የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ከዞን፣ ከከተማ አሥተዳደሮች፣ ከብሔራዊ ፓርኮች እና ከማሕበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ጽ/ቤት የዘርፉ መሪዎች ጋር የ2017 በጀት ዓመት የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን በባሕር ዳር ከተማ ገምግሟል፤ የቀጣይ ተግባራትን በተመለከተም ውይይት አካሂዷል። እየተባባሰ የመጣው የተፈጥሮ ሀብት መመናመን ደግሞ የውይይቱ ማዕከል ነበር፤ ለችግሩ መሠረታዊ ምክንያት የአጠቃቀም ክፍተት በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው የተመላከተው።
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ እንዳስታወቀው የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ሕግ ወጥቶ እየተተገበረ ነው። ይህን መሠረት በማድረግም ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በአካባቢ ላይ የሚመጣን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከልም የተፈጥሮ ሀብት መመናመንን መከላከል፣ በከተሞች አካባቢ ብክለትን መቀነስ፣ አካባቢን በተገቢው መንገድ መጠበቅ እና መንከባከብ እንዲሁም ልማቶች፣ የኢኮኖሚ እና ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎች ከአካባቢው ጋር የተዛመዱ እንዲሆኑ እየተሠሩ ያሉ ተግባራት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ለትውልድ የሚሻገር መሰል ተግባራትን በማከናወን የነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ችግር ውስጥ እንዳይገባ ማድረግ እንደሚገባም ነው በውይይቱ የተመላከተው።
ክልሉ በገጠመው የሰላም እጦት ምክንያት በርካታ ሥራዎች ወደ ኋላ እንደተመለሡ በውይይቱ ተነስቷል። በክልሉ የሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች እና ጥብቅ የደን ስፍራዎች እንዲራቆቱ እና ጉዳት እንዲደርስባቸውም ሆኗል። ይሁን እንጂ በችግር ውስጥ ሆኖም ሕብረተሰቡን በማሳመን እና የተፈጥሮ ሀብቶቹ የትውልድ እንጂ የዛሬዎች ብቻ አለመሆኑን በማስተማር በርካታ የጥበቃ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው የተባለው።
በአካባቢ ጥበቃ ሥራ መልካም ተሞክሮ ከተነሳባቸው መካከል በሰሜን ወሎ እና ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቀጣና የሚገኘው የአቡነ ዮሴፍ ዝጊት አቡሃይ ጋራ የማሕበረሰብ ጥብቅ ሥፍራ አንዱ ነው፤ ጥብቅ ሥፍራው 10 ሺህ 333 ሄክታር መሬት ይሸፍናል።
በውይይት መድረኩ የተገኙት የጥብቅ ሥፍራው ኃላፊ ዲያቆን አወቀ መለሰ የደን ጥበቃ እና አጠቃቀም ሥርዓት በመዘርጋት እና ቁጥጥር በማድረግ የተሻለ ውጤት መታየቱን አስረድተዋል። በ18 ቀበሌዎች ከ16 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን በተለያዩ አደረጃጀቶች በመከፋፈል ጥብቅ ሥፍራዎችን እንዲንከባከብ እና እንዲጠቀም መሠራቱን እና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያመላከቱት።
ዲያቆን አወቀ እንዳሉት ጥብቅ ስፍራው በ2008 ዓ.ም በክልሉ መንግሥት ዕውቅና አግኝቶ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ጥበቃ እየተደረገለት ይገኛል። የተከዜ ወንዝ ገባር የሆኑ 20 ወንዞችን እና 724 ምንጮችንም የያዘ ነው።
የአቡነ ዮሴፍ የቃል ኪዳን ሥነ ሥርዓት፣ የጉልት መቅጫ (የደቦ) እና ዘመናዊ የአስተዳድር ሥርዓቶች ተዘርግተው አካባቢን ለመጠበቅ እየተሠሩባቸው ያሉ አሠራሮች መሆናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል። የሐይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን እና ተሰሚነት ያላቸውን ግለሰቦች በመወከል ጥብቅ ስፍራውን በተመለከተ ግንዛቤ በመፍጠር የባለቤትነት ስሜት እንዲዳብር ተሠርቷል።
በሌላ በኩል በጥብቅ ስፍራው ላይ ያልተገባ ሥራ በሚሠሩ ጥፋተኞች ላይ የተጠናከረ ርምጃ ሲወሰድ ቆይቷል። ለአብነትም 28 ግለሰቦች ከጥፋታቸው እንዲታረሙ ሲደረግ 19 ግለሰቦች ደግሞ በገንዘብ ተቀጥተዋል።
እንደ ዲያቆን አወቀ ማብራሪያ የፀጥታ ችግሩ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት እና የዱር እንስሳትን ቆጠራ ለማድረግ ዋነኛ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል፤ ሆኖም ችግሩን ተቋቁሞ እየተሠራ ነው። በቀጣይም ድክመቶችን አርሞ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል የተሻለ ለመሥራት ታቅዷል።
ሌላው በውይይት መድረኩ ተገኝተው ሪፖርት ያቀረቡት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አካባቢ እና ደን ጥበቃ ተጠሪ ጽ/ቤት ቡድን መሪ አቶ ሙሉ ስሉጥ ናቸው። በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት ታቅደው የተፈፀሙትን ዋና ዋና ተግባራት እና የገጠሙ ችግሮችን አቅርበዋል። የተራቆቱ መሬቶችን በደን የመሸፈን እና የአፈር ለምነታቸው እንዲመለስ የማድረግ፣ የደን ጥበቃና ቁጥጥር፣ የአካባቢ ብክለትን እና መጤ አረሞችን የመከላከል፣ ከተሞችን ምቹ እና አረንጓዴ የማድረግ ሥራዎች መከናወናቸውን በማንሳት ተግባራቱም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።
ቡድን መሪው እንደተናገሩት በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ሙከራዎች ቢኖሩም ይበልጥ መሥራትን ይጠይቃል፤ ለአረንጓዴ አሻራ ልማት የሚውል ችግኝ ጣቢያ ተዘጋጅቶ ችግኝ የማፍላት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። የተፈጥሮ ሀብት እንዲራቆት ባደረጉ አካላት ላይም አስተማሪ የእርምት እርምጃ እየተወሰደ ነው። ለአብነትም በእርሻ መሬት፣ በደን ይዞታዎች፣ በወንዞች እና በሌሎች ሀብቶች የኬሚካል ብክለት እና ጉዳት ባደረሱ አካላት የማስጠንቀቂያ እና ሕጋዊ እርምጃ ተወስዷል። የሕግ ጥሰት በፈፀሙ 19 ግለሠቦች ላይ አስተዳደራዊ ቅጣት ተወስዷል።
በክልሉ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት የተፈጥሮ ደን በመከለል እንዲጠበቅ እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ በልስቲ ፈጠነ ናቸው። በክልሉ በተመረጡ አካባቢዎች ከዐሥር በላይ የማሕበረሰብ ጥብቅ ሥፍራዎችን እና ብሔራዊ ፓርኮችን በመጠበቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሠራ ነው ብለዋል። ክልሉ በገጠመው የሰላም እጦት ምክንያት ብሔራዊ ፓርኮች ችግር ደርሶባቸዋል ነው ያሉት። በችግር ውስጥ ሆኖም ተሞክሮ ሊወሰድባቸው የሚችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
ክልሉ ከእርሻ እና ከእንስሳት እርባታ በተጨማሪ የደን ልማትን አንድ የኢኮኖሚ ምንጭ አድርጎ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል። ምክትል ኃላፊው እንደተናገሩት የአማራ ክልል ከደን ውጤቶች እና ግብይት በየዓመቱ ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር እንዲያገኝ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል፤ ከውጭ ሀገር የሚገባን የደን ውጤትም በሀገር ውስጥ እንዲመረት ተደርጓል። ይህም የውጭ ምንዛሪን በመቀነስ እና የሥራ ዕድል በመፍጠር ሚናው የላቀ ነው። ለአብነትም በ2017 በጀት ዓመት ከአካባቢ እና ደን ጥበቃ ዘርፍ ከ55 ሺህ በላይ ወገኖች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት።
የአካባቢን ብክለት ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራት ከባለፉት ወራት ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ለአብነትም የአረንጓዴ አሻራ እና የጽዱ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭን ለማስቀጠል በርካታ የማሕበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ከአራት መቶ ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ፕላስቲክ ተሰብስቦ እንዲወገድ መደረጉን አቶ በልስቲ ተናግረዋል። ከ315 ሺህ በላይ ሜትሪክ ኪዮብ በላይ ደረቅ ቆሻሻም ተሰብስቧል።
የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ “ዛሬ ያለንን ሀብት በአግባቡ መጠበቅ ካልቻልን ነገ ለውጤት መብቃት አንችልም” ብለዋል። የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ለትውልድ የሚሻገር ሥራ በመሆኑ በነቃ እና በበቃ ሁኔታ መሥራት እንደሚገባ በመጥቀስ “ለልጆቻችን ጥሩ አካባቢን ገንብቶ ለማስተላለፍ ዛሬ ጠንክሮ መሥራት ይገባል” ብለዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ሥራ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መከላከልን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል፤ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ የሚከሰቱ እንደ ጎርፍ፣ ድርቅ፣ የመሬት መንሸራተት፣ ወቅቱን ያልጠበ ዝናብ እና መሠል ችግሮችን አካባቢን በመጠበቅ ልንከላከላቸው የሚችሉ መሆናቸውን አቶ ተስፋሁን አመላክተዋል።
እንደ ጣና ሐይቅ፣ ዓባይ ወንዝ እና ሌሎች የውኃ ሀብቶችን በመጠበቅ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ለማግኘትም እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል። የአካባቢ ጥበቃ በቅንጅት መሥራትን ይጠይቃል። በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በጥብቅ ሥፍራዎች ላይ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ፣ የሰደድ እሳት እና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዲጋረጡበት አድርጎ ነበር። በችግር ውስጥ ሆኖም ታዲያ ጉዳት የደረሰባቸውን ጥብቅ ሥፍራዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመጠበቅ እንዲያገግሙ የተግባር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል። ሕግ ተከብሮ ሀብቶቻችን እንዲጠበቁ ይደረጋል ያሉት ኃላፊው የአረንጓዴ አሻራ ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲሰጡ በትኩረት እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል።
የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ የማሳደግ ኃላፊነት አለብን ያሉት አቶ ተስፋሁን ብዝኃ ህይወቱን ከጉዳት ለመታደግ በትብብር እየሠራን ነው ብለዋል።
በቀጣይ ወራት በዕቅዱ ያልተከናወኑ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ትኩረት መሠጠቱን አብራርተዋል። ለዚህም ከተቋማት ጋር ለመሥራት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው አብራርተዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የመጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም