ማዕከሉ ለሕዝብ ቅሬታ ምላሽ እየሰጠ ነው

0
32

ተቋማት ለሕዝብ የሚሰጡት አገልግሎት መጉላላት የበዛበት፣ የጊዜ ወርቅነት የተረሳበት፣ ሁሉም በእኩል የማይስተናገድበት እና የእጅ መንሻ የሚዘውረው ሆኖ ያለፉትን ዓመታት ተሻግሯል፡፡ ዓለም ወደ አንድ መንደር እየመጣ ባለበት በዚህ ዘመን እንኳ ዜጎች ባሉበት ሆነው መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ማግኘት የማይችሉበት አሠራር ሥር የሰደ ችግር ሆኗል፤ እነዚህ ሁሉ ክፍተቶች እንደ ሀገር ዕድገትን ለማረጋገጥ ፈተና ይሆናሉ፡፡

አገልግሎት ሰጪ ተቋሙም ዛሬ መወጣት የነበረበትን የሥራ ኃላፊነት በሰበብ አስባቡ ወደ ነገ በመግፋቱ መንግሥት በዕቅዱ መሠረት እንዳይጓዝ ያደርገዋል፡፡ ይህም ምርታማነትን ይገድባል፤ ዕድገትን ይጎትታል፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሥር ሰደው ሀገር ቀውስ ውስጥ እንድትገባ ያደርጋታል፡፡

ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አገልግሎት ፖለቲካዊ ቀውስ ሲያጋጥም ሀገራትን የሚያስተዳድር፣ ገበያ ሲናጋ ልማትን የሚያቀርብ፣ ሥርዓት ሲደክም ታማኝነትን የሚገነባ፣ በአጠቃላይ የሀገራት የተደበቀ ሞተር፣ የአመራር ነፍስ እና የሰውነት ቅርስ ማሳያ ነው፡፡

የሕዝብን አገልግሎት ቀዳሚ አጀንዳቸው ያደረጉ ሀገራት ከውድቀት ወጥተዋል፡፡ ለአብነት ጃፓን ከ1945 እ.አ.አ በኋላ እንደገና የተገነባችው፣ ሲንጋፖር ከትንሽ ወደብነት ወደ ዓለም አቀፍ ማዕከልነት የተለወጠችው፣ ሩዋንዳም ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ካደረሰባት ስብራቷ የተፈወሰችው ጠንካራ የሕዝብ አገልግሎትን በማስፈናቸው ነው።

የዘመናዊት ሲንጋፖር መሥራች እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሊ ኩዋን ዩ የሲንጋፖርን ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በመገንባት እና ብቃትን በሕዝብ አስተዳደር ውስጥ በማስገባት ዛሬ በአርዓያነት የምትጠቀስ አድርገዋታል፡፡ “ንጹህ እና ውጤታማ መሆንን መረጥን፤ ያ ውሳኔ ሁሉንም ነገር ለወጠው” በማለት ነው እንዴት ሲንጋፖርን እንደገነቧት የተናገሩት፡፡

ሲንጋፖር ዛሬ በዓለም ላይ ለሚገኙ ሀገራት ተሞክሮ መሆን የሚችል የሲቪል ሰርቪስ አሠራር ባለቤት ሆናለች፡፡ ብቃትን መሠረት ያደረገ አስተዳደርን ከመገንባት ጀምሮ አገልግሎት ሰጪ አካላት በሙስና እንዳይታለሉ የተሻለ ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅምን ተግባራዊ አድርጋለች፡፡ ጠንካራ የሙስና መከላከያ እርምጃዎችን መውሰዷ፣ ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን እና ቴክኖሎጂን መጠቀሟ ለውጤታማነት አብቅቷታል፡፡

የሕዝብ አገልግሎት የአስተዳዳሪነት ጥበብ የሚገለጥበት እና ዕሴቶችም ወደ ተግባር የሚለወጡበት ነው። እነዚህ አሠራሮች ሲናበቡ እና ሲመጋገቡ ደግሞ የሕዝብ እርካታ ከፍ ብሎ ይወጣል፡፡ ለሕዝብ የሚሰጥ አገልግሎት የሰብዓዊነት የደም ሥር መሆኑ በተግባር የሚረጋገጥበት እንደሆነም ነው መረጃው ያነሳው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀገራችን የሚታየውን ስር የሰደደ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለማረም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ አስተዳደራዊ ችግሮች በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል አለመተማመንን የሚፈጥሩ እንዳይሆኑ፣ ውጤታማ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን፣ ተገልጋይም በመጣበት ቅጽበት ተስተናግዶ የሚመለስበትን የአገልግሎት አሰጣጥን ለመፍጠር ትኩረት መሰጠቱን አክሏል፡፡

የአንድ መሶብ አገልግሎት ደግሞ ዋነኛው ነው፤ አሠራሮችን በቴክኖሎጂ በማዘመን ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ከብልሹ አካሄዶች የጸዳ ማድረግን ግብ ያደረገው አሠራሩ ሕዝብ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍ ያለ እርካታ እንዲኖረው ለማስቻል ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል ነው የተባለው፡፡

የአማራ ክልልም በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የተቀላጠፈ እና በዘመናዊ መንገድ የታገዘ አሠራርን ለመስጠት ለአንድ ማዕከል የመሶብ አገልግሎት ትኩረት ሰጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም እንደ ክልል እንዲሁም በባሕር ዳር ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁትን ጨምሮ በሌሎችም ለማስፋት በትኩረት እየተሠራበት ይገኛል፡፡

የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ተገልጋዮችን ከእንግልት እና ካልተፈለገ ወጪ እየታደገ መሆኑን ደግሞ በማዕከሉ እየተገለገሉ ያገኘናቸው ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው አባት አያሌው አንዱ ነው፡፡

የአንድ ማዕከል የመሶብ አገልግሎት ለተገልጋዩ ትልቅ እፎይታን የሰጠ ነው ያለው ነዋሪዉ ወደ ማዕከሉ የመጣው የመንጃ ፈቃድ ለማሳደስ መሆኑን ነግሮናል፡፡ ነዋሪው እንዳለው በቀደሙት ጊዜያት መንጃ ፈቃድ ለማውጣት እና ለማሳደስ ረጅም ጊዜ መጠባበቅ ግድ ይል ነበር፡፡ ተራ መጠበቅ፣ መብራት የለም የሚል ምክንያት፤ አገልግሎት የሚሰጥ ሰው (ባለሙያ) የለም እና ሌሎችም ሰበቦች ፈተና እንደነበሩ አስታውሷል፡፡ የአንድ ማዕከል ግን ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥበት መሆኑ እንዳስደሰተው ተናግሯል፡፡ “መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለሕዝብ ቅሬታ እና ምሬት ምላሽ የሰጠ ታላቅ የለውጥ መንገድ ነው፤ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” ብሏል፡፡

አገልግሎት ለማግኘት ወደ ማዕከሉ መጥታ ያገኘናት የይልማና ዴንሳ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ይርበብ ፈጠነ በበኩላቸው ማዕከሉ ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ይደረግ የነበረውን እንግልት የሚያስቀር መሆኑን አንስተዋል፤ እርሳቸውም በማዕከሉ ያለ ውጣ ውረድ እና እንግልት በአጠረ ጊዜ መስተናገዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ኢትዮ ቴሌኮምን እና የባንክ አገልግሎትን ጨምሮ 11 ተቋማት መግባታቸውን እና 48 አገልግሎቶች በመሰጠት ላይ መሆናቸውን የስማርት ባሕር ዳር ፕሮጀክት ጽ/ቤት ተወካይ አስተባባሪ ሰውነት አስማረ ተናግረዋል፡፡ ተቋማትን ወደ ማዕከል ከማስገባት ባሻገር ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡

ማዕከሉ ብዙ አገልግሎቶችን  ከመስጠት በተጨማሪ ተገልጋዮች አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ አግኝተው እንዲመለሱ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይም ጥናት እየተደረገ ተጨማሪ አገልግሎቶችን ለማስገባት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ተማረ አቤ የክልሉ መንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥን የፈተሸበት አሠራር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ዋና አገልግሎቶችን እና እርስ በእርስ የሚተሳሰሩ ተቋማትን በአንድ ቦታ ለመስጠት የተቋቋመ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፍጥነት እና የሥራ ጥራት ተጨማሪ አበርክቶው ነው፡፡ ይህም ተገልጋዩን ከእንግልት ከመታደግም ባለፈ የጊዜ ብክነትን በእጅጉ የሚቀንስ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

በመስከረም ወር መግቢያ 2018 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት 10 የክልል እና አራት የፌደራል ተጠሪ ተቋማት ወደ ማዕከሉ ገብተው ለተገልጋዮች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የሥራ እና ክህሎት፣ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት፣ የመሬት፣ የገቢዎች፣ የማዕድን ሀብት፣ የትምህርት፣ የፍትሕ፣ ኢሚግሬሽን፣ የፖስታ አገልግሎት፣ የከተማ ልማት፣ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ፣ የሲቪል እና የቤተሰብ ምዝገባ፣ የንግድ እና ገበያ ልማት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሌሎችም በማዕከሉ ሥራ የጀመሩ ተቋማት እና አገልግሎቶች ናቸው፡፡

አስተባባሪው እንዳሉት ተቋማት ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ የተደረጉት ጥናት ተደርጎባቸው ነው፡፡ ብልሹ አሠራር፣ ቅሬታ እና አቤቱታ የሚበዛባቸው፣ ተገልጋዮችን ለእንግልት የሚዳርጉ ዘርፎች ወደ ማዕከሉ እንዲገቡም ተደርጓል፡፡

ማዕከሉ በተሟላ ቴክኖሎጂ ታግዞ አገልግሎቶችን ከመስጠትም ባሻገር ከሙስና እና ከብልሹ አሠራር የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት የተደራጀ ነው፡፡ አገልግሎቶችን በአካል ከመስጠት በተጨማሪ  በበይነ መረብ የታገዘ አሠራርም ተዘርግቷል፡፡

በየዕለቱ አገልግሎት ያገኙ ደንበኞች መረጃ እንደሚያዝ ያስታወቁት አስተባባሪዉ፣ ባለፉት ሁለት ወራት ከአምስት ሺህ በላይ ደንበኞች በማዕከሉ አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ማዕከሉን የማስተዋወቅ እና የግንዛቤ ሥራ አለመሠራቱ በማዕከሉ የሚገለገሉ ደንበኞች ቁጥር በሚፈለገው ልክ እንዳይሆን እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ማዕከሉን የማስተዋወቅ ሥራ እንዲሠራም ጠይቀዋል፡፡

የአገልግሎት ጥራት የማዕከሉ መለያ ነው ያሉት አስተባባሪው፣ ለዚህም ተገልጋዮች ተገቢ እና ፈጣን አገልግሎት ማግኘት እና አለማግኘታቸው በየጊዜው ክትትል እንደሚደረግ ነው ያስታወቁት፡፡  የአስተያየት እና የጥቆማ መቀበያ አማራጮችም መኖራቸውንም አክለዋል፡፡

የመሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ የባሕር ዳር ከተማን የልማት ሥራዎች ጎብኚተዋል፡፡ በዚህ ወቅት የክልሉ ሕዝብ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ዘመናዊ አሠራርን መከተል ግዴታ መሆኑን የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና ሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ባንችአምላክ አንስተዋል፡፡ ለዚህም ትልቁ መፍትሄ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መሆኑ ታምኖበት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋት እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የክልሉን የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጨምሮ የባሕር ዳር እና ደሴ ከተሞች የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ ተጠናቅቆ ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል። በጎንደር ከተማም በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

በቀጣይም በክልሉ የተለያዩ ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ አንስተዋል፡፡ ከቴክኖሎጂ እና ከተቋም ግንባታ በተጨማሪ የሠለጠነ እና ተቋማቱን የሚመጥን የሰው ኀይል የማሟላት ሥራም ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል፡፡

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሕዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here