ምቹ አካባቢን ለመፍጠር ተቋማት  የድርሻቸዉን እንዲወጡ ተጠየቀ

0
10

 

የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል። የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ የባለሥልጣኑ ከፍተኛ መሪዎች፣ የከተማ፣ የዞን፣ የብሔራዊ ፓርኮች እና ጥብቅ ሥፍራዎች የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኃላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ እንደተናገሩት ክልሉ በችግር ውስጥ ሆኖም  በአካባቢ ጥበቃ የተሻለ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። የአካባቢ፣ የደን እና የዱር እንስሳት ሀብቶችን በአግባቡ በመጠበቅ፣ በማልማት እና ዘላቂነትን በማረጋገጥ ለሰው እና ለዱር እንስሳት መኖሪያ ምቹ የሆነ ክልል እንዲሆን በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ልማት ዘላቂ የሚሆነው የአካባቢ ጥበቃ ሕጎች ተከብረው ሲሠሩ ነው፤ በመሆኑም ተገቢው ክትትል እና ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል።

አቶ ተስፋሁን እንደተናገሩት የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የተሰጠውን ሥልጣን እና ተግባር በውጤታማነት ለመምራት የሚያስችል የዕቅድ ትውውቅ አድርጓል። ይህ ዕቅድ የክልሉ መንግሥት ካቀደው የ25 ዓመት አሻጋሪ ዕቅድ በመነሳት ተቋሙ የተሰጠውን ሥልጣን እና ተግባር በተገቢው መንገድ ውጤታማ አድርጎ ለመምራት የሚያስችል ነው።

አካባቢ ጥበቃ ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ  ለሰው ልጆች መኖሪያ ምቹ እና ጽዱ አካባቢን ለመፍጠር ድርሻው የጎላ እንደሆነ ነው አቶ ተስፋሁን የተናገሩት። የአማራ ክልልም  የአካባቢ ጥበቃ ተግባራትን በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በክልሉ ያሉ ወንዞችን እና ሐይቆችን ከብክለት ለመከላከል መሠራቱን እና እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። የአካባቢ ጥበቃ ሥራ የአንድ ወቅት እና የአንድ ተቋም ሥራ ብቻ ባለመሆኑ ሁሉም ተቋም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።

ብርቅየ እንስሳት እና አዕዋፍ የሚገኙበትን ብዝኃ ሕይዎት ጥበቃ እና እንክብካቤ ማድረግ እንደተቻለም ነው የጠቆሙት። ብሔራዊ ፓርኮችን የመንከባከብ እና የመጠበቅ እንዲሁም የተራቆቱትን መልሶ እንዲያገግሙ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።

በቀጣይ እነዚህን ተግባራት አጠናክሮ በማስቀጠል የብዝኃ ሕይወት ሀብቶችን መጠበቅ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን መገንባት ይገባል ብለዋል።

በማጠቃለያ መድረኩ በ2017 በጀት ዓመት የላቀ አፈፃፀም ላመጡ በአካባቢ፣ በደን እና ዱር እንስሳት ዘርፍ ለከተማ አስተዳደሮች፣ ዞኖች፣ ብሔራዊ ፓርኮች እና የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራዎች ዕውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጳጉሜን 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here