ማሩከስ

0
99

በሰሜን አፍሪካ በማግሬብ ክልል ውስጥ የምትገኝ ሀገር ናት። በሰሜን በሜዲትራኒያን ባሕር እና በምዕራብ የአትላንቲክ ውቅያኖስ የባህር ዳርቻዎች እንዲሁም  በምስራቅ ከአልጄሪያ ጋር የመሬት ድንበሮችን ትዋሰናለች፤ በደቡብ በኩል ደግሞ አወዛጋቢው የምእራብ ሳሃራ ግዛት አላት። ሞሮኮ የስፔን ሴኡታ፣ ሜሊላ እና ፔኖን ዴ ቬሌዝ ዴ ላ ጎሜራ እና በርካታ ትናንሽ በስፔን ቁጥጥር ስር ያሉ ደሴቶችን ይገባኛል ትጠይቃለች። ሞሮኮ ሚለው ስያሜ በስፔኖች ያገኘችው ነው፤ ከዚያ በፊት በአልሞራቪድ ሥርወ መንግሥት ጊዜ ዋና ከተማ በነበረችው ማራኬሽ በተወሰደው ማሩከስ በሚል ስያሜ ነበር የምትጠራው፡፡

 

ሞሮኮ ወደ 37 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ አላት፤ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷም 168 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡። እስልምና ይፋዊ እና ዋነኛው ሀይማኖት ሲሆን አረብኛ እና በርበር ኦፊሴላዊ ቋንቋዎቿ ናቸው። በተጨማሪም ፈረንሳይኛ እና የሞሮኮ የአረብኛ ቀበልኛ በሰፊው ይነገራል። የሞሮኮ ባህል የአረብ፣ የበርበር፣ የአፍሪካ እና የአውሮፓ ባህሎች ድብልቅ ነው:: ዋና ከተማዋ ራባት ስትሆን ትልቁ ከተማዋ ካዛብላንካ ናት።

 

ሞሮኮ በ15ኛው እና በ16ኛው ክፍለ ዘመን በፖርቱጋል እና ኦቶማን ቱርክ፣ በኋላ ደግሞ በፈረንሳይ እና በስፔን ቅኝ ግዛት ስር ቆይታለች፡፡ በ1956 እ.አ.አ ነጻ ወጥታለች፡፡ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ በአንጻራዊ ሁኔታ የተረጋጋች ሆና ቆይታለች። በአፍሪካ አምስተኛ ትልቅ ኢኮኖሚ ያላት ሲሆን በአፍሪካም ሆነ በአረቡ ዓለም ከፍተኛ ተጽዕኖ የምታሳድር ሀገር ናት፡፡ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች መካከለኛ የኃይል ሚዛን አላት። በአረብ ሊግ፣ በአረብ ማግሬብ ህብረት፣ በሜዲትራኒያን ባሕር እና በአፍሪካ ህብረትም አባል ናት።

 

ሞሮኮ የተመረጠ የፓርላማ አሃዳዊ ከፊል ህገ-መንግሥታዊ ንጉሣዊ አገዛዝ አላት። የስራ አስፈፃሚው አካል በሞሮኮ ንጉሥ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ነው። የህግ አውጭነት ስልጣን የተሰጠው ለሁለቱ የፓርላማ ምክር ቤቶች ማለትም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለምክር ቤት አባላት ነው። የዳኝነት ስልጣን የሕጎችን፣ ምርጫዎችን እና ሕዝበ ውሳኔዎችን ትክክለኛነት የሚገመግም ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ነው። ንጉሡ በተለይም በወታደራዊ፣ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ሰፊ የአስፈጻሚነት እና የሕግ አውጭነት ስልጣን አላቸው።

 

የሞሮኮ አብዛኛው  ክፍል ተራራማ ነው። የአትላስ ተራሮች በዋነኛነት በሀገሪቱ መሃል እና በደቡብ ይገኛሉ። የሪፍ ተራራዎች በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ይገኛሉ፡፡ በሁለቱም ክልሎች በዋናነት የሚኖሩት የበርበር ሰዎች ናቸው። አልጄሪያ ሞሮኮን በምስራቅ እና በደቡብ ምስራቅ ትዋሰናለች። ይሁን እንጂ  የሁለቱ ሀገራት ድንበር ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ተዘግቷል፡፡ የሞሮኮ ዋና ከተማ ራባት ከኦውድ ቡ ሬግ ወንዝ አጠገብ  ትገኛለች። ትልቁ ከተማዋ እና ዋናው ወደብ ካዛብላንካ ነው።

 

በሰሜናዊ እና በማዕከላዊ ተራሮች ከሚገኙ ለምለም ደኖች አንስቶ፣ በምስራቅ እና በደቡብ ክልሎች ውስጥ ከፊል ደረቃማ እንዲሁም በረሃማ አካባቢዎች የሞሮኮ የተለዩ የአየር ንብረት መገለጫዎች ናቸው። የሞሮኮ የባህር ዳርቻ ሜዳዎች በበጋ ወቅት መጠነኛ የሙቀት መጠን ያጋጥማቸዋል።

በሞሮኮ ኢኮኖሚ ውስጥ ቱሪዝም በጣም ወሳኝ ከሆኑት ዘርፎች አንዱ ነው። በሀገሪቱ የባሕር ዳርቻ፣ ባሕል እና ታሪክ ላይ ያተኮረ ጠንካራ የቱሪስት ኢንዱስትሪ አላት። በ2023 14 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎች ጎብኝተዋታል። እ.አ.አ 2024 ሞሮኮ  በ16 ሚሊዮን  ሰዎች የተጎበኘች ሲሆን ይህም ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ሰባት በመቶ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

 

የቱሪዝም ዘርፉ በሞሮኮ በጥንታዊ ከተሞቿ እና ባሕሏ ላይ ያተኮረነው። ዘመናዊው የቱሪስት ኢንዱስትሪ በሞሮኮ ጥንታዊ እና እስላማዊ ቦታዎች እና በመልክአ ምድሩ እና በባህላዊ ታሪኩ ላይ መሰረት አድረጓል። 60 በመቶ የሞሮኮ ቱሪስቶች ለባህሏ እና ለቅርሶቿ ሲሉ ይጎበኟታል። አጋዲር ዋና የባሕር ዳርቻ ሪዞርት ሲሆን ምቹ ማፊያዎች አሉት። የአትላስ ተራሮችን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ዋና ማረፊያቸው ያደርጉታል፡፡። በሰሜን ሞሮኮ ውስጥ ያሉ ሌሎች ሪዞርቶችም በጣም ተወዳጅ ናቸው።

 

ለጎብኝዎች በመንግሥት ድጎማ የሚሰጣቸው እና ዋጋቸው ውድ ያልሆኑ ቁሳቁሶች የሚሸጡባቸው ትላልቅ ገበያዎች አሉ፡፡ ይህም በርካሽ ዋጋ ቅንጡ እቃዎችን መግዛት ስለሚያስችላቸው ጎብኝዎች ሞሮኮን ይመርጧታል፡፡ ደህንነታቸውም የተጠበቀ በመሆኑ ከስጋት ነጻ ናቸው፡፡

አብዛኛዎቹ የሞሮኮ ጎብኚዎች አውሮፓውያን ናቸው፡፡ የፈረንሳይ ዜጎች ከሁሉም ጎብኝዎች 20 በመቶ ድርሻ ይይዛሉ። አብዛኛዎቹ አውሮፓውያን ሞሮኮን በሚያዚያ እና በነሐሴ መካከል ይጎበኛሉ። ካዛብላንካ በሞሮኮ ውስጥ ዋና የሽርሽር ወደብ ነው።

 

በማራኬች የሚገኘው የሜጆሬል እፅዋት የአትክልት ስፍራ ታዋቂ የቱሪስት መስህብ ነው። በ1980 እ.አ.አ በፋሽን ዲዛይነር ኢቭ ሴንት ሎረንት እና ፒየር በርጌ ከመንግሥት የተገዛ ነው። እ.አ.አ. ከ2006 ጀምሮ በአትላስ እና ሪፍ ተራሮች ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ እና የጀብዱ (አድቬንቸር- ለአብንት እንደ አደን)  በሞሮኮ ቱሪዝም ፈጣን የእድገት አሳይቷል። እነዚህ ቦታዎች ከመጋቢት መጨረሻ እስከ ህዳር አጋማሽ ድረስ የእግር ጉዞ ጉብኝቶች አሏቸው። መንግሥት የጫካ ላይ ረጅም ጉዞዎችን ወይም ሀይኪንግ ላይ መዋለ ንዋይ እያፈሰሰ ነው። ከቱኒዚያ ጋር በመወዳደር የበረሃ ቱሪዝምን በማልማት ላይ ይገኛል።

 

ጌት ዮር ጋይድ የተሰኘው ድረ ገጽ በሞሮኮ አሉ  ያላቸውን አስር ነገሮች አስቀምጧል፡፡ የመጀመሪያው በማራካች አቅራቢያ ባለው የሙቅ አየር ፊኛ በረራ ላይ በአትላስ ተራሮች አስደናቂ እይታዎች ይደነቃሉ። በበርበር ሰዎች ባሕላዊ ቁርስ ይደሰታሉ፡፡ የመታሰቢያ የበረራ ሰርተፍኬት ይሰጣሉ፡፡ በጭራሽ የማይረሳ ጠዋት ያሳልፋሉ ይላል ዘገባው።

በሁለተኛ ደረጃ ማራኬክ የኡዙድ ፏፏቴዎች ሲሆኑ ድንቅ የጎብኝ መዳረሻ ናቸው። ጉብኝቱ የእግር ጉዞ እና ፏፏቴዎቹን በቅርብ ሆኖ ማድነቅ እና የጀልባ ጉዞን ያካተተ ነው።

 

ሦስተኛው የአጋፋይ በረሃ ሲሆን የተለያዩ አስደሳች ኩነቶችን ለጎብኝዎች ያቀርባል! ኳድ (ባለአራት እግር ሞተር ሳይክል ግልቢያ፣ ጀንበር ስትጠልቅ የግመል ግልቢያ፣ እና ከዋክብት በታች ባህላዊ የሞሮኮ እራት ጎብኝዎች ያጣጥማሉ። ምሽቱን በማይረሳ የእሳት ዳር ትርኢት ያጠናቅቃሉ፡፡

የአትላስ ተራሮች፣ የኦሪካ መንድር የሦስት ቀናት ጉብኝት፣ የሳህራ በረሃ ጉዞ፣ የሜርዙጋ በረሃ ጉብኝት እና ምግቦች፣ የሀሰን ሁለተኛ ጥንታዊ መስጊድ፣ የበርበር ሙዚየም፣የኦርዛዛት እና አይት ቤንሀዱ ጥንታዊ መንደሮች እና ስነ ሕንጻ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጎብኝዎችን የሚያሳትፉ መዳረሻዎች ናቸው፡፡

 

ከዋና ዋና የጎብኝዎች መዳረሻዎች በተጨማሪ ፌስ፣ አሳውራ፣ ታንጊር፣ አርሳውድ እና ሌሎች ከተሞች በቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ጎብኝዎች የሚያስተናግዱ ናቸው፡፡ ጎብኝዎችም ተመላልሰው ይጎበኟቸዋል፡፡

 

(ቢኒያም መስፍን)

 

በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here