ማንን ይዞ ጉዞ

0
84

ለፍጥረታት ሁሉ መሠረታዊ ጉዳይ ሲሉ ይጠሩታል። ያለ እሱ ለመኖር መሠረታዊ ነገሮችን ማግኘት የማይቻል መሆኑንም በማሳያነት ያነሱታል – አፈር። የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚሉትም፤ አፈር የሰውም ሆነ የእንስሳት ምግብ የሚመረትበት ከመሆኑም ባሻገር ያለ አፈር ሕልውናን ማስቀጠል የሚታሰብ አይደለም።

ይህ የተፈጥሮ ሀብት በምድር ለሚበቅሉት አዝርዕት ሁሉ መብቀያ፣ በአጠቃላይ ለፍጥረታት ሁሉ የምግብ መገኛ መሆኑን በመገንዘብ ጤንነቱን እና ደህንነቱን መጠበቅ የውዴታ ግዴታ ነው። ይሁን እንጂ አሁን ላይ አፈር በተለያዩ ምክንያቶች ደህንነቱ ለችግር መጋለጡን ባለሙያዎች አረጋግጠዋል። በተለይም የአፈር አሲዳማነት ለሰብሎች ዕድገት ጠንቅ እየሆነ መምጣቱ አሳሳቢ እንዳደረገው ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚያብራሩት። ይህም በምርታማነቱ ላይ እያሳደረው ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ችግሩ ደግሞ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ህልውናቸው በግብርና ላይ ለተመሠረተ ሀገራት አሉታዊ ተጽዕኖው የከፋ ነው።

 

ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ከፍተኛ ዝናብ ባለባቸው አካባቢዎች ላይ የአሲዳማነት መጠኑ እየከፋ በመምጣቱ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል። በተመሳሳይ ግብርና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ አሁን ከሚታረሰው 21 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውሰጥ 45 በመቶው በአፈር አሲዳማ የተጠቃ ነው። የአፈር አሲዳማነትን አሉታዊ ተጽዕኖ በኢትዮጵያ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ 85 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የሚኖርበት አካባቢ መሆኑ ነው።

በግብርናው ዘርፍ በትርፍ አምራችነቱ የሚታወቀው አማራ ክልል በምርታማነቱ እንዳይቀጥል ከገጠሙት እንቅፋቶች መካከል የአፈር አሲዳማነት ተጠቃሽ ነው። ለግብርና ሥራ ዋና ግብዓት በሆነው አፈር ላይ የሚከሰተው የአፈር አሲዳማነት (ጨዋማነት) በምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን መረጃዎች ያመላክታሉ።

 

በክልሉ የአፈር አሲዳማነት ችግር ጎልቶ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች መካከል የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እና የምዕራብ ጎጃም ዞን ተጠቃሽ ናቸው። ችግሩም የሰብል ምርታማነትን በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ዋናው እንደሆነ ይጠቀሳል። ታዲያ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የመፍትሔ ተግባራት በአርሶ አደሮች እና በግብርና ባለሙያዎች ዘንድ እየተከናወኑ ነው። የችግሩ አሳሳቢነትም የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ልብ ይሏል።

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባንጃ ወረዳ ውስላ ክንዴካን ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ደሴ በላቸው ለበኩር ጋዜጣ እንደተናገሩት የመሬታቸውን ለምነት ለመጠበቅ የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ። የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ማዘጋጀት እና መጠቀም ደግሞ ቀዳሚው ተግባራቸው ነው። በአሲዳማ የተጠቃውን መሬታቸውን በኖራ ማከምም ተጨማሪ ሥራቸው መሆኑን ነግረውናል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ሦስት ጥማድ መሬታቸውን በኖራ በማከም እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም የአፈር ለምነቱ እንዲመለስ አድርገዋል። በቀጣይም በቀሪ ግማሽ ሄክታር መሬታቸው ላይ ኮምፖስት እና ኖራ በመጠቀም በአሲዳማነት የተጠቃውን መሬታቸውን ወደቀደመ ለምነቱ ለመመለስ ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።

 

በችግሩ ምክንያት ከዚህ በፊት መሬታቸው ገብስ፣ አተር እና ስንዴ ማብቀል አቁሞ እንደነበር አርሶ አደሩ ያስታውሳሉ። ነገር ግን አርሶ አደር ደሴ በስልክ እንደነገሩን ከመሬታቸው የአፈር ናሙና ለግብርና ባለሙያ በማሳየት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በአሲድ የተጠቃውን መሬታቸው ሲያክሙ እና ሲንከባከቡ ቆይተዋል። በዚህም ከፍተኛ የምርት ጭማሪ ማግኘታቸውን ነው የሚናገሩት። በተለይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (መደበኛ፣ ቨርሚ እና ባዮ ሳላሪ ኮምፖስት) በመጠቀማቸው የአፈሩን ለምነት ከመጠበቅ ባለፈ የሚዘሩትን ሰብል ከበሽታ እንደሚከላከልላቸው ተሞክሯቸውን አካፍለውናል።

ሌላው ሐሳባቸውን በስልክ ያጋሩን የምሥራቅ ጎጃም ዞን የጁቤ ወረዳ ዶገም ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር አንዷለም ምሕረቴ ናቸው። የአፈር አሲዳማነት መሬታቸውን ከምርት ውጪ አድርጎት እንደነበር አስታውሰው የተፈጥሮ ማዳበሪያ እና ኖራን በመጠቀም በአፈር አሲዳማነት ተጎድቶ የነበረውን መሬታቸውን ለምነቱ እንዲመለስ አድርገዋል።

 

አርሶ አደር አንዷለም እንዳሉት አንድ ሄክታር የእርሻ መሬታቸው በአሲድ በመጠቃቱ ለማምረት ፈተና ነበር። ይሁን እንጂ ከ2013 ዓ.ም ጀምረው የአፈር ናሙና ለግብርና ባለሙያ አሳይተው ምርመራ ተደርጎ ኖራ መጠቀም እንደጀመሩ ነግረውናል። የአፈር አሲዳማነት ችግሩ አሳሳቢ እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደሩ በኖራ በማከም እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ አቀናጅተው በመጠቀማቸው ደግሞ በፊት ይገኝ ከነበረው ከሁለት እጥፍ በላይ ጭማሪ ምርት ማሳየቱን ተናግረዋል። የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀምም ለሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የሚወጣውን ወጪ በመቀነስ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

እንደ አርሶ አደሩ ማብራሪያ አሁን ላይ ሦስት ጥማድ መሬታቸው ሙሉ ለሙሉ ለምነቱ ተጠብቆ ምርት እየሠጣቸው ነው። በ2017/18 የምርት ዘመንም 20 ኩንታል ኖራ በመግዛት መሬታቸውን በማከም ምርታማነቱን ለመጨመር እየሠሩ ነው። በኖራ ማከም ምርታማነትን የመጨመር አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት አርሶ አደሩ የተጎዳውን መሬት ማከም እንዲቻል መንግሥት በቂ ኖራ እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ስማቸው ለበኩር ጋዜጣ በስልክ እንደተናገሩት በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከጃዊ ወረዳ በስተቀር በሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች መጠኑ ቢለያይም የአፈር አሲዳማነት ችግር ተከስቷል። ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም አስታውቀዋል። ምክትል ኃላፊው እንዳሉት በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከሚታረሰው 407 ሺህ 226 ሄክታር መሬት ውስጥ 187 ሺህ ሄክታሩ በአሲድ መጠቃቱን አረጋግጠዋል።

 

በመሆኑም ይህንን የተጎዳ መሬት ለምነቱን በመመለስ ምርታማነቱ እንዲጨምር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። በኖራ ማከም አንዱ ተግባር መሆኑን ነው የተናገሩት። ከአንድ ሺህ 900 ሄክታር በላይ መሬት በኖራ ለማከም በዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን በማንሳት ለዚህም 48 ሺህ ኩንታል ኖራ ጥቅም ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል። ቢሆንም ግን የኖራ አቅርቦቱ መሠረታዊ ችግር መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም የኖራ ማምረቻ ፋብሪካዎችን በማስፋፋት በቂ ኖራ መመረት እንዳለበት ነው የጠየቁት። ኖራን በበቂ መጠን እና በወቅቱ አለማቅረብ መሠረታዊ ጉድለት መሆኑን በመግለጽ የአርሶ አደሮችን ሐሳብ ተጋርተዋል።

ምክትል ኃላፊው እንደገለፁት በዚህ ዓመት (በ2017 ዓ.ም) የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል 48 ሺህ ኩንታል ኖራ ለመጠቀም የታቀደ ሲሆን  ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም አራት ሺህ 500 ኩንታል ያህሉ ቀርቧል። ሁለት ሺህ 616 ኩንታሉ ደግሞ ለአርሶ አደሩ ተሠራጭቶ በ52 ሄክታር መሬት ላይ መቀላቀል ተችሏል።

 

አርሶ አደሩ ኖራን ከአፈር ጋር ሲቀላቅል የአፈሩን የእርጥበት መጠን መለየት እና ሌሎች ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይጠበቅበታል። አቶ አዲሱ እንደተናገሩት ከኖራ አቅርቦቱ በተጓዳኝ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ በስፋት እንዲያዘጋጅ ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው። አርሶ አደሩም የተፈጥሮ ማዳበሪያን (ኮምፖስት) በመጠቀም በአፈር አሲዳማ የተጠቃውን መሬት ለምነቱን እንዲመለስ ጥረት ማድረግ እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ጎጃም ዞን የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ቢሆንም ካለው ችግር ስፋት አኳያ አስቸኳይ መፍትሔ ይሻል ተብሏል። የዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ በላይነህ ጌትነት ለአሚኮ በኵር ጋዜጣ በስልክ እንደገለፁት በዞኑ ከሚታረሰው 300 ሺህ ሄክታር ውስጥ 25 በመቶው በጠንካራ አሲድ የተጎዳ ስለመሆኑ በምርምር መረጋገጡን አመላክተዋል። ችግሩ እየከፋ መሄዱም አሳሳቢ እንዳደረገው ነው የተናገሩት። “የአፈር አሲዳማነትን ቀድሞ መከላከል ካልተቻለ መሬቱ ከተጠቃ በኋላ ወደ ነበረበት ለመመለስ ሌላ ፈተና ነው” ብለዋል።

 

በዚህ ዓመት 46 ሺህ 650 ኖራ ለማቅረብ ታቅዷል። እስካሁንም ስምንት ሺህ 287 ኩንታል ኖራ ወደ ዞኑ የገባ ሲሆን ስድስት ሺህ 32 ኩንታሉ ለአርሶ አደሩ ተሠራጭቷል። እንደ ባለሙያው ማብራሪያ በኖራ ይታከማል ተብሎ በዕቅድ ከተያዘው ከአንድ ሺህ 548 ሄክታር መሬት ውስጥ 262 ሄክታር ብቻ ነው ማከም የተቻለው። በመሆኑም “ማግኘት የሚገባንን ምርት እንዳናጣ  የአፈር ጥበቃ ላይ ሰፊ ዘመቻ እና ርብርብ መደረግ አለበት” ብለዋል። ለሌሎች የግብርና ግብዓቶች ትኩረት እንደሚሰጠው ሁሉ ለአፈር አሲዳማነትም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል። በአሲዳማነት የተጠቃን አፈር የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ለምነቱን መመለስ ካልተቻለ በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትልም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

 

አርሶ አደሮች መሬታቸው በአፈር አሲዳማነት አልተጠቃም የሚል ግምታቸውን በማስቀረት የአፈር ናሙና በባለሙያ በማስወሰድ የአፈሩን ጤንነት ለማወቅ እንዲመረመር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። ከዚህ በተጨማሪም አርሶ አደሮች የአፈርን አሲዳማነት ሊከላከሉ የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን  እንዳለባቸው መክረዋል።

በአማራ ክልል የአፈር አሲዳማነት በተለያዩ አካባቢዎች የአፈሩን ለምነት እየጎዳው መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ባለሙያው አምሳሉ አድማስ ለአሚኮ በኵር ጋዜጣ ተናግረዋል። በክልሉ የአፈር አሲዳማነት የሚያጠቃቸው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ አካባቢዎችን መሆኑ ደግሞ “ችግሩን እጅግ አሳሳቢ አድርጎታል” ነው ያሉት። ካለው የችግሩ ስፋት እና አሳሳቢነት አኳያም አስቸኳይ መፍትሔ እና የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

 

በአማራ ክልል ከሚታረሰው አምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 36 በመቶው በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን ባለሙያው አረጋግጠዋል። ቢሮው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የኖራ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

ባለሙያው አቶ አምሳሉ እንዳብራሩት የአፈር ኬሚካላዊ ይዘት ፒ ኤች (PH) ከሚጠበቀው በታች ሲሆን እና የአልሙኒየም እና ማግኒዢየም ንጠረ ነገሮች ክምችት በሚበዙበት ጊዜ የአፈር አሲዳማነት ይከሰታል።  እንደ ፖታሺየም እና ካልሺየም ያሉ ንጥረ ነገሮች በተለይ ከፍተኛ ዝናብ በሚዘንብባቸው አካባቢዎች በዝናብ ታጥበው መጠናቸው ስለሚቀንስ ለአሲዳማ አፈር መፈጠር ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ጠቁመዋል። ከፍተኛ የሆነ የዝናብ ስርጭት፣ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎችን በአግባቡ አለመሥራት፣ ሰብልን እያፈራረቁ አለመዝራት፣ ለረዥም ዓመታት (በተከታታይ) መሬትን ማረስ፣ መሬትን አለመንከባከብ፣ የደን መጨፍጨፍ፣ በጥንቃቄ ጉድለት የምንጠቀማቸው ፀረ አረም እና ፀረ ተባይ መድኃኒቶች፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያን አዘውትሮ አለመጠቀም፣ የተዛባ የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ አጠቃቀም፣ የተዛባ አስተራረስ እና የሰብል ተረፈ ምርትን ከማሳው ሙሉ ለሙሉ ማንሳት ለአፈር አሲዳማነት መከሰት ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

 

በክልሉ የሚገኘው የመርሐቤቴ የኖራ ማምረቻ ፋብሪካ ከተቋቋመ ስምንት ዓመታትን ቢያስቆጥርም ወደ ሥራ አለመግባቱን ተናግረዋል። የደጀን የኖራ ማምረቻ ፋብሪካም ቢሆን በፀጥታው ችግር ምክንያት በሙሉ አቅሙ መሥራት አለመቻሉን ነው ያስረዱት። ይህም ለኖራ አቅርቦት ፈተና መሆኑን ጠቅሰዋል። በዚህም ምክንያት ኖራ ከፌደራል እየቀረበ ስለመሆኑ ነው ያብራሩት። በክልሉ በ2017/18 የምርት ዘመን ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀውን 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ቀድሞ የአፈርን ጤንነት መጠበቅ እንደሚገባ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።

በ2017/18 የምርት ዘመን በአማራ ክልል በአሲድ የተጎዳውን መሬት ለማከም የፌደራል መንግሥት 556 ሚሊዮን ብር መድቦ ግዥ በመፈፀም ለአርሶ አደሩ ኖራ ለማቅረብ እየሠራ ነው ብለዋል። 370 ሺህ 800 ኩንታል ኖራ በማቅረብ 12 ሺህ 360 ሄክታር መሬት ለማከም መታቀዱንም አስታውቀዋል። እስካሁንም 126 ሺህ ኩንታል ለክልሉ ቀርቦ  85 ሺህ ኩንታል የሚሆን ኖራ ችግሩ በስፋት በተከሰተባቸው ዞኖች ተሠራጭቷል። አራት ሺህ 300 ሄክታር መሬት በኖራ ማከም መቻሉንም ገልፀዋል።

 

ይሁን እንጂ ከችግሩ ስፋት አኳያ ሥራው ጅምር መሆኑን ጠቁመዋል። ችግሩን ለመከላከል ታዲያ የአፈር አሲዳማነትን በኖራ ማከም፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያን (ኮምፖስት) አዘውትሮ መጠቀም፣ ሰብልን በፈረቃ መዝራት፣ በምርምር የተረጋገጡ አሲዳማነትን መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን መጠቀም፣ የሰው ሠራሽ አና የተፈጥሮ ማዳበሪያን እንዲሁም የግብርና ኖራን አቀናጅቶ መጠቀም፣ ዛፎችን መንከባከብ፣ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ማከናወን፣ የኖራ ማምረቻ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ማድረግ፣  የእፅዋትን (የሰብሉን) ቅሬት ወይም ቃርሚያውን ከነስሩ ነቅሎ ከመውሰድ ይልቅ የተወሰነውን ማሳ ላይ በመተው እና ከአፈር ጋር መቀላቀል የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል የሚረዱ መፍትሔዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ባለሙያው አክለውም አርሶ አደሩ አሲዳማ መሬት ላይ ኖራ ሲቀላቀል የግብርና ባለሙያን ምክረ ሐሳብ መቀበል እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአጠቃላይ ለሰው ልጆች፣ ለእፅዋት እና ለእንስሳት ጤንነት ይጠበቅ ዘንድ የአፈርን ጤንነት እና ለምነት መጠበቅ ይገባል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here