የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በመጪው ክረምት ወቅት የሚጠበቀውን የአየር ጠባይ ትንበያ ይፋ አድርጓል:: የክረምት ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የሰሜን፣ ሰሜን ምዕራብ፣ የደቡብ ምዕራብ፣ የመካከለኛው፤ የሰሜን ምሥራቅ እና የምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ አስታውቀዋል።
ተቋሙ አያይዞ እንዳስታወቀው አልፎ አልፎ ከሚኖረው ተደጋጋሚነት ያለው ከባድ ዝናብ ጋር በተያያዘ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑት ረባዳማ ቦታዎች የወንዝ ዳርቻዎች እና በከተሞች አካባቢ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሥራዎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ እንዲያስችል አስፈላጊውን የጥንቃቄ ሥራ ከወዲሁ በቅንጅት መከናወን እንዳለበት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጠው መረጃ አስገንዝቧል።
በባሕር ዳር ከተማ የጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ባይህ ዘርይሁን በከተማዋ ከፍተኛ ዝናብ ሲኖር በተለይም ጉዶ ባሕር አካባቢ ውኃ ከሞላ ከፍተኛ ጎርፍ ማስከተሉ የሁልጊዜ ችግር ነው:: በመሆኑም ለውኃ ማስተንፈሻ ተብለው የተሠሩ ማፋሰሻዎችን ከተማ አስተዳደሩ ተከታትሎ እንዲያስከፍት ጠይቀዋል::
በዚህ ዓመት ከንቲባ ኮሚቴ ይከፈቱ ብሎ ወስኖ በሕገ ወጥ ቤቶች ግንባታ ምክንያት መከፈት ያልቻሉት ማፋሰሻዎችም ከባድ ጎርፍ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አቶ ባይህ እና ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት ውስጥ ናቸው::
በከተማዋ ትንሽ ዝናብ ከጣለ መንገዱ ሁሉ በውኃ ስለሚሞላ መንገድ ከመጥረግ ባልተናነሰ የማፋሰሻ ጽዳት ትኩረት ተደርጎ እንዲሠራ አቶ ባይህ ጠቁመዋል:: ለዚህ ተግባርም ከተማ አስተዳደሩን ከመጠበቅ ባለፈ ነዋሪው በየአቅራቢያቸው ባለው ተፋሰስ ቆሻሻ ከመጣል መቆጠብ፣ ተፋሰሱ ከተዘጋም የማጽዳት ኃላፊነት እንዳለባቸው አስተያየት ሰጭው ያምናሉ:: ነገር ግን በቆሻሻ የተዘጋውን ተፋሰስ ነዋሪዎች እንዲያፀዱ ቢጠየቁም ፈቃደኛ እንዳልሆኑም ተናግረዋል::
በጣና ክፍለከተማ የሽምብጥ ቀበሌ ነዋሪዋ ወ/ሮ ገነት ጌታቸው በበኩላቸው ክረምት ዝናብ መጣል ሲጀምር የሚከሰተው ጎርፍ ሁልጊዜም ስጋት በመሆኑ ለማፅዳት ባይችሉም ክረምት ከመግባቱ በፊት ብር አዋጥተው ለማስጠረግ እንደሚሞክሩ ተናግረዋል:: ሆኖም ግን ይላሉ ወ/ሮ ገነት ከየት እንደመጣ የማይታወቅ በርካታ የውኃ መያዣ ፕላስቲክ በብዛት በየተፋሰሱ ስለሚጣል ከደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር እኩል የሆነ የማፋሰሻ ቦታዎችን የማዘጋጀት እና የመከታተል ሥራን ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዳልሠራ ጠቁመዋል::
ክረምት ካልደረሰ በቆሻሻ ፍሳሽ ፣ አፈር እና ደረቅ ቆሻሻ ተሞልተው የሚቆዩት ማፋሰሻዎች አንዳንድ ቦታ ላይ ለመኪና መሻገሪያ ተብለው የተሠሩ ድልድዮችን በሥር ለማጠናከር ተብሎ የሚጨመር ብረት ቆሻሻ በመያዝ ለጎርፍ ሥጋት መሆኑን ነው የገለፁት::
በባሕር ዳር ከተማ አካባቢ ጥበቃ ጽዳት እና ውበት ጽ/ቤት የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ እና መልሶ መጠቀም ቡድን መሪ ወ/ሮ በላይነሽ አምሳሉ እንደገለፁት በከተማዋ በ27 የጽዳት ማህበር አንድ ሺህ 200 ሠራተኞች ቤት ለቤት ቆሻሻ በመሰብሰብ እና መንገድ ለማጽዳት ተሰማርተዋል:: ማፋሰሻ /የዲች /ቦዮችን ደግሞ በየ15 ቀኑ ያፀዳሉ::
ቡድን መሪዋ እንደሚሉት ሀገር አቀፉ የአካባቢ ጥበቃ አዋጅ በመኖሪያ ቤት እና በንግድ ቦታዎች አካባቢ ህብረተሰቡ 50 ሜትር ዙሪያውን እንዲያፀዳ የተቀመጠ ሕግ በመኖሩ በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ቢዘጋጅም ቸልተኝነት አለ::
የጽዳት ችግሩ ከአቅም በላይ ሲሆን ህብረተሰቡን ያስተባበረ ጽዳት በየጊዜው ይደረጋል:: በህብረተሰቡ ዘንድ የጽዳት ግንዛቤው ቢኖርም በየአካባቢው በቆሻሻም ሆነ መፋሰሻ ጽዳት እንዲመጣ የሚደረገው እንቅስቃሴ በቂ አይደለም::
ማፋሰሻዎችን በከፍተኛ ደረጃ እየዘጋ ያለው በየአካባቢው የሚደረግ ግንባታ ተረፈ ምርት መሆኑን የጠቆሙት ቡድን መሪዋ ፤ ህብረተሰቡ የፈጠረውን ይህን ችግር በተደጋጋሚ መንገር ለውጥ ስላላመጣ ከደንብ ጽ/ቤት ጋር በመነጋገር ቀነ ገደብ አስቀምጦ በማስጠንቀቅ ለመቅጣት እየተሞከረ ነው::
በከተማው ያሉት ፋሲሎ እና ግሽ አባይ ቀበሌ ደግሞ ትልቅ ችግር የሆነው በውኃ መያዣ ፕላስቲኮች /በተለምዶ ሀይላንድ በሚባሉት/ ተጸዳድተው የሚጥሉ ሰዎች በመብዛታቸው አማራጭ የጋራ መጸዳጃ እንዲያስቀምጡ ምክክር እየተደረገ ይገኛል::
መፋሰሻዎች ከአካባቢ ጥበቃ ጽዳት እና ውበት ጽ/ቤት በተጨማሪ የመንገዶች ባለሥልጣን ጽ/ቤት በጋራ የሚሠሩበት ሥለሆነ ትልልቅ ማፋሰሻ ቦዮችን ከሰኔ አንድ ጀምሮ ሠራተኞችን ይዞ ለማጽዳት መታሰቡን ቡድን መሪዋ ጠቁመዋል::
በየሰፈሩ ያሉ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ /ኮበልስቶን/ መንገዶች እና ማፋሰሻዎች /ዲች ቦዮች/ ከፍተኛ ችግር የሆነውን የሃይላንድ ፕላስቲክ ቆሻሻ መልሶ ሥራ ላይ ለማስገባት ግንዛቤ ተፈጥሮ 13 ማህበራት ወደ ሥራ ገብተዋል:: እነዚህ ማህበራት እና ግለሰቦች ወደ አዲስ አበባ መላክ በመጀመራቸው አሁን ችግሩ ይቀንሳል የሚል ተስፋ መኖሩን ጠቁመዋል::
ወ/ሮ በላይነሽ ከተማው የሁሉም ሰው ስለሆነ ጽዳቱን እንዲጠበቅ በህብረተሰቡ እና በመንግሥት ትብብር የሚሠራ እንጅ በጽ/ቤቱ ጥረት ብቻ ለውጥ የሚመጣ ባለመሆኑ ማህበረሰቡን ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚፈልግ ጠቁመዋል:: ሃይላንድ በየመንገዱ እንዳይወድቅ፣ የተቀመጡ ብረቶችን ግለሰቦች እየሰረቁ ሲሸጡ እንደማህበረሰብ ዝም ማለቱ ተገቢ አለመሆኑ ወ/ሮ በላይነሽ ጠቁመዋል:: በዘላቂነት ችግሩ እንዲፈታ ህብረተሰቡ ተደጋጋሚ ግንዛቤ ተፈጥሮለት ሕጉን መተግበር ካልቻለ ሌላ አስገዳጅ ሕግ አውጥቶ በምክር ቤት ለማፀደቅ እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል:: ግለሰቦች በአካባቢያቸው እና በማፋሰሻ ቦታዎች ላይ ቆሻሻ ከጣሉ እና ካላፀዱ በገንዘብ መቅጣት የሚቻልበት ሕግ ለማውጣትም ነው የታሰበው ብለዋል ::
በንግድ ድርጅቶች አካባቢም ተደጋጋሚ ጥፋት ከታየ ቅጣት ይኖራል ያሉት ወ/ሮ በላይነሽ፤ ሃይላንድ እንደገና ገበያ ላይ የሚውል ስለሆነ በየሰፈሩ ለሚዞሩ ወጣቶች በመሸጥ ወደ ገቢ መቀየር ይገባል:: በውኃ መያዣ ኘላስቲኮች መጸዳዳቱ በረጂ ድርጅቶች ድጋፍ በየክፍለ ከተማው ሊሠሩ የታሰቡ መፀዳጃዎች የሚፈቱት ችግር እንደሆነ ወ/ሮ በላይነሽ ጠቁመዋል:: የጎርፍ አደጋ የሁሉም ስጋት ስለሆነ ሁሉም በየበሩ ያለውን መፋሰሻ ማጽዳት ከቻለ ስጋት መቀነስ እንደሚቻል ነው የተናገሩት::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም