ሜዳ ቴኒስ እና አዳዲስ ፊቶች

0
206

በዓለም ላይ ተወዳጅ ከሆኑ ስፖርቶች መካከል የሜዳ ቴኒስ አንዱ ነው። የሜዳ ቴኒስ ስፖርት በአስፋልት፣ በሸክላ እና በሰው ሠራሽ ሳር በተነጠፈለት ሜዳ የሚዘወተር ነው። ስፖርቱ በሁለቱም ፆታዎች በነጠላ እና በጥንድ ይከናወናል። በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ እንደተጀመረ የሚነገርለት የሜዳ ቴኒስ ስፖርት አሁን ላይ ሀገራችንን ጨምሮ በሁሉም የዓለም ማዕዘን እየተዘወተረ ይገኛል። በዓለም አቀፍ የሜዳ ቴኒስ ዋንጫ፣ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች እና  በአራቱ የግራንድ ስላምን  በመሳሰሉ ግዙፍ እና ተጠባቂ የውድድር መድረኮች ይከናወናል። እነዚህ መድረኮችም በርካታ ስፖርተኞች ራሳቸውን እንዲያሳዩ እና ስፖርቱን እንዲቀላቀሉ ዕድሉን ፈጥረዋል።

ባለፉት ዓመታትም  ባለ ተሰጥኦ የሜዳ ቴኒስ ኮከቦች በስፖርቱ አልፈዋል። አሁን ላይም በርካታ የመጪው ዘመን ፈርጦችን እየተመለከትን እንገኛለን። ለአብነት ከቀደሙት ስፖርተኞች ውስጥ ከሴቶች የዊሊያምስ ቤተሰቦች፣  እህትማማቾቹን ሴሪና እና ቬነስን ማንሳት ይቻላል። ከወንዶቹ ደግሞ ራፋኤል ናዳል እና  ሮጀር ፌደረር በቀዳሚነት የሚጠቀሱ የቀድሞ የሜዳ ቴኒስ ኮከቦች ናቸው።

ከምንጊዜም የሜዳ ቴኒስ ተጫዋቾች  መካከል ስሟ በቀዳሚነት የሚነሳው ቬኑስ ዊሊያምስ በዘርፉ በርካታ ክብሮችን መጎናጸፏ አይዘነጋም። ሰባት የነጠላ ውድድሮችን ስታሸንፍ 14 የጥንድ ውድድሮችንም ማሸነፍ ችላለች። በተለያየ ጊዜ አራቱንም የግራንድ ስላም ውድድሮችንም ማሸነፍ የቻለች ብርቱ የቀድሞ ስፖርተኛ ነበረች። በኦሎምፒክ በነጠላ እና በጥንድ የወርቅ ሜዳሊያንም ለአሜሪካ አስገኝታለች።

በፈረንጆቹ ሚሊኒየም በአወስትራሊያ ሲድኒ በተደረገው የኦሎምፒክ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያን ማስገኝቷን የታሪክ ማህደሯ ያሳያል። ከሃያ ዓመታት በላይ በዘለቀው የሜዳ ቴኒስ ህይወቷ ለቁጥር የሚታክቱ ክብሮችን ተጎናጽፋለች። ለብዙ ሴት ስፖርተኞችም መነቃቃትን ፈጥራለች።

ሴሪና ዊሊያምስም የታላቅ እህቷን ፈለግ በመከተል በሜዳ ቴኒስ ስፖርት ከሃያ ዓመታት በላይ የነገሰች የምንጊዜም ታላቅ ስፖርተኛ ናት። 23 የነጠላ ግራንድ ስላም ውድድሮችን በማሸነፍ የሚስተካከላትም የለም። በነጠላ እና በጥንድ በተለያየ ጊዜ አራቱንም የግራንድ ስላም ውድድሮችን ማሸነፏን መረጃዎች ያመለክታሉ።  በኦሎምፒክ መድረኮች ደግሞ  አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማሸነፏን የታሪክ ማህደሯ ያስነብባል።

የቀድሞዋ ስፖርተኛ ሴሪና ለረጅም ሳምንታት የደረጃ ሰንጠረዡን በመምራትም ከሌሎቹ ሴት ስፖርተኞች በተሻለ  ስሟ በክብር መዝገብ ተቀምጧል። ለ319 ሳምንታት የዓለም ቁጥር አንድ በመሆን የሴቶች የሜዳ ቴኒስ ደረጃውን መምራቷን የዓለም አቀፉ የሜዳ ቴኒስ ማህበር መረጃ ያሳያል። ይህቺ ብርቱ ስፖርተኛ በዓለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ስፖርተኞች መካከልም አንዷ እንደነበረች አይዘነጋም።

ሩሲያዊቷ የቀድሞዋ የሜዳ ቴኒስ ፈርጥ ማሪያ ሻራፖቫም  በዓለማችን ከታዩ የሜዳ ቴኒስ ስፖርተኞች መካከል አንዷ  በመሆኗ ታሪክ ሲዘክራት ይኖራል።

ስዊዘርላንዳዊው ሮጀር ፌደረር ከጥቂት ስኬታማ የሜዳ ቴኒስ ኮከቦች ውስጥ ከቀዳሚዎቹ መካከል ይጠቀሳል። የቀድሞው ስፖርተኛ በአጠቃላይ በስፖርት ህይወቱ መቶ የነጠላ ውድድሮችን ያሽነፈ የምንጊዜም ሁለተኛው የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ነው። ሃያ ዋና ዋና የነጠላ ውድድሮችን እና ስምንት  የዌምብልደን የነጠላ ፉክክሮችን በማሸነፍም ባለ ክብረወሰን ነው። ሮጀር ፌደረር የሎሪየስ ሽልማትንም አምስት ጊዜ የወሰደ ብቸኛው የሜዳ ቴኒስ ሰው ነው። በአጠቃላይ በ24 ዓመታት የስፖርት ህይወቱ ብዙ ክብረወሰኖችን በመጎናጸፍ ባለታሪክ ስፖርተኛ ነው።

ሌላኛው የቀድሞ ስፖርተኛ ራፋኤል ናዳልም ከስኬታማ ስፖርተኞች ውስጥ አንዱ ስለመሆኑ አያጠያይቅም። ስፔናዊው የቀድሞ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ከወጣትነቱ ጀምሮ አሸናፊነትን ባህሉ ያደረገ እንደነበር ብዙዎቹ መስክረውለታል። 22 የነጠላ ግራንድ ስላም ውድድሮችን ማሸነፉን መረጃዎች ያሳያሉ። በአጠቃላይ ደግሞ 92 የነጠላ ውድድሮችን ማሸነፍ ችሏል። ናዳል የሮጀር ፌደረር ትልቅ ተፎካካሪ እንደነበረም አይዘነጋም።

ሰርቢያዊው ኖቫክ ጆኮቪች ሁለቱን ስመጥሮች ተከትሎ በዘርፉ ያንጸባረቀ ስፖርተኛ ነው። ሮጀር ፌደረር እና ራፋኤል ናዳል ከስፖርቱ ዓለም ከተገለሉ በኋላ የ36 ዓመቱ ጆኮቪች የዓለምን የሜዳ ቴኒስ ስፖርት በብቸኝነት ለመቆጣጠር በቅቷል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን እርሱን የሚገዳደሩ የላቀ ተሰጥኦ ያላቸው የመጪው ዘመን የሜዳ ቴኒስ ኮከቦችን እየተመለከትን ነው።

ከእነዚህ ድንቅ ባለተሰጥኦች መካከልም ካልሮስ አልካራዝ አንዱ ነው። የ20 ዓመቱ ስፔናዊ በዘርፉ የካበተ ልምድ ያለውን ኖቫክ ጆኮቪችን የሚገዳደር ባለ ክህሎት የሜዳ ቴኒስ ተፎካካሪ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል። አልካራዝ በ19 ዓመቱ በሜዳ ቴኒስ የደረጃ ሰንጠረዥን የመራ ብቸኛው ታዳጊ እንደነበረ የሚታወስ ነው። ወጣቱ ባለተስፈኛ በአጠቃላይ 12 ዋና ዋና ውድድሮችን እስካሁን መርታቱን መረጃዎች አመልክተዋል። ገና በአራት ዓመት ዕድሜው የሜዳ ቴኒስ ስፖርትን እንደጀመረ የሚነገርለት አልካራዝ በቀጣይ ጊዜያት የዓለምን የሜዳ ቴኒስ ይቆጣጠራል ተብሎ ብዙ ግምት ተሰጥቶታል።

አሁን ላይ  በወቅታዊው የደረጃ ሰንጠረዥም ቢሆን ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠው። በ2021 እ.አ.አ በ17 ዓመቱ በፍሬንች ኦፕን (French Open) የሜዳ ቴኒስ በመካፈል የመጀመሪያው በዕድሜ ትንሹ ተወዳዳሪ እንደነበረም ይታወሳል። የሀገሩን ልጅ ራፋኤል ናዳልን መንገድ ተከትሎ ገና ከወዲሁ በክብረወሰን በመታጀብ ስኬታማ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።

ብዙዎቹ የስፖርቱ አፍቃሪዎችም ክስተት ነው ሲሉ ይገልጹታል። በዘመናት የማይደበዝዝ ታሪክ ለመጻፍም እየተንደረደረ ያለ የመጪው ዘመን ኮከብ መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛል።

ጣሊያናዊው ጃኒክ ሲነርም በቀጣይ ዓመታት ዓለም ማየት ከሚፈልጋቸው የሜዳ ቴኒስ ተጫዋቾች አንዱ ስለመሆኑ ሲጫወት ማየት በቂ ነው። ሲነር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እና እያደገ የመጣ የ22 ዓመት ስፖርተኛ ነው። በአልሸነፍ ባይነቱ የሚታወቀው ሲነር ተጋጣሚዎቹ መቋቋም የማይችሉት ፈጣን ምቶችን በመሰንዘርም ይታወቃል። ምቶችን ሲሰነዝር  የኳሷ ፍጥነት  እንደ ሮኬት የፈጠነች መሆኗ በተደጋጋሚ ይነገራል።

ይህም በሜዳ ቴኒስ ስፖርት ታሪክ አምስተኛው ፈጣን ምት ሆኖ ተመዝግቧል። ይህን ባለ ተሰጥኦ በርካቶቹ ከቀድሞው ሲዊዘርላንዳዊ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋቹ ሮጀር ፌደረር ጋር ያመሳስሉታል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም ከኖቫክ ጆኮቪች በመቀጠል ሁለተኛ ሆኖ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ተቀምጧል። የሮጀር ፌደረር እና  የራፋኤል ናዳል ጡረታ መውጣትን እንዲሁም የኖቫክ ጆኮቪች ዕድሜው መግፋትን ተከትሎ ከሁለቱ ኮከቦች በተጨማሪ ኦስትሪያዊው ዶምኒክ ቲም እና  ግሪካዊው ስጢፋኖስ ሲሲፓስም  በመጪው ጊዜያት በሜዳ ቴኒስ ስፖርት ከሚነግሱ ባለተሰጥኦዎች መካከል ይገኙበታል።

በሴቶችም የአንጋፋዎቹ ዘመን ማብቃቱን ተከትሎ ወጣቶቹ ቦታውን ተክተው  እያንጸባረቁ ናቸው።  ከሴት የሜዳ ቴኒስ ፈርጦች መካከል የወቅቱ የዓለም ቁጥር አንዷ ፖላንዳዊት ኢጋ ስዋቲክ ቀዳሚውን ቦታ ትይዛለች። የ22 ዓመቷ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ከቀድሞ የሜዳ ቴኒስ ስፖርተኛ ቤተሰብ ነው የተወለደችው። በዋና ዋና የሜዳ ቴኒስ መድረኮች እየተወዳደረች ያለች የመጀመሪያ ፖላንዳዊም መሆን ችላለች።

ወጣቷ የሜዳ ቴኒስ ስፖርተኛ እስካሁን 18 የነጠላ ውድድሮችን ማሽነፏንም መረጃዎች ያመለክታሉ። ገና ከወዲሁ ብዙ ክብሮችን ያሳካችው ስዋቲክ በመጪው ዘመን የዓለምን የሜዳ ቴኒስ ስፖርት ይቆጣጠራሉ ተብለው ግምት ከተሰጣቸው ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ ትይዛለች። በ14 ዓመቷ ዋና ዋና የወጣቶችን መድረክ በማሸነፍ ከዚህ የደረሰችው ኢጋ ስዋቲክ አሁን ላይ ቁጥር አንድ በመሆን የደረጃ ሰንጠረዡን መምራት ከጀመረች 94 ሳምንታት አልፏታል።

የወቅቱ የዓለም ቁጥር ሦስቷ  አሜሪካዊቷ ኮኮ ጋውፍ በሜዳ ቴኒስ ስፖርት  ሌላኛዋ ተስፋ የሚጣልባት ስፖርተኛ ናት። በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት የተወለደችው ኮኮ ጋውፍ በ2019ኙ የዌምብልደን ውድድር በመሳተፍ የመጀመሪያዋ የመድረኩ ወጣት የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች እንደነበረች ይታወሳል። የ20 ዓመቷ ጋውፍ ከሜዳ ቴኒስ ስፖርት ጋር የተዋወቀችው በ13 ዓመቷ እንደሆና  መረጃዎች ያስነብባሉ።

ከዛን ጊዜ በኋላ በአጠቃላይ ሰባት የነጠላ ውድድሮችን ረታለች። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለች እና እየጠነከረች የመጣችው አሜሪካዊት የሜዳ ቴኒስ ባለ ክህሎት፣ ወደዚህ ስፖርት የመጣችው እህትማማቾችን ሴሪናን እና ቬኑስን በማየት እንደሆነ በአንድ ወቅት ለሲቢኤስ (CBS) ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግራለች።

በዘርፉ ተሳክቶላትም አስደናቂ ብቃቷን እያሳየች ትገኛለች። በቀጣዮቹ ጊዜያት የስፖርቱ አፍቃሪያን ማየት ከሚፈልጓቸው ባለ ክህሎቶች አንዷ ጋውፍ መሆኗንም በርካታ የስፖርት የመገናኛ አውታሮች ዘግበዋል። በተጨማሪም የወቅቱ  የዓለም ቁጥር ሁለቷ ቤላሩሳዊቷ አርያና ሳባላንኬ፣ ካዛኪስታናዊቷ ራይባኪና፣  አሜሪካዊቷ ጀሲካ ፔጉላ ከመጪው ዘመን የሜዳ ቴኒስ ኮከቦች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

የዓለም አቀፉ የሜዳ ቴኒስ ማህበር ድረገጽ እና ቢቢሲ ስፖርት የመረጃ ምንጮቻችን ናቸው።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here