የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም
አፍሪካ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን የሚገመት ሕዝብ አላት። በሕዝብ ብዛት የዓለምን 16 በመቶ ድርሻ ይዛለች። 54 ሀገራት ያሏት አፍሪካ ሶስት ሺህ የሚጠጉ ጎሳዎች አሏት። እያንዳንዱ ሀገራት ልዩ የሆኑ ባህሎች፤ ቋንቋዎች እና ማንነቶች አሏቸው። አፍሪካ በብዝኀ ማንነቷ ትታወቃለች። ደቡብ አፍሪካ 11 ቋንቋዎችን የሀገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋዎች እንዲሆኑ በሕግ መደንገጓ ብዝኀ ማንነትን ለማስተናገድ የተደረገ ሙከራ ነው።
አፍሪካን በጀት ሳፋሪስ ድረገጽ “የአፍሪካ ዝነኛ ባህሎች እና ልማዶች” ሲል በዝርዝር ጽፏል። ሁለቱን ጎሳዎች አጠር አድርገን እንመልከታቸው። ማሳይ እና ሃድዛ ይባላሉ።
ማሳይ ጎሳ
ዝነኛ ባህል እና ማንነትን ይዞ ብዙ ሺህ ጎብኚዎች የሚያደንቁት አንዱ በታንዛኒያ እና ኬንያ የሚገኘው ማሳይ ጎሳ ነው። ይህ ጎሳ በግምት 840 ሺህ ሰዎችን በውስጡ እንደያዘ ይነገርለታል። ቀይ ልብስ በብዛት ያዘወትራሉ። ረጃጅም ቁመት አላቸው። በቀይ ቀለም ያሸበረቀውን ልብሳቸውን ሹካ ብለው ይጠሩታል። ቀይ ቀለምን የተቀደሰ ነው ብለው ስለሚያስቡ ለልብሱ ቀለም ያላቸው ፍቅርም ከዚህ እምነት የሚነሳ ነው።
ቀይ ቀለም በዚህ ጎሳ ውስጥ ደምን ይወክላል። ቀይ ቀለም የልብሳቸው መልክ መሆኑ ከዱር አራዊት ጥቃት እንደሚጠብቃቸው ያስባሉ። ብርቱካናማ ቀለም የአብሮ መኖር እና እንግዳ ተቀባይነት ምሳሌ ነው። የወዳጅነት እና የመድመቅ መግለጫም ጭምር ነው። ሰማያዊ ቀለም ለእንስሶቻቸው ውኃ የሚሰጣቸው የሰማይ ምልክት ነው። አረንጓዴ የመታደስ እና የምርት፤ ቢጫ ደግሞ የማደግ እና የመራባት ማሳያዎች ሆነው በጎሳው ውስጥ ያገለግላሉ። በምሥራቅ አፍሪካ የማሳይ ጎሳዎች አለባበስ ከሌሎች የተለዬ እና ያሸበረቀው የጎሳ አለባበስ በሚል በልዩነት ይታወቃል።
ማሳይ ጎሳዎች ጦረኞች እና አርብቶ አደሮች ናቸው። በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በምሥራቅ አፍሪካ ጫካዎች በመዘዋወር ኖረዋል። በዚህ ጎሳ ውስጥ ትልቁ መከበሪያ ከብት ነው። ለዚህ ነው አንድ የማሳይ ጎሳ አባል ስኬታማ ነው ለማለት ያለውን የከብት ብዛት እና የልጆችን ቁጥር ማየት የተለመደው። በዚህ ጎሳ ልጆች ሀብቶች ናቸው።
ማሳዮች ዛሬም ድረስ የሰለጠነው የምዕራቡ ዓለም አኗኗር ሳይለውጣቸው በምሥራቅ አፍሪካ ሳፋሪ ሜዳዎች እና ጫካዎች ውስጥ ከብቶችን በማርባት፤ መንገዶችን ሞልተው በመዘዋወር፤ አዳሙ የሚሉትን የዝላይ ዳንስ በማቅረብ ተወዳጅ ሆነው ቀጥለዋል። አዳሙ የሚሉት ተወዳጅ ዳንስ በዚህ ጎሳ ውስጥ ብቻ የሚታወቅ ነው። ደማቅ ቀይ ልብሳቸውን ለብሰው ይዘልላሉ። ከመሬት ወደ ላይ በመዝለል ይከወናል። ዳንሱ የሚከወነው ወንዶች ሚስት አግብተው ትዳር ከመመስረታቸው በፊት ችግሮችን ለመጋፈጥ ብቁ ናቸው ወይ? ጥንካሬና አቅማቸውስ ምን ያህል ነው? የሚለውን ለማወቅ ነው። ወንዶች ክብ ሰርተው ለመዝለል በሚያመች አፈራማ መሬት ላይ ይቆማሉ። ለትዳር የተዘጋጀው ጎረምሳ በየተራ ወደ መድረኩ እየቀረበ ከመሬት ወደ ላይ በመዝለል ይደንሳል። ዳንሱ መዝለል ብቻ አይደለም። እስክስታ የሚመስል ዓይነት እንቅስቃሴም አለው። በድምጽም ይዘፍናሉ። ይደንሳሉ። በዚህ ጊዜ ጥሩ የደነሰ እና ወደ ላይ ከፍ ብሎ የዘለለ ወንድ በአካባቢው ቆንጆ የተባለችውን ልጅ ያገባል።
የጎሳው ታላላቅ ሰዎች የሚወዱትን እና የሚያከብሩትን ሰው ምራቃቸውን በመትፋት ፍቅራቸውን ይገልጹለታል። በሰላምታ መንገድ ይገለጻል፤ ከክፉ መንፈስ መጠበቂያ ሆኖ ያገለግላል። መልካም ምኞትም ነው ብለው ያስባሉ። ምራቅ መትፋት በሰለጠነው ዓለም ነውር ይሁን እንጂ በማሳዮች ዘንድ ግን እርኩስ መንፈስን የማባረሪያ ዘዴ ተደርጎ ይወሰዳል። ሕጻን ሲወለድ ግንባር ላይ መትፋት፤ ሰው ሲገናኝ እጁ ላይ መትፋት ለዘመናት የኖረ ልማድ ነው።
የእንስሳትን ደም መጠጣት በዚህ ጎሳ ውስጥ ተወዳጁ ባህል ነው። ደም መጠጣት ሰውነትን ያድሳል ብለው ያምናሉ። የላም ደም እና ወተትን ቀላቅለው ሲጠጡ፤ የዱር እንስሳትን ግን ፈጽሞ አይመገቡም። በአንዳንድ ልዩ ልዩ አጋጣሚዎች የአሳማ ስጋን ይመገባሉ።
ሃድዛዎች
በታንዛኒያ የሚኖሩት እነዚህ ጎሳዎች በቁጥር እስከ አንድ ሺህ 300 ድረስ ይገመታሉ። ቀደምት አትክልት እና ፍራፍሬ የመልቀም ታሪክ ያላቸው ሃድዛዎች፤ በታንዛኒያ አሩሻ ክልል ውስጥ ኤያሲ ሐይቅ ዳርቻዎች ሰፍረው፤ በዚህ ዘመን ይኖራሉ ተብለው የማይጠበቁ ጎሳዎች ናቸው።
በታንዛኒያ ከ50 ሺህ ዓመታት በፊት በድንጋይ ዘመን የኖሩ ቀደምት የአደን እና ፍራፍሬ ለቀማ ልምምዳቸውን ዛሬም ድረስ በትንሽ የሕዝብ መጠን ያስቀጠሉ ጎሳዎች ሆነው ይጠቀሳሉ። የሰለጠነው ዓለም ሃድዛዎች ጥንት የቀረውን አደን እና ፍራፍሬ ለቅሞ የመኖር ልማድ በምናገኝበት ብቸኛው አህጉር አፍሪካ ውስጥ መኖራቸው ይደንቃል ይላል። በዚህ ጊዜ ሃድዛዎች በልዩ አኗኗራቸው የዓለም ብቸኛዎቹ ሳይለወጡ የቀሩ አዳኞች እና ፍራፍሬ ለቃሚዎች ሆነዋል።
ሃድዛዎች በአፍሪካ ውስጥ ለረጅም ዓመታት በመኖር ብቻ አይደለም ልዩ የሆኑት። ይልቁንስ ልዩ በሆነው የአደን አቅማቸው እንጂ። በአነፍናፊ ውሾች ታጅበው የዱር እንስሳትን አድነው ይመገባሉ። ፍራፍሬ በመልቀምም የተካኑ ናቸው። የሳር ምድር እና ቁጥቋጦዎች፤ መልከ ብዙ የእጽዋት ዓይነት ባለበት ይኖራሉ። በጥቅጥቅ ጫካዎች የዱር እንስሳትን አድነው ይመገባሉ። ከርከሮ፣ ዝንጀሮ፣ ጦጣ ከተገኘ ምርጥ ምግባቸው ነው። ጨጓራውን ማጠብ የሚባል ነገር አይታሰብም። ውኃ ሳይነካው ዝም ብሎ መብላት ነው። ሌላውን ስጋ ቀቅለው ይመገቡታል።
በዚህ ጎሳ ውስጥ ወንዶች አደን ወጥተው ስጋ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል። ማር መኖሩን የምታመላክተውን ወፍ በመከተል ውሻ ይዘው ጫካ ይገባሉ። ሲመለሱ ምርጥ የጫካ ማር ይዘው ነው። የሴቶች ድርሻ አትክልት እና ፍራፍሬ ለቅሞ ማብላት ነው።
ሃድዛዎች የሚናገሩት ቋንቋ ሃድዛን ይባላል። ይህ ቋንቋ የትኛውም የአፍሪካም ይሁን የዓለም ክፍል ውስጥ አይነገርም። ከየትኛውም ቋንቋ ጋር ዝምድና የሌለው ግሉል ቋንቋ ነው ሲል አፍሪካ ጂኦግራፊክ ድረገጽ ጽፏል። ቋንቋውን ሲያወሩ ላንቃቸውን በብዛት ይጠቀማሉ። ምላስን ከላንቃ ጋር በማጣበቅ በሚያወጡት ለጽሑፍ በሚያስቸገር አነጋገር ከንፈራቸውን አሞጥሙጠው ድምጻቸውን ለማውጣት ይሞክራሉ። ከቃል ይልቅ የሚያወጡት ድምጽ የበለጠ ትኩረትን ይስባል። ቱሪስቶች ስማቸውን ሲጠይቋቸው የሚናገሩበት መንገድ ይገርማል፤ ግርታንም ይፈጥራል። የተናገሩትን ቃል ለመጥራት ከባድ ነው። ወፍ የሚናገር ወይም የሚጮህ ሊመስላችሁ ይችላል።
ሃድዛዎች ለረጅም ዓመታት ሊሰብኳቸው የሞከሩትን ሚሽነሪዎችን አልተቀበሏቸውም። ይልቁንስ በሰው ልጆች እኩልነት ከማመን ሌላ ሃይማኖት የላቸውም። በታሪካቸው ረሃብ የሚባል አደጋ ገጥሟቸው አያውቅም። በዙሪያቸው ያሉ ሌሎች ሕዝቦች የረሃብ ሰላባ ሲሆኑ ሃድዛዎች ራሳቸውን ይመግባሉ። ለዛሬ ከሚበሉት በስተቀር ለነገ በሚል ትርፍ ማስቀመጥ በባህላቸው አይፈቀድም። ከሚበላው ውጪ የሚሰበስብ ጨካኝ ተብሎ ይታመናል። ሃድዛዎች አካባቢዎችን ከመቀየር ይልቅ መላመድን ያውቁበታል። ድርቅ ሲመጣ ምግብ ወዳለበት አካባቢ በመሄድ መኖር ይቀጥላሉ።
በሃድዛዎች አፈታሪክ መሰረት ጎሳው አራት የእድገት ምእራፎች አልፏል። ጥንታዊው እና የመጀመሪያው ገርናንቤ በመባል የሚታወቁት ናቸው። ረጃጅም ጸጉር ነበራቸው። ልብስ አይለብሱም። ምንም የጦር መሳሪያ ወይም ምግብ ማብሰያ እሳት አልነበራቸውም። ጥሬ ስጋ ተመጋቢዎች ነበሩ። ሁለተኛው ምእራፍ ዥዥንቤ በመባል የሚታወቁትን ጎሳዎች ያካትታል። ኑሯቸው ዋሻ ውስጥ ነበር። ጸጉራቸውን የሚላጩ ውሻዎችን ይዘው የሚያድኑ ነበሩ። ሃማካዋንቢ የሦስተኛው ምዕራፍ ሲሆን የሃድዛ ጎሳዎች የኖሩበት ነው። በቁመት አጫጭሮች ናቸው። ምግባቸውን በአደን ያገኙ ነበር። ቀስት፣ ድስት እና እሳትን በመጠቀም ምግባቸውን የሚያዘጋጁ ነበሩ። ከሌሎች የአፍሪካ ጎሳዎች ጋር የንግድ ልውውጥ የጀመሩት እነዚህ ጎሳዎች ስለመሆናቸው አፍሪካን በጀት ሳፋሪ ጽፏል። ሉኩቹኮ የሚባለውን የቁማር ጨዋታም የጀመሩት እነዚህ ሦስተኛ የትውልድ ምእራፍ ጎሳዎች ናቸው ይባላል።
የሃድዛ የመጨረሻው የጎሳ የዘመን ምእራፍ ሃማይሽኔቢ በመባል የሚታወቀው እና ዛሬም ድረስ በአደን እና ፍራፍሬ ለቀማ የሚተዳደረው ነው። የጎሳው አባላትን በስም መጥራት የጀመረ፤ ለቦታዎች ስያሜ የሰጠ፤ መንገዶችን እና መተላለፊያዎችን የፈጠረበት ዘመን ነው።
ሃድዛዎች አሁን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ገጥመዋቸዋል። በቱሪስቶች አማካይነት አልኮል መጠጣት ጀምረዋል። ለበሽታ ወረርሽኝ እየተጋለጡ ናቸው። የግብርና ስራ መስፋፋት አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ እያደረጋቸው ነው። የቀደመውን አኗኗር ለመቀጠል እየተቸገሩ ናቸው።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም