ማዜ ብሔራዊ ፓርክ

0
48

ፓርኩ በደቡብ ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ክልል በጋሞ ጐፋ ዞን ነው የሚገኘው፡፡ ከአዲስ አበባ 460 ኪሎ ሜትር  ርቀት ላይ ነው የተከለለው፤ አጠቃላይ ስፋቱም 210 ካሬ ኪሎ ሜትር ተለክቷል፡፡

በፓርኩ ቀጣና ከሚገኙት ወንዞች ትልቁ ማዜ ሲሆን የፓርኩ ስያሜም ይህንኑ መነሻ ያደረገ ነው፡፡ የምስረታ ጊዜው 1997 ዓ.ም ወይም 2005 እ.አ.አ ነው፡፡ ለምስረታው ዋነኛው መነሻ ምክንያት ለአደጋ የተጋለጠውን አጋዘን መሰል “ስዋይን ኸርት ቢስት”ን ለመጠበቅ መሆኑ ነው ለንባብ የበቃው – በድረ ገጹ፡፡

በፓርኩ ክልል መካከለኛ እና ከፍያለ የአካል ግዝፈት ያላቸው 39 የዱር እንስሳት ተመዝግበዋል፡፡ ከነዚህ መካከል “ስዋይን ኽርት ቢስት” ጐሽ፣  አቦሸማኔ፣ ዝንጀሮ፣ የዱር አሳማ እና ጦጣ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከዓእዋፍም 196 ዝርያዎች መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ በየወንዞቹ ዓሣ መኖሩም ተጠቅሷል፡፡

በፓርኩ ክልል እንደ መልካምድራዊ አቀማመጡ የሚገኙት የዕፅዋት ዝርያዎችም የተለያዩ ናቸው፡፡ ከፍታ ባላቸው ቀጣናዎች ደን፣ መካከለኛ ከፍታ ባላቸው ቀጣናዎች ቁጥቋጦ እና ዝቅ ያለው ደግሞ ሳር ለበስ ነው፡፡

ፓርኩ በብዝሃ – ህይወት ሀብት የታደለ ሲሆን ከመሬት ወለል ከ1000 እስከ 2000 ሜትር ከፍታ ያለው መሆኑ ለምቹነት አብነት ሆኖ ተጠቅሷል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ በፓርኩ ቀጣና የሚኖሩ የጋሞ ህዝብ አኗኗር፣ ባህላዊ ክዋኔዎችን ለመቃኘት የተመቸ ነው፡፡

ማዜ ብሔራዊ ፓርክ ለመድረስ ከአዲስ አበባ ቦሌ ተነስቶ አርባ ምንጭ በአውሮኘላን ከዚያም 95 ኪሎ ሜትር በተሽከርካሪ መጓዝን ይጠይቃል፡፡ ለጐብኚዎች ማረፊያ ሎጂ እና የድንኳን ሰፈርም አለው፡፡

ለዘገባችን ኢትዮጵያን ዋይልድ ላይፍ፣ ናሽናል ፓርክ  አሶሴሽን እና ፊልም ፊክሰር ድረገፆችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here