የዘጠና ሁለቱ ዓመቱ የእድሜ ባለፀጋ 42 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የሮም ማራቶን ለ30ኛ ጊዜ ሮጠው ባለፈው ዓመት ካስመዘገቡት ሰዓት አስር ደቂቃ በማሻሻል ማጠናቀቃቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
ጣሊያናዊው አንቶኒዮ ራኦ በ1933 እ.አ.አ ከሮም ወጣ ባለች ካለባሪ በተሰኘች ከተማ ነው የተወለዱት፡፡ እድሜያቸው 10 ዓመት ከሞላቸው ጀምሮም መኖሪያቸውን በሮም አድርገዋል፡፡ ከታዳጊ ጓደኞቻቸው ጋር በመወዳደር የጀመሩት የማራቶን ሩጫም የህይወታቸው አንድ አካል ሆኖ ሰላሳ ዓመታት መዝለቁን ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡
አንቶኒዮ ራኦ ባለፉት 30 ተከታታይ የሮም ማራቶን ተሳትፈዋል፡፡ በውጤቱም ከሰባት ሰዓት በታች በመጨረሳቸው በሳቸው እድሜ ላይ ለሚገኝ ሰው አስደናቂ መሆኑን ነው የገለፀው ድረ ገጹ፡፡
የአንቶኒዮ ራኦ ከፍተኛ ስኬት ሆኖ የተመዘገበው በ2023 እ.አ.አ የተካሄደው የማራቶን ውድድር ነበር፡፡ በሳቸው የእድሜ ምድብ ማለትም ከ90 ዓመት በላይ ከሆናቸው አዛውንቶች ቀድመው በስድስት ሰዓት ከ14 ደቂቃ፣ 16 ሰከንድ በመጨረስ ክብረ ወሰን አሻሽለው አጠናቀዋል፡፡
ይህም 30ኛ ተከታታይ የሮም ማራቶን ተሳትፏቸው መሆኑንም ልብ ይሏል፡፡
አነቶኒዮ ራኦ በ92 ዓመታቸው በ2025 እ.አ.አ መጋቢት ወር አጋማሽ ለተሳተፉበት የማራቶን ሩጫ በየሳምንቱ ከ20 እስከ 30 ኪሎ ሜትር ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸው ነው የተጠቀሰው፡፡
“ውድድሩን እጨርሳለሁ ብዬ አላስብኩም ነበር፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ቀናት ጤንነቴ ጥሩ ላይ አልነበረም፤ ያም ሆኖ ካለፈው ዓመት ካስመዘገብኩት ሰዓት 10 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ማጠናቀቅ ችያለሁ” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም “መራመድ፣ መሮጥ ህይወት ነው፤ ሁሉም እንዲሳተፍ እጋብዛለሁ” በሚለው መልእክታቸው ድረ ገጹ ጽሁፉን አደማድሟል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም