ማጠር መፍትሄ አይሆንም!

0
130

በዚህ የሃሳቤ አምድ ለመጻፍ መነሻ የኾነኝ ጥላሁን ወንዴ “ታጠርን” በሚል የፃፈው እና በኩር መስከረም 20/2017 ዓ.ም ይዛው የወጣችው ጽሁፍ ነው:: ጥላሁን እርሱ ካደገበት  ባሕል እያፈነገጥን መውጣታችንን መነሻ እድርጎ በየሰፈራችን የተፈጠረው የብረት ፍርግርግ አጥር የቀጣይ የኑሯችን የሥጋት ምንጩ እንደኾነ ይገልጻል::

መነሻ ሥጋቱ ልክ ነው ብየ ብስማማም የሥጋቱን ምንጭ ባግባቡ አልገለፀም ብዬ አስባለሁ፤ ምክንያቱም የእንጨት እና የብረት አጥር መነሻውም መድረሻውም ፍርሀት ነው ብዬ ሥለማስብ ነው:: ፍርሃት በተለያየ መንገድ የሚፈጠር አይነተ ብዙ ነገር መኾኑን የሥነልቡና ባለሙያዎች በተለያየ መንገድ ይገልጹታል:: መነሻው ምንም ይሁን ምን የፍርሃቱ መሠረታዊ ምንጭ በግለሰቡ ላይ ሥነልቡናዊ ቀውስ መድረሱን ግን አስረግጠው ይነግሩናል፤ አንዳንዴም ችግሩ ሲሰፋ የማኅበረሰብ ይኾናል ይሉናል::

እንደኔ በእኛ ድህነት አንዱ የሥነልቦና ችግር መነሻ ይመስለኛል፤ ድህነታችን በተለያየ መንገድ እየተመነዘረ ከአካላዊ ባለፈ አዕምራዊ ጥቃቱን እያሰፋብን መጥቷል::

የአሁኑ ዘመን የሰፈር አጥር ከኢትዮጵያዊነት ሥነምግባር የወጣ፣ የሕግ የበላይነት አለመረጋገጥ እና በማሕበራዊ ሚዲያ ሸቃጮች በሚነዛ የሃሳብ ሸቀጥ ምክንያት በሐገራችን ከሚመለኩ ሐይማኖቶች ሥርዓት ያፈነገጠ ጉዳይ ነው:: የሰፈር አጥር ማጠር ልማድ የሆነው የሕግ የበላይነት ባለመቀበሉ፣ የሌሎችን መብት በመጣስና የግል ጥቅሙን በማግበስበሱ እንደ ጀግና የሚቆጠር ሰው እየተበራከተ በመምጣቱ ነው ብዬ አስባለሁ::

ጥላሁን መንገዶች የማን ናቸው ብሎ ይጠይቃል፤ ጥያቄው ለውይይት መነሳቱ ልክ ነው:: ነገር ግን መንገዶች የተሠሩት ማሕበራዊ አገልግሎት እንዲሠጡ፣ ማሕበረሰቡ የተመቸ የመኖሪያ እና የሥራ አካባቢ እንዲኖረው ታስቦ ቢኾንም የሕግ የበላይነትን የሚያስከብር የሕግ አካል በተለያየ መንገድ ሥራውን እንዳይከውን በመደረጉ እንደ ድሮው “በሕግ አምላክ” ብለን መብታችንን ማስከበር ባለመቻላችን እንዲሁም አቤት ብለን የምንደመጥበት የፍትሕ አደባባይ እንደ ፍላጎታችን ባለማግኘታችን የመጣ ችግር በመኾኑ ሰፈርን አጥሮ ቀድሞ መከላከልን አንድ አማራጭ እንድናደርግ አስችሏል ብዬ አስባለሁ::

አንዳንድ ግለሰቦች ገንዘብን ለማግኘት ብቻ በማሰብ በተለያዩ የማሕበራዊ ሚዲያዎች የተዛባ መረጃን በማቅረብ  በኅብረተሰቡ ላይ የፍርሃት ቆፈን እንደ ኩንታል እንዲጫነው በማድረጋቸው ማኅበረሰባዊ እሴቶቻችን እንዲሸረሸሩ አድርጎናል::

መረን የለቀቀ የሚዲያ አጠቃቀም መኖር ሕዝባዊ አንድነታችንን በመፈረካከስ ማሕበራዊ እሴቶቻችን እንዲዳከሙ አድርጓል፤ የማሕበራዊ እንቅስቃሴ እንደ ማሽን ጥርስ ተስተካክሎ እና ዙሩን ጠብቆ መሽከርከር ካልቻለ፤ በተለይም ደግሞ ጥርሶቹ ከተሸራረፉ ወይም ከተሰበሩ የማሽኑ ዙር እየተንገጫገጨ ሌላውን የማሽኑን ክፍል እንዲሰበር ብሎም ሥራ እንዲያቆም እንደሚያደርገው ሁሉ የማኅበራዊ እንቅስቃሴን የሚያውኩ፣ ብሎም የሚያዛቡ፣ ከማኅበራዊ እሳቤ የሚያስወጡ እንቅስቃሴዎች በተበራከቱ ቁጥር የማኅበረሰብ ኑሮ እክል ይገጥመዋል፤ የወደፊት ጉዞውም በሥጋት ውስጥ ይወድቃል:: አለፍ ሲልም ሊቋረጥ ይችላል ይላሉ የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁራን:: እኛም እየገጠመን ያለው የማኅበረሰብ አዙሪት ምስቅልቅሎሽ በየጊዜው የሚፈጠሩ የማኅበረሰብ ሳንካዎች ወዲያው መፍትሔ ሳይሰጣቸው መቅረት እና ለኢትዮጵያውያን የመኖር እሴቶች ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱትና መሠረት የኾኑት የሐይማኖት ተቋማት እና የፍትሕ ተቋማት ሚናቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ እየተደረጉ መምጣታቸው ነው ለዚህ ችግር የዳረገን::

በተደጋጋሚ የሚነገሩ የ “እኛ እና እነሱ’’ ፍልስፍናዎች እርስ በእርስ ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅን፣ አንድነታችንን ከማጠንከር ይልቅ ልዩነታችን እንዲጎላ በማድረጋቸው አዕምሯችን በፍርሃት ሥነልቡና እንዲዋጥ፣ የሰው ልጅ ለሰው ጥላ እና ከለላ ከመኾን ይልቅ የሥጋት ምንጩ እንዲኾን አድርጎታል:: ከዚሀ በፊት የሰው ልጅ ጌታ እና ባሪያ፣ ጭሰኛ እና ባላባት፣ ሃብታም እና ድኃ፣ ወዘተ … እየተባለ ይደርስበት የነበረውን የእኛ እና እነሱ የማኅበረሰብ ክፍፍል አሁን ደግሞ የቋንቋ ልዩነትን መሠረት ያደረገ የብሔር ልዩነት ፈጥሮ ግጭት እንዲባባስ እና ሰላማችንን እንድናጣ በመደረጉ አይደለም በሰፈራችን የአስተዳደር ወሰንን የተሻገረ ግጭት በማስነሳት ዘመዶቻችን የጥይት እራት እንዲኾኑ፤ ሕይወታቸውን እንዲያጡ፣ ለስራ መዋል የነበረበትን ጉልበት፣ ገንዘብ እና ጊዜን ለጦርነት እንድናውል በመደረጉ ከድህነታችን ላይ ሌላ ድህነትን እንድንጨምር እና ኑሯችንን የሥጋት እንዲኾን አድርጎታል::

አሁንም ቢኾን ከችግሩ ለመውጣት በብረት አጥር ሠፈርን ማጠር ሳይኾን የእኛና እነሱ አጥርን የሚያፈርስ ስብእናን መገንባት ወደር የማይገኝለት ሥራ ነው፤ ክፉው የእንጨት እና የብረት አጥር ሳይኾን በሥጋት ሥነልቡና የተሞላ አዕምሮ ነው:: የገንዘብ ድህነት በሥራ፣ የብረት አጥር በእርስ በእርስ መተማመን ይቀየራል፤ ጠንክሮ የሠራ ድህነትን ያሸንፋል፣ የብረት አጥርም ከብረት አጥር ይልቅ መተማመን የተሻለ ደህንነታችንን እንደሚያስጠብቅልን በማወቅ እንደሚፈርስ ልንረዳ ይገባናል::

ፍሬአለም ሽባባው “ሀገር በአንድ ሽ ቀን” በሚለው መጽሃፏ ላይ የሰው ልጅ የመጀመሪያው ኀላፊነት ራስን መቻልና ሕይወትን በሥርዓት መምራት ነው:: ከዚያ ካለፈ ደግሞ አካባቢን ወደ ተሻለ ነገር መቀየር ነው:: ይህን ስብእና የሚያገኙት ደግሞ በልጅነታቸው በሚያገኙት እንክብካቤ እና ስልጠና ነው ትላለች:: እንደ ፍሬዓለም ገለጻ የጥላቻ እና የክፋት ሥራዎችን ከመሥራት ይልቅ ለሕዝብ ማገልገል፣ ሌሎች እንዲጠቀሙ ማድረግ፣ በጎነት እና ሌሎች የሠሩትን መልካም ሥራ እንኳን ለማስተዋል አቅምን ይጠይቃል ትላለች:: እንደ እርሷ እሳቤ ጥፋት፣ ሥጋት መፍጠርና ክፋት ከእውቀት ነፃ የኾነ ማንኛውም ሰው እየተነሳ የሚሠራቸው ሲኾን መልካም ሥራ ግን  አቅምን የሚጠይቅ እንደኾነ ታስረዳናለች::

ሥለዚህ ከብረት አጥር ይልቅ የሚያስፈራውን የአዕምሮ አጥር በማፍረስ ልጆቻችንን በጥሩ ስነምግባር በማነጽ፣ በቤታችን፣ በሠፈራችንና በሐገራችን ላይ የሰላም አየር እንዲነፍስ ማድረግ

እንችላለን:: ይህን ማድረግ ካልቻልን በብረት አጥር መታጠር ብቻ ሳይኾን በጥላቻ ቁልፍ ጭንቅላታችንን መቆለፉ ስለማይቀር አደጋው የከፋ ይኾናል:: ከብረት አጥር ይልቅ የተቆለፈ አዕምሮ ያስፈራል፤ ከተዘጋ የእግረኛ መንገድ ይልቅ መፍትሄን ማመንጨት የማይችል ጭንቅላት ያስፈራል::

ወደድንም ጠላንም ሠፈራችንን በብረት አጥር ብናጥርም ባናጥርም የአካባቢያችንን ሰላም የሚያስጠብቅልን እና ደህንነታችንን የሚያረጋግጥልን በጥሩ ሥነልቡና የጠነከረ፣ ከሥራ የዘለለ አማራጭም አቋራጭም መንገድ እንደሌለ የሚረዳ ኅብረተሰብ መፍጠር እንዳለብን ሥንረዳ ብቻ መኾኑን ልናውቅ ይገባል:: በተለያዩ ጊዜያት እየሰማናቸው እና እያየናቸው እንደዋዛ ያሳለፍናቸው ጉዳዮች እንደልማድ እንዲሁም እንደ መደበኛ ኑሮ ተወስደው አሁን ልንቋቋማቸው በማንችላቸው ሁኔታ በመስፋፋታቸው ነው ሰፈራችንን ለመጠበቅ ወደ ብረት አጥር የወሰደን:: ስለዚህ አሁንም ጊዜው ገና በመኾኑ ሳንሰለች እና ጊዜ ሳንወስድ ልንሠራበት ይገባል:: እንደቀልድ የሚመስል ስሰማው ያስገረመኝን አንድ ታሪክ ልንገራችሁ እና ጽሁፌን ልቋጭ::

ወደ ቀድሞው የባሕር ዳር አውቶብስ መናኽሪያ መልእክት ለመላክ በሔድኩበት ጊዜ የመጓጓዣ ታሪፍ ከተለመደው ጨምሯል፤ ፖስታ ለመላክም ያላግባብ እንዲከፈል እየተደረገ መኾኑን ተመለከትኩ:: ምክንያቱ ምን እንደኾነ ስጠይቅም አንዱ የሚኒባስ ረዳት እኛም ክፍያ ቢበዛብን ነው አለኝ፤ ነገሩን ለማጣራት እንዴት ብዬ ጥያቄ አነሳሁ፤ ከዚህ መናኽሪያ ይጀምራል ብሎ ወጉን ቀጠለ:: “የመውጫ ተብሎ ለመንግስት በደረሰኝ እንቆርጣለን፣ ከአጥሩ ሳንወጣ የባለመሬት ተብሎ መናኽሪያው ከመሠራቱ በፊት መሬቱ የእኛ ነበር ያሉ ጎረምሶች ደግሞ ’’የባለ መሬት’’ ብለው 200 ብር ይቀበሉናል:: ከዚያም በየመንገዱ ኬላ የጣሉ ደግሞ በሰበብ እያስከፈሉን ነው የምንሄደው:: ለባለቤቱ ምን እናስረክበው?” ብሎ ሲነግረኝ ከዚህ በፊት ከሰማኋቸውና እየለመድኳቸው ከመጣኋቸው ጉዳዮች ሁሉ ወደ ከፋ ነገር እየመጣን መኾኑ ገባኝ፤ ግን አሁንም ምላሽ የለኝም፤ የፍርሃቴን መጠን ከመጨመር ውጭ::  ስለዚህ አብረን ዝም እንበል ብንልም አይቻልም፤ ብንጮህም ሰሚ የለም፤ የተሻለው ለቀጣዩ አብረን ተባብረን ጥሩ የሚባል ስብእና መገንባት ነው ብዬ አስባለሁ::

(አዲሱ ታደገኝ)

በኲር ጥቅምት 4  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here