆኑ የቅኔ መምህር፣ ምን ያህል እንዳስተማሩ በማየት ከራሳቸው ጋር ሊያነጻጽሩ ነው:: በተማሪዎቹ መካከል ፉክክር እንዳለ ሁሉ፣ በመምህራኑም መካከል የእኔ እሻል እኔ እሻል ውድድር አለ:: በጥንቱ የቅኔ ትምህርት ይትባህል፣ አለቃ እገሌ ዘንድ የተማረ፣ መምህር እገሌ ዘንድ ቅኔ እየዘረፈ መባል ብዙ ስምና ክብር አለው::

ከተማሪዎች መካከል አንድ ሃይለኛ ተማሪ አለ:: መምህሩ ሳይቀሩ ይፈሩታል:: ታዲያ የዚያን ዕለት መምህሩ በበኩላቸው ችሎታቸውን ለማሳየት ያህል ቅኔውን ሲዘርፉት፣ አንድ ላላ ተደርጎ ሳይረገጥ መነበብ ያለበትን “ታምረሃ” (የተዓምር ድርጊት) የሚል ቃል የኔታ እርግጥ አድርገው “ታምረሃ” ብለው ያነባሉ:: ይሄኔ ያ ጎበዝ ተማሪ “የኔታ ልመልስልዎት” ይላቸዋል:: የኔታ አፍረውም ተናደውም ቢሆን ምሬታቸውን ዋጥ አድርገው ሲያበቁ፤ “እሺ የእኔ ልጅ፣ መልሰኝ” አሉ:: “ታምረሃ” አይጠብቅም ያላሉት:: ይላቸዋል:: የኔታም አላልተው በድጋሚ ይሉታል::

በነዚያ ሁሉ ታዋቂ መምህራን ፊት ተማሪያቸው ስህተት ስላገኘባቸው በጣም ተናደዋል::

ስነ-ሥርዓቱ ሁሉ አለቀና እንግዶቹ ሁሉ ተሸኙ:: የየኔታ ቤት አፋፍ ላይ ነው:: የጎበዙ ተማሪ ቤት ታች ሜዳው ላይ ነው:: ለተማሪው የየኔታ ቤት ቁልጭ ብሎ ካፋፍ ይታየዋል:: የኔታ ማለዳ ተነስተው እደጃቸው ካለው የወይራ ዛፍ ቅርንጫፍ ቆርጠው አርጩሜ መልምለው፣ በጋቢያቸው ሸፍነው ቁልቁል ሲወርዱ ተሜ ያስተውላቸዋል::

ት/ቤት እንደተለመደው የኔታ፣ ተማሪዎቹ ቅኔ እንዲዘርፉ ሲመሩ፣ ሳያውቁ ያሉት አስመስለው የትናንትናውን “ታምረሃ” የሚል ስህተት በመድገም ተረግጠው አነበቡት:: ተሜ ግን እንደ ትላንቱ “ልመልስዎት” ሳይላቸው ጭጭ አለ:: የኔታ ትንሽ እንደ መናደድ ብለው፣ አሁንም ያችን “ታምረሃ” ረገጥ አድርገው ተናገሯት:: ተሜ አሁንም ጭጭ፣ የኔታ በጣም ተናደዱ፤ ጮክ ብለው፤ በጣም ረግጠው “ታምረሃ!” አሉ:: ተሜ አቀርቅሮ እረጭ:: የኔታ ትዕግስታቸውን ጨርሰው፤

“አንተ አትመልሰኝም እንዴ?” ሲሉ ጠየቁት በጋለ-ቃል::

ተማሪው ሲመልስ፤

“አይ የኔታ፣ ይቺ እንኳ ውስጠ-ወይራ ናት” አላቸው:: ውስጠ ወይራ የተደበቀ ሚስጥር ማለት ሲሆን ተሜ ማለት የፈለገው በቀጥታ የተደበቀች ዱላ አለች ነው:: ውስጠ-ወይራ ታሪካዊ አመጣጧ ይሄ ነው::

ይሞክሩ

ልጅቱ የእግር ኳሷን በመምታት አምስት ሜትር ያህል ብታርቀውም ኳሱ ግን ተመልሶ ወደ እርሷ መጣ፤ እንዴት?

ዝሆንን በአንድ እጅ ማንሳት የሚቻለው እንዴት ነው?

አስራ ሁለት አሶች ነበሩኝ፤ ግማሾቹ ቢሰምጡ ስንት ይቀረኛል?

መልስ

ኳሱን ወደላይ ስለመታችው በመሬት ስበት ምክንያት ተመልሷል::

በወረቀት ላይ የዝሆን ስዕል በመሳል::

12፤ ምክንያቱም አሳ አይሰምጥም::

 

ነገር በምሳሌ

ሁለት የተመኘ፣ አንድም አላገኘ

ይህንንም ያንንም መመኘት ውጤቱ አያምርም::

 

ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ :-

ራስ ወዳድ መሆንን ያመለክታል::

 

መስጠት ቤት አይፈታም፡መርዳት ችግር አያመጣም፡፡

 

      

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here