ማሶአላ ብሔራዊ ፓርክ ከአፍሪካ በደቡብ ምሥራቅ በህንድ ውቅያኖስ፣ በማዳጋስካር ደሴት ላይ ነው የሚገኘው::
የፓርኩ ስፋትም 2400 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ወይም 240 ሺህ ሄክታር ተለክቷል:: ከዚህ ውስጥ 2300 ኪሎ ሜትር ስኩዌሩ ጥቅጥቅ የየብስ ደንን ሲይዝ 100 ኪሎ ሜትር ስኩዌሩ የህንድ ውቅያኖስ ቀጣናን ያቀፈ ነው::
በ1997 እ.አ.አ ሰፊ የየብስ እና የውቅያኖስ ቀጣናን አካቶ የተመሰረተው ፓርኩ ጥቅጥቅ ደን፣ የባህር ዳርቻ፣ ረግረጋማ እና ዛጐል የተነጠፈባቸው ስነምህዳሮችን ይዟል::
ማዳጋስካር ከአህጉራት ፈንጠር ብላ ለብቻ መፈጠሯ የ10 ልዩ ብርቅዬ እንስሳት እና እፅዋት መገኛ እንድትሆን አስችሏታል::
ከብርቅዬ የዱር እንስሳት እንደ ጦጣ በዛፍ ላይ የሚንጠላጠለው ፍራፍሬን የሚመገበው አይኑ ጐላ ጐላ ያለው “ሊመር” የተሰኘው አንዱ ሲሆን “ሊመርን” በማደን የተፈጥሯዊ ቀጣናውን ሚዛን የሚያስጠብቀው “ፎሳ” የተሰኘው በመጠኑ አነር የሚያክለው ስጋ በልም ተጠቃሽ ነው::
በአካል መጠናቸው አነስተኛ ከሆኑት ደግሞ ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ከማንኛውም ዳራ ጋር መመሳሰልን በተፈጥሮ የተቸረው እስስት ሌላኛው ብርቅዬ መሆኑን ድረ ገፆች አስነብበዋል::
ፓርኩ ብርቅዬ ማለትም በሌሎች ቀጣና የማይገኙ እፅዋትንም ይዟል:: ከነዚህ ብርቅዬዎች እፅዋት መካከል “ትራፈርስ ትሪ” የተሰኘው ዘንባባ መሰል ጐድ ጐድ ብለው ውኅ የሚይዙ ቅጠሎች ያሉት፣ ፍሬዎቹ ለዱር እንስሳቱ በምግብነት የሚያገለግሉ ዋነኛው ተጠቃሽ ነው::
በተጨማሪም ፓንዱኑስ እና ኦርኪድ ሌሎች በቀጣናው የሚገኙ ብርቅዬ የእፅዋት ዓይነቶች ሆነው ተመዝግበዋል::
በህንድ ውቅያኖስ ቀጣና በደሴቷ ዳርቻ ባለ ቅንፍ ጀርባው ግዙፍ “ሁዌል” እና ሌሎች የዓሣ ዝርያዎችም መጠለያ ነው::
በፓርኩ ቀጣና የምግብ እና ማረፊያ አገልግሎት የሚሰጠው ብቸኛው የማሶአላ ሎጂ 14 እንግዶችን የመያዝ ዓቅም፣ ከፍ ባለ ቁመት እና ጣሪያ፣ በረንዳ ያላቸው ጐጆዎችን አካቶ ይዟል::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ናቹራል ወርልድ ሳፈሪ፣ ፍራይድ ፓስርት እንዲሁም ዋይልድ ማዳጋስካር ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም