በአማራ ክልል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የወባ በሽታ ምርመራና ሕክምና በዘመቻ መልክ መሰጠት መጀመሩን የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
የወባን ስርጭት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በተለይ መገናኛ ብዙኃን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ኢንስቲትዩቱ ጥሪ አቅርቧል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ እንዳስታወቁት ለአንድ ወር የሚቆየው ዘመቻ “ትኩሳት ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የወባ ምርመራና ሕክምና እንዲያገኙ እንተባበር!” በሚል መሪ ሐሳብ ይካሄዳል። የወባ በሽታ ምርመራ በሽታው በስፋት በሚስተዋልባቸው 40 የተመረጡ ወረዳዎች ይካሄዳል። በዚህም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በምርመራዉ የወባ በሽታ የተገኘባቸው ሰዎች ወዲያው ሕክምና ይደርግላቸዋል። ይህም የበሽታውን ስርጭት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመከላከል ያስችላል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ በተያዘው ዓመት ክልሉ የወባ በሽታ በስፋት ተከስቶበት ነበር። ሆኖም በሽታውን ለመከላከል የአካባቢ ቁጥጥር ሥራዎች በመሠራታቸው የስርጭት መጠኑ መቀነሱን ነው የጠቆሙት።
ዘመቻው በስኬት እንዲጠናቀቅ ተገቢ የሰው ኃይል ከመመደብ ባለፈ አስፈላጊው በጀትና ግብዓት ቀደም ብሎ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም