“ምንም ካለመሥራት ሠርተህ መውደቅ የተሻለ ነው”

0
154

የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

ከ50 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ቆይቷል፤ በቲያትር፣ ፊልም እና ድራማ ትወና እንዲሁም በቲያትር ዝግጅት አንቱታን አትርፏል:: በስክሪፕት አጻጻፉ እና በቲያትር መድረክ ፈጠራው እንዲሁም በተዋንያን መረጣው የተዋጣለት መሆኑን የሥራ ባልደረቦቹ ይመሠክራሉ:: ከእነ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድህን፣ ሲራክ ታደሰ፣ ተክሌ ደስታ እና ሌሎችም የጥበብ ሰዎች ጋር በጋራ ሠርቷል፡- አርቲስት ስዩም ተፈራ:: አሚኮ ከአርቲስት ስዩም ተፈራ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል::

የመጀመሪያ የቲያትር ዝግጅትህ ምን ነበር?

“ቤቱን” የሚለው ቲያትር የመጀመሪያው ድርሰት እና ዝግጅቴ ነው:: ጽፌ ከጨረስኩ በኋላ ለጋሽ አባተ አነበብኩለት፤ “ለምን አታዘጋጀውም?” አለኝ:: ልብ አርግ ከዚያ በፊት “ባለ ካባ እና ባለ ዳባ” የሚል ቲያትር ብቻ ነው የሠራሁት:: በጋሽ አባተ መኩሪያ ሀሳብ ተስማማሁ:: ልምምዱን ከ12 ሰዓት በኋላ ነበር ያደረግነው፤ ይህም እንዳንረበሽ እና ትኩረትን ለመሰብሰብ ነበር:: በሦስት ጥንድ ገጸ ባሕሪያት ነበር ያስጠናሁት፤ ምክንያቱም በሦስት ቲያትር ቤቶች እኩል ለማሳየት ነበር የፈለኩት:: ሦስተኛው ጥንድ ሊሠራ አልቻለም፤ ፈረሰ:: ሁለቱ ጠንክረው ለውጤት በቁ:: በአዲስ ከተማ ሲቲ ሆል እና መዘጋጃ ቤት ቲያትሩ እንዲከፈት አደረኩ:: በቲያትሩ ፍቃዱ ተክለማርያም፣ ሱራፌል ጋሻው፣ ተሾመ አንዳርጋቸው፣ ሌላ ተሾመ የሚባል ልጅ እንዲሁም እኔ እና ገለታ ተክለጻድቅ በትወና ተሳትፈናል፤ በጣም ቆንጆ ነበር::

ሁለተኛው ቲያትሬ “ስመኝ ስንት አየሁ” የሚል ነው:: ቀደም ብሎ ሲሠራ ገጸባሕሪውን እወደው ነበር:: የአዲስ ከተማ ሲቲ ሆል ኃላፊዎች ገጸ ባሕሪውን ተጫወተው አሉኝ፤ በደስታ ተቀበልኩ:: እንደገና አዘጋጀው አሉኝ ጭራሽ (በሳቅ) አልኩኝ:: በዚህ መሠረት አዘጋጅም ተዋናይም ሆንኩኝ::

(በሳቅ ይጀመራል) አንድ እይታ (ሲን) ላይ እኔ በእስተርጅና ትንሽ ልጅ ለማግባት ፈልጌ (ገጸ ባሕሪው ማለት ነው) ክርክር ውስጥ እገባለሁ:: እናም ፍርዱን የሚሰጠው ተመልካች ነበር:: ፍርድ እንዲሰጥ ተመልካቹ ጉዳዩ ይላካል:: ታዳሚው የቲያትሩ ተሳታፊ ነው ማለት ነው:: ምን ትላላችሁ? ሲባል “ይሄ ሽማግሌ እንዴት አድርጎ ያገባታል? የለም እንደዚህ ነው እያለ ተመልካቹ ይከራከራል፤ እኔ ከሕዝቡ መካከል ሆኜ ነው ፍርዴን የምቀበለው:: አንዱ ተመልካች ሲሰድበኝ ላጥ አደረኩና በካልቾ ስለው እየሮጠ ከአዳራሹ ወጣ (ሳቅ)፤ ይህች ገጠመኝ ታስቀኛለች::

በደራሲ መንግሥቱ ወርቁ “ባለ ካባ እና ባለ ዳባ” በተሰኘው ቲያትር ለመተወን እንዴት ተመረጥክ? አድናቆትም ሰጥተውሃል ይባላል፤ እስኪ ስለሱ ንገረን?

አርቲስት ተፈሪ ብዙአየሁ ከውጪ ሀገር እንደመጣ ከወጣቶች ጋር መሥራት እንደሚፈልግ ገለጸ:: ወጣት ተዋንያን ወወክማ ይገኛሉ ተብሎ ተነገረው:: ወዳለንበት መጥቶ ለፈተና ሰበሰበን፤ የቲያትር አጭር ስክሪፕት ሰጥቶን እሱን አጥንተን እንድተውን አደረገን:: ከነበሩት ወጣቶች መሃል የኔን ትወና ወደደው:: በዚህም መሠረት ባለ ካባ እና ባለ ዳባ ላይ እንድጫወት መርጦ ስክሪፕት ሰጠኝ::

ከአብየ መንግሥቱ አንደበት ብዙ ጊዜ ግልጽ ብሎ አድናቆት አይወጣም፤ ቢያደንቁህም ዝም ብለው ነው የሚያዩህ:: ልምምዶቻችንን እንኳ ተደብቀው ነው የሚከታተሉት:: ስንለማመድ መጣሁ አይሉንም፤ ስንበተን ጥሩ ነው ብለው ከተደበቁበት ይወጣሉ:: መጀመሪያ የት እንደተደበቁ እንኳን ፈልገን አናገኛቸውም:: አንድ ቀን ( ድምጹን እንደ አብየ ወርቁ በማስመሰል እና ጮክ በማለት) “ተፈሪ ይሄ ልጅ ብቻ ነው ገጸባህሪየን ያገኘልኝ፤ እናንተ አልደረሳችሁበትም፤ እሱ ደርሶበታል” እንዳሉት ተፈሪ ነገረኝ:: እኔ በወቅቱ ጀማሪ ነበርኩ:: ትንሽ ቆየና (አሁንም የአብዬ መንግሥቱን ድምጽ በማስመሰል) “እንዳትነግረው እንዳይሞት፤ እንዳይበላሽ ነገር ግን ጥሩ የተጫወተልኝ እሱ ነው” ብሎ ተፈሪ ነገረኝ::

የሎሬት ጸጋየ ገብረ መድህን ቴዎድሮስ የሚለው ቲያትር ላይ የጎንደር ቀበልኛ (accent) የሚያስተምራችሁ ተቀጥሮ ነበር ይባላል፤ እውነት ነው?

የቲያትሩ መቼት ጎንደር ላይ ስለሆነ በአካባበቢው የሚነገረውን ቀበልኛ እና ቅላጼ እንድንጠቀም አስተማሪ ተቀጥሮ ነበር:: በቲያትሩ የሚሳተፈው ተዋናይ ሁሉም ተራኪውን ጨምሮ ቀበልኛውን ይለማመድ ነበር:: እኔ በአጭር ጊዜ ውስጥ የገጸ ባህሪውን አነጋገር ዘይቤ በቶሎ ያዝኩት:: ጋሽ ጸጋየም በደንብ ወደዱት:: ነገር ግን ሌሎቹ ተዋንያን በተለያዩ ምክንያቶች ቀበልኛውን ከራሳቸው አነጋገር መለየት አልቻሉም:: በዚህ ምክንያት የጎንደሩ ቀበልኛ ቀረ:: ለማንኛውም ግን ተሞክሮ ነበር የሚለው የሚሰመርበት ጉዳይ ነው::

እሱ ገጸ ባህሪ ሳይሆን እብድ ነው የተባልክበት አጋጣሚ አለ፤ አጫውተን?

ከአርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ ጋር “ያልተከፈለ እዳ” የሚል ቲያትር ላይ የእብድ ገጸባህሪ ይዤ ተጫውቻለሁ:: በመጀመሪያ ከወጋየሁ ንጋቱ ጋር ነው የምትሠራው ስባል ደስ አለኝ:: ታላቅ አክብሮት ስለነበረኝ በመጀመሪያው ቀን ስክሪፕቱን እያነበብን ስንለማመድ ከፍርሀቴ የተነሳ ተንተባተብኩ:: አብረውኝ ሲራክ ታደሰ እና ተክሌ ደስታ ነበሩ፤ አይዞህ ብለው አበረታቱኝ፤ እንደምንም ብየ ጨረስኩ:: በሂደት በደንብ ተለማምጄ ቲያትሩን ለመጫወት በቃሁ::

ቲያትሩን ከሠራነው በኋላ ጋዜጣ ላይ የወጣ መጣጥፍ ነበረ፤ መጣጥፉ “ወጋየሁ ንጋቱ ድንቅ ብቃት ያለው ተዋናይ ነው፤ ቲያትሩንም ድንቅ አድርጎ ተጫውቶታል፤ ነገር ግን ቲያትሩን የተጫወተው ከአንድ እብድ ጋር ነው” ይላል:: ይህን ግን የነገሩኝ ካለፈ በኋላ ነው፤ ወዲያው ሰምቸው ቢሆን ኖሮ ደረቴን አስፍቼ (ኮራ ብየ) አረጅ ነበር::

በእርግጥ ወጋየሁም በአድናቆት ነግሮኛል:: ምስክር ሆኜ የምጫወትበትን ቲያትር አንስቶ የነገረኝን አልረሳውም፤ እንዲህ አለኝ “ከአክስቴ ቤት ሆኜ ከእሷ ጋር ቲያትሩን እያየሁ ቲያትሩ የእውነት የሆነ ያክል ‘እናንተስ እንደፍጥርጥራችሁ ምናለ ይሄን ሰውየ ባትጫወቱበት’ ብላ በንዴት ጮኸች፤ ስዩሜ እኛ ተዋናዮች ነን አንተ ግን አይደለህም” ብሎ ነገረኝ:: ሁለቱም ሁነቶች አስደስተውኛል:: ከወጋየሁ ጋር መተዋወቅ፣ አብሮ ቲያትር ላይ መጫወት ትልቅ ነገር ነበር:: ከእሱ ጋር ወግ አይቻለሁ::

በእንግሊዝኛ ቋንቋ ቲያትር አዘጋጅተሀል?

“ፒክኒክ ኢን ዘ ባትል ፊልድ” (picnic in the battlefield) የሚል የእንግሊዝኛ ቲያትር አዘጋጅቻለሁ:: እስከማውቀው ድረስ በመድረክ ቀርቦ ለሕዝብ የታየ የእንግሊዝኛ ቲያትር የለም:: ነገር ግን ለአንዳንድ ስነ ስርዓቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተሠርቶ ቀርቦ ያውቃል:: ውጪ ሀገር ሄደው ያቀረቡም አሉ:: ይሄኛው ግን ለሕዝብ የቀረበ ነው፤ ለሕዝብ ሲቀርብም የመጀመሪያው መሰለኝ:: ፒክኒክ ኢን ዘባትል የሚለውን ቲያትር አንብቤ ሀሳቡ ደስ አሰኘኝ:: ለጌታቸው ታረቀኝ ቆንጆ ቲያትር ነው ብየ ነገርኩት፤ አነበበው እና “ታዲያ ለምን አታዘጋጀውም?” አለኝ:: በእንግሊዝኛ? አልኩት “አዎ” አለኝ፤ እየቀለደብኝ መሰለኝ:: ምክንያቱም እሱ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ነው፤ እኔ አይደለሁም:: የምችል ይመስልሀል? አልኩት፤ “ትችላለህ” አለኝ:: ምንም ካለመሥራት ሠርተህ መውደቅ የተሻለ ነው:: እንዳውም ትልቅ ክብር ነው:: ልጆችን አስጠንቼ አሠራሁ፤ ከመውደቅ ይልቅ እንዳውም ለራሴም ለሌሎችም የሚገርም ነገር ነው የሠራሁት:: በእንግሊዝኛ የትምህርት ወረቀት ሳይኖረኝ ቲያትር መሥራት ትልቅ ነገር ነው፤ እድለኛም ነኝ እላለሁ::

ከሥራዎችህ የምትወደው የትኛው ነው?

ሁሉንም እወዳቸዋለሁ፤ ነገር ግን የበለጠ ሮሚዮ እና ጁሊየትን እወደዋለሁ:: ምክንያቱም ብዙ ታሪክ አለው:: ብዙ ተዋንያን የራሳቸውን ጥረት ስላደረጉበት፤ ሌሎች አያሌ ደግሞ ራሳቸውን የለወጡበት ስለሆነ:: እኔም ራሴ ደግሞ ይሄን ያህል ሰው ሰብስቤ ማሠራት የሚያስችል አቅም እንዳለኝ የተረዳሁበት በመሆኑ ነው:: በዚህ ላይ የጋሽ አባተ መኩሪያ እገዛ አለበት:: በመጀመሪያ ከመቶ በላይ ተዋንያን ነበሩ መድረክ ላይ የሚሠሩት:: ከዚያ አሳጥርልን ተብየ የመጨረሻ 64 ነው ያደረስኩት:: ሮሚዮ እና ጁሊየት ደስ ይለኛል::

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here