ማን ነው የከለከለህ?

0
135

“ባለፉት 25 ዓመታት በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ፣ የተለያዩ ሀገራት ዜግነት፣ የኢኮኖሚ አቅም፣ የትምህርት ታሪክ ካላቸው ሰዎች ጋር ሰርቻለሁ። የተረዳሁት ነገር ቢኖር የሰው ልጅ ከየትም ቢመጣ፣ ምንም ዓይነት ፈተናዎች ቢገጥሙት፣ ሁሉም ሰው ውስጥ ያልተነካ አቅም እንዳለው ነው”  ሲል የሊሚት ለስ መጽሐፍ ደራሲ ጂም ክዊክ ጽፏል። የሰው ልጆች አቅም ገና ድንግል ነው።

የሰው ልጆች የማደግ፣ የመለወጥ፣ የመሻሻል አቅም ገደብ አልባ ነው፤ ልዩነቱን የሚፈጥሩት ሰዎች ራሳቸው ናቸው።  ብዙው ሰው የመጨረሻ አቅሙን የተጠቀመ ይመስለዋል። አንዳንዱ አቅሜን አሟጥጬ ተጠቀምሁ፤ ከዚህ በኋላ በቃኝ ሲል እንሰማለን። የሰው ልጅ የፈጠራ፣ ውስብስብ ችግሮችን የመፍታት እና ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ የማበርከት ሙሉ አቅሙ ጥቅም ላይ አልዋለም ሲሉ የሰብዕና እና ስነ  አዕምሮ ምሁራን ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት የሰው ልጆች ችሎታ፣ ሀብት እና አቅም እየባከነ ነው ይላሉ።

የ “ዩ ካን ዊን” መጽሐፍ ደራሲ ሺቭ ኬራ  “የላቀ አዕምሮ ያላቸው ሰዎች  በሕልም ይመራሉ፤ ደካማ አዕምሮ ያላቸው ደግሞ በምኞት ይኖራሉ” እንደሚለው ጠንካራ ሰዎች ያለማቋረጥ ይጓዛሉ፤ አጥር ጥግ አይቆሙም፣ ከጀመሩት ጉዞ የሚመልሳቸው ድንበር የለም። ሕልማቸውን ለማሳካት ሲሉ የሚከፍሉትን ሁሉ ከፍለው ይገሰግሳሉ። በቃኝ ብለው አይቆሙም። በእርካታ ተንበሽብሸው አይዘናጉም።

ሳይኮሎጂ ቱዴይ ገደብ አልባ ሰዎችን የራሳቸው መርከብ ካፒቴኖች ናቸው፤ በሕይወታቸው የሚገጥሟቸውን አይረግሙም፤ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች እንደ ማደጊያ እድል ይጠቀማሉ ሲል ጽፏል። በዚህም ጥንካሬያቸው ላይ ያተኩራሉ፤ ለትክክለኛው የሕይወት ጥሪያቸው ይኖራሉ። መኖር የሚፈልጉትን ሕይወት ራሳቸው ይፈጥሩታል እንጂ ከሰው አይጠብቁም። የውስጣቸውን ድምጽ ያደምጣሉ፤ ኀላፊነት ለመውሰድም አይፈሩም ሲል ይገልጻቸዋል።

ለርን ማይንድ ፓዎር ገጽ ሰዎች በአዕምሯቸው የሚፈጥሯቸውን አሳሪ አስተሳሰቦች በምሳሌነት ጠቅሷል። “በመረጥሁት ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን ብቁ አይደለሁም፤ ጓደኛ ለማግኘት ያልቻልሁት ቆንጆ ስላልሆንሁ ነው፤ የሕልሜን ስራ ለመጀመር በቂ ልምድ የለኝም፤ አዲስ ነገር ለመማር እድሜዬ ገፍቷል፤ ጓደኛ ለማፍራት አልችልም” እና ሌሎች መሰል አስተሳሰቦች በሰዎች ውስጥ ገደብ የማበጀት አቅም አላቸው። እነዚህ ልምምዶች የሰውን ልጅ አዕምሮ ለተሸናፊነት እጅ የሰጠ እንዲሆን ያደርጉታል። በውጤትም ፍርሃት፣ ጥርጣሬ፣ ጭንቀት፣ ተስፋ ማጣት፣ አንድ ቦታ መቆም፣ ተዓምራትን መጠበቅ፣ መማረር እና እድልን የመርገምን እሳቤ ያላብሳሉ።

