ማኅበረሰቡ ለተባባሰ የጤና ችግር እንዳይጋለጥ እየተሠራ ነው

0
133

ማኅበረሰቡ  ለተባባሰ የጤና ችግር እንዳይጋለጥ እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል፤ ቢሮው  “ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መልዕክት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን  በማስመልከት በጤናው ዘርፍ  አበረታች ውጤት ላስመዘገቡ ሴቶች ዕውቅና ሰጥቷል።

የጤና ባለሙያዎች የጸጥታ ችግር ሳይበግራቸው ማኅበረሰቡ  ለተባባሰ የጤና ችግር እንዳይጋለጥ  እያደረጉ መሆኑንም የቢሮው ኃላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ከማሰብ ባለፈ የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማሳደግ  ትኩረት የሚደረግበት መሆኑንም  ኃላፊው ገልፀዋል።

“የጤና ባለሙያዎች   በክልሉ ያለው ግጭት   ሳይበግራቸው  ማኅበረሰቡ  ለተባባሰ የጤና ችግር እንዳይጋለጥ፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና በመስጠት ሕይወት እንዳይጠፋ አድርገዋል” ነው ያሉት። ይህም በተላላፊ በሺታዎች ይሞቱ የነበረውን የሕጻናት እና የእናቶችን ሞት በመቀነስ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳስቻለ ተናግረዋል።

አቶ አብዱልከሪም በአሁኑ ወቅት በሁሉም መስክ የሚገኙ ሴት የጤና ባለሙያዎች ወቅታዊ ችግር ሳይበግራቸው የጤና አገልግሎቱን  በጥራት፣ በፍትሐዊነት እና  በዘላቂነት  ማኅበረሰቡን እያገለገሉ ነው።

በዕውቅና በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ  የእናቶች ጤንነት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል። ተቋማት የሴቶች ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩም ጠይቀዋል።

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የመጋቢት 8  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here