የግብርና ግብዓትን እያሳራጩ መሆኑን የሕብረት ሥራ ማሕበራት አስታውቀዋል። በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የአድማስ ሁለገብ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማሕበራት ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ መሠረት ወርቄ እንደገለፁት በ2016/2017 የምርት ዘመን የግብዓት ስርጭት ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርስ ወደ ተግባር ተገብቷል። ለምርት ዘመኑ የሚያገለግል ከ842 ሺህ በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዩኒየኑ ለማስገባት በዕቅድ መያዙን ለበኩር ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥም (ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ) 58 በመቶ ያህሉ ወደ አድማስ ሁለገብ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማሕበራት ዩኒየን ማዕከላዊ መጋዝን እንደገባ አስታውቀዋል:: 163 ሺህ ያህል ኩንታል የአፈር ማዳበሪያም ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን አስረድተዋል::
የተፈጠረው ወቅታዊ የፀጥታ መደፍረስ በአንዳንድ አካባቢዎች ስርጭቱን ለማከናወን እንቅፋት እየፈጠረ ቢሆንም አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም ለአርሶ አደሩ የሚደርስበት መንገድ እየተመቻቸ ነው ብለዋል:: ሰላማዊ በሆኑ አካባቢዎች ግብዓት በበቂ ሁኔታ መሰራጨቱንም አክለዋል::
አርሶ አደሩ ለመስኖ ዘር በቂ የአፈር ማዳበሪያ ወስዶ እየዘራ መሆኑን የገለፁት አቶ መሠረት በአሁኑ ወቅትም ለቦቆሎ እና ለድንች ዘር ግብዓት እየወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል::
እንደ አቶ መሠረት ማብራሪያ የገባውን የአፈር ማዳበሪያ አርሶ አደሩ በፈለገው መጠን እና በፍትሃዊ መንገድ ለማሰራጨት እየተሰራ ነው። ዩኒየኑ ግብዓትን ከማቅረብ ባሻገር የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት 56 ሺህ ኩንታል ቦቆሎ ገዝቶ ለማሕበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማድረስ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል::
ሌላው ሐሳባቸውን ለበኩር የሰጡት የሰሜን ሸዋ ዞን ሕብረት ሥራ ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ባዬ ከበደ እንዳሉት በዞኑ በምርት ዘመኑ ከአንድ ሚሊዮን ስድስት ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማስገባት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። እስካሁንም ከ472 ሺህ በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መግባቱን ተናግረዋል:: ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከ150 ሺህ በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን አስታውቀዋል::
በተመሳሳይ 28 ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር ለመግዛት ታቅዶ እስካሁን 12 ሺህ 500 ያህል ኩንታል ግዥ መፈፀሙን ገልፀዋል::
በዞኑ በአንዳንድ አካባቢዎች ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ግብዓት ለማድረስ መቸገራቸውን ተናግረዋል። ለአብነትም በዞኑ የሚገኘው መንዝ ዩኒየን ግብዓት እንዳልደረሰዉ አንስተዋል። ችግሩን ለማቃለልም ከወደራ ዩኒየን በማዘዋወር እየተሠራ ነው ብለዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም