አካል ጉዳተኞች መብታቸው እና ጥቅማቸው እንዲከበር ማኅበረሰቡ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ተጠቆመ። በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን የቢሮ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ ገብቷል። በወቅቱ ያናገርናቸው የማሕበሩ አባላት ለመብታቸው መከበር ሁሉም አካል ከጎናቸው ሊሆን እንደሚገባ ጠይቀዋል።
“አስፈላጊ ነገሮች ከተሟሉላቸውም ማንኛውንም ነገር መሥራት እንችላለን፣ የማንችለው አንችልም የሚለውን ቃል ነው” ብለዋል።
የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ኃላፊ ታከለ ቢሆን “ሁኔታዎች ከተመቻቹልን ማንኛውም ጉዳት የሌለበት ሰው የሚሠራውን ሥራ መሥራት እንችላለን” ብለዋል። የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዓላማውም የተደበቁ አካል ጉዳተኞችን አደባባይ ማውጣት መሆኑን ገልጸዋል።
አካል ጉዳተኞች መብታቸውን እና ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ ማኅበረሰቡ ልዩ ድጋፍ ማድረግ አለበት ያሉት አቶ ታከለ የቦታ አለመመቻቸት ፈታኝ እንደሆነባቸው ጠቁመዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት ታዲያ የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን የራሱ ቢሮ ተገንብቶለት ወደ ሥራ መገባቱ እንዳስደሰታቸው አክለዋለል።
የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የልፍኝ በላቸዉ አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ተግባር መሥራት የሁሉም ማኅበረሰብ ኃላፊነት ነው ብለዋል።
አካል ጉዳተኞች የብዙ ዕውቀት ምንጭ ናቸው ያሉት ኃላፊዋ ይህን በመገንዘብ አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ሥራ መሥራት ይገባል ብለዋል። ይህን ታሳቢ በማድረግ ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም