የኑሮ ውድነት እና የገበያ አለመረጋጋት አሁንም የዜጎች ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የምግብ ሸቀጦች እና ምርቶች ላይ ቀደም ሲል ተከስቶ የነበረዉ የዋጋ ጭማሪ ሳያንሰዉ ከሰሞኑ ደግሞ ይበልጥ ዋጋዉ በከፍተኛ ደረጃ አሻቅባል። የዋጋ ጭማሪ በተለያየ መንገድ ሊከሰት የሚችል ሲሆን ከምክንያቶች መካከል በዋነኛነት የሰላም እጦት እና ግጭቶች ዋነኞቹ መሆናቸዉም ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነዉ።
ለዋጋ ጭማሪው ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጨማሪም የፍላጎት መናር፣ የማምረቻ ወጪ መጨመር፣ በኢኮኖሚ ውስጥ የገንዘብ መጠን በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ለዋጋ ንረት መነሻ ምክንያቶች ናቸው፡፡
እነዚህ ተፈጥሯዊ የሆኑ የዋጋ ንረት መንስኤዎች እንደተጠበቁ ሆነው ሰው ሠራሽ በሆኑ ምክንያቶች ሲባባሱ ደግሞ ችግሩ ለዜጎች ፈተና ይሆናል፡፡ ለአብነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያጋጠመው የእርስ በእርስ ግጭት እና የሰላም መደፍረስ ተጠቃሽ ነው፡፡ በግጭቱ አማካኝነት አርሶአደሮች ተረጋግተው እንዳያመርቱ፣ ያመረቱትንም ወደ ገበያ እንዳያቀርቡ በማድረግ፣ በህገወጥ ነጋዴወች እና ደላሎች በሚፈጥሩት ሰዉ ሰራሽ እጥረት (ምርቶችን እና ሸቀጦችን በመደበቅ) እና በሚፈጥሩት ረጅም ቅብብሎሽ እንዲሁም ህገ ወጥ ነጋዴወችን እና ደላላወችን መቆጣጠር አለመቻል የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ካደረጉት መካከል ተጠቃሾች ናቸዉ።
ከሰሞኑ በምርቶች ላይ ስለተፈጠረው የዋጋ መጨመር አሚኮ የባህርዳር ከተማ ሸማቹን አነጋግሮ ባገኘዉ ምላሽ “ከወር በፊት ከአትክልት እና ፍራፍሬ ጀምሮ ሁሉም ምርቶች ላይ ገበያው ከነበረበት ይበልጥ ሊረጋጋ እንደሚችል ተስፋን ሰጥቶን የነበረ፤ ቢሆንም በዚህ ሁለት ሳምት ውስጥ ደግሞ የአብዛኛዎቹ ምርቶች ዋጋ እጥፍ በሚባል ደረጃ ጨምሯል በተለይ ዘይት እና የወጥ እህሎች ላይ በእጅጉ ጨምራል ስለዚህ መንግስት ይቆጣጠርልን” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ነዋሪወች ያነሱትን የምግብ ዘይት እጥረት እንደሚፈታ ታምኖበት በባህርዳር ከተማ እና በሌሎች የዞን ከተሞች የምግብ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ ለመክፈት ፈቃድ ለወሰዱ በርካታ ነጋዴወች የፋብሪካ ቦታ በነጻ ከመስጠት በተጨማሪ ማምረቻ ማሽኖችን ከቀረጽ ነጻ እንዲገባላቸ ተፈቅዶላቸዉ የምግብ ዘይት ማምረት የጀመሩ አምራቾች ቢኖሩም በቁሚነት እና በሚፈለገዉ መጠን እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ በኩል ያላቸዉ ተነሳሽነት ግን እምብዛም በመሆኑእና የአቅርቦት ችግሩ ባለመቀረፉ የሚያስተዛዝብ እና መንግስትንም ቆም ብሎ እርምት እንዲወስድ የሚጠቁም ሆናል።
ይህን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር እና ለመከላለል ያስችለዉ ዘንድ የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ከሰሞኑ ገዢ እና ሻጭን ለማገናኘት ያለመ ውይይት አካሂዶ ነበር፡፡ በውይይቱ ላይ የዘይት ፋብሪካዎችም ሆኑ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ከመንግሥት የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ ዋጋ ምርቶቻቸውን እያቀረቡ እንዳልሆነ ተጠቁማል፡፡
የክልሉ መንግስትም የዋጋ ንረት በተከሰተ ጊዜ ገበያውን ለማረጋጋት ምርትን በስፋት ለሸማቹ በቀጥታ ለሚያቀርቡ ጅምላ ነጋዴዎች በተለያዩ ከተሞች ጊዜያዊ ሸዶንችን የማስተላለፍ ሥራ መሰራቱን፣ የግብይት እሴት ሰንሰለቱን ጠብቆ ምርት ቀጥታ ከሸማቹ እንዳይደርስ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን እና ደላላወችን ለመቆጣጠር እየተሠራ መሆኑን በተለይ በዘይት ምርት ላይ ተመሳጥረው ዋጋ በጨመሩ ነጋዴዎች ላይ ሱቅን እስከ ማሸግ የሚደርስ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የዋጋ ንረትን በዘላቂነት በመከላከል የኑሮ ውድነት የዜጎች ፈተና እንዳይሆን ለማድረግ ይቻል ዘንድ ከሁሉም በፊት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ሰላም ይረጋገጥ ዘንድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻዉን ስራ በመስራት የሰላም ሁኔታው እንዲረጋጋ ማድረግ ይገባል፡፡ በመንግስት በኩልም የገበያ ማዕከላትን መገንባት፣ ከእሁድ ገበያዎች በተጨማሪ አማራጭ ገበያን በማስፋት፣ ሕገ ወጥነትን በዘላቂነት በመከላከል እና የነዳጅ ዋጋን ማረጋጋት ላይ አተኩሮ መስራት ላይ ትኩረት ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር ነዉ።
በኲር የመጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም