ምርጫዉ እና ተጠባቂ ሁነቶች

0
153

እንደ ነፍሰ ጡር ሴት ቀን ሲቆጠርለት እና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እነሆ ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም ይደረጋል። የ78 ዓመቱ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድጋሚ መንበረ ስልጣኑን ለመያዝ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ሆኖ ይወዳደራል። ከግራ ዘመም ዲሞክራቶችም የጆ ባይደን ምክትል የሆነችው ካማላ ሀሪስ ልዕለ ኃያሏን ሀገር ለመምራት የምትፎካከር ይሆናል።
ለወራት በተለያዩ ድራማዊ ክስተቶች እና የሴራ ትንተናዎች ዓለምን ሲያነጋግር የከረመው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል። አዛውንቱ ትራምፕ ከዚህ በፊት 45ኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን እ.አ.አ ከ2017 እስከ 2021 ማገልገሉ አይዘነጋም። የ60 ዓመቷ ካማላ ሀሪስ ደግሞ እ.አ.አ ከ2021 ጀምሮ እስካሁን የጆ ባይደን ምክትል ሆና እያገለገለች ትገኛለች። የ24 ስዓታት ዕድሜ ብቻ በቀረው በዚህ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሜሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ መላው ዓለም ውጤቱን በጉጉት የሚጠብቀው ይሆናል።
ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫው 160 ሚለዮን በላይ አሜሪካውያን ድምጽ ለመስጠት ተመዝግበዋል። ወይዘሮ ካማላ ሀሪስ የባይደንን እግር በመተካት የነጩን ቤተመንግሥት ዙፋን ትረከባለች? ወይስ ባልተገራ አንደበቱ የሚታወቀው ዶናልድ ትራምፕ ድጋሚ ከነጩ ቤተ መንግሥት ይዘልቃል? የሚለው አጓጊ ሆኗል።
የዶናልድ ትራምፕ መንገድ እና አቋም አሜሪካን ብቻ ኃያል (Americanism ወይም Make America Great Again) ማድረግ የሚለውን ርዕዮት የሚያቀነቅን ሲሆን ዓለም አቀፋዊነትን በጽኑ ያወግዛል። ይህ ደግሞ አሜሪካ በፕላኔታችን የሚኖራትን ተጽዕኖ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል። ምክንያቱም በየቀጣናው ኃያላን ብቅ ብለዋልና በሚል ብዙዎች ሐሳብ ያነሳሉ።
ምዕራባውያን እና አሜሪካ አንባገነን ናቸው የሚሏቸው መንግሥታት ጥምረት ፈጥረው አሜሪካን ለመጋፈጥ ከፊቷ ቆመዋል። በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረው የፖለቲካ ምስቅልቅል እና የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት መጦዝ፤ ዋሺንግተን ግጭቶችን የመፍታት አቅሟ እየቀነሰ ስለመምጣቱ ማሳያ መሆኑን ዓለም አቀፍ ቀውስን በመተንተን የሚታወቀው ዓለም አቀፉ የክራይሲስ ግሩፕ መረጃ አመልክቷል።
በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት የቀኝ ዘመሙ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩው ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያን እና የዩክሬንን ጦርነት የሚያስቆመው እርሱ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገር ተደምጧል። የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ወዳጅ እና አድናቂ እንደሆነ የሚነገርለት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም ወታደራዊ እና የገንዘብ ድጋፍ አደርጋለሁ ብሏል። ፑቲን ከዩክሬኑ መሪ ዘለንስኪ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጥ አደርጋሉሁም ብሏል ዶናልድ ትራምፕ። ይሁን እንጂ ሩሲያ አሁን የያዘቻቸውን የዩክሬን ግዛቶች ለመልቀቅ ፈቃደኛ ስለማትሆን ጉዳዩን ውስብስብ ሊያደርገው ይችላል ነው የተባለው።
በሌላ በኩል የዲሞክራት ፓርቲ ዕጩዋ ካማላ ሀሪስ ከዩክሬን ጎን እንደምትቆም በተደጋጋሚ በአጽንኦት መናገሯ አይዘነጋም። “ከዩክሬን ጎን በመቆሜ ኩራት ይሰማኛል፤ የዩክሬንን ክብር ለማስመለስ ጠንክሬ እሠራለሁም” ስትል መናገሯን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ የፊታችን የካቲት ወር 2017 ዓ.ም ሦስተኛ ዓመቱን ይደፍናል። በዚህ የተራዘመ ጦርነት ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ከ100 ሺህ እስከ 120 ሺህ የሚገመቱ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። በርካቶችም ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል።
የሩሲያን እና የዩክሬንን ጦርነት እኔ ነኝ የማስቆመው የሚለው ዶናልድ ትራምፕም ይመረጥ፤ “ዩክሬን ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” ያለችው ካማላ ሀሪስም ትመረጥ፤ ከፕሬዝዳንታዊው ምርጫ በኋላ ነገሮች የበለጠ አስከፊ እንደሚሆኑ የቢቢሲ ዋና የዓለም አቀፍ ዘጋቢ እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆነችው ሌይዝ ዱሴ ተናግራለች።
ሌላው ጉዳይ የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ውጥረት ነው። ሁለቱ ዕጩ ፕሬዝዳንቶች በመካከለኛው ምሥራቅ ያላቸው አቋም ብዙም የተለያየ አይደለም። ካማላ ሀሪስ እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት በመግለጽ በንጹሀን ፍልስጤማውያን ላይ የሚደርሰው ግድያ ግን መቆም አለበት የሚል አቋም እንዳላት የቢቢሲ መረጃ ያስነብባል። ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ራሱን እንደ ሰላም መሲህ በመቁጠር በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም አሰፍናለሁ እያለ ይገኛል። “ወደ ሰላም የምንመለስበት እና ሰዎችን መግደል የምናቆምበት ጊዜ ነው” ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
የእስራኤል – ሀማስ ጦርነት ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። በጋዛ መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ጥፋት ደርሷል። ከአንድ ዓመት በላይ በሆነው እና አሁንም በቀጠለው ጦርነት ከ42 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ፤ ከ92 ሺህ በላይ ደግሞ ቆስለዋል። 677 ሺህ የሚሆኑ ዜጎችም የረሀብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። አሁን ጦርነቱ አድማሱን አስፍቶ ኢራን እና ሌባኖስ ጋር ደርሷል። ታዲያ አሜሪካውያን የመካከለኛው ምሥራቅን የፖለቲካ ምስቅልቅል ለምርጫ ቅስቀሳ እንደ መሳሪያ ቢጠቀሙበትም ወደ ፊት ቀጣናው ከትርምስ ሊወጣ እንደማይችል የቢቢሲ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዋና ዘጋቢ እና የፖለቲካ ተንታኟ ታብራራለች።
ዶናልድ ትራምፕ በሚያራምደው ፖለቲካዊ አቋሙ ምክንያት በምዕራባውያን አይወደድም። ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኖ የሚመረጥ ከሆነ አሜሪካ 32 ሀገራትን በአባልነት ከያዘው ከሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ራሷን የምታገል ይሆናል። ዋሺንግተን በየዓመቱ ለዚህ ወታደራዊ ድርጅት ከ60 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ታወጣለች። ይህም የድርጅቱን 70 በመቶ ወጪ የምትሸፍነው አሜሪካ ስለመሆኗ ነው የሚወጡ መረጃዎች የሚጠቁሙት። ዶናልድ ትራምፕ ተሳክቶለት ድጋሚ ከነጩ ቤተ መንግሥት ከገባ ወታደራዊ ድርጅቱ የመፍረስ አደጋ ይጠብቀዋል። በሰሜን አትላንቲክ የጦር ድርጅት የሚመኩት ምዕራባውያንም የህልውና ስጋቱ እንቅልፍ እንደሚነሳቸው እየተነገር ነው። ወይዘሮ ካማላ ሀሪስ ከተመረጡ ግን ወታደራዊ ድርጅቱ በተሻለ ጥንካሬ በዋሺንግተን እጅ እንደሚዘወር ያምናሉ።
አሜሪካ ለአፍሪካ አህጉር መረጋጋት እና ዕድገት በምትጫወተው ሚና ምክንያት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው የአፍሪካውያንን ትኩረትም ስቧል። ለምዕራባውያን ትላንትም ዛሬም የዳቦ ቅርጫት የሆነችው አህጉራችንን ኃያላኑ (አሜሪካ፣ ምዕራባውያን፣ ሩሲያ እና ቻይና) የኃያልነት የፉክክር ሜዳ አድርገው ይጠቀሙባታል። ይህ ጉዳይ ታዲያ የአሜሪካን የምርጫ ውጤት ይበልጥ ውጥረት ውስጥ ሊከተው ይችላል የሚል ስጋትን አሳድሯል። ምንም እንኳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአፍሪካ እና የአሜሪካ ግንኙነት ቢላላም ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ የአህጉሪቱ ሀገራት መንግሥታት ደካማ በመሆናቸው፣ ድህነት በመጨመሩ፣ የሕዝቦች ጤና በመጓደሉ፣ የጸጥታ ችግር በመኖሩ እና ግጭቶች በመስፋፋታቸው አሁንም የአሜሪካ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።
ታዲያ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ለአፍሪካ አህጉር ተጽዕኖው ቀላል እንዳልሆነ ነው የተነገረው። በርካታ የአፍሪካ መሪዎች የቀኙ ጽንፍ ፓርቲ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ የሚመረጥ ከሆነ በጆ ባይደን አስተዳደር የተወጠኑ እና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ሊዘነጉ ይችላሉ በሚል ስጋት አድሮባቸዋል።
ማንም ይመረጥ ማን በቀጣይ አራት ዓመታት አሜሪካን ለመምራት ነጩ ቤተ መንግሥት የሚገባው ሰው ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ትልቅ ስጋት የሚፈጥረውን እና በየአቅጣጫው የጦርነት ነጋሪት የሚጎሰምበትን ምድር ማረጋጋት ይጠበቅበታል።
ሁለቱንም ዕጩዎች አንድ ከሚያደርጓቸው ጉዳዮች መካከል ሕገ ወጥ ስደትን ለመቆጣጠር ቃል መግባታቸው ነው። ምንም እንኳ ሀገሪቱ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ አጠራር “የስደተኞች ሀገር” ተብላ ብትገለጽም ለስደተኞች ቦታ እንደሌላት ግን ዕጩ ፕሬዝዳንቶች ባደረጓቸው ንግግሮች ተረጋግጧል።
በተመሳሳይ የአሜሪካ ምርጫ ውጤት በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ነው የተነገረው። ዶናልድ ትራምፕ የሚመረጥ ከሆነ የአየር ንብረት ለውጥን እና የተፈጥሮ አደጋን ለመከላከል እና ለአካባቢ ጥበቃ የሚወጡ ዕቅዶች እና ፖሊሲዎች የማይተገበሩ እንደሆኑ ያምናል። እናም ለእነዚህ የሚወጣውን ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያቆም በተደጋጋሚ ዝቷል። ይህ ደግሞ መላውን ዓለም ተጎጂ ያደርጋል ተብሏል።
ኔቸር ዶት ኮም ሁለት ሺህ ሰዎችን ያካተተ የዳሰሳ ጥናት ማድረጉን በደረ ገጹ አስነብቧል። ታዲያ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ማሕበራዊ ፍትሕ እና የሕዝብ ጤና የሚያሳስባቸው ሰዎች ካማላ ሀሪስን እንደሚመርጡ መግለጻቸውን በጥናት ዳሰሳው ሰፍሯል። በአንጻሩ ኢኮኖሚያዊ እና የጸጥታ ጉዳዮች የሚያሳስባቸው አሜሪካውያን በሩሲያ እና በዩክሬን እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ጦርነቶች ያከትማሉ በሚል ተስፋ ዶናልድ ትራምፕን ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአራት ዓመታት በፊት በጆ ባይደን ከተሸነፈ በኋላ ደጋፊዎቹ በካፒቶል ከተማ አመጽ አስነስተው እንደነበር አይዘነጋም። ምናልባት ዘንድሮም ውጤቱ አሜሪካውያንን ወደ ሌላ የእርስ በእርስ ጦርነት እና ብጥብጥ ሊዳርግ ስለሚችል መጠርጠሩ አይከፋም ሲል ሮይተርስ ትንታኔውን ይቋጫል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here