የሰው ልጆች ምኞት ላይ ለምን ይቀራሉ፤ ያሰቡትን እንዳያሳኩ፤ የሚፈልጉትን እንዳያደርጉ የሚያደርጋቸው፤ ከልባቸው መሻት የሚከለክላቸው ማን ነው? ማን ነው የከለከለህ? የሊሚት ለስ መጽሐፍ ደራሲ ጂም ክዊክ የከለከለህ አስተሳሰብህ ነው ይላል። አስተሳሰባቸው ደካማ በመሆኑ ብዙዎች ከአቅማቸው በታች ያልፈለጉትን ሕይወት ኖረዋል። ጥቂቶች ደግሞ አስተሳሰባቸውን በማጠንከራቸው ከታሰሩበት ገመድ አምልጠው፣ በጥሰው ያለከልካይ እስከ መቃብር ድረስ ተጉዘዋል። አሻራቸውን ለትውልድ በዘመናት ሰነድ መዝግበው አልፈዋል።

ጂም አስተሳሰብን ሲተረጉመው “ስለ ማንነታችን፣ ዓለም እንዴት እንደሚሰራ፣ ስለምንችለው፣ ስለሚገባን፣ ስለማይቻለው፤ ያለን ጥልቅ እምነት፣ ግምት እና አመለካከት ውጤት ነው” ይላል። አንድ በገመድ መታሰር የለመደ ሕጻን  ዝሆን ነበር ሲል ጂም ሐሳቡን ይቀጥላል። ሕጻኑ በልጅነቱ የታሰረበትን ገመድ በጥሶ ለመሄድ አቅም አንሶት በእስራቱ ለዓመታት ቀጥሏል። በየጊዜው ገመዱን በጥሶ ለማምለጥ ሲሞክር ኖሮ ተስፋ ይቆርጣል። ዝሆኑ እያደገ ሲመጣ ግን እንኳን የታሰረበትን ገመድ ይቅርና ግዙፍ ዛፍን ታግሎ መጣል የሚችል አቅም ይፈጥራል። ከዓመታት በኋላ ዝሆኑ አድጎ ከገመዱ በላይ የሆነ አቅም ገነባ። ይሁን እንጂ ዝሆኑ ገመዱን በጥሶ ለማለፍ አልሞከረም። ለምን? በልጅነቱ ገመዱን መበጠስ እንደማይችል ሲለማመድ አድጓልና ነው። ጂም “የሰው ልጆችንም የሚገድቧቸው አስተሳሰቦች ልክ እንደዚያ ገመድ ናቸው” ይላል።

ጂም ክዊክ የሚገድቡንን አስተሳሰቦች እንዴት እንሻገር በሚል የመፍትሔ ሐሳቦችን ሰንዝሯል። የመጀመሪያው እውነቱን መረዳት ነው። ከሚሰማህ ነገር በላይ የምታየው እውነት ምንድን ነው? ለምሳሌ ሰው በተሰበሰበበት መድረክ መናገር ትፈራለህ እንበል። እናስ ከተናገርህ በኋላ ምን ተፈጠረ? ሰዎች ታስጠላለህ አሉህ? ወይስ መድረኩን ለቅቀህ ውጣልን አሉህ? በእርግጠኝነት ማንም አይልህም።

እናም ከዚህ ቀደም የገነባሃቸው ደካማ አስተሳሰቦች ምን ያህል በጆሮህ ሹክ እያሉ ገደብ እንደሰሩልህ ልብ በል ይላል ጂም። በመቀጠልም አዲስ እምነት መፍጠር የድንበር መስበሪያው ስልት ነው። አቅማችንን የሚገድቡት ሐሳቦች ምናልባትም “ሁልጊዜ” ወይም “በፍጹም” የሚሉ ሊሆኑ ይችላሉ። እዚህ ላይም ምሳሌ እናንሳ። ሁልጊዜ እደባደባለሁ ወይም በትምህርት በፍጹም አይሳካልኝም ብለህ ልታስብ ትችላለህ። ይህ ሐሳብ ግነት አለበት። አእምሮህ ነገሮችን እያጋነነብህ ነው እንጂ ሰው ሁልጊዜ ሰውን አይደባደብም ወይም ደግሞ በትምህርቱ በፍጹም ውጤት አልባ አይሆንም። ስለዚህም ትክክል የሆኑ  አዳዲስ  ሐሳቦችን በመፍጠር በጎታቾቹ ተካባቸው። በትምህርትህ ጥሩ ውጤት ያመጣህበትን ጊዜ አስታውሰው እስኪ። አዲስ እምነት ፍጠር። እናም እንዲህ በል” በትምህርቴ ሁልጊዜ “ኤ” አላመጣም፤ ጠንክሬ ባነብብ ግን “ኤ” የማምጣት እድሌን አሳድገዋለሁ”።

ጂም ኪዊክ በትምህርት ሒደት ሰባት ውሸቶችን እንጋፈጣለን ሲል ይጠቅሳቸዋል። እነዚህ ውሸቶች የሰው ልጅ ሙሉ አቅሙን እንዳይጠቀም ሰባራ፣ ሰንካላ የሚያደርጉት ናቸው። አስተውሎት የተገደበ ነው ብሎ አዕምሯችን ሊያስብ ይችላል፤ ግን ውሸት ነው። እናም አስተውሎቴ ያድጋል ብለህ ስራ እንዲያድግ አድርገው። ሁለተኛው ውሸት የሰው ልጅ የሚጠቀመው 10 በመቶ ብቻ አቅሙን ነው የሚለው ነው። ይህን ውሸት “እኔ በተቻለኝ መጠን ሙሉ አቅሜን  ለመጠቀም  እየተማርሁ ነው” ብለህ ተረዳው። ሦስተኛው ውሸት መውደቅ መሳሳት ነው የሚለው ነው። ይህን ውሸት በአዲስ አስተሳሰብ መተካት አለብህ። ስሕተቶች እየሞከርህ፣ አዲስ መንገድ ለማግኘት ጥረት እያደረግህ መሆንህን የሚያረጋግጡልህ ናቸው። መሳሳት ለመማር እድል ነው እንጂ ውድቀት ሆኖ አያውቅም።  ሕይወት ከሌሎች ጋር ፉክክር አይደለም፤ አንተ ራስህ ትናንት ከነበርህበት  ዛሬ የደረስህበት እንጂ።  መሳሳት ውድቀት እንዳይመስልህ፤ ውድቀትስ ለመማር አለመቻል ነው።

እውቀት ኀይል ነው የሚለው አራተኛው ውሸት ነው። እውቀት ገቢራዊ መሆን አለበት። እውቀት ብቻውን ቢሸከሙት ትርጉም አልባ ነው። ስለዚህ አንተ እውቀትን እና ድርጊትህን አጣምረህ በመኖር እሳቤህን ቀይር። አዲስ ነገሮችን መማር ከባድ ነው የሚለው አምስተኛው ውሸት ነው። እንዴት መማር እንዳለብህ ስትማር፤ የመማር ፈተናው መዝናኛህ ይሆናል። ቀላል ነው፤ ትደሰትበታለህ። የሰው ምላስ ክፉ ነው የሚለው ስድስተኛው ውሸት ነው። የሰዎች ትችት እና ነቀፌታ ብዙዎችን ሲሰብር አይተሃል። አንተ ግን ይህንን የሚገድብህን አመለካከት በአዲስ ተካውና ወደ ፊት ተራመድ። “እኔን መውደድ፣ ማድነቅ፣ እና ማክበር የሌሎች ጉዳይ አይደለም፤ የራሴ ሕይወት እንጂ” ብለህ አስብ።

የመጨረሻው እና ሰባተኛው አቅምህን የሚገድበው ውሸት ሊቅነት” ጂኒየስነት” በተፈጥሮ የሚገኝ ነው የሚለው ነው። ጭንቅላት በጥልቅ ሙከራ እና ድግግሞሽ የሚመጣ ነው ብለህ በአዲስ አስተሳሰብ ቀይረውና የታሰርህበትን ገመድ በጥሰህ ተራመድ።

የሰው ልጆች አቅማቸውን የሚገድቡባቸውን እንቅፋቶች ከለዩ በኋላ መነሳሳት ውስጥ መግባት አለባቸው። መነሳሳትም ለምን የሚልን ጥያቄ በመፍታት መጀመር አለበት። ተነሳሽነት የዓላማ፣ የአቅም እና ትናንሽ ድርጊቶች ውጤት ነው። ዓላማችን አንድን ነገር ለምን እንደምናደርገው ግልጽ መልስ ይሰጣል። አቅማችን ደግሞ አዕምሯችን እና ሰውነታችን ተባብረው ለድርጊት እንዲተጉ ያደርጋሉ። ጠብታ ውኃ አለት ትሰብራለች እንደሚባለው በሒደት የገነባናቸውን ትናንሽ የሚገድቡ አመለካከቶች  በአዲስ መተካትም ሒደትን ይጠይቃል።

የሰው ልጆች በአኗኗራችን የፈጠርናቸው አቅማችንን የሚገድቡ አመለካከቶች ለመለወጥ ጊዜ እና ጥረት ይፈልጋሉ። የሚከፈለውን ዋጋ ከፍለን ከለወጥናቸው የሕይወት ዘመናችንን መልካም የሚያደርጉ ናቸው። የምንፈልገው እምነታችን እኛን እንዲገልጸን መፍቀድ የራሳችን ምርጫ ነው። እምነታችንን መለወጥ፣ አስተሳሰባችንን መቃኘት፣ ድርጊት ውስጥ መግባት፣ አዎንታዊ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር  መዋል፣ በራስ ላይ መስራት፣ የታሰርንባቸውን ጎታች ገመዶች በጥሰን የልባችንን መሻት እንድናገኝ ያግዙናል ሲል ለርን ማይንድ ፖዎር  አስፍሯል።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የታኅሳስ 28  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here