የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ በአሜሪካ፣ካናዳ እና ሜክሲኮ አስተናጋጅነት ከሁለት ዓመታት በኋላ ይከናወናል። ሀገራትም በእግር ኳስ ድግሱ ለመሳተፍ የማጣሪያ ውድድሮችን እያከናወኑ ነው። በሦስት ሀገራት በሚደረገው በዚህ ግዙፉ የዓለም የእግር ኳስ መድረክ 48 ሀገራት ይሳተፉበታል። ከእነዚህ መካከል ዘጠኙ የአፍሪካ ሀገራት እንደሚሆኑ የዓለም የእግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ (ፊፋ) መረጃ ያመለክታል።
በመድረኩ ለመሳተፍም የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ውድድሮች በስምንት ምድብ ተከፍለው ነው እየተከናወኑ ያሉት። እንደ ፊፋ መረጃ ምድባቸውን በበላይነት የሚያጠናቅቁ ሀገራት በቀጥታ በዓለም ዋንጫው የሚሳተፉ ይሆናል። ሁለተኛ ሆነው የሚጨርሱት ደግሞ እርስ በእርሳቸው በጥሎ ማለፉ ተገናኝተው በመጨረሻ አሸናፊው ሀገር ዘጠንኛ ሆኖ በዓለም ዋንጫው ይሳተፍል።
በአሰልጣኝ ገብረ መደህን ኃይሌ የሚመራው የኢትዮጵያ በሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫው ለመሳተፍ ማጣሪያውን እያከናወኑ ከሚገኙት ቡድኖች ውስጥ አንዱ ነው። አሰልጣኝ ገብረ መድህን የማጣሪያ ውድድር ከመጀመሩ ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ነበር በወርሃ ጥቅምት መጨረሻ አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ተክተው የተሾሙት። አሰልጣኙ ቡድኑን ሲረከቡ ተፎካካሪ፣ ጠንካራ እና ጥሩ እግር ኳስ የሚጫወት ቡድን መገንባት የተሰጣቸው ኃላፊነት እንደነበር አይዘነጋም። በዓለም፣ በአፍሪካ እና በቻን የማጣሪያ ውድድሮች ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ግዴታ ተጥሎባቸው ጭምር ነው ሥራቸውን የጀመሩት።
ብሄራዊ ቡድኑ በምድብ አራት ከግብጽ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሴራሊዮን እና ጅቡቲ ጋር የማጣሪያ መርሀ ግብሩን እያደረገ ነው። እስካሁንም አራት ጨዋታዎችን አከናውኗል። ምንም እንኳ ዋሊያዎቹ ሁለቱን መርሀ ግብሮች በሜዳቸው ማድረግ ቢኖርባቸውም የካፍን የጥራት ደረጃ የሚያሟላ አንድም ስቴዲየም በሀገራችን ባለመኖሩ ሁሉንም ጨዋታዎች ከሀገር ውጪ አከናውነዋል።
በዚህም መሰረት ከሴራሊዮን ጋር በሜዳው ማከናወን የነበረበትን ጨዋታ ያለምንም ግብ ሲያጠናቅቅ በተመሳሳይ ከቡርኪናፋሶ ጋር በሀገር ውስጥ መከናወን የነበረበትን ጨዋታ ደግሞ ሦስት ለባዶ ተሸንፏል። ከጊኒቢሳው እና ከጅቡቲ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ደግሞ በአንድ አቻ ውጤት ማጠናቀቁ አይዘነጋም።
ዋሊያዎቹ ካለፉት አራት መርሀ ግብሮች ሦስት ነጥቦችን በመሰብሰብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ:: ግብጽ በአስር ነጥቦች ምድቡን እየመራች ነው። ጊኒቢሳው በስድስት ነጥቦች ሁለተኛ፣ ቡርኪናፋሶ በአምስት ነጥቦች ሦስተኛ፣ ሴራሊዮን በአምስት ነጥቦች አራተኛ እና ጅቡቲ ደግሞ በአንድ ነጥብ ግርጌ ላይ ተቀምጣለች። ኢትዮጵያ ሁለት ግቦችን ብቻ ስታስቆጥር አምስት ግቦች ደግሞ ተቆጥረውባታል።
ይህን ደካማ ውጤትም ብዙዎች እየተቹት ይገኛሉ:: የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከጅቡቲ ጋር አንድ አቻ መለያየቱ የሚታወስ ሲሆን ዋሊያዎቹ ከ38 ዓመታት በኋላ ነው ለተጋጣሚው ጅቡቲ እጅ የሰጡት። ይህን ውጤትም ብዙዎቹ የብሄራዊ ቡድኑን የውጤት ቀውስ ማሳያ ሲያደርጉት ይስተዋላል።
ብሄራዊ ቡድኑ በ2026ቱ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እያሳየ ያለውን አቋም በተመለከተ አሚኮ በኲር ስፖርት ዝግጅት ክፍል በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ አካዳሚ መምህር ከሆኑት ደምስ ጋሹ (ዶ.ር) ጋር ቆይታ አድርጓል።
የስፖርት ባለሙያው በየትኛውም መመዘኛ ብሄራዊ ቡድኑ በሁሉም የሜዳ ክፍል እየተሻሻለ ወይም እያደገ አለመሆኑን ያስረዳሉ። ከዚህ በፊት በመጀመሪያው የሜዳ ክፍል በቀላሉ ግብ የሚቆጠርበት፣ ግብ ከተቆጠረበት በኋላም በቀላሉ የሚረበሽ ነበር፤ ቡድኑ በቀላሉ የቆሙ ኳሶችን መከላከል የማይችል ጭምር ነበር።
የፊት መስመሩም ቢሆን ግብ የማስቆጠር ትልቅ ችግር እንደነበረበት በተደረጉ ጨዋታዎች ተመልክተናል። ከላይ የተጠቀሱት የብሄራዊ ቡድኑ የትናንት ችግሮች ዛሬም አለመቀረፋቸውን የስፖርት ባለሙያው ተናግሯል። ይህ ደግሞ ችግሮች ላይ መሰረት ያላደረገ የስልጠና እና የልምምድ ውጤት ነው ይላሉ፤ ደምስ ጋሹ (ዶ.ር)
ምንም እንኳ ብሄራዊ ቡድኑ ሜዳ ላይ በሚያሳየው እንቅስቃሴ እና ባስመዘገበው ውጤት ብዙዎች ቢተቹትም አሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌ ግን ውጤቱ እና የቡድኑ እንቅስቃሴ አስከፊ አይደለም እያሉ ነው። አሰልጣኙ ከጊኒቢሳው እና ከጅቡቲ ጨዋታ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ቡድኑ በመገንባት ሂደት ላይ ያለ በመሆኑ ብዙ ውስብስብ ችግር እየታየበት አለመሆኑን አስረድተዋል።
ኳስ ይዞ በመጫወት እና ፈጣን የሽግግር ሂደት ማድረጉንም በመልካም ጎኑ አንስተዋል። ረጅም ጊዜ የቆየው እና የብሄራዊ ቡድኑ የገነገነ ችግር ነው የሚባለው ግብ የማስቆጠር እና የመከላከል ችግር አሁንም አለመቀረፉን ግን አሰልጣኙ አልሸሸጉም።
አሰልጣኝ ገ/መድህን ቡድኑ በመገንባት ሂደት ላይ እና በመሻሻል ላይ ነው ቢሉም እንደ ስፖርት ሳይንስ ባለሙያው ደምስ ጋሹ (ዶር) ማብራሪያ ግን በውጤት ብቻ ሳይሆን በአጨዋወትም ተስፋ የማይጣልበት፣ ከመርህ ጋር የሚጣረስ፣ በተመሳሳይ የአጨዋወት ዘይቤ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ የሚገባ፣ የተጋጣሚ ቡድንን ከግምት የማያስገባ የጨዋታ ስልት ነው ባለፉት አራት ጨዋታዎች የታየው።
ይህም ብሄራዊ የቡድኑን ለዓለም ዋንጫ የማለፍ ዕድል የጠበበ አድርጎታል ብለዋል፤ ባለሙያው። አሰልጣኝ ገ/መድህን በክለብ ደረጃ ጥሩ ክብረ ወሰን ቢኖረውም በብሄራዊ ቡድኑ ግን ያስመዘገበው ውጤት እና የገነባው ቡድን አስደሳች የሚባል አይደለም።
በተመሳሳይ ጊዜ ብሄራዊ ቡድን እና ክለብ እንዲያስለጥን መፈቀዱ የችግሮች መንስኤ መሆኑን የስፖርት ባለሙያው ያምናል። ብሄራዊ ቡድን ለማሰልጠን የሚሾም አንድ አሰልጣኝ ትኩረቱ ኃላፊነት በተሰጠው ቦታ ብቻ እንዲሆን ሌላ ተጨማሪ ክለብ ማሰልጠን እንደማይችል በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ሕግ ተቀምጧል።
ትልቅ ትኩረት በሚፈልገው የእግር ኳስ ስፖርት ፌዴሬሽኑ ያስቀመጠውን ሕግ በመሻር አሰልጣኙን መቅጠሩ አይዘነጋም። ይህ ደግሞ ከብሄራዊ ቡድኑም ባሻግር በኢትዮጵያ መድን ውጤት ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮ ተመልክተናል።
ታዲያ በቀጣይ በሚደረጉ መርሀ ግብሮች ሀገራችንን የሚመጥን የተሻለ እንቅስቃሴ የሚያደርግ እና ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግብ ቡድን ለመገንባት እስካሁን የነበረውን ሂደት በሚገባ መገምገም ያስፈልጋል፤ የባለሙያው ምክረ ሀሳብ ነው። አንድ ወጥ ወይም ግትር የጨዋታ ስልት መጠቀም ዋጋ እንደሚያስከፍል ከዚህ ማጣሪያ ተመልክተናልና መታረም አለበት ብልዋል፤ ደምስ ጋሹ (ዶ.ር)::
ይህ ችግር በዋናው ብሄራዊ ቡድን ብቻ ሳይሆን በሁለቱም ፆታዎች፣ በሁሉም የእድሜ እርከን ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ባለሙያው ይናገራሉ። ይህ ደግሞ እግር ኳሱን የሚመራው አካል ድክመት መሆኑን ጨምር ተናግረዋል። የቆሙ ኳሶችን መከላከል፣ ያለባቸውን የትኩረት ማጣት ችግር መቅረፍ እና የአሸናፊነት ስነ ልቦናቸውን ከፍ ማድረግ በቀጣይ የአሰልጣኙ የቤት ሥራ ነው።
በሀገራችን አንድም ደረጃውን የጠበቀ የካፍን የጥራት መመዘኛ የሚያሟላ ስቴዲየም ባለመኖሩ ብሄራዊ ቡድኑ ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደረ ሌላኛው ምክንያት ተደርጎ ይነሳል። ዋሊያዎቹ በሜዳ እጦት ምክንያት ስደተኛ ከሆኑ ሰነባብተዋል። በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የማጣሪያ ውድድሮችን ከሀገር ውጪ ማድረጋቸውም አይዘነጋም።
ይህም ያለ ደጋፊ መጫወት ከሚያመጣው ተጽዕኖ ባለፈ የአየር ጸባዩም ሌላ ጣጣ ይዞ ይመጣል። ታዲያ የባሕር ዳርን፣ የአደይ አበባን፣ የድሬድዋን እና የአዋሳን ስቴዲየሞች በማጠናቀቅ ዋሊያዎችን ከስደት መመለስ ለነገ የማይባል ተግባር መሆን እንዳለበት ባለሙያው ጠቁመዋል።
በቅርቡ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ለኢቢሲ ስፖርት በሰጡት ቃለ ምልልስ እ.አ.አ በ2029 ወይም 2031 በፈረንጆች የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። ዋሊያዎችን ከስደት የሚታደግ አንድም ደረጃውን የጠበቀ ስቴዲየም ሳይኖር እና ሰቴዲም ለማደስ ዓመታትን በሚፈጅበት ሀገር ጥራት ያለው አራት እና አምስት ስቴዲየም የሚያስፈልገውን ግዙፍ የእግር ኳስ ድግስ ለማዘጋጀት ማሰብ ግን ትንሽ ግርታን ይፈጥራል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ደረጃውን የጠበቀ ስቴዲየም መገንባት የቅንጦት አለመሆኑን የሚመለከተው አካል ሊያስብበት ይገባል።
ዋሊያዎች በሴራሊዮን እና በቡርኪናፋሶ ባደረጉት ግጥሚያ ብዙ ተመልካች እንዳልነበር የኦል አፍሪካ ዶት ኮም መረጃ ያሳያል። ከሴራሊዮን 50 ከቡርኪናፋሶ ደግሞ 385 በድምሩ 435 ተመልካች ብቻ ሁለቱን መርሀ ግብር ተከታትሎታል። ደረጃውን የጠበቀ ስቴዲየም አለመኖር ዋሊያዎቹን የተመልካች ድሀ ከማድረጉም በተጨማሪ ፌዴሬሽኑ የሚያገኘውን ገቢ አሳጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባሳለፍነው ህዳር ወር ከሴራሊዮን እና ከቡርኪናፋሶ ጋር በሞሮኮ ቤን መሀመድ ኤል አብዲ ስቴዲየም ነበር ጨዋታውን ያደረገው።
ከሞሮኮ አቻው ጋር በፈጠረው መልካም ግንኙነት የሆቴል፣ የስቴዲየም እና ሌሎች ወጪዎች እንደተሸፈኑለት እና ወደ ገንዘብ ቢቀየር 70 ሺህ የአሜሪካን ዶላር እንደሚገመት በወቅቱ ፌዴሬሹኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ መገለጹ ይታወሳል።
የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በቀጣይ 2017 ዓ.ም መጋቢት ወር የሚደረግ ሲሆን ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር መርሀ ግብሯን የምታከናውን ሲሆን ቀሪ መርሀ ግብሮች ደግሞ በ2018 መስክረም ወር የሚደረጉ ይሆናል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